Skip to main content
x
የጥቅምት አብዮት በአዲስ አበባ

‹‹የጥቅምት አብዮት›› በአዲስ አበባ

የቀድሞዋ ‹‹ሶቪየት ኅብረት›› እውን የሆነችው እ.ኤ.አ. በ1917 በሩሲያ ከተከናወነው የጥቅምት አብዮት (የኦክቶበር ሪቮሉሽን) በኋላ ነበር፡፡ አብዮቱን የመራው ቭላድሚር ኢሊዪች ዑልያኖቭ ባጭሩ በሚታወቅበት ስሙ ቭላድሚር ሌኒን ነበር፡፡ በተከታታይ ዘመናት ምሥራቅ አውሮፓን ያጥለቀለቀው ሌኒናዊው አብዮት አፍሪካም ኋለኛው ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ በ1967 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ዘውዳዊ ሥርዓት የገረሰሰውና ሥልጣን የጨበጠው ወታደራዊው ደርግ ሶሻሊዝምን ተቀብሎ ‹‹መመሪያችን ማርክሲዝም ሌኒንዝም ነው›› በማለት አገሪቱን ለ17 ዓመታት መርቷል፡፡ ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ በብሔራዊ ቤተ መንግሥትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ መካከል ለሌኒን የመታሰቢያ ሐውልት በ10ኛው ዓመት የአብዮትና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ምሥረታ በዓላት አጋጣሚ መትከሉ ነበር፡፡ ይህ ፎቶ ሐውልቱ በተተከለ በሁለተኛው ዓመት (1979 ዓ.ም.) የጥቅምት አብዮት 69ኛ ዓመት ለማሰብ የሶቪየት ኅብረት ማኅበረሰብ በአዲስ አበባ ሲያከብሩ ያሳያል፡፡

  • ሔኖክ መደብር

ሀገሬ! ምን አጥተሽ!

በብዙ መከራ ÷ እኽል ውኃው ታጥራ

ሰው ሁሉ ቢያደላ ÷ ለደስታ ለተድላ

ለስሙ ያኽል እንጂ ÷ ፍላጎቱ አይሞላ

አንቺ የሌለሽበት ÷ ሀገሬ በስተ ኋላ።

የሰው ዘር በመላ ÷ አካልና ጥላ

ገላሽ ገላው አብራ ÷ ጣምራ ተሰናስላ

ኑሮና ተግባሩ ÷ ሰላሙና ጤና

አዋዋሉ ሁላ ÷ ፍፁም አይቃና

አንቺ የሌለሽበት ÷ ሀገሬ በዝቷላ!

ከሥጋው ተዋደሽ ÷ ከነፍሱም ተጣብቀሽ 

በደም ሥሩ ሠርገሽ

ያካሉን ግልጥታ ÷ ዕርቃኑን የሸፈንሽ 

ስንቱን አጀግነሽ

በኪነ ጥበቡ ÷ ሀገሬ ምን አጥተሽ!

ገመናሽ የሚታይ ÷ እስከዚህ አጋልጦሽ።

ለክብርሽ ቦታ አጥተን ÷ ለስምሽ ክብር ነፍገን 

እኛ እንጂ ያሳጣንሽ 

ስንቱን በቤትሽ ÷ አቅፈሽ ደግፈሽ

ስንቱን በደጅሽ ÷ አንከባክበሽ ኖረሽ

ስንቱ እንዳማረልሽ

ሀገሬ ውስጥሽ ÷ ማን ገብቶ ባየልሽ!

ገመናስ የለሽ ÷ እርግጥ በባሕርይሽ።

በጥንተ ተፈጥሮ ÷ ግብረ መዋዕሉ

ሕጉን ከነደንቡ ÷ ከነአገባቡ

አምላክ ያደለሽ ÷ በኪነ ጥበቡ

የሴም በረከቱ ÷ የካም ሲሳይ ምግቡ

የያፌት ወጭቱ ÷ የእንጀራ መሶቡ 

ኾነሽ ካጠገቡ

የተፈጥሮ መብቱን ÷ ሰውሽ መገንዘቡን

ማን አየስ? በቅርቡ!

ከለምለሙ መስክሽ ÷ ረፍቱ ውኃሽ ዳር

()ርጥብ የሚያደርቅ ÷ ደረቅ የሚያከስም

ቃል ኪዳን ተዋርሰሽ ÷ ለዘለዓለም

ፍሬ አልባ ረገን ÷ ከሁሉ ዘን፤

አንቺ ዐጸደ ወይን ÷ አንቺ ዐጸደ ወይን 

ሀገሬ ለምን?

እኛስ ያለ ምክንያት ÷ ያላፈራራን።

ሀገሬ!

ሀገሬ ሀገሬ! የሚልሽ ቀን ማታ

ያውም የውዴታ ÷ ፍቅሩ ከዚ ጎልታ፤

የቀን ውሎ አሳቡ ÷ የሌት ሕልሙ ሌላ

ሌላው እጁ ገብተሽ ÷ እጁ በበረታ፣

እጅሽ ተቆራኝታ፤

ሀገር ህልውናሽ ÷ ስንቴ ስንቱ ቦታ

በስንቱስ ዱለታ ÷ በከንቱ የተፈታ!

ያሳስብሽ ይኾን? ዛሬም ያውውነታ።

የሰላምሽ ኬላ ÷ በእብሪት ተደፍራ  

በተንኮል ተሢራ

ሀገሬማላማሽ ÷ ስምሽም ቢጠራ

ገቢው ወጪው ጋራ 

የሰላሙ አለቃ ÷ የሰጠሽ እልቅና

ከሰውነት ተራ ÷ መቼም አይወጣና! 

የሰው ዘር ጠቅላላ ÷ ሰላሙ ላይረጋ

በነፍስና ሥጋ ÷ በከንቱ እየተጋ

ቢበድልሽ ነጋ ÷ ይቅርምትይ ነጋ

ሀገሬ አንች ኾነሽ ÷ የሥርየቱ ዋጋ።

  •   ኃይለ ልዑል ካሣ፣ (መስከረም 2010 .ም.)

ከሕዳሴው ግድብ ራስጌ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም 62 በመቶ በደረሰበት አጋጣሚ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮና የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ስፍራውን ጎብኝተዋል፡፡ የግድቡን የሲቪል፣ የሐይድሮና ኤሌክትሮ መካኒካል የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረውም ተመልክተዋል። ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሳያረጋግጡ አላለፉም፡፡ እንደ ተቋሙ መግለጫ፣ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ (ፎቶ) የግድቡ ግንባታ በተጀመረው ፍጥነት ያለምንም ማቋረጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተው፣ ግድቡ ኃይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ በመጠጋት ላይ እንደሆነም አስረድተዋል። ጎብኚዎቹም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ሲገቡ፣ የተጋመሰውን ግድብ ለማጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው በመቀጠል አዲስ ታሪክ መጻፍ እንደሚኖርባቸው የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወየሳ ፈይሳ አስገንዝበዋል።

ከሕዳሴው ግድብ ራስጌ

*******