Skip to main content
x
በርካቶችን የሚቀጥፈው የነርቭ መዋቅር ክፍተት

በርካቶችን የሚቀጥፈው የነርቭ መዋቅር ክፍተት

በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በአደጋ፣ በበሽታና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በየቀኑ 151,600 ሰዎች ሲሞቱ በተቃራኒው ደግሞ በየደቂቃው 250፣ በየሰዓቱ 15,000፣ በየዓመቱም 360,000 ሕፃናት ይወለዳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እንደተወለዱ የሚሞቱ፣ አልያም ዕድሜ ልካቸውን አብሯቸው ከሚቆይ የአካል ጉዳት ጋር አብሮ ለመኖር የሚገደዱ አሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱ የተለያዩ ሕመሞች መካከል ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ የጤና ዕክሎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በቅርቡ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በየደቂቃው ከሚወለዱ 250 ሕፃናት መካከል ሦስት በመቶ አልያም አዲስ ከሚወለዱ 33 ሕፃናት መካከል አንዱ ከተለያዩ በወሊድ ጊዜ ከሚፈጠሩ ዕክሎች ጋር ይወለዳል፡፡ እክሎቹ በሕፃናቱ ጤናና የመኖር ዕድል ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት አሉታዊ ተፅዕኖ ለየቅል ሲሆን፣ በርካታ ሕፃናት ሞተው እንዲወለዱ፣ አልያም ከተወለዱ በኋላ እንዲሞቱ፣ በሕይወት የሚኖሩበት አጋጣሚ ከተፈጠረም አካል ጉዳተኛ እንዲሆኑ ምክንያት ናቸው፡፡

ከውልደት ጋር ከሚፈጠሩ የጤና ዕክሎች መካከል ‹‹ኒውራል ቲውብ ዲፌክትስ›› ማለትም ከአንጎል ተነስቶ ህብለሰረሰር ድረስ የሚወርዱት የነርቭ ቱቦዎች የነርቭ መዋቅራቸውን ሳይዙ ሲቀሩና ክፍተት ሲኖራቸው የሚከሰተው ችግር ዋነኛውና አደገኛው ነው፡፡ ይህ በሁለት ዋና ዋና የአካል ክፍሎች ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር ይታወቃል፡፡ በፎሊክ አሲድ ወይም በቫይታሚን ቢ9 እጥረት ከእናትዬው የአመጋገብ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ይከሰታል፡፡ ፅንሱ በዚህ የዕድገት ዕክል የሚያጠቃው እናቲቱ መፀነሷን ገና ሳታውቅ ነው፡፡

ከኒውራል ቲውብ ዲፌክት ጋር የሚወለዱ ሕፃናት በጀርባቸው አጥንት እንዲሁም በአንጎላቸው ዕድገት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡ በጀርባ አጥንታቸው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ህብለሰረሰራቸው በትክክል እንዳይዘጋ ሲያደርግ በአንጎል ላይ የሚከሰተው ደግሞ የአንጎልና የራስቅል ዕድገትን የሚገታ ነው፡፡ በራስ ቅላቸው ውስጥ ውኃ እንዲቋጠርና ጭንቅላታቸው እንዲያብጥ አልያም ጭንቅላታቸው ከወትሮው ትልቅ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርግ ዕክልም አለ፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2016 ባወጣው ሪፖርት በየዓመቱ 300 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናት ከኒውራል ቲውብ ዲፌክት ጋር ይወለዳሉ፡፡ ችግሩ ካደጉት አገሮች ይልቅ በታዳጊ አገሮች ይበዛል፡፡ ባላፈው ዓመት የኢትዮጵያ ኒውሮሰርጂካል ሶሳይቲ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ በኢትዮጵያ ህብለሰረሰራቸው ያልገጠመና ጭንቅላታቸው ውኃ የቋጠረ ሕፃናት ቁጥር በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ከሚመዘገበው በ20 በመቶ ይበልጣል ብሏል፡፡ በአገሪቱ በየዓመቱ 60 ሺሕ ሕፃናት ከእነዚህ ዓይነት የጤና ዕክል ጋር ይወለዳሉ፡፡ እነዚህ የጤና ዕክሎች ለአብዛኛዎቹ ሕፃናት ሞት ምክንያት ቢሆኑም በሕክምና ዕርዳታ የሕፃናቱን ሕይወት መታደግ ይቻላል፡፡

የ32 ዓመቷ ዶ/ር ዮርዳኖስ አሻግሬም ለዚሁ ተግባር ነው ሰሞኑን ወደ አገራቸው የሚመለሱት፡፡ ለኢትዮጵያ ‹‹የመጀመሪያ ሴት›› ኒውሮሰርጂን የሆኑት ዶ/ር ዮርዳኖስ በየዓመቱ የሚካሄደውን ማንዴላ ስኮላርሺፕ ፕሮግራም በመከታተል ላይ ሲሆኑ፣ በዚህ ወር ውስጥ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ሪች አናዘር ፋውንዴሽን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡ ዶ/ር ዮርዳኖስ ወደ አገር ውስጥ እንደተመለሱ ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር በኒውራል ቲውብ ዲፌክት አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሕፃናትን ማከም ነው፡፡

ዶ/ር ዮርዳኖስ ተልዕኳቸውን የሚፈፅሙት ከኒውራል ቲውብ ዲፌክት ጋር የሚወለዱ ሕፃናትን ለመቀነስ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ከሚደግፈው ሪች አናዘር ፋውንዴሽን ጋር ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 በበጎ ፈቃደኞች የተቋቋመው ፋውንዴሽኑ፣ ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮችን መርዳት ዓላማው ያደረገ ነው፡፡ ፋውንዴሽኑ የተለያዩ የኒውሮ ቲውብ ዲፌክት ያለባቸውን ኢትዮጵያዊ ሕፃናትን ለመርዳት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በቅርቡ አዘጋጅቶ እንደነበር ከጽሑፉ መረዳት ተችሏል፡፡

ፋውንዴሽኑ ሲቋቋም በአገሪቱ የነበረው አንድ ቀዶ ሐኪም ብቻ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ያሉት ቁጥር ወደ 25 እንዲያድግም ድጋፍ ማድረጉን በላከው መረጃ አስፍሯል፡፡ ‹‹ከዶ/ር ዮርዳኖስ ጋር በመሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ እንችላለን፤›› ያሉት የፋውንዴሽኑ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ማሪነስ ኮኒንግ ናቸው፡፡ ፋውንዴሽኑ እንደተቋቋመ በአገሪቱ ዕክሉ ኖሮባቸው የሚወለዱ አብዛኛዎቹ ሕፃናት ይሞቱ እንደነበር ታዝበዋል፡፡ ነገር ግን ሕፃናቱ የሚሞቱት በቀላል ሕክምና መዳን ሲችሉ ነው፡፡

ፋውንዴሽኑ እ.ኤ.አ በ2020 በየዓመቱ ከነርቭ መዛባት ጋር በሚፈጠር የጤና ዕክል የሚጠቁ ሕፃናትን ቁጥር ወደ አምስት ሺሕ ለማድረስ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ነርሶችና ፊዚዮቴራፒስቶች የማሠልጠን እንዲሁም ተገቢውን የሕክምና ቁሳቁሶች ማቅረብና ሌሎችም የሕክምና ድጋፎችን ያዘጋጃል፡፡ ዶ/ር ዮርዳኖስም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል በመሆን የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ 

‹‹ከሪች አናዘር ፋውንዴሽን ጋር ከኒውሮ ዲፌክት ጋር የሚወለዱ ሕፃናትን ማከም የሚያስችል ኢትዮጵያዊ የነርቭ ቀዶ ሐኪሞችንና ሌሎችንም በሕክምናው የሚሳተፉ ባለሙያዎችን እናፈራለን የሚል ተስፋ አለን፣›› ያሉት ዶ/ር ዮርዳኖስ ናቸው፡፡ በፎሊክ አሲድ ወይም በቫይታሚን ቢ9 እጥረት ምንክንያት የሚከሰተው ይህ የጤና ችግር አመጋገብ በማስተካከል መቀረፍ የሚችል ነው፡፡ የተለያዩ ፍራፍሬዎች፣ ቡናማ ቀለም ያለው ሩዝ በመመገብና ሌሎችም በቫይታሚን ቢ9 የበለፀጉ ምግቦችን በመጠቀም መከላከል ይቻላል፡፡

ይሁንና በአፈር ውስጥ የሚገኝ የፈንገስ ዝርያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚበቅሉ አዝርዕት የፎሊክ አሲድ ይዘታቸው እንዲጠፋ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህም የምግቦችን የንጥረ ነገር ይዘት መጨመርን (ፉድ ፎርቲፊኬሽን) አስመልክቶ የወጣው መመሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል ግድ ይላል፡፡ አለዚያ ግን በቀላሉ መከላከል በሚቻለው የኒውሮ ቲዩብ ዲፌክት የሚጠቁ ሕፃናት ቁጥር ይጨምራል፡፡