Skip to main content
x
የውጭ ምንዛሪ ለውጡ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ወጪን አናረ

የውጭ ምንዛሪ ለውጡ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ወጪን አናረ

በቅርቡ በውጭ ምንዛሪ ላይ በተደረገው የ15 በመቶ ለውጥ ምክንያት፣ በየካቲት 2010 ዓ.ም. ለሚደረገው አራተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እንዲያገለግሉ የተገዙ 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 128 ሺሕ ፓወር ባንኮች ዋጋ በ144 ሚሊዮን ብር አደገ፡፡

የግዥ ውላቸው በግንቦት 2009 ዓ.ም. የተፈረመው የእነዚህ ዕቃዎች አቅርቦት መጀመርያ በነበረው ውል መሠረት መንግሥት ለአቅራቢዎቹ 665 ሚሊዮን ብር መክፈል የነበረበት ቢሆንም፣ ከአምስት ወራት በኃላ በተደረገው የብር ምንዛሪ ለውጥ ምክንያት የተጠቀሰው ጭማሪ ተከስቷል፡፡

‹‹ውሉ ሲፈረም በውጭ ምንዛሪ ስለነበረ የብር ምንዛሪ ተመን ማስተከከያው የመግዣውን ወጪ ሊጨምር ችሏል፤›› ሲሉ የዕቃዎቹን ግዥ የፈጸመው የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የዕቃዎቹ ግዥ የተፈጸመው በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች አቅራቢነታቸው ከሚታወቁት ሌኖቮና ሁዋዌ ከተባሉ ኩባንያዎች ነው፡፡ በአገልግሎቱ በኩል ግዥው ተፈጽሞ ለማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚቀርበው የሁለቱ ዕቃዎች ግዥ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፉ ይታወሳል፡፡ ስድስት ወራት የፈጀው የግዥው ሒደት በቅሬታዎችና በአቅራቢ ኩባንያዎች መካከል በተፈጠሩ አለመግባባቶች የተሞላ ነበር፡፡

ለወራት የዘለቀው ቅሬታ ጨረታው ተሰርዞ እንደገና እንዲደገም አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ግዥው ተፈጽሞ ዕቃዎቹ ግንቦት 2009 ዓ.ም. ይቀርባሉ ተብሎ የታቀደ ቢሆንም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

የዕቃዎቹ አቅርቦት እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ድረስ ተራዝሞ የጥቅምት ወር መጀመርያ ሳምንት በመንግሥት ከተደረገው የብር ምንዛሪ ለውጥ ጋር ሊገጥም ችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት መጀመርያ በነበረው የዕቃዎቹ ዋጋ ላይ ጭማሪ አምጥቷል፡፡

የግዥው አካሄድ መጀመርያ ከታቀደለት ጊዜ መጓተቱ ካስከተለው የወጪ ጭማሪ በተጨማሪ፣ የቆጠራው ጊዜ ከኅዳር 2010 ዓ.ም. ወደ የካቲት 2010 ዓ.ም. እንዲራዘም ሆኗል፡፡

በመንግሥት 3.5 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እየተደረገ ላለው ዝግጅት፣ አብዛኛው ወጪ ለቆጠራው ለሚያስፈልጉ ግብዓቶች ግዥ ላይ ይውላል፡፡

አንድ ሳምንት ይፈጃል ተብሎ ለሚጠበቀው ቆጠራ ከ190 ሺሕ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ፡፡ ከተገዙት 180 ሺሕ ታብሌቶችና 128 ሺሕ ፓወር ባንኮች ውስጥ አብዛኛዎቹ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መረከብ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በየካቲት 2010 ዓ.ም. ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የቆጠራው ውጤት በስድስት ወራት ውስጥ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡