Skip to main content
x

እስኪ እንጠያየቅ!

በአበራ ዋቅጋሪ

በደርግ ጊዜ ካሳሁን ገርማሞ የሚባል ሰው በፖሊስ ፕሮግራም ውስጥ ‹‹ተጠየቅ!!›› ይል ነበር በግጥም፡፡ ተጠየቅ በቀድሞው የሙግትና የክርክር ሥርዓት ከሳሽ ወይም ጠያቂ ክሱንና የክሱን ምክንያት በዳኛ ፊት ይዘራና ተከሳሹን ወይም ተጠያቂውን፣ ክስህን ስማና በል መልስህን ስጥ ብሎ የሚያስገድድበት ወግ ማዕረግ ያለው ጥሪና ጩኸት ነበር፡፡ ሳይጠየቁ መቅረት እንዲህ ‹‹ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ›› ሳይደላደል በፊት ተጠየቅ ፖለቲካው ውስጥ ዜጋ መንግሥትን፣ ምንዝር አለቃን፣ ተማሪ አስተማሪን ደፈሮ መልስ ስጥ የሚልበት መሣሪያ መሆን ሞክሮ ነበር፡፡ ዛሬም ሆድ ከአገር የሚሰፋበት ኢትዮጵያ ውስጥ ብንኖርም፣ ሐሳብን የመግለጽና ተጠየቅ የማለት ነፃነት የጥቂቶች ፍር ፍር ጉዳይ ሆኖ ቢቀርም የሚጠየቅ፣ መልስ የሚሰጥ ባይኖርም እስቲ እኔም በሕይወቴ አንዴ ቀና ብዬ ለሁልሽም ጥያቄ ብደረድር አይጠላብኝም ብዬ ተነሳሁ፡፡

እስከ ዛሬ ባሳለፍኩት (ስልሳዎቹ ውስጥ በገባ) ዕድሜዬ እንዳስተዋልኩት የፖለቲካ ሰዎች ማውራት ይወዳሉ እንጂ ጆሮ አልፈጠረባቸውም፡፡ አሳሳቢ ጉዳዮችን የተመለከቱ በሳል ጽሑፎችን በጋዜጣና በመጽሔት ላይ አውጥቶ በእነዚያ ላይ በመነጋገር የራሳቸውንም የሕዝብንም አመለካከት የማበልጸግ ባህል የላቸውም፣ አላየሁባቸውም፡፡ ሊነጋገሩበት የሚገባ ጉዳይን ያዘለ ነገር በጋዜጣ ወጥቶ ሲያገኙ እንኳ ያንን በመነሻነት ተጠቅመው የአስተሳሰብ መበለፃፀጊያ አያደርጉትም፡፡ በግል ወዳጅነት ውስጥ እየተጨዋወቱ ሐሜቱን ለማስነካት ችግር የለም፡፡ አንዱ በሌላው ሐሜት ላይ እያከለ በአንድ ቁጭታ ብቻ የሐሜት ተራራ መፍጠር ይቻላል፡፡ ለመተራረም በሚደፍር ውይይት ጭውውትን የሐሳብ መበለፃፀጊያ ማድረግ ግን የሐበሻ ኮሶ እንደ መጠጣት የሚፈራ ነው፡፡

ሥራችንና ነገር ዓላማችን ሁሉ አላዋቂነት አፈትልኮ እንዳይወጣ መከላከል፣ ያላወቁትን እንዳወቁ ያላጣሩትን እንዳጣሩ አስመስሎ መሸምጠጥ፣ የሚገናኘውንም የማይገናኘውንም እየዘበዘቡ ሌላውን አላናግር በማለት አዋቂነትን ለማሳየት መፋጨር፣ ወይም ላይ ላዩን የሚጨዋወቱ እየመሰሉ ግን ሐሳብ ለሐሳብ ሳይነካኩ እንደ ተኩላዎቹ ወደ ሰማይ አንጋጦ የየግል ጩኸትን መጮህ ነው፡፡ በእኛ ዘንድ በሰፊው የተለመደው ውይይት የዚህ ዓይነት ነው፡፡

ሌላም ዓይነት ውይይት አውቃለሁ፡፡ አንድ ወዳጅ አለኝ፡፡ በተገናኘን ቁጥር የሚፈልገው ስለኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳዮች ብናወራ ነው፡፡ ብዙ ሰው ከሚቀባበለውና እሱ ነጋ ጠባ ከሚያመነዥከው አስተሳሰብ የተለየና አዕምሮን በማስረጃ የሚሞግት ጽሑፍ አግኝቼ በሰጠሁት ጊዜ፣ እሱን ቶሎ ቶሎ አሻምዶ ይጨርስና በትኩሱ ከተገናኘን እያደነቀልኝ ፍንክንኩ ይወጣል፡፡ ብዙ ነገሮች እየመዘዝን እናወራለን፣ ብዙ ነገሮች ላይ እንግባባለን፡፡ በዚያ ዕለት ያገኘነውን የአስተሳሰብ ለውጥ ወዳጄ ይዞ ለማቆየት የሚያደርገው ጥረት ግን የለም፡፡ አንብቦ ያደነቀውን ጽሑፍ ከልሶ የማንበብና ጭማቂ ነጥቦች የማስቀረት ልማድ የለውም፡፡ እና ያስገባቸው አዲስ ነገሮች ዋል አደር ሲል ሁሉም በንነው ሊጠፉት ይችላሉ፡፡ ወይም የለመዳቸውን አስተሳሰቦች የሚያትቱ መጻሕፍትን አግኝቶ ሲያነብ ፊት ወደ ነበረበት ደረጃ ይመለስና የዱሮ አቋሞቹን እንደገና ሲያመነዥክ አገኘዋለሁ፡፡ ወዳጄን የመሳሰሉ ሰዎች ብዙ አሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ሰዎች ከንባብም ሆነ ከጽሑፍ ያገኙትን አዲስ ዕይታ ከራሳቸው ጋር ለማቆየት ስለማይጣጣሩ ወደ ዱሮአቸው እንዳይመለሱ እንደ ሞግዚት ከሥር ከሥራቸው ማለት ያስፈልጋል፡፡

ባሉበት የሚሄዱትንም ሆነ እንደ ተኩላ ሽቅብ የሚጮሁትን ሰዎች ብዙ አይቼያቸው ስለጠገብኳቸው፣ አብዛኛው ውሎዬ ከመጽሐፍት ጋር ሆኗል፡፡ ከሰዎች ጋር በተቀላቀልኩ ጊዜም ሆነ በሚዲያ ላይ አፍ ሲተረተር ታዝቦ ማሳለፍን ሠልጥኜበታለሁ፡፡ ኖሬ ኖሬ ግን ብልጭ ይልብኛል፣ ምክንያቱም ምንም ቢያሳልፉ የሚለበልብ ነገር ተናግሮ አናጋሪ አይጠፋም፡፡ የ2010 ዓ.ም. ጥቅምት አጋማሽ ዕለታት በብዙ ብልጭታና ጥያቄ ሰውነቴ የተወረረባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡

እውነተኛው ምክንያት ገና ባልታወቀው የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ግጭት ብዙ ሰው መሞቱን፣ ብዙ ንብረት መውደሙንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን መፈናቀላቸውን ሰምቶ ሐዘን የገባው ልቦናዬ ጥቅምት አጋማሽ ላይ በ‹ኢኤንኤን› ቴሌቪዥን ላይ በገብረ ጉራቻ የተቃጠሉ መኪኖችን በማየት አልተገረመም ነበር፡፡ የዕለቱ ዕለት ማታ መሰለኝ፣ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋዜጠኛዋ ጃዋር መሐመድን ከዚህ ቀደም ኦሮሚያ ውስጥ በቅዋሜ ለደረሰ የንብረት መውደም ኃላፊነት መውሰዱን አንተርሳ የገብረ ጉራቻ የመኪኖች ቃጠሎ የእነሱ ሥራ ስለመሆን አለመሆኑ ትጠይቀዋለች፡፡ ጃዋር በሙሉ ልብ ሆኖ ባለፈው ትግል በተመረጡ ዒላማዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዳቸውን አስተማምኖ፣ የአሁኑ ቃጠሎ ግን ገበያ ውስጥ በቆሙ መኪኖች ላይ ያለምርጫ ከሌላ አካባቢ በመጡና በደኅንነቱ ክፍል ተነሳስቶ የተካሄደ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡ ማመን አልቻልኩም፡፡ ጆሮዬ ጋለ፡፡ ጃዋር መሐመድ የተማረና እንደበተ ስል መሆኑ አጭበርብሮኝም እንደሆነ አላውቅም ስለሱ ብዙ ነገር ሲታማልኝ በአንድ ጆሮዬ ሰምቼ በአንድ ጆሮዬ አፈስስ ነበር፡፡

የጃዋርን የእምነት ቃል ከመስማቴ በፊት፣ በ2008 ዓ.ም. ኦሮሚያ ውስጥ የደረሰው ውድመት ሁሉ የድንገተኛ ደምፍላት ውጤት ይመስለኝ ነበር፡፡ አሜሪካ ገብቶ የ21ኛው ክፍለ ዘመንን የሥልጣኔ ኑሮና ውኃ የተጎነጨ ሰው በአንዲት ደሃ አገር ውስጥ ተቋማትንና ንብረቶችን አውድሙ የሚል አመራር ይሰጣል ብዬ በምን አስቤው! አሳፋሪ የትግል ዘዴውን በኩራት ከመቀበሉ ይበልጥ ያስደነቀኝ ነገር ደግሞ በገብረ ጉራቻና በኩዩ በደረሰው ጥፋት ውስጥ የለንበትም ማለቱ!

ጃዋርና ባልደረቦችህ እስቲ ልጠይቃችሁ! የገብረ ጉራቻውን ቃጠሎ ማንም ያነሳሳው እዚያ በደረሰው ውድመት ውስጥ፣ ሌላም ቦታ በደረሰው ውስጥ፣ ገና ወደፊትም ሊደርስ በሚችለው የሩምታ ትግልና ጥፋት ውስጥ እጃችሁ ቀጥታ ባይኖርበትም እጃችሁ እንዳለበት እንዴት አልታያችሁም? ውድመትን በትግል ዘዴነት ባርካችሁ ለወጣቱ የሰጣችሁ ሰዎች ጥፋትን ይዞ በሚመጣ ቅዋሜ ውስጥ ሁሉ ባትሳተፉም፣ ተሳታፊ ለመሆን እንደበቃችሁ ለመገንዘብ የእኔ ማስታወስ ያስፈልጋችኋል? በዚህ ‹‹ድንቅ›› አመራራችሁ የኦሮሞ ወጣቶች ትግል ከጥፋት ጋር ተዛምዶ እንዲታይ፣ አሻጥረኞች ሊያቀናብሩትና ሊያደርሱት ለሚችሉት ውድመት ሁሉ ማላከኪያ እንዲሆን ማድረጋችሁስ ይገባችሁ ይሆን? የኦሮሞዎች ትግል ከውድመት ጋር መዛመዱስ ቀሪው ሕዝብ ኦሮሞን በሥጋት እንዲመለከት የሚያደርግ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ትግል መጥፎ የወገብ ስብራት እንደሆነ ይታወቃችሁ ይሆን?

በዚያው በአሜሪካ ድምፅ በኩል የተሰማ የ‹‹ኮሙዩኒኬሽን›› ሰው መረጃ የገብረ ጉራቻው ግርግርና ቃጠሎ ከሌላ አካባቢ በመጡ ሰዎች የተነሳሳና የተያዙም እንዳሉ ጠቆም ያደረገ ነበር፡፡ የሰማሁትን አውጥቼ አውርጄ ሳልጨርስ በቡኖ በደሌ ዞን በተወሰኑ ወረዳዎች ውስጥ ሞት፣ መፈናቀልና የቤቶች ቃጠሎ የተፈጸመበት ጥፋት መድረሱን ‹‹ኢኤንኤን›› በምሥል አስደግፎ አረዳኝ፡፡ ምሽት ላይ ደግሞ በአሜሪካ ድምፅ የ12 ሰዎችን ሞት፣ የ52 ቤቶችን ቃጠሎና 1,500 ያህል ሰዎችን መፈናቀል ካሳወቀ መረጃ ጋር አሁንም ግርግሩ ከሌላ አካባቢዎች በመጡ ሰዎች እንደተነሳሳና የኦሮሞን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ ሆን ብሎ የማጋጨት ሴራ ያለ ስለመሆኑ፣ በ‹‹ኢኤንኤን›› እና በማኅበራዊ ሚዲያ የቀረቡት የቃጠሎ ምሥሎች በኮምፒዩተር ጥበብ የተቀናበሩ ስለመሆናቸው አሁንም በ‹‹ኮሙዩኒኬሽን›› ሰው ተነገረ፡፡

ከዚያ ዕለት በኋላም ሕዝብን ከሕዝብ የማጫረስ ደባ እየታየና ግጭቶች እየተበራከቱ ስለመሆናቸው አንዳንድ ተቃዋሚዎችም መሰከሩ፡፡ በዚህ ቢበቃን ስል ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ ስኳር በሕገወጥ መንገድ ሊተላለፍ ነው በሚል ወሬ ጭነትን መንገድ ከልክሎ ለማስቀረት በተካሄደ ግብግብ ምክንያት፣ አሥር ወጣቶች በመከላከያ ታጣቂዎች ስለመገደላቸው የአምቦ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ኃላፊ በዚያው በአሜካ ድምፅ ላይ ተናገረ፡፡ የባሰ ሊመጣ ነው ስል በማግሥቱ ደግሞ ወጣቶች ከሽማግሌዎች ጋር ተነጋግረው መረጋጋት እንደተፈጠረና የቀብር ሥነ ሥርዓትም በሰላም እንደተከናወነ ሰማን፡፡ ከጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የዋልታ ዜና ደግሞ ጥቂት ወሬ አገኘን፡፡ የአምቦውን ግርግር ያስነሳው ከፊንጫ ስኳር በሕገወጥ መንገድ ሊተላለፍ ነው የሚል ሐሰተኛ ወሬ እንደነበረና የመንግሥት ተቃዋሚ ብቻ ሳይሆን ደጋፊ በመምሰልም ወጣቱን እያሳሳቱ፣ አካባቢውን የሁከት አውድማ ለማድረግ የሚሹ ኪራይ ሰብሳቢዎች እንዳሉ የኦሮሚያ ‹‹ኮሙዩኒኬሽን›› ቢሮ ኃላፊ አሳወቀን፡፡

የተባለውን ሁሉ ተመርኩዤ የራሴን መንደርደሪያ ላስቀመጥ፡፡ ከየአቅጣጫው በተወረወረልን ከቅምሻ የማይሻል መረጃ ውስጥ የኦሮሞ ወጣቶችን አሳስቶ ደምፍላት ውስጥ በማስገባት ብሔርን ከብሔር የማጋጨት ተንኮል እየተካሄደ ነው የሚል መልዕክት እናገኛለን፡፡ የተንኮል ሥራ ሊኖር ይችላል፡፡ የዴሞክራሲን ለውጥ የሚሹ እንዳሉ ሁሉ ያለው የአንድ ፓርቲ የበላይነት ሥርዓት ጠንክሮ ቢቆይ የሚፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንደሚባለው ግርግሩን መጠቀሚያው አድርጎ የሚመለከትም ይኖራል፡፡ ጭራሽም የአገሪቱን መበታተን ጥቅሜ ያለ ቡድን በስውር እየተንቀሳቀሰ ይሆን ይሆናል፡፡ ወይም በመጨራረስ ጅምር አንጰርጵሮና በፀረ ፍጅት ስም የራሱን ጭፍጨፋ አካሂዶ የለየለት ፈላጭ ቆራጭነትን ለማስፈን የሚያደባ ስውር ተጓዥም ይኖር ይሆናል፡፡ የተንኮሉ ዓይነትና ዓላማ ምንም ይሁን ምን፣ የተንኮሉ ተላላኪዎች ከሌላ አካባቢም የመጡ ይሁኑ የወንዝ ልጆች፣ ወጣቱን ጥፋት ውስጥ ሊማግዱ የሚችሉት ለዚያ የሚመች ክፍተት ካገኙ ብቻ ነው፡፡ ወጣቱ ውስጥ አካባቢያችን እየተዘረፈ ነው በሚል ብግነት መወራጨት፣ መጤ የሕዝብ አባላትን ከዝርፊያና ከጭቆና ጋር ደርቦ የሚያይ ወይም ለዚያ የቀረበ ስሜት ካለ በእርግጥም ለተንኮለኞች የሚመች ክፍተት አለ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ክፍተት በቀላል ሆይ ሆይታ ተነድቶ የአገር ልጆችን እስከ መጨፋጨፍ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ከባድ ውድቀት ነው፡፡

ይህንን ውድቀት መቀየርና የመሰሪዎችን ተንኮል ማምከን የእነሱን ፍላጎት የሚቃረኑ ኃይሎች ተግባር ነው፡፡ ኦሕዴድ፣ የኦሮሚያ አስተዳደር፣ ኦፌኮ-መድረክና ሌሎችም ቡድኖች ታዲያ ልጠይቃችሁና ሕዝብን ከሕዝብ የማባላት ሴራ እየተካሄደ ነው እያላችሁ የምትጮሁት ወደ ማን ነው? የሕዝቦችን መባላት የማትሹ እስከሆነ ድረስ፣ የትግል ኃላፊነቱ ራሳችሁን የሚመለከት ሆኖ ማን ምን እንዲየደርግላችሁ ፈልጋችሁ ነው? ድብቅ ተንኮለኞችን አንጠርጥሮ የማጋለጥና ወጣቶች ለተንኮል እንዳይበገሩ የመግራት ሥራዎችን አንድ ላይ ማስኬድ ትኩረትንና ኃይልን ሊሻሙ ይችሉ ይሆናል፡፡ ከመሰሪዎች ጋር ተሽሎክልኮ እነሱን በማያጠራጥር ማስረጃ ማጋለጥ ከባድ ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር ከባድ ከመሆኑ በተጨማሪ ወሳኝ አይደለም፡፡ ወሳኙ ሥራ ቁርጠኝነት ካለ በቀላሉ ሊከናወን የሚችለው ወጣቱን እንዳይጠመዘዝ አድርጎ የማስተካከሉ ሥራ ነው፡፡ ይህ ሥራ ሰፋፊ ትንታኔን የያዙ ጥራዞችን ማዘጋጀትንና የአሠልጣኞች ሥልጠና ምናምን የሚባል ዝባዝንኬ የማይፈለግ፣ ፍጅትን ሆነ ከፍጅት በማትረፍ ሽፋን የሚመጣ ፈላጭ ቆራጭነት አዝመራችን ከመሆኑ በፊት አውዳሚ የትግል ስልትን በማስቀረትና በሁለት በኩል ሲያደሩ የነበሩ የጥርጣሬና የመቃቃር ድሮችን በጣጥሶ ጉዳትህ ጉዳቴ በመባባል የሚጀምር፣ ከዚያም ተባብሮ የትኛውንም በደል በመፃረርና ለመብቶች በመቆም የሚጠናከር ነው፡፡ እናስ ታዲያ፣ ‹‹ስንቱን ክፉና ደግ ያሳለፉ ሕዝቦች እንዳይጫረሱ›› የተጨነቁት ኃይሎች ወደዚህ ተግባር ውስጥ ከመግባት ፈንታ ምን እየጠበቁ ነው? ወይስ ከዚህ የሚያዘገይ በሶ ጨብጠዋል? ከክልል ወደ ክልል ሄዶ ስብሰባ ማካሄድ መልካም ጅምር ቢሆንም ይህ ለጥያቄው መልስ አይሆንም፡፡ ጥያቄው መልስ የሚያገኘው ክልላዊ አመለካከትን አስፍቶ በየክልሉ ውስጥ ከሚገኙ መጤዎች ጋር በተጨባጭ የክልሌ ልጆች ተባብሎ ለመተቃቀፍ መብቃትን ሲያሟላ ነው፡፡

የኢፌዴሪ ፓርላማ የ2010 የሥራ ዘመን መክፈቻ የሆነውን የፕሬዚዳንቱን ንግግር በማፅደቂያ ዕለተ ስብሰባ ላይ (ጥቅምት 16) ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለጥያቄዎቹ መልስ በሰጡበት ጊዜ፣ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ቀውስን በተመለከተ ከአንደበታቸው አንዲት ማር ንግግር ጠብ ብላ ነበር፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም ንግግሪቱ የእኔ ሕዝብና የእነሱ ሕዝብ የሚል ልዩነት ትልቅ ችግር ፈጣሪ መሆኑን የጠቆመችና እንከን የማይወጣላት ነበረች፡፡ ‹‹ሕዝቤ›› እና ‹‹ሕዝባቸው›› የሚል ክፍፍልን ግን የክልሎች ገዢዎችም ሆነ ፓርቲዎች ከሐሳባቸው የፈጠሩት ነገር አይደለም፡፡ ብሔር ብሔረሰባዊ ማንነትንና ቋንቋን በተከተለ የአስተዳደራዊ ይዞታ ቅያስ አማካይነት የተከናወነ ተጨባጭ ክፍፍል ነው፡፡ ብሔረተኛ ስብስቡ፣ አድልኦውና ገዥነቱም ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጫት ንግድ ጋር አያይዘው በእነሱ ግራ አጋቢ ቋንቋ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› በማለት ጠቆም ያደረጉት ችግርም ‹‹ሕዝቤ›› እና ‹‹ሕዝባቸው›› ከማለት ጋር በቀጥታ የተገናኘ የጥቅም ሽኩቻ ሊያመነጭ እንደሚችል ዕውቅ ነው፡፡ የጫት ንግድ ለዚያ አካባቢ ገበሬዎች፣ ለጫት ቀንጣሾችና ለጫት ላኪዎችም ሆነ ለመንግሥታዊ አካላቱ ብርቱ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ በደርግ ዘመን የጫት ላኪዎች ማኅበር አባል ለመሆን በጉቦ፣ በሹምና በኢሠፓ በኩል ይደረግ የነበረውን አቋራጭ ጉዞ፣ ደርግ ገና ከመውደቁም ያንን የሲሳይ ማጀት ለመቀራመት ምን ያህል ሽሚያና ፍንቀላ እንደተካሄደ የሚያውቅ ያውቃል፡፡ ‹‹የሶማሌ ብሔራዊ ክልል››፣ ‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል›› ወዘተ የሚባል ቅርፅ ከተፈጠረ በኋላም ከጫት ንግድ የበቀሉ ከበርቴዎችና አዲስ መጥ ቋማጮች በንግዱ ውስጥ ያሉ ተቀናቃኞችን ከውድድር ውጪ ለማዳከምና ሥፍራ ለማስለቀቅ፣ ‹‹በእኛ ብሔራዊ ክልል ውስጥ የሌላ ብሔር ሰው እየከበረ/ንግዱን አላስይዝ እያለ›› የሚል ጨዋታን ከመጫወት እንደማይመለሱ ጥርጥር የለኝም፡፡

አሁን ልጠይቅ፡፡ የሶማሌና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች በተፈጠሩበት፣ በየክልላቸው የሶማሌና የኦሮሞ ብሔረተኛ ፓርቲዎች እየገዙና ብሔረተኛ አመለካከትን እየነሰነሱ ባለበትና መደበኛም ይሁን ልዩ የተባሉት ታጣቂዎች በዋናነት ለየክልሉ ባለቤት ከተባሉት ብሔሮች ውስጥ በተደራጁበት ሁኔታ ውስጥ፣ የመንግሥት ሹሞቹም ሆኑ ታጣቂዎቹ ‹‹ሕዝቤ›› እና ‹‹ሕዝቤ ያልሆነ›› ከሚል አመለካከት እንዴት ነው ሊያመልጡ የሚችሉት? ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ፌዴራል መንግሥትም ለክልሎች ሊያበረክቱት የሚችሉት ምን መፍትሔ አላችሁ? የክልል መስተዳድሮችስ ልጠይቃችሁና እንደተለመደው በሥልጠናና በኮንፈረንስ ወገንተኝነትን ልታፀዱ ነው? የብሔርተኛ አፈር፣ ውኃና አየር እየተመገበ የሚኖርን አዕምሮ ከብሔርተኛ አድሎ ፅዳ ብሎ ኮንፈረንስ ማካሄድ የጤና ሥራ ነው?

በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ካሉ ተቃዋሚዎች አካባቢ፣ ከኢሕአዴግ ጋር ድርድር ይዘናል ከሚሉትም መሀል፣ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት አልቻለምና መተላለቅ ከመድረሱ በፊት ይውረድ የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በዚያች የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ጋብ ከማለቱ በቀር 2008 ድፍን ዓመትን ይዞ ቅዋሜያዊ ሁከት፣ የሰዎች ሞትና የንብረት ውድመት ሲደጋግመን ነው የቆየው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ከተነሳ በኋላ ደግሞ ጭራሽ በግዝፈቱ በአገራችን ውስጥ ታይቶ የማያውቅ የመቶ ሺዎች መፈናቀል የተከሰተበት ግጭት በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ከመድረሱ ሌላ ከብሔር ጥቃት ጋር የተነካካ ሁከት ብቅ ብቅ እያለ ነው፡፡ ከንብረት ቃጠሎ በላይ የሚሞቱትና የሚፈናቀሉት ወገኖቻችን ናቸው፡፡ የምናፈናቅለውም አይዟችሁ ብለን የምንረዳና መልሶ ለማቋቋም ደፋ ቀና የምንልም እኛው ነን፡፡ ተገደሉ፣ ሞቱ እየተባለ ሲነገርም የሚወራው ስለዶሮ ነፍስ አይደለም፡፡ የምንገዳደልም/የምንገድልም፣ የምንሞትም፣ አልቅሰን የምንቀብርም እኛው ነን፡፡ ይህ ከቶ ሊቀጥል የማይገባው ችግር ነው፡፡ ለዚህም ተብሎ የኢሕአዴግ መንግሥት ይውረድ የሚል መግለጫ ቢወጣ ወይም መፈክር ቢስተጋባ ፈጽሞ ነውር አይሆንም፡፡

ፓርቲዎች ‹‹ከሚደራደሩበት›› አዳራሽ ተቀንጭቦ በዜና በተወረወረልን መሠረት (ኢሕአዴግ ይውረድ የሚል መግለጫ የሰጠ ተደራዳሪ ድርጅትን በተመለከተ) ከኢሕአዴግ ዋነኛ ተደራዳሪዎች የተሰማው ‹‹ይህማ አመፅ ነው ሽብር ነው›› የሚል ቃል ግን ‹‹ይውረድ›› ማለትን ወንጀል ያስመሰለና ‹‹በእኛ አገር መቼም አይሰማ የለ›› ያስባለ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ ተደራዳሪዎች እስቲ ተጠየቁ! ኢሕአዴግ እንዲወርድ መጠየቅ ከንግግር መብትነት ወጥቶ አመጽ ወይም ሽብር የሚሆነው በምን ሒሳብ ነው? ለመሆኑ ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ የሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ በፊት ሊወርድ የሚችልበት ቀዳዳ በሕገ መንግሥታችን ውስጥ የለም? ለመሆኑ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60(1) ሥራ ላይ እንዲውል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክር ቤቱን ይሁንታ ይዞ ምክር ቤቱን እንዲበትንና ሌላ እንዲያስመርጥ ሰላማዊ ጫና የሚያደርጉ ሕጋዊ ስብሰባዎችና ሠልፎች ቢከታተሉ አመፅ ሊባል ነው?

ኢሕአዴግ እንዲወርድ የጠየቁትን ደግሞ ልጠይቅ! ሐሳባችሁ ኢሕአዴግ ወርዶ ሽግግር ምናምን የሚባለውን ለማቋቋም ከሆነ፣ ይህንን ለማድረግ የምትችሉት ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በማፍረስ ሊሆን ነው፡፡ ታዲያ እዚህ ጋ እንዴት ነው የምትደርሱት? ኢሕአዴግ ሥርዓቱን ለማፍረስ እሺ እስኪላችሁ ጠብቃችሁ ነው? ወይስ ወደደም ጠላ አስገድዳችሁ ልትጥሉት? ለመሆኑ የምትጥሉትስ ‹‹ልማታዊ›› የሆነውን የፀጥታ ኃይልን ምን ከምን አድርጋችሁ ነው? በኃይል ወይስ በፖለቲካ ረትታችሁ? ወይስ ኢሕአዴግ ከነፀጥታ ኃይሉ እስኪወላልቅና ትርምስምስ እስኪፈጠር ጠብቃችሁ ከዚያ እናንተ የሕዝቦች አሰባሳቢ ልትሆኑ?

ሕዝብን በሰፊው የረታ የፖለቲካ ኃይል እንዳለመኖሩ፣ ኢሕአዴግና አጋሮቹ የማይናቅ የፖለቲካ ተሰሚነት እንደሚኖራቸው ጥርጥር የለውም፡፡ በአገር ውስጥ አነሰም አደገ ዋና ተቃዋሚ ልትባሉ የምትችሉት መድረክ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓና ሌሎችም እርስ በርሳችሁ በሆነ መርሐ ግብር እንኳ መተሳሰር ያልቻላችሁ፣ ከመቀራረብ ይልቅ መናቆር የሚበልጥባችሁ ሆናችሁ ሳለ ሕዝቦችን እንደምን ማሰባሰብ ይቻላችኋል? ወይስ ለዚያን ጊዜ የተቀመጠ ምትኃት አላችሁ? ፈረንጅ አገር ያላችሁትስ? አዲስ መጥ የአገር ልጅን ከማን ጋር ሲውል ታየ እያሉ እስከ ማግለልና እስከ ማቅረብ ድረስ፣ ጽሑፎችን በወጡበት ድረ ገጽ ብቻ የ‹‹ጠላት›› እና ‹‹የወዳጅ›› ብሎ እስከ መፈረጅ ድረስ በኩርርፍና በጥላቻ የተጠመዳችሁ ሆናችሁ ሳለ፣ አገር ውስጥ ላለው ውስብስብ መቋሰል ምን ልትፈይዱ ነው? ልታባብሱ ነው? ወይስ ልታሽሩ?

የኢሕአዴግን መውረድ ከጠየቁት ውስጥ ምናልባት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 60(1) መሠረት ምክር ቤት ተበትኖ በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ ምርጫ እንዲደረግ ያቀደና ወደዚህ ምዕራፍ ላይ በፖለቲካ ስበት ለመድረስ ያሰበ ቢኖርስ ብዬ ደግሞ ልጠይቅ! ልዩ ልዩ ተቃዋሚ ቡድኖችንና ኢሕአዴግን ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕዝቦችን ማርኮ ወደ ተፈለገው ምዕራፍ ሊወስድ የሚችል የፖለቲካ መርሐ ግብር ያዘጋጃችሁና በይፋ ያስተዋወቃችሁ ማንኛችሁ ናችሁ? የፖለቲካ ቡድኖች አቋማቸውን እያጠጋጉ በግንባርና በኅብረት መልክ እንኳ ቁጥራቸውን ያሳነሱበት የሕዝቦችም ምርጫ እነሱው ላይ የሚከማችበት ሁኔታ ባልተፈጠረበት ምርጫ ቢካሄድ ከፌዴራል እስከ ክልሎች፣ ከዚያም አልፎ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ምክር ቤቶች የውጥንቅጥ ቡድኖችና ፍላጎቶች መጯጯሂያ ከመሆን አያመልጡም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ለሥርዓት አልባነት ደረቱን የሰጠ ሁኔታ አሁን ካለንበት የተሻለ ነው?

እነዚህ ጥያቄዎች በሌላ ገጻቸው ኢሕአዴግን የሚመለከቱ ጥያቄዎችንም አዝለዋል፡፡ እስከ ዛሬ እንደኖርነው ባልታወቀ ጊዜ ሁከት፣ የሕይወትና የንብረት ጥፋት፣ መፈናቀል ከሚያስከትሉ ግጭቶችና ግንፈላዎች ጋር ወደፊትም እየኖርን ድብልቅልቃችን የሚወጣበትን ቀን ልንጠብቅ ነው? መታመስና ግጭቶች ቆመው ወጣቶቻችንም በሁከት ከመሞትና ከመታሰር ተንፍሰውና ወደ አዎንታዊ ፖለቲካ ዞረው የተረጋጋ ኑሮ ውስጥ መግባትን ሲበዛ እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ የሚገላግል መርሐ ግብር ኢሕአዴግ አለህ? በቅዋሜ እየተዋከብክ ባለህበት፣ ከአንዳንድ ምልክቶች እንደሚገባንም፣ የራስህን የውስጥ ኅብረት አጥብቀህ ማዝለቅህም በሚያጠራጥርበት በዛሬው የፖለቲካ አቅምህ ብቻህን ያልተውሸለሸለ መፍትሔ መስጠት ይቻልሃል?????

እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ሁላችንንም ሊያሳስቡን ይገባል፡፡ ዛሬ የምንገኝበትን የሞትና የሽረት ፈተና በማስተዋል፣ በኢሕአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎች ውስጥ ያሉ የሕዝብ ሰላምና የዴሞክራሲ ተቆርቋሪዎች ሁሉ በቶሎ ተንቀሳቅሰው ወደ መበታተንና ወደ መባላት የሚወስዱ የሚመስሉ የውር ለውር ፖለቲካዊ ልፊያዎችን የሚቀይርና የዴሞክራሲ ተስፋችንን የሚያተርፍ መፍትሔ እስካላመጡ ድረስ ዶፍ አለልን!! አለልን ከማለት ይልቅ ትክክል የሚሆነው፣ የከፋ አበሳ አስቆጣሪ ሁኔታ ውስጥ እናንተም እኛም እንድንገባ ቲኬት ትቆርጡልናላችሁ ብሎ ማለት ነው፡፡ በዚያ ሰዓት ላይ ፀረ ዴሞክራቶችና የሥልጣን ጥመኞች ለዚህ አበቁን እያሉ ከማማረር ይልቅ ያጣነው ያልለፋንበትን ነው፣ ያገኘነው የፈቀድነውን ነውና ይበለን ማለት ትክክል ይሆናል፡፡

ደግሜ የምጽፍ ስለማይመስለኝ በሆዴ ያለውን ላራግፍ፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) በሚል ትርጉሙ ሲሠራበት እሰማለሁ አነባለሁ፡፡ የዚያ ዓይነት ጦርነት ሕዝብ በሁለት ተዋጊ ወገኖች ተስቦ የሚተጫጨድበት ነው፡፡ የናይጄሪያው የቢያፍራ ጦርነት የእርስ በርስ ጦርነት ነበር፡፡ በቅርቡ ማዕከላዊ አፍሪካ አገር ውስጥ የታየው የሴሊካና የአንቲባሊካ ግብግብ ሕዝብን በአደገኛ ድጡ እያንሸራተተ የእርስ በርስ መጨፋጨፍን ሊያስከትል ችሏል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በዕድሜዬ ሕዝቦች ወዶ ገባ የሆኑበት የእርስ በርስ ጦርነት አላውቅም፡፡ በኤርትራም ሆነ በትግራይ ውስጥ የነበሩት ጦርነቶች ሕዝብን እየማገዱም ቢሆን በመንግሥትና በሽምቅ ተዋጊዎች መካከል የተካሄዱ ነበሩ፡፡ ‹‹ቀይ ሽብር›› እና ‹‹ነጭ ሽብር››ም እንደዚያው የእርስ በርስ ውጊያዎች አልነበሩም፣ ሕዝቦች ወገን ለይተው አልተፈሳፈሱምና፡፡

የእርስ በርስ ውጊያ ጅምር በትንሹም ቢሆን የተከሰተበት ወቅት ቢኖር ኦነግና ቢጤዎቹ ፀረ ነፍጠኛ ግብግብ ባነሳሱበት የአፍላ ወቅት ነበር፡፡ ዛሬ ግን እዚያም ብልጭ ድርግም የሚሉት ብሔር ነክ ግጭቶች በቶሎ ትክክለኛ መፍትሔ ካላገኙ፣ ዓይተነው የማናቀው መሰያየፍ እንዳያጥለቀልቀን እፈራለሁ፡፡ የዚያ ዓይነቱን የመፈሳፈስ ጅምርማሪ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስቆማለሁ የሚል ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭነት ከመጣ ደግሞ የሚያሸክመን ገዥ፣ አሁን ፊሊፒንስ ውስጥ ካለው መግደል ከማይታክተውና ከማይሰቅቀው አራጅ የከፋም የሚሆን ይመስለኛል፡፡

ይህ ሁሉ እንዳያገኘን የፖለቲካ ቡድኖቻችንና ፓርቲዎቻችን ይደርሱልን ይሆን? እስከ ዛሬ ከማውቀው ተነስቼ ሳስባቸው ኩርፊያቸውንም መራርነታቸውንም ግትርነታቸውንና ዳተኝነታቸውንም አሽቀንጠረው የመልካም ተስፋ ችቦ የመሆናቸው ነገር ያጠራጥረኛል፡፡ ከዚያ ይልቅ ለዴሞክራሲ ገና አልተዘጋጀንም፣ አፍኖ መግዛትም ታፍኖ መገዛትም ገና ቅም አላለንም የሚል ወለም ዘለም ውስጥ የሚከርሙ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ነገር ስናገር፣ ፖለቲከኞቹ ትክክል ነገር ሠርተው እኔን ስህተተኛና ጨለምተኛ እንዲሉኝ እየተሳልኩ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡