Skip to main content
x
ዝንቅ

ዝንቅ

በድርቅና በግጦሽ እጦት ምክንያት ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ተሰደው የነበሩ ሳላዎች ወደ መኖሪያቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡

ፎቶ በታምራት ጌታቸው

አዳምና ሔዋን

ቀዳማዊው ጽልመት ሲወርድ በዙሪያቸው

ቅጠሎች ደከሙ ሞገስ ሰልችቷቸው፤

በጠራው ፀጥታ ውበት አጋጥማቸው

ዘዴዎችዋን ሁሉ ገለጸላቸው፡፡

በጠራራው ፀሐይ መካነ ገነት

ፀሐይ ይሞቃሉ ወፍም መላእክት፤

አስተማረቻቸው ሰማያዊ ምክር

ከቃጠሎው ንዳድ ከሃሩር ሲሸሹ ከሞቃቱ አየር

ያዩት ነገር የለም ከህልም በስተቀር፡፡

እጆቻቸውንም ውበት ጠፋፈረች

እንዲበርድላቸው ምንጯ ውስጥ ነከረች

ቀኑም ዘመም ሲል ሲቃረብ ሌሊቱ፤

ወዲያው አንቀላፉ ቆነጃጅቶችም እንደሚተኙቱ፤

ከዚያም አረፍ ብላ ጥቂት እንደቆየች፤

ነቅታ ከአፈራቸው አይላ አበበች፡፡

  • ከማርጆሪ ፒክቶል (1883 እስከ 1922)

ትርጉም ዳዊት ዘኪሮስ

 

‹‹ለምን?›› ብሎ የጠየቀኝ አልነበረም?

አንዲት ሴት ወይዘሮ በባቡር ጉዞ ላይ ሳሉ አጠገባቸው ባለው ወንበር ላይ የተቀመጠንጣ ስለነበር አንድ ሠራተኛ መጥቶ ይህ ወንበር ለሰው መቀመጫ እንጂዕቃ ማኖሪያ አልተፈቀደምና እባክዎ ያንሱ ሲላቸው ‹‹አላነሳም›› አሉት፡፡ ‹‹ቢያነሱ ይሻልል እምቢ ካሉ ላለቃዬ እነግራለሁ›› ቢላቸውም ‹‹ሂድ ንገር›› አሉት፡፡ ሂዶ ስነግረው አለቅየው መጥቶ ያንሱ እንጂ ለምን አላነሳም ይላሉ? ብሎ ቢነግራቸው ‹‹አላነሳም›› በሚለው ሐሳባቸው ጸንተው የማይበገሩ ሆኑበት፡፡ በመጨረሻም ለዋናው ኃላፊ ተነግሮት ይመጣና ‹‹ይህን ሻንጣ ያንሱ›› ሲላቸው ‹‹አላነሳም›› አሉት፡፡ ዋና ኃላፊውም ‹‹ለምን›› ሲላቸው ‹‹ገና አሁን አዋቂ ሰው መጣ፡፡ እኔ የቸገረኝ እኮ እስካሁን ድረስ ‹‹ለምን›› ብሎ የጠየቀኝ ባለመኖሩ ነበር፡፡ አንተ ‹‹ለምን›› ስላልከኝ አመሰግንናለሁ፡፡ በመሠረቱ ግን ሻንጣው የእኔ አይደለም፡፡ ሲሉት በመደነቅ ይቅርታ ጠየቃቸው፡፡

******

የሰው ነገር - በችሎት ፊት

አንድ ሲራራ ነጋዴ መንገድ ሲሔድ ቆይቶ ቀን በምሳ ሰዓት ከአንድ ዛፍ ሥር አረፍ ብሎ ምሳውን ቆሎ ቆርጥሞና ውሃ ጠጥቶ ጉዞውን ሲቀጥል ሁለት መቶ ጠገራ ብር ረስቶ ሄደ።

አንድ ገበሬ አግኝቶለት ያንን ገንዘብ ሊሰጠው ከኋላ እየሮጠ ተከተለውና ‹‹ሰውዬ ቆም ብህ ጠብቀኝ፤ ጥለኸው የሔድከው ገንዘብህን አግኝቼልሃለሁ፤›› አለው። ነጋዴውም ‹‹ያገኘኸው ገንዘብ ስንት ነው?›› ሲለው ‹‹ሁለት መቶ ብር›› አለው።

ነጋዴው ግን ‹‹እኔ የጠፋብኝ ገንዘብ ሦስት መቶ ብር ነው። አንዱን መቶ ብር የት ደብቀህ ነው ሁለት መቶ ብር የምትሰጠኝ። ሞልተህ ካላመጣህ አልቀበልህም እከስሃለሁ። እንዲህ በዋዛ አንላቀቅም›› አለው።

ገበሬውም ገንዘቡን እንደያዘ ወደ ኋላ ተመለሰ። ነጋዴው የመሠረተው የውሸት ክስ በይግባኝ ተይዞ ወደ አፄ ቴዎድሮስ ሲቀርብ የሁለቱን አባባል ካዳመጡ በኋላ ነጋዴውን ምን ያህል ገንዘብ ነው የጠፋህ? ሲሉት ‹‹ሦስት መቶ ጠገራ ብር ነው›› አላቸው።

ገበሬውንም ‹‹ምን ያህል ገንዘብ አገኘህ?›› ሲሉት ‹‹ሁለት መቶ ጠገራ ብር ብቻ ነው›› አለ።

ከዚያ በኋላ ‹‹አንተ ነጋዴው ጠፋብኝ የምትለውን ሦስት መቶ ብር ከጣልህበት ቦታ ፈልገህ አግኝ። ሁለት መቶ ብር ያገኘኸው ገበሬ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ጠፋኝ የሚል ሌላ ሰው እስከሚመጣ ድረስ ራስህ ልትጠቀምበት ትችላለህ›› ሲሉ ፈርደው ፋይሉ ተዘጋ።

  • መክብብ አጥናው ‹‹የአባቶች ጨዋታ›› (2005)

 

***

ገበሬው

አንድ በሬ ብቻ የነበረው አንድ ድሃ ገበሬ ነበር፡፡ ታዲያ ሌላ አጣማጅ በሬ ተውሶ ለማረስ በጠየቀ ጊዜ ሁሉም ይከለክሉት ነበር፡፡

አንተ ልመና ብቻ ነው የምታውቀው፡፡ይሉት ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን በእርሻ ላይ ሳለም በእንስራ ሙሉ ወርቅ ያገኝና ይደብቀዋል፡፡ ከዚያም የበሬውን ሸኮና ቆረጠው፡፡ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተውይህን ለምንድነው ያደረከው?” ብለው ሲጠይቁትአልፈልገውም ለድሆችም ይሁንአላቸው፡፡ እነርሱምአንተም ድሃና በቤትህ ውስጥ የምትበላው የሌለህ ሆነህ እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ?” አሉት፡፡

እርሱ ግን ድርጊቱን ገፍቶበት ሲያበቃበሬውን እግዚአብሔር ስለሰጠኝ አሁን ደግሞ ለድሆች ምግብነት ይዋል፡፡ብሎ መለለሰላቸው፡፡ ሁኔታው ግራ ቢገባቸውም በሬውን አርደው ለድሆች አከፋፈሉት፡፡ ገበሬውም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሚስቱንከረጢት ስጪኝና ተከተይኝ፡፡አላት፡፡

አብረውም ሄደው ወርቁን ቆፍረው ከወጡ በኋላ ባለፀጋ ሆኖ ሃብት ሞልቶት ለእግዚአብሔር አስራት እያስገባ መኖር ጀመረ፡፡

  • ፋጢማ አሊ ‹‹በርታ ተረት››

**********

ፀሐይን እንዲህ አላት

‹‹ዛራቱስትራ የሠላሳ ዓመት ጐልማሳ በሆነ ጊዜ አገሩንና የአገሩንም ወንዞች ትቶ ወደ ተራራ ሄደ፡፡ በዚያም የገዛ ራሱን መንፈስና ብቸኝነቱን በመደሰት ምንም ስጋት ሳይሰማው አሥር ዓመት ኖረ፡፡ በመጨረሻ ልቡ ተመለሰ፡፡ አንድ ቀን ማለዳ ተነሣ፡፡ በፀሐይዋ ፊለፊት ቆሞ እንዲህ ሲል ተናገራት፡፡

ትልቅ ኮከብ ሆይ፤ ብርሃንሽን የምታድያቸው ባይኖሩሽ ኖሮ ደስታሽ ምን ይሆን ነበር፡፡ አሥር ዓመት ሙሉ በየዕለቱ እስከዋሻዬ ድረስ ትመጭ ነበር፡፡ እኔና አብረውኝ ያሉት ንስርና እባብ ባንኖር ኖሮ ስለብርሃንሽና ስለጉዞሽ ሐሳብ ይገባሽ ነበር፡፡ ግን እኛ በየጧቱ እንጠባበቅሽ ነበር፡፡ ተትረፍርፎ ካንቺ የሚፈሰውን ወሰድን፤ ስለሱም መረቅንሽ፡፡

እነሆ፤ ስለጥበቤ ሐሳብ ገባኝ፤ ብዙ ማር እንዳከማቸች ንብ ለመውሰድ የተዘረጉ እጆች አስፈለጉኝ፡፡ ወዲያ ለመስጠትና ለማደል እፈልጋለሁ፡፡ በሰዎች መካከል ያሉት ጠቢባን በሞኝነታቸው፤ ድሆችም በሀብታቸው እስኪደሰቱ ድረስ፡፡ በዚህ ዓላማ ምክንያት አሁን ቁልቁል መውረድ አለብኝ፡፡ ሁልጊዜ በየምሽቱ እንደምታደርጊው፣ በባሕሩ ማዶ አልፈሽ በታችኛው ዓለም ላሉት ብርሃን ለመስጠት እንደምትሄጅ፣ እጅግ ባለፀጋዋ ኮከብ ሆይ፡፡

እኔም እንዳንቺ ወደታች ‹‹መጥለቅ›› አለብኝ፤ የምወርድላቸው ሰዎች እንደሚሉት፡፡ ከመጠን በላይ የሆነውን ደስታ እንኳ ያለቅናት የምታይ፣ ሰላምን የተመላሽ ዓይን ሆይ፣ እንግዲህ መርቂኝ፡፡

ተርፎ ለመፍሰስ የሚፈልገውን ዋንጫ መርቂ፣ ውኃው ከሱ እንደ ወርቅ ይፈስ ዘንድ፤ የደስታሽንም ማንፀባረቅ (ሪፍሌክሽን) ወደመላው ዓለም ይሸከምልሽ ዘንድ፡፡ እነሆ ይህ ዋንጫ እንደገና ባዶ ለመሆን ፈለገ፤ ዘራቱስትራም ዳግመኛ ሰው ለመሆን ተመኘ፡፡

እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ›› (1956)