Skip to main content
x
ዓባይ ባንክ የ30 በመቶ የትርፍ ዕድገት አስመዘገበ
የዓባይ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ታደሰ ካሳ

ዓባይ ባንክ የ30 በመቶ የትርፍ ዕድገት አስመዘገበ

ዓባይ ባንክ ከ872 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በማግኘት፣ በ2009 ዓ.ም. ከግብር በፊት ያገኘው ትርፍ በ30 በመቶ በማደግ 249 ሚሊዮን ብር እንደረሰ ሲያስታውቅ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱንም በ53 በመቶ ማሳደጉን ገልጿል፡፡

ባንኩ ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት እንደተገለጸው፣ በሁሉም የባንክ አገልግሎት ዘርፎች ብልጫ የታየባቸው ውጤቶች በማስመዝገብ የትርፍ መጠኑ በ30 በመቶ እንዳደገ አስታውቋል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ታደሰ ካሳ እንደገለጹት፣ የባንኩ ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ 6.8 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከ2008 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ41 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዓመቱ በሁሉም የተቀማጭ ዓይነቶች (በቁጠባ ሒሳብ፣ በተንቀሳቃሽ ሒሳብ ተቀማጭና በጊዜ ገደብ ተቀማጭ) በኩል ትልቅ ዕድገት እንዳሳየ አቶ ታደሰ ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ በቅርቡ በጀመራቸው በወለድ ነፃ ተቀማጭ፣ በሕፃናት፣ በሴቶችና በወጣቶች ተቀማጭ ሒሳቦች ላይ የታየው ዕድገት አበረታች እንደሆነ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ዓባይ ባንክ ለተለያዩ ዘርፎች የሰጠው አጠቃላይ የብድርና ቅድሚያ ክፍያዎች መጠን ወደ 4.3 ቢሊዮን ብር ሲያድጉ፣ ከካቻምናው አኳያም የ37 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ ለተለያዩ የንግድ ዘርፎች የሰጠው ብድር ከ2008 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በተለይም ለወጪ ንግድ የሰጠው የብድር መጠን ከፍተኛ ድርሻ ነበረው ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ 24 በመቶው ለዓለም አቀፍ ንግድ ሥራዎች የዋለ ሲሆን፣ በገንዘብ ሲገለጸም 1.02 ቢሊዮን ብር ያህል ነበር፡፡ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ 21.8 በመቶ፣ ለትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን የዋለው ብድር 19.1 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ በተለይ ለትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የሰጠው ብድር ከ2008 ዓ.ም. አኳያ በ83 በመቶ ዕድገት ታይቶበታል፡፡ ካቻምና ለዚህ ዘርፍ የ445 ሚሊዮን ብር ገንዘብ ሲያበድር፣ በ2009 ዓ.ም. ግን በእጥፍ ያህል ጨምሮ ወደ 815 ሚሊዮን ብር አሳድጎታል፡፡ በአንፃሩ ለግብርና፣ ለማዕድንና ለውኃ ሀብት የሰጣቸው ብድሮች ከ2008 ዓ.ም. አኳያ አነስተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

የባንኩ ደንበኞች ቁጥር በ45 በመቶ አድጎ 337,120 የደረሰ ሲሆን፣ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠንም 8.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የ39 በመቶ ጭማሪም አሳይቷል፡፡

ባንኩ ዓምና ከፍተኛ ውጤት ካገኘባቸው ዘርፎች ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ የኋላ ገሰሰ ‹‹ምንም እንኳ በዓለም አቀፍ የባንኮች አሠራር ውስጥ የታየው የፖሊሲ ለውጥ የውጭ ምንዛሪ ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም ባንኩ 123 ሚሊዮን ዶላር ማሰባሰብ ችሏል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ይህ አፈጻጸም የ53 በመቶ ብልጫ በማሳየት ከ2008 ዓ.ም. የተሻለ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ ካሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ከወጪ ንግድ የተገኘው 79 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ በስዊፍት ከተላኩት የውጭ አገር ገንዘቦች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከጠቅላላ በጀቱ የ13 በመቶ ድርሻ እንደነበረውም ተጠቅሷል፡፡

ዓባይ ባንክ በ2009 ዓ.ም. 34 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በክልልና በአዲስ አበባ በመክፈት የቅርንጫፎቹን ብዛት 144 አድርሷል፡፡ በነባሮቹና በአዳዲሶቹ ቅርንጫፎቹ አማካይነት 105,142 አዳዲስ ደንበኞችን እንዳፈራ አስታውቋል፡፡ ይህም የመደበኛ ቁጠባና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞቹን ቁጥር ከ337 ሺሕ በላይ ለማድረስ አስችሎታል ተብሏል፡፡ በዚህ ረገድም የ45 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን አስታውቋል፡፡

የዓባይ ባንክ የተከፈለ ካፒታል በአሁኑ ወቅት አንድ ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. 344 አዳዲስ ባለአክሲዮኖችን የተቀበለ ሲሆን፣ የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር ወደ 3,929 ከፍ ማለቱም ታውቋል፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር መጨመር ግን የዓመታዊ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል መጠኑ ላይ ብዙም ቅናሽ አላሳየም፡፡ ባንኩ የአንድ ሺሕ ብር ዋጋ ላለው አክሲዮን የከፈለው የትርፍ ድርሻ 229 በመቶ ሆኗል፡፡ በ2008 ዓ.ም. በአንድ አክሲዮን የነበረው የትርፍ ድርሻ ክፍፍል 230 በመቶ ነበር፡፡