Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

ከሁለት ዓመት በፊት ከሜክሲኮ ወደ ሰባተኛ የሚሄደውን ታክሲ ለመሳፈር በጠዋት መነሳት ነበረብኝ፡፡ እንደ ወትሮው በትራንስፖርት ተጠቃሚ ስላልተጨናነቀ ብዙ ሳልደክም ከታክሲው ጋቢና ቁጭ አልኩ፡፡ ታክሲው ስላልሞላ ወያላው እየተጣራና ሾፌሩ መሪውን  እንደያዘ አንገቱን ወደ ኋላ እያጠማዘዘ ተሳፋሪው መሙላቱና አለመሙላቱን ያይ ነበር፡፡ ከምሠራው ሥራ አንፃር ወደ መሥሪያ ቤቴ በጠዋት ለመድረስ ስለቸኮልኩ ሐሳቤ ጉዞዬ ላይ ነበር፡፡ በዚህ መሀል ነበር የአንድ ምስኪን የኔቢጤ የልመና ድምፅ ከሐሳቤ ያባነነኝ፡፡

      ˝ወገን. . . ወንድሜ . . . አንድ አንድ ብር ጣል ጣል አድርጉልኝ፤’’

      ‘’ጎበዝ. . . ተባበሩኝ ያለእናንተ ማንም የለኝ፤’’

     ‘’ ስለእመብርሃን. . . ስለኢየሱስ አንድ አንድ ብር ጣሉልኝ፤’’

ከጋቢና ኋላ ያሉት ተሳፋሪዎች እንደ አቅማቸው የሰጡትን ለቃቀመ፡፡  እኔም የሰውዬው ሁኔታ ስላሳዘነኝ ሃምሳ ሳንቲም ከኪሴ ለማውጣት ኪሴን ብዳብስ አንድ ብር  (ሳንቲም ሆኖ አይደል) ወጣ፡፡ ተንጠራርቼ ሰጠሁት፡፡ የኔቢጤው ያገኘውን ሰብስቦ በታክሲው ፊት ለፊት አልፎ ሾፌሩን በመስኮት ቆጣ ብሎና ድምፁን ዝቅ አድርጎ ሲያነጋግረው ሰማሁ፡፡

"አንተ ደደብ! እንደ ሸቀጥ ሰው ላይ ሰው ደርበሃል አይደል? ለመኪናው አታስብም?  መኪናው አንድ ነገር ይሁን ብቻ፤" አለው፡፡ ሾፌሩ ምንም መልስ ሳይሰጥ አንገቱን ደፍቶ ዝም አለ፡፡ የኔቢጤው ከሄደ በኋላ ነገሩ ግራ ገብቶኝ ሾፌሩን የኔቢጤው ሲያነጋግረው ለምን እንደፈራ ጠየኩት፡፡

    "ጌታው ታክሲው እኮ የሱ ነው፤" አለኝ፡፡

  "የለማኙ ማለቴ የኔቢጤው?" ስል በመገረም ጠየቅኩት፡፡

"ሰውዬው ሀብታም የኔቢጤ ነው፤" ሲል መለሰልኝ፡፡ ወዲያው ስለራሴ አሰብኩኝ ያልተከፈለ የሱቅ ዕዳ አለብኝ. . . የቤት ኪራይ ክፍያዬ ሦስት ቀን አልፎታል. . .  ወጪዬን በመፍራት በዝግታ እየተራመድኩ ባለሁበት ሰዓት ለኔቢጤ  የሰጠሁት አንድ ብር ቆጨኝ፣ ለሀብታም የኔቢጤ፡፡

በቅርቡ ደግሞ ምክትል ኢንስፔክተር ኃይሉ ከበደ በሰይፉ ፋንታሁን ታዲያስ አዲስ ፕሮግራም ላይ በስልክ ቀርበው፣ "የየኔቢጤ ብር ቆጠራ አደከመን፤" የሚል ሰሞታ አቅርበው ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በተለምዶ ሰባ ደረጃ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ካላቸው ቤት እየወጡ የዳቦ መግዣ እያሉ ይለምኑ ነበር ሀብታሟ የኔቢጤ፡፡ ቁጠባውን እንጃ እንጂ ይህንን ሥራቸውን (ይቅርታ ልመናቸውን) ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከውኑት ኖረዋል፡፡ የለመኑትን ብር ታዲያ በፌስታል እየቋጠሩ ቤታቸው ላይ መከመር ተያያዙት፡፡

በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ ከ1970ዎቹ ጀምረው ከቤታቸው የቆለሉት ብር መጥፎ ጠረን ፈጥሮ የአካባቢውን ሰዎች ስላስቸገረ ለፖሊስ ጥቆማ ያደረጉት (ሰዎቹ ግን ምን ዓይነት አፍንጫ ነው ያላቸው? ከራሳቸው ቤትና ግቢ አልፎ ከሌላ ቤት ያለውን የብር ጠረን የሚለየው? ለማንኛውም የፖሊስ ሪፖርት ነው)፡፡ ፖሊስ ወደ ሥፍራው አምርቶ ቤታቸውን ሲፈትሽ ታዲያ ያልተጠበቀ ሁኔታ ገጠመው፡፡ ለመቁጠር የሚያስቸግር፣ በሚያሳዝን ሁኔታ እንደ ቆሻሻ የተጠራቀመ የብር ክምር፣ በርካታ ብሮችና ሳንቲሞች በፌስታል፣ በልብሶችና በተለያዩ ድሪቶዎች እየተጠቀለሉ ክፍሉን ሞልተዋል፡፡

መቁጠር የሰለቻቸው ፖሊሶች ብሩን አቅራቢያው ወደሚገኝ ባንክ ይወስዱታል፡፡ ከባንክ ውስጥ የድሮ ብሮች ከአሁኑ ብሮች ተለይተው፣ የተጣበቁ ብሮችን ለማቃናት፣ ሳንቲሞችን ለመቁጠር ብዙ ጊዜ ወስደው አስቸጋሪውን ጠረን ተቋቁመው 39,346 ብር ቆጥረው ቅዳሜ ስለሆነና ሰዓቱ ስለመሸ፣ መጠኑ ያልታወቀ ብር ለሰኞ እንዳስተላለፉ ነበር ምክትል ኢንስፔክተሩ የተናገሩት፡፡

ሀብታም የኔቢጤዎች ያሉት በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም፡፡ በገጠሩም አሉ፡፡ የገጠሩን ሀብታም የኔቢጤ  ካነሳን  አባ አዝመራውን የሚያህላቸው የለም፡፡  አዝመራው የሚል ቅጽል ስም  ያወጣላቸው መፅዋቹ የአካባቢው ማኅበረሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም እሳቸው የሚለምኑት ገንዘብ አይደለም፡፡ አዝመራ (እህል) ነው፡፡ ያውም በቀኝ እጅ የሚሰጥ  ሰው ብቻ ነው የሚቀበሉት፡፡ ማንም በግራ እጁ ደፍሮ ከሰፈረላቸው  የእርግማን መዓት ያዥጎደጉዳሉ፡፡ ከእሳቸው አንደበት ስለማርያም. . . ስለእግዚአብሔር ብሎ ነገር  የለም፡፡ በቀኝ ይሰፈርልኝ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሀብት አላቸው (እሳቸውን ሳይጨምር)፡፡ የናጠጠ የገጠር ቤት፣ ብዙ ልጆችና የልጅ ልጆች  አሏቸው፡፡  በዚህ የልመና ሥራቸው ታዲያ ከሁሉም ልጆች ጋር  ተጣልተዋል፡፡ ተው ያለህ ይበቃሃል ይሏቸዋል ልጆቹ፡፡

እሳቸው ታዲያ ምን ገዷቸው ያለሥራ? (ለእሳቸው ሥራቸው ልመና አይደል) ከመኖር እየሠራሁ ብሞት ይሻለኛል ብለው ልጆቻቸውን አፍንጫችሁን ላሱ ብለዋቸዋል፡፡ በገበያ ቀናት የተለያየ ዓይነት ስልቻ ቋጥረው በጠዋቱ ወደ ገበያ እብስ ይላሉ፡፡ ‹‹ልጄ ጎሽ በቀኝ ነው እሽ. . .  የጤፉን ከጤፍ ሽልጫ ነው የሚደረገው. . .  በቆሎ ነው ግዴለም በዚህኛው ሽልጫ ውስጥ ጨምሪ. . .›› የልመናው ሥራ ጋብ ሲልና ገበያው መበተን ሲጀምር የእሳቸው ገበያ ይጀመራል፡፡

ታዲያ የአባ አዝመራውን እህል መሸመት የለመዱ ነጋዴዎች እየተሻሙ የቅዳሜ ሹር ገበያ ያስመስላሉ፡፡ እናም አዝመራው ከሰው በላይ ገንዘባቸውን ቋጥረው አንድ ሁለት ብለው መጠጥ  ቀማምሰው ወደ ቤታቸው እያንጎራጎሩ  ያገኙትን ሰው እያሳቁ  ‹እየፎገሩ› ይሄዳሉ፡፡ "አንተ ሰሞኑን ያችኛዋ ቀላ ያለች ልጅህ  በግራ እጇ አትሰፍርልኝ  መሰለህ. . . በእውነት ለአንተ ስል ብቻ ነው በትንሽ እርግማን  ብቻ የማርኳት. . ." ይላሉ፡፡ ታሪኩ ይቀጥላል፡፡

(ብርሃኑ በቀለ - ድሳካር፣ ከአዲስ አበባ)