Skip to main content
x
የምርት ጥራት ከቀበሌ ጀምሮ ቅድሚያ ካልተሰጠው በምርት ገበያ ብቻ በሚደረግ ቁጥጥር የትም አይደረስም

‹‹የምርት ጥራት ከቀበሌ ጀምሮ ቅድሚያ ካልተሰጠው በምርት ገበያ ብቻ በሚደረግ ቁጥጥር የትም አይደረስም››


ዶ/ር ብርሃኑ አምሳሉ፣ የመልካሳ ማዕከል የቆላ ጥራጥሬ ሰብሎች ምርምር አስተባባሪና ተመራማሪ

       በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር በሚገኘው የመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የቦሎቄ ተመራማሪ ዶ/ር ብርሃኑ አምሳሉ  በማዕከሉ የቆላ ጥራጥሬ ምርምር ሥራዎችን በኃላፊነት ያስተባብራሉ፡፡ እሳቸው የሚያስተባብሩት የተመራማሪዎች ቡድን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መጠነ ሰፊ ምርምሮችን በማድረግ ለአርሶ አደሩ የተሻለ ምርታማ የሚያደርጉ ምርጥ ዘሮችን (ቴክኖሎጂ) በማቅረብ ስኬታማ እየሆነ መምጣቱ ይነገርለታል፡፡ በተለይ በቦሎቄ ምርት የተሻለ ስም ማስመዝገብ መቻሉ አገሪቱ ወደ ውጪ ገበያ ከሚላከው የቦሎቄ ምርት ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ እገዛ እያደረገ መሆኑም ይገለጻል፡፡ በዚህም የተነሳ የምርምር ቡድኑ ከሁለት ዓመት በፊት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተዘጋጀው የሽልማት ፕሮግራም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሸልሟል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ግብርና ምርመር ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው የመስክ ጉዞ  ዮናስ ዐብይ ዶ/ር ብርሃኑን አግኝቶ በቦሎቄ ላይ እያተደረጉ ስላሉ ምርምሮች፣ ተግዳሮቶችና ተያያዥ ጉዳዮች አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመልካሳ የግብርና ምርምር ማዕከል በብሔራዊ ደረጃ ከሚያስተባብራቸው ሥራዎች መካከል የቆላ ጥራጥሬዎችን የሚመለከቱ ይገኛሉ፡፡ ስለነዚህ ሥራዎቻችሁና ከጥራጥሬ ዓይነቶች ለቦሎቄ የተለየ ትኩረት ስለመስጠታችሁ ቢያብራሩልን፤

ዶ/ር ብርሃኑ፡- የቆላ ጥራጥሬ የምንላቸውና የምርምር ሥራ ከምናከናውናቸው ውስጥ ቦሎቄ፣ ማሾ፣ ደገራና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ነገር ግን ሰፊውንና ዋና ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ቦሎቄ ላይ ነው፡፡ እንዲያውም ከ85 በመቶ በላይ

የሚሆነውን ጊዜያችንንም፣ ገንዘባችንን ሰጥተን የምንሠራው በቦሎቄ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንዲሁም በማሾና ለሌሎች ላይ በቅደም ተከተል እየሠራን ነው፡፡ በእነዚህም ላይ ትኩረት የተደረገው የገበያ ሰብሎች በመሆናቸው ነው፡፡

በቦሎቄ ላይ ከሠራናቸው ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ምርምሩን በተለያየ መልኩ ቃኝቶ የምርምር ሥራዎችን መጀመር ነው፡፡ አንደኛው ገበያ ተኮር ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆነውን በመለየት ለአገር ውስጥ በሚል ምርምር ማከናወን የሚሉትን ያካትታሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የትኩረት አቅጣጫችሁን በየትኛው የቦሎቄ ሁኔታ ላይ ነበር ምርምራን  የጀመራችሁት?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- ገበያ ተኮር ሊሆን የሚችለውና ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ነጭ ቦሎቄ በመሆኑ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣው ደግሞ ዥንጉርጉሩ ቦሎቄ ሲሆን ይህኛው በገበያ ተፈላጊነት ያለው ቦሎቄ ነው፡፡ ሌሎችንም ተጨማሪ ዝርያዎች በሒደት እያመጣን ነው፡፡ ለገበያ ተኮር ከሆኑት ውስጥ ነጩ ቦለቄ (ትንሹ ዝርያ) ላይ ብቻ ሳንወስን ወደ ትልቁ ዘርም ገብተናል፡፡

ለአገር ውስጥ ምግብ (ፍጆታ) የሚፈልጉት በብዛት የቀይ ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ በእነዚህ የምርምር ሥራ በማከነወን ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ እያደረግን ነው፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ተወስኖ የቆየውም ቀይ ቦሎቄም ቢሆን ወደ ውጪ ገበያ እየገባ ነው፡፡ እኛ በምርምር ማዕከላችን ተሻሽሎ የሚወጣውን ቴክኖሎጂ (የተሻሻለ ዝርያ) ለአገር ውስጥ ብቻ ነበር ስንለቅ የቆየው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን የውጪ ገበያ ፍላጎቱ በመጨመሩ ቀይ ቦሎቄ ከነጩ እኩል ኤክስፖርት ለመደረግ ችሏል፡፡

እነዚህን ዝርያዎች በተመለከተ ከእንግዲህ የምናከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ከነበሩ ዝርያዎች ጋር ያላቸውን ልዩነት እናጠናለን፡፡ በሽታን በመቋቋም በኩል ያላቸውን ችግሮች ለይቶ ማወቅ፣ ለገበያ ሲቀርቡ የሚኖራቸውን የመታሸግ ባህሪና ሌሎች ሊለዩ የሚገባቸውን ጉዳዮች ለይተን በማጥናት ወደ ምርምሩ አምጥተን ዝርያዎቹን ማፍለቅ ይሆናል ዋና ሥራችን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚሁ የምርምር ማዕከል ከዚህ በፊት የተሠሩ ምርምሮችን ምን ይመስላሉ?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- የምርምር ማዕከሉ እንደሌሎች ጥራጥሬና የሰብል ዓይነቶች ሁሉ ምርምር ማድረግ ከጀመረ ከ40 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህም ዓመታት የቆየ ምርምር ቦሎቄን ብቻ በተመለከተ እስካሁን ከ50 በላይ ዝርያዎች (ተሻሽለው)በብሔራዊ ደረጃ ተለቀዋል፡፡

እነዚህም ለምግብነት (ለአገር ውስጥ ፍጆታም) ሆነ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡትን ይጨምራሉ፡፡ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ዝርያዎችን በተመለከተ የምናካሂደው ምርምርም በዚህ መልኩ እያሰፋን የምንሄደው ከመንግሥትና ከውጪ አገሮች ለጋሾች በምናገኘው አገዛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ምርምር ተቋም ያላችሁ አቅም ምን ያህል ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- በእርግጥ ከአጠቃላይ አገራዊ ጉዳይ ከሚፈልገው አንፃር አቅማችን ውስን ነው፡፡ ቀደም ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ምርምር እያካሄድን ያለነው ከመንግሥት በምናገኘው በጀትና ከውጪ አገሮች በዕርዳታ በምናገኛቸው ፕሮጀክቶች ነው፡፡ ከመንግሥት የምናገኘው በጀት በቂ ባለመሆኑ ቴክኖሎጂ ለማፍለቅም፣ ለማስፋፋትም የሚኖረን አቅም ውስን በመሆኑ የተጠቀምነው መንገድ ከአጋር አካላት ጋር መሥራት ነው፡፡ ከባለድርሻ አካላት ስንል ደግሞ ከአርሶ አደር እስከ ላኪዎች ድረስ ያሉትን በማሰባሰብ የምክክር ጉባዔያትን እናዘጋጃለን፡፡ ይህን ጉባዔም በእኛ አጠራር የቦሎቄ ቴክኖሎጂ ማፍለቂያና ማስፋፊያ ፕላትፎርም ይባላል፡፡ ይህ ፕላትፎርም ደግሞ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ፣ በደቡብ ክልል ያሉትን ጨምሮ እስከ ብሔራዊ ደረጃ አለን፡፡ በእነዚህ ፕላትፎርሞች በመታገዝም ነው ቴክኖሎጂውን የምናስፋፋው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ፕላትፎርሞች ከአርሶ አደር እስከ ላኪ ያካተቱ ብለው በገለጿቸው ውስጥ የናንተ ድርሻ ከቴክኖሎጂ ማፍለቁ ባሻገር ምንድነው? ሌሎችስ?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- በፕላትፎርሙ ውስጥ በርካታ አካላት ውስጥ ሲኖሩ ለመጥቀስም ያህል፣ አርሶ አደሮች፣ ዘር አምራቾች፣ ማኅበራት፣ ነጋዴዎች፣ የዘር ጥራት ተቆጣጣሪዎችና ሌሎች ተያያዥ ሥራ የሚያከናውኑ አካላት በእሴት ሰንሰለት ውስጥ የምንገናኝ አካላት ሁሉ ይጨምራል፡፡ ከእነዚህ አጋሮች ጋር እንመካከረለን፣ ድርሻም እንከፋፈላለን፡፡ የዘር አቅርቦቱ ላይ የእኛ አቅም ውስን ስለሆነ መነሻ ዘር እናባዛለን፡፡ ያባዛነውንም ዘር ለዘር አባዥ አካላት ነው የምንሰጠው፡፡ የዘር አባዥ አካላት የምንለው ደግሞ በውስጡ ዘር አምራች አርሶ አደሮች፣ ዘር አምራች ማኅበራት፣ የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ማኅበራት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቋቋሙ ያሉ የክልል ምርጥ ዘር ድርጅት ኢንተርፕራዞችንና የግል ባለሀብቶችን ይጨምራል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ቴክኖሎጂውን ወይም መነሻ ዘሮችን እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የዘር አቅርቦት (መነሻ ዘርንም ሆነ የተባዛ ዘርን) በአገር አቀፍ ደረጃ ለሌሎች የሰብል ዓይነቶችን ጨምሮ ውሱንነት መኖሩ ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ በስንዴ፣ በገብስና በቆሎ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደር በሚፈለገው መጠን እየቀረበ አለመሆኑ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቦለቄስ በኩል እናንተ የምታቀርቡት ከፍላጎት አንፃር እንዴት ይላካል?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- በዚህ ጉዳይ እኛ እያቀረብን ያለው ቴክኖሎጂ ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ነገር ግን የሚቻለውን ያህል ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ ከቴክኖሎጂ ማፍለቁ ባሻገር በዚሁ ሰንሰለት ውስጥ ውስንነት በሁሉም በኩል አሉ፡፡ በተለይ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ረገድ በቂ ዘርም እየተባዛ አይደለም፡፡ ያለን የዘር አባዦችም በቁጥር ውስን ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ይህንን የተሻሻለ ዝርያ በመውሰድ ሰብል የሚያመርቱ አርሶ አደሮች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሁሉ አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ ችግሮች አሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያልተማከለ የዘር ማባዛት ሥርዓትን በማምጣት ያልተማከለ ዘር አምራቾች፣ ማኅበራትን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና ሌሎች አካላትን እየጨመርን ወደ ዘር ማባዛቱ ሥርዓት እያስገባን ያለነው፡፡ ይህም ቢሆን ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ይቀርፈዋል ባይባልም ቢያንስ በመጠኑም ቢሆን የዘር አቅርቦቱን ሊያሻሻል ይችላል በሚል እምነት ነው፡፡ ይህ እንዳለም ሆኖ እጥረቱን በይበልጥ ለመቅረፍ በቂ የሆነ መሬት ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የዘር ማብዛቱ ላይ ለተሰማሩ የግል ድርጅቶች፣ ማኅበራትም መሬት በስፋት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እንደሚታወቀው በአብዛኛው ዘር አባዦች የተሰማሩት በተወሰኑ የሰብል ዓይነቶች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በበቆሎ፣ በስንዴና ገብስ ላይ ነው በስፋት የተሰማሩት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እንኳ አብዛኞቹ ዘር አባዦች የሆኑት የአገር ውስጥም ሆኑ የውጪ ድርጅቶች በቁጥር አንድ ተብሎ ሊገለጽ በሚችል መልኩ ብንመለከት በበቆሎ የዘር ማምረቱ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በቆሎ በባህሪው ከሁሉም ሰብሎችና የጥራጥሬ ዓይነቶች የተሻለና ከፍተኛውን ምርት ሔክታር የሚሰጥ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎም ስንዴና የመሳሰሉት ይመጣሉ፡፡ የአገዳና ብርዕ ሰብሎች እንዲሁ ይከተላሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የዘር አባዥ ድርጅቶች ቀዳሚ ፍላጎት የበቆሎ ዘር ማባዛቱ ላይ ነው የሆነው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው አብዛኞቹ አምራቾች በቦሎቄ ላይ እንዲሰማሩ ጥያቄዎችን ስናቀርብላቸው ቶሎ የሚቀበሉን፡፡

ሪፖርተር፡- ለውጪ ገበያ እየቀረበ ያለው የጥራጥሬ ዓይነት የሚያስገኘው ውጭ ምንዛሪ በፍጥነት እያደገ ስለመምጣቱ ከመንግሥት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በእናንተ የምርምር ማዕከል የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች ለዚህ የውጭ ምንዛሪ ዕድገት የራሱ ድርሻ አለው ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- ይኼ እውነታ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ በማቅረብ አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ከሚገኙ የግብርና ምርቶች ውስጥ የጥራጥሬ ምርት አንደኛው ነው፡፡ ከግብርና ምርቶችና ሰብሎች ካየን የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ ካሉት የሚቀድመው ቡና ሲሆን፣ ቀጥሎ የሚመጡት ሰሊጥና የቅባት እህሎች ነው፡፡ በእርግጥ ቡናና ሰሊጥ ከዓመት ዓመት የሚዋዥቁ ቢሆንም፣ የጥራጥሬ ዘርፍ እነሱን ይከተላል፡፡ ከጥራጥሬ ብቻ ካየነው ትልቁ (የውጭ ምንዛሪ አስገቢው) የቦሎቄ ምርት ነው፡፡ እነ ማሾ፣ እነ ሸንኮራ የመሳሰሉት ጥራጥሬዎች ቦሎቄን ተከትለው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ቦሎቄን ብቻ ወደውጭ ገበያ በመላክ እያገኘን ያለነውን ብንመለከት እንኳ 100  ሚሊዮን ዶላር አያንስም፡፡ ይኼ እንግዲህ ዝቅተኛ ገቢው ብንመለከተው ነው፡፡ አሁን ያለንን ደረጃም ቢሆን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡ ቦሎቄን የማምረት ሥራን በበርካታ ቦታ እንዲሸፍን ማድረግ አንዱ ተግባር ነው፡፡ ምናልባት ብዙ ሰው ያውቀዋል ተብሎ የማይታሰበውን አንድ ምሳሌ ማንሳት እችላለሁ፡፡ ለአብነትም በደቡብ ጎንደር ጋይንት አካባቢ ነጭ ቦሎቄ ተመርቶ ወደ ውጭ ገበያ ይላካል  ተብሎ በብዙ ሰው አይገመትም፡፡ አሁን ይኼ ሥራ ኤስኤንቪ (SNV) ከተባለው የሆላንድ ድርጅት ጋር በመሆን የተሠራ ነው፡፡ በዚሁ ቦታ አንድ ዩኒየን ብቻ በራሱ አምርቶ ባለፈው ዓመት ቦሎቄ ለውጭ ገበያ አቅርቦ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ አስገብቷል፡፡ ከነዚህ አሠራሮች አንፃር ሥራችንን የበለጠ በማስፋፋት ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜቃ ለአገሪቱ እያበረከትን ነው ማለት እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት የዚህ የጥራጥሬ ዓይነት ከአገሪቱ የማምረት አቅም ብዙ መሥራት የሚጠበቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደተመራማሪ ከእናንተ የተለቀቀው ቴክኖሎጂ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያደርገው እገዛ አርኪ የሚባል ደረጃ ደርሷል ይላሉ?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- ከምርምር ተቋም ያወጣነው ቴክኖሎጂ አገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማምጣት ሲችል የሚሰጠው እርካታ ይኖራል፡፡ ጥሩ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ የምትፈልገውን ይህል ሠርተናል ወይ የሚለውን ካየን ግን ገና በቂ አይደለም፡፡ ማደግ ይኖርበታል፡፡ መለወጥም ይኖርበታል፡፡ አንደኛው ማደግና መለወጥ ያለበት ጉዳይ በጥራት በኩል ያሉ ጉዳዮችን ይመለከታል፡፡ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ሊለዩ የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠትና ከቴክኖሎጂ ማቅረቡ አንስቶ እስከ ዘር ማባዛቱና አርሶ አደሩ ድረስ ባሉ ሰንሰለቶች ጥራትንና ምርታማነትን የሚቀንሱ ችግሮች ላይ ብዙ ሊሠሩ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘር ጥራት ጋር በተገናኘ በአገር ውስጥ ቦሎቄን ፕሮሰስ በማድረግና በማሸግ የተሰማሩ ላኪዎች የሚያነሱዋቸው ችግሮች አሉ፡፡ በተለይ አርሶ አደሮች ለላኪዎች ምርትን በሚያቀርቡበት ወቅት ዝርያዎችን ይቀላቅላሉ ይባላል፤

ዶ/ር ብርሃኑ፡- ለመግለጽ እንደሞከርኩት በዚህ ዘርፍ የጥራት ጉዳይ ማደግ ያለበት መሆኑን የምናምነው ጉዳይ ነው፡፡ በእርግጥ የዘር አባዦች እስካሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በጥሩ ሁኔታ የተለቀቀውን ዝርያ አምርተው እያቀረቡ ነው፡፡ ችግር ከዚያ በኋላ አካላት በኋላ ዘርን ከዘር የመቀላቀል ነገር አለ፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ አንዱን የቦሎቄ ዝርያ ከሌላው የቦሎቄ ዓይነት ጋር መቀላቀል ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ሌሎች ባዕድ ነገሮችን የመጨመር ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን በመቅረፍ ረገድ ገበያው ላይ ብዙ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ጥራት ማረጋገጥ እስካስፈለገ ድረስ ገበያው ላይ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

የቦሎቄ ግብይት በኢትዮጵያ ንግድ ገበያ በኩል በማዕከል መሸጥ መቻሉ ጥሩ ዕድል ነው፡፡ አሁን ችግሩ ጎልቶ ያለው በታች ደረጃ ያለው ገበያ ላይ ነው፡፡ በቀበሌ ወይም በትናንሽ ከተማ፣ አቅራቢውንም ባተኮረ መልኩ ጥራት ያለው ግብይት ይካሄዳል ወይ የሚለው መታየት ያለበት ጥያቄ ነው ፡፡ ጥራት ያስከፍላል ወይ? ገበያስ ያስገኛል ወይ የሚሉ ጉዳዮች ላይ በአግባቡ መሠራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በምን መልኩ የታችኛው ገበያ ሊመራ ይገባል ይላሉ?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- ለምሳሌ የታች አቅራቢዎችን በተመለከተ ጥራትን ትኩረት ያደረገ የዋጋ ተመን እስከመተመን ድረስ ሊሠራ ይችላል፡፡ ቦሎቄ በኩንታል 1,000 ብር በዚያ ዋጋ ይሸጣል እንበል፡፡ ጥራቱን ምንም ዓይነት ቢሆን በተመሳሳይ ዋጋ መሸጥ ምን ማለት ሊሆን ይችላል? ብለን ማየት አለበን፡፡ አንደኛ ደረጃ ጥራት ያለው ዋጋ 1500 ብር ወይም 2000 ብር ነው ብለህ ብትጀምርና ጥራቱ ላነሰው እንዲሁ ያነሰ ዋጋ ቢወጣለት ሁሉም አቅራቢ ለተሻለ ጥቅሙ ሲል የተሻለ ምርት በተሻለ ጥራት ያቀርባል፡፡ አሁን ዋጋውን ከጥራቱ አኳያ ምርት ገበያ ላይ ብቻ ብትወስነው ዋጋ የለውም፡፡ ምርትም ገበያ ላይ ያለው አሠራር ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ መሠራት ያለበት ቀበሌ ላይ ነው፡፡ የምርት መገበያያን ዓይነት አሠራር ማሳየቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በአግባቡ ግብይቱን ለማካሄድ ያስችለናል፡፡ ለችግሩ የተሻለ ትኩረት መስጠት የሚገባው ግን ከታች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ከታች ግብይትን በተመለከተ አቅራቢዎችን ወይም አምራቾችን ማን ነው ሊያግባባቸው የሚገባው? ማንስ ነው በጥራቱ በኩል ሊቆጣጠራቸው የሚገባው የሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች ሁሉ አብሮ መታየት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጨረሻም በእናንተ በተመራማሪዎች በኩልስ  በዚህ ረገድ ምን ተስፋ ነው የሚጠበቀው?

ዶ/ር ብርሃኑ፡- በእኛ የምርምር ዘርፍ በተቻለን መጠን እያደረግን ያለነው አዳዲስ ዝርያዎችን በማፍለቅ፣ ነባር የሆኑ አሮጌ ዝርያዎችን መተካት ነው፡፡ ለምሳሌም ለረዥም ዓመታት ስንሠራበት የቆየነው እንደ አዋሽ -1 የሚባለው የቦሎቄ ዝርያ አንዱ ነው፡፡ ይኼንን ዝርያ በአዋሽ -2 በሚባለው ዝርያ ለመተካት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ከአዋሽ -2 ወደ አዋሽ -3 በመሄድ የተሻለ ዝርያም እያወጣን ነው፡፡ አሁን ያለው ከፍተኛ ችግር የነቀዝ ችግር ነው፡፡ የነቀዝ ተፅዕኖ መቋቋም የሚችል ዝርያ ማፍለቅ ጀምረናል፡፡ እንዲሁም ገበያውን ተኮር ያደረጉ ሌሎች ዝርያዎችን እንዲሁ በየመስኩ እያወጣን ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቁ ነጭ ቦሎቄ ወደ ገበያው በደንብ አልገባም፡፡ ያንን ወደ ገበያው ማስገባት ያስፈልገናል፡፡ ዥንጉርጉሩ ቦሎቄም እንደፈለግነው መጠን ገና ወደገበያው አልገባም፡፡ ዥንጉርጉሩ ቦሎቄ እንደ ነጩ ሁሉ ተመሳሳይ ዋጋ ያለው ሲሆን፣ አሁን ወደገበያ ማስገባት የግድ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ነጩ ቦሎቄ ነው በስፋት እየተመረተ ያለው፡፡ ስለዚህ በሌሎችም በስፋት መሠራት አለበት፡፡ በአጠቃላይ በነዚህና በሌሎችም ጨምሮ የመነሻ ዘር ማቅረቡን በማጠናከር ላይ እንገኛለን፡፡