Skip to main content
x
የኖርዌይ ልዑል አልጋ ወራሽ ጉብኝት

የኖርዌይ ልዑል አልጋ ወራሽ ጉብኝት

ከግማሽ ምዕት በኋላ ከኖርዌይ ንጉሣዊ ቤተሰብ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያን እየጎበኙ ያሉት አልጋ ወራሹ ልዑል ሃኮን ማገኑስ እና ባለቤታቸው ልዕልት ሜቲ ማሪት አዲስ አበባ ጥቅምት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲደርሱ በብሔራዊ ቤተመንግሥት የክብር አቀባበል ያደረጉላቸው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ከባለቤታቸው ወ/ሮ መዓዛ አብርሃም ጋር በመሆን ነው፡፡ ‹‹እንኳን ደህና መጡ ወደ ምድረ ቀደምት ኢትዮጵያ›› በሚል ጽሑፍ ጭምር አቀባበል የተደረገላቸው ልዑል ሃኮን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አያቴ የዛሬ 50 ዓመት በረገጣት መሬት ታሪክን በመድገሜ ደስተኛ አድርጎኛል፤›› ብለዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ባደረጉት ምክክር አገሮቹ ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ገልጿል። ኢትዮጵያና ኖርዌይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት 1940 ዓ.ም. ነው።  የሥርዓታዊ አቀባበል ልዩ ልዩ ገጽታ ፎቶዎቹ ያስቃኛሉ፡፡

  • በዳንኤል ጌታቸው

*****

ቡና? . . . . .ማኪያቶ?

ምክኑስ? አልኩ፡፡

ነገሩ የምፀት ነው፡፡

ብዙ አስቤ ተመራምሬ፣

በዚህ የእኔ ዐዋቂነት ላይ አትኩሬ፣

ራሴን ከፍ አድርጌ አክብሬ፣

በለቀምኩት፣ ባካበትኩት ጥሬ ዕውቀት

ብዙ ኮርቼ፤

ከኩራቴም ብዛት፣ ብዙ፣ እጅጉን ብዙ ታብቼ፣

እጅጉን ብ-ዙ ቆይቼ፣

ድንገት - እንዴው ድንገት

ጎዶሎ አንደበቴ ብትፈታ አንድ ጥያቄ ተጠይቄ፤

      ‹‹ቡና ይምጣልዎ ማኪያቶ?››

የምትል፤

      ‹‹ለማንኛውም እስቲ ጉዳዩ ይቅረብልኝ

      ‹‹በመጀመሪያ ተጠንቶ፡፡››

ብዬ ተነፈስኩኝ፤ ጥናት ልምድ ሆኖብኝ፡፡

እናም፣ ሊጠጣ የቀረበ ቡና፤ እናም ማኪያቶ፤

እንዲመለስ ሆነ፤ ዳግም እንደገና ሊቀርብ ተጠንቶ፡፡

ሲጠና፤

ሁሉም በረደና፤

በሪዱ ቆይቶ ቀረበና፤ በመብረዱም ተናቀና፤

ሊጠና የሄደው ማኪያቶ፣ ደግሞም ቡና፤

ተጎልቶ ከዚያው ቀረ፤ እንዳልነበረ ተረሳና፤

ደግሞ እስኪፈላ ሌላ ቡና፡፡

መጋቢት 1966 ዓ.ም.

  • ዮናስ አድማሱ ‹‹ጉራማይሌ›› (2006 ዓ.ም.)

******

በሩ ግን አልተዘጋም

በአንድ መንደር ውስጥ አግብታ ብዙም ሳትቆይ ባሏን በሞት የተነጠቀች አንዲት ሴት ትኖር ነበር፡፡ አጠገቧ ዓይኗን የምታሳርፍባትና የምታጽናናት ብቸኛ ልጅ ነበረቻት፡፡ አንድ ልጇንም በርኅራኄና በፍቅር አሳደገቻት፡፡ ይሁን እንጂ በጥንቃቄ ብታሳድጋትም ልጇ ካደገች በኋላ የበለጠ ወደ ዓለም አዘነበለችና መንደሯን ለቅቃ ወደ ዋናው ከተማ ጥላት ኮበለለች፡፡ የልጅቷ እናት በሐዘን ተሰብራ ልጄ ከዛሬ ነገ ትመለስ ይሆናል ብላ ብትጠብቃትም እሷን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፡፡

የኮበለለችው ልጇ እንድትመለስ ሌትና ቀን እየጸለየች ዓመታት አለፉ፡፡ አንድ ምሽት አንድ የእግር ዱካ ድምፅ ወደ ቤቷ በሚወስደው ጠባብ መተላለፊያ እየተቃረበ ሲመጣና ወደ በሩም ተጠግቶ የበሩን እጀታ እየፈራ እየተባ ሲነካ ሰማች፣ እጀታውም ድምፅ አሰማ፡፡ በእንቅልፍ ሰመመን እንዳለች አንድ ሰው ወደ ውስጥ መዝለቁን እናት ትሰማና ካልጋዋ ተፈናጥራ በመነሳት ወደ በሩ ታመራለች፡፡ የኮበለለችው ልጇ ናት፡፡ ልቧ በደስታ እየዘለለ ልጇን በፍቅር በእቅፏ ውስጥ ወሸቀቻት፡፡ እንደተቃቀፉም፣ ልጇ፣ ‹‹እማዬ፣ በዚህ በእኩለ ሌሊት ለምን በሩን አልቆለፍሺውም?›› ብትላት፣ እናት የልጇን ጸጉር እየደባበሰች፣

‹‹ልጄ ሆይ፣ አንቺ ከኮበለልሽበት ቀን ጀምሮ ምናልባት አንድ ቀን ስትመለሺ ልትቀበልሽ ሁሌ ዝግጁ የሆነች እናት እንዳለሽ እንድታውቂና ሳታመነቺ እንድትገቢ በማሰብ በሩ በቀንም ሆነ በሌሊት ተቆልፎ አያውቅም›› ስትል መለሰችላት፡፡

  • ኃይሌ ከበደ ‹‹ምስካይ›› (2004)