Skip to main content
x
የትራፊክ አደጋን ዜሮ የማድረግ ‹‹ህልም››

የትራፊክ አደጋን ዜሮ የማድረግ ‹‹ህልም››

ትርፍ መንገደኛ አሳፍራ ስትከንፍ የነበረችው ባጃጅ የመገልበጥ አደጋ ያጋጠማት በድንገት ነበር፡፡ በአደጋው ከአንዷ መንገደኛ በስተቀር የከፋ ጉዳት የደረሰበት አልነበረም፡፡ ከአሽከርካሪው ጎን በትርፍ ተጭና የነበረችውና ወደ ትምህርት ቤት በመጓዝ ላይ የነበረችው የ18 ዓመቷ ኮረዳ ግን እንደወጣች ነበር የቀረችው፡፡ በደረሰባት አደጋ ሕይወቷ ያለፈው ወዲያው ነበር፡፡ የእርሷ ሕልፈት ያለእናት ያሳደጓት አባቷን የሞት ያህል የከበደ ሐዘንና ችግር ላይ የጣለ ነበር፡፡

አባትየው ዕድሜና በሽታ የተጫናቸው ናቸው፡፡ የስኳር በሽታ ታማሚ ሲሆኑ፣ ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ኢንሱሊን (የስኳር ሕመምተኞች መርፌ) የምትወጋቸውም እርሷ ነበረች፡፡ በመሞቷ ግን ሁሉም ቀረ፡፡ ለተፈጠረው አደጋ ተጠያቂ የነበረው አሽከርካሪው ክስ ተመሥርቶበት በእስር ተቀጣ፡፡ የሚያሳዝነው ነገር እሱም ለአቅመ ደካማ እናቱ ብቸኛ ልጃቸውና የገቢ ምንጫቸው መሆኑ ነበር፡፡ እናትየው ልጃቸው በመታሰሩ ለከፋ ችግር ተዳረጉ፡፡ የባጃጁ ባለቤትም በሕይወቱ ያፈራው ብቸኛ ንብረቱ በደረሰበት አደጋ እንዳልነበረ ሆኖ በመበላሸቱ ባዶ እጁን ቀረ፡፡

ይህ ክፉ አጋጣሚ አንድ የትራፊክ አደጋ ከአደጋው ሰለባዎች ባሻገር በማኅበረሰቡ ላይ ምን ያህል ጉዳት፣ የሥነ ልቦና ችግር፣ የገንዘብና የንብረት ኪሳራ እንደሚያደርስ ያሳያል፡፡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኢንስፔክተር አሠፋ መዝገቡም የትራፊክ አደጋ ምን ያህል አስከፊ ገጽታ እንዳለው ለኅብረተሰቡ ለማስተማር ይህንን አጋጣሚ በማሳያነት ያነሳሉ፡፡ አደጋው የደረሰው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሲሆን፣ ከተከሰተ ትንሽ ቆየት ብሏል፡፡

ማኅበረሰቡ ከትራፊክ አደጋ ራሱን እንዲጠብቅ መሰል አደጋዎችን በምሳሌነት በማንሳት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና መድረኮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ቢሠሩም ለጉዳዩ ጆሮ የሰጠው ያለ አይመስልም፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም ከባድ አደጋዎች ሲከሰቱ ይስተዋላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ቀን ከሌሊት የትራፊክ አደጋ ስለመከሰቱም ይሰማል ይታያልም፡፡ ሕፃን አዋቂ ሳይል ስንቱ በትራፊክ አደጋ ሕይወቱን ያጣል፡፡ ስንቱ እንደ ወጣ ይቀራል፡፡

ወደ ቱሉ ዲምቱ በሚወስደው በአዲሱ የፍጥነት መንገድ ላይ በአንድ አቅጣጫ ሲከንፍ የነበረ አንድ ሞተረኛ አንድ ተሳቢ ካለው የጭነት መኪና ጋር ይጋጫል፡፡ ወጣቱ ሞተረኛ የጭንቅላት መከላከያ (ሔልሜት) አላደረገም ነበር፡፡ በተከሰተው ግጭት ከአንገቱ በላይ እንዳልነበረ ሆነ፡፡ ‹‹በደረሰበት አደጋ ሙሉ ለሙሉ ጭንቅላቱ እንዳልነበረ ነው የሆነው፡፡ ማን መሆኑን ለማወቅም አስቸጋሪ ነበር፡፡ አደጋውን ያባባሰውም ሔልሜት አለማድረጉ ነው፤›› በማለት ነበር ምክትል ኢንስፔክተሩ ሁኔታውን የገለጹት፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ በለገጣፎ አደባባይ ላይ የደረሰውም አሰቃቂ የትራፊክ አደጋ ለሕይወቱ የሚጨነቅ፣ የሚሳሳ አሽከርካሪ የለም እንዴ? ያሰኛል፡፡ አይሱዙ መኪና የሚያሽከረክረው የ23 ዓመት ወጣት የመገልበጥ አደጋ ያጋጠመው አደባባዩን በመዞር ላይ ሳለ ነበር፡፡ አደጋው የደረሰው ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ ሲሆን፣ በደረሰው አደጋ ወጣቱ ሕይወቱን አጥቷል፡፡ አደጋው የደረሰው በተቃራኒው ቀን ስምንት ሰዓት ላይ ቢሆን ኖሮ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ሁለቱ አደጋዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እንደደረሰው አደጋ የቆዩና የተረሱ አይደሉም፡፡ ባሳለፍነው ረቡዕ የተከሰቱ ናቸው፡፡

በየዕለቱና በየሰዓቱ የሚመዘገቡት የትራፊክ አደጋዎች በብዙዎች ሕይወት ላይ ጥቁር ጠባሳ ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ዜጎች በሰላም ከቤት ወጥተው በሰላም ስለመመለሳቸው ዋስትና እስኪያጡ አደጋው አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ተሽከርካሪዎች ትራንስፖርትን በማቀላጠፍ ከሚሰጠት ጥቅም ባልተናነሰ መጠን በገዳይነታቸው እንዲታወቁ ሆኗል፡፡ የትራፊክ አደጋ ብዙዎችን እንደ ቅጠል አርግፏል፡፡ ለአካል ጉዳት ዳርጓል፡፡ ቤት ንብረትም እንዳልነበረ አድርጎ አጥፋቷል፣ እያጠፋም ይገኛል፡፡ እስካሁን የትራፊክ አደጋ ያላጋጠማቸው ብዙ ቢሆኑም፣ ሁሉም ግን በተለያየ አጋጣሚ በተለያየ ሁኔታ ቢያንስ አንዴ ከአደጋው ለጥቂት ያመለጡ አሊያም በተዓምር የተረፉ ናቸው፡፡

በገዳይነቱ በዓለም ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ አደጋው ይበልጥ የሚበዛውም እንደ አፍሪካ ባሉ በኢኮኖሚ ደካማ በሆኑ አኅጉሮች ነው፡፡ በአኅጉራቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ከሚመዘገብባቸው አገሮች መካከል በጣም ዝቅተኛ የሆነ የተሽከርካሪ ብዛት ያላት ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ መካተት የነበረባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ጊዜም የትራፊክ አደጋ አሳሳቢነትን አንስተው ነበር፡፡   

አባላቱ የኤችአይቪ ወረርሽኝ እያገረሸ መሆኑንና ጉዳዮን አስመልክቶ መንግሥት ምን እያደረገ እንደሚገኝ ጥያቄ ሰንዝረው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኤችአይቪን አስመልክቶ የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ከኤችአይቪ በላይ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡ በክልል ከተሞች በተለይም በሞተር ሳይክሎች የሚደርሰው አደጋ አሳሳቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   

በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ4,500 ሰዎች በላይ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከ12 ሺሕ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይም ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ይደርሳል፡፡ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ብቻ 477 የሞት አደጋ ተመዝግቧል፡፡ ወደ 2,000 በሚሆኑ ዜጎች ላይም ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

ይኼንን ሰው ሠራሽ በሰው ዘር ሁሉ የተቃጣ የሚመስልን አደጋ ለመከላከል ብዙ ሥራዎች በዘመቻ መልክ እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የሚደርሰው የአደጋ መጠን በመቀነስ ፈንታ በተቃራኒው እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ‹‹አዲስ አበባን ብቻ ስንመለከት በየዓመቱ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ በስድስት በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡ ይህንን አሳሳቢ የሚያደርገው በዓለም አቀፍና በአፍሪካ ደረጃ ያለን የተሽከርካሪ ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ የሚደርሰው አደጋ ከፍተኛ መሆኑ ነው፤›› የሚሉት የአዲስ አበባ መንገድ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊው አቶ ጂሬኛ ሂርጳ ናቸው፡፡ በአገሪቱ የሚገኘው የተሽከርካሪ ብዛት አንድ ሚሊዮን እንደማይደርስም ይናገራሉ፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት የትራፊክ አደጋ ትልቅ የጤና ችግር እየሆነ መጥቷል፡፡ በአደጋው በየቀኑ ሕይወታቸውን የሚያጡ፣ በሚደርስባቸው አደጋ የሕክምና መሥጫዎችን የሚያጨናንቁ ብዙ ናቸው፡፡ በከተማው ውስጥ 14 በመቶ የሚሆነውን አደጋ የሚያደርሱት ሚኒባሶች (ታክሲዎች) ናቸው፡፡ 15 በመቶ የሚሆነውን የሞት አደጋ የሚያደርሱት ደግሞ የመካከለኛና የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 58 በመቶ ለሚሆነው በትራፊክ አደጋ የሚከሰትን ሞት እያስከተሉ የሚገኙት አውቶብስን ጨምሮ የተለያዩ የትራንስፖርትና ሌሎች በንግድ ላይ የተሠማሩ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከቤት መኪናዎች አንፃር ሲታይ አነስተኛ ሆኖ ሳለ በእነሱ የሚደርሰው አደጋ የትየለሌ መሆኑ ነው፡፡   

‹‹ለምንድነው በንግድ ላ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ አደጋ የሚያደርሱት የሚለው ጥያቄ ሌላ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ያለውን ሁኔታ ለመግለጽ ያህል ግን ለንግድ ቅድሚያ ስለሚሰጡና አንድ ሰው መሥራት ከሚገባው ጊዜ በላይ የመሥራትና ሌሎችም አግባብነት የሌላቸው ሁኔታዎች ይታያሉ፤›› በማለት የሚደርሰው አደጋ ቁጥር እንዲጨምር እያደረጉ እንደሚገኙ፣ በሚገባ ሊጤኑና መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገነቱ ደሳለኝ፣ ኤጀንሲው የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ በአምስት ዓመታት ውስጥ በ50 በመቶ ለመቀነስ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም አጠቃላይ የመንገድ ደኅንነት ሕጎችን ማስፈጸም እንደሚያስፈልግና፣ ይህንንም ለማድረግ የሚያግዙ የተለያዩ አሠራሮችን ለመዘርጋት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን የማዘጋጀት ሥራም የዚሁ አካል ሆኖ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ በዋና ዋና መንገዶች ላይም የደኅንነት ካሜራዎችን በመግጠም የትራፊክ ፍሰቱን የመቆጣጠር ሥራ ለመሥራት በዕቅድ መያዙን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ዓምና በትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠንቶ ይፋ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ 68.3 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች ምቹ በሆኑ መንገዶች ላይ ነው፡፡ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከልም 85.9 በመቶ የሚሆኑት በአሽከርካሪዎች ስህተት፣ 3.3 በመቶ በተሽከርካሪው የቴክኒክ ብቃት ጉድለት፣ 2.8 በመቶ በእግረኛ ችግር፣ 0.7 በመቶ በመንገድ ችግር የሚከሰቱ ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ የትራፊክ አደጋዎች የሚከሰቱባቸው ምክንያቶችም በፍጥነትና በቸልተኝነት ማሽከርከር ነው፡፡ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ ጠበቅ በማድረግ አደጋ ከማድረስ እንዲቆጠቡ ማድረግን ያለመ አዋጅም ዓምና ፀድቋል፡፡ አዋጁ ከዚህ ቀደም ሲሠራበት የነበረውን ደንብ ቁጥር 208/2003 በ395/2009 የተካ ነው፡፡ የተሻሻለው አዋጅ ጥፋት ያጠፋው አካል የሚቀጣበትን ስድስት ዕርከኖች አዘጋጅቷል፡፡

ለአንደኛ የጥፋት ዕርከን የሚመዘገብበት የጥፋት ነጥብ አይኖርም ግን 100 ብር ይቀጣል፡፡ በሁለተኛ የጥፋት እርከን የመጀመርያው የጥፋት ነጥብ ተይዞበት 150 ብር ይቀጣል፡፡ በሦስተኛ የጥፋት ዕርከንም ሁለተኛ የጥፋት ነጥብ እንዲያዝበትና 200 ብር ቅጣት እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃዱ እስከመታገድ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ በባለሥልጣኑ የሚሰጠውን የተሃድሶ ሥልጠና እንዲወስድና የማሽከርከር ብቃቱን እንዲያረጋግጥ ካልተደረገ በስተቀር ፈቃዱን መልሶ ማግኘት እንዳይችል ቅጣት ይጣልበታል፡፡ በተባለው ጊዜ ውስጥ ቅጣቱን አለመፈጸምም በእያንዳንዱ በሚያልፉ ቀናት የቅጣቱን አምስት በመቶ ተጨማሪ እንዲቀጣ የሚያስገድደው ቅጣት ይጣልበታል፡፡ አዋጁ ሌሎችንም ዝርዝር ጉዳዮች ያካተተ ቢሆንም እስካሁን ተፈጻሚ ሲሆን አልታየም፡፡    

የትራፊክ ደንቡን በተመለከተ ተሻሽሎ የወጣውን ደንብ ተግባራዊ ለማድረግ ለደንብ ማስከበሮች፣ ለትራፊክ ፖሊሶችና፣ እንዲሁም ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት የደንቡ አተገባበር ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩልም የወጣውን አዋጅ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ባለው የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅም የማይታሰብ ስለሆነ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቩ ነጥቦች ላይ ለማተኮር የመለየት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹ስለዚህም ምን ላይ ትኩረት አድርገን ብንሠራ ውጤታማ እንሆናለን? የሚለውን በቅደም ተከተል ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም በአዲስ አበባ ለሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ዋነኛ መንስኤዎች ምን ምን ናቸው? የሚለውን መለየትና ልናተኩርበት የሚገባንን መምረጥ ነበረብን፤›› በማለት አዋጁን ወደ ማስፈጸሙ ሒደት ከመግባቱ በፊት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገቢ መሆኑን አቶ ጂሬኛ ይናገራሉ፡፡

በዚህ መሠረት የተዘጋጀው የአዲስ አበባ የትራፊክ ደኅንነት ስትራቴጂ ሰባት አቅጣጫዎችን ይዟል፡፡ ስትራቴጂው ተስፈኛ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከተማው ውስጥ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ወደ ዜሮ ማውረድ የሚል ራዕይ ይዟል፡፡ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም የትራፊክ አደጋን በተለይም የሞትና የከባድ የአካል ጉዳት አደጋን በግማሽ የመቀነስ ግብ አለው፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ የተለያዩ የትኩረት አቅጣጫዎችን አውጥቷል፡፡

‹‹ብዙ አደጋ እየደረሰ የሚገኘው በዋና መንገዶች ላይ ነው፡፡ በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን የሚያጡ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ የአደጋው ሰላባዎች የሚገጩት በቀለበት መንገዶች ላይ ነው፡፡ ቀጥሎ በዋና መንገዶች ላይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ 86 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚደርሰውም በእግረኞች ላይ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጂሬኛ የትራፊክ ደኅንነት ስትራቴጂ አስተዳደር ሥርዓቱን ማጠናከር ቅድሚያ የተሰጠው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የእግረኛን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችሉ ሥራዎች በስፋት ሊሠራባቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ቁልፍ የሆኑ፣ እንደ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ በፍጥነት ማሽከርከር፣ የመሳሰሉ የደኅንነት ሕጎች ላይም በደንብ መሥራት ግድ ይላል፡፡ ጠጥቶ በማሽከርከር የሚደርስን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ከባለፈው ክረምት ጀምሮ በተደረገ ጥረት አበረታች ለውጥ ማየት ተችሏል፡፡

በትንፋሽ ውስጥ የሚገኝን የአልኮል መጠን በሚለካው መሣሪያ ከተፈተሹ በከተማው ከሚገኙ 66,000 ሰዎች መካከል 1,000 የሚሆኑት ብቻ ናቸው ከተፈቀደው በላይ አልኮል ጠጥተው የተገኙት፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ በተደረገ አንድ ጥናት ከመጠን ያለፈ አልኮል ጠጥቶ ማሽከርከር 9.7 በመቶ ይደርስ ነበር፡፡ በተሠሩ ዘመቻዎች ግን ቁጥሩ ወደ 3.4 በመቶ ወርዷል፡፡ ‹‹ይኼ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በየዓመቱ በስድስት በመቶ እየጨመረ ይሄድ የነበረው የአደጋው መጠንም ዘንድሮ በሦስት በመቶ ዕድገቱ ቀንሷል፤›› የሚሉት አቶ ጂሬኛ፣ የቀነሰው በየዓመቱ የሚያድገው የአደጋዎች ቁጥር እንጂ ከዓመት ዓመት የሚደርሰው አደጋ አሁንም እየጨመረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡     

አሳሳቢነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የመንገድ ደኅነነት ጉዳይን ማኅበረሰቡ ላይ ለውጥ መፍጠር በሚችል መልኩ እንዴት መዘገብ ይቻላል የሚል ሐሳብ የያዘ የአንድ ቀን የጋዜጠኞች ሥልጠና ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሒልተን አዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ ሥልጠናውን ያዘጋጀው ሮልፍ ሮዜክራንዝ የተባለ ጋዜጠኛ፣ የንግግር ባለሙያ ከግሎባል ሄልዝ አድቮኬሲ ኢንኩቤተር ጋር በመተባበር ነው፡፡