Skip to main content
x
የምርጫ ሥርዓታችን ትልቁ ፈተና ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የማካሄድ እንጂ የመወከል ጉዳይ ነው ብዬ አላምንም

‹‹የምርጫ ሥርዓታችን ትልቁ ፈተና ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የማካሄድ እንጂ የመወከል ጉዳይ ነው ብዬ አላምንም››

አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንትና አንጋፋ ፖለቲከኛ

አቶ ሙሼ ሰሙ የቀድሞው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከማንኛውም የፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን ያገለሉ ቢሆንም፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ስለአገሪቱ ፖለቲካና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች በግላቸው ሐሳቦችን ይሰነዝራሉ፡፡ ከፓርቲ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ የተገለሉት አቶ ሙሼ በአንድ የግል ባንክ በኃላፊነት በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር እያካሄዱት ስላሉት ድርድርና ባለፈው ሳምንት ስምምነት ላይ በደረሱበት፣ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት ወደ ቅይጥ ትይዩ የመቀየርና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከነአምን አሸጋፊ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት (ገዥው ፓርቲ) ጋር ዘለግ ላለ ጊዜ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ድርድር እያደረጉ ነው፡፡ በተለይም በአገሪቱ የምርጫ ሕጎችና የምርጫ ሥርዓት ላይ የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ደርሰዋል፡፡ እስካሁን ያለውን ድርድር እንዴት ያዩታል? እንዴትስ እየገመገሙት ነው?

አቶ ሙሼ፡- በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል የሚባለው እየተደረገ ያለው ድርድር የተሟላ ውክልና ያለውና ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተሟላ ሁኔታ የሚወክል ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በድርድሩ እየተሳተፉ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት እንደተመረጡም መረጃው የለኝም፡፡ እነዚህ ብቻ ናቸው በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከታቸውና ኢትዮጵያ ላይ መወሰን ያለባቸው ብዬም አላምንም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ እየተደራደሩ የሚገኙበት ነገር የሙያ ጉዳይ ይፈልጋል፡፡ ባለሙያ የሆነና በምርጫ ሥርዓት ውስጥ በቂ ግንዛቤና ዕውቀት ያለው ሰው ቢሳተፍበት ጥሩ ነው፡፡ ሁለተኛ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ውጪ በተለያየ መንገድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተቃዋሚ ወገን ሚና የነበራቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች እነዚህ ጉዳዮች ላይ ቢሳተፉ ጥሩ ነበር፡፡ ይህ አለመሟላቱ ትልቅ ጉድለት አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች እያኮረፉ የወጡ፣ ነገር ግን በዚህ ሒደት መሳተፍ የሚገባቸው አካላት የሚካተቱበት ዕድል መኖር አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም መነሻው ሰፊ ነገር ነበር፡፡ በኋላ ግን እየጠበበ እየጠበበ መጥቶ በምርጫውና በምርጫ ቦርድ ዙሪያ ላይ ነው ትኩረት ያደረገው፡፡ ምክንያቱም ይህንን ውይይት የጋበዘው ወይም ደግሞ ዕውን እንዲሆን ያደረገው በኢትዮጵያ የተነሳው የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ አለመረጋጋት ካስነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ የውክልና ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫው ተገፍተው ወጥተዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ተሳትፎውን የሚያሳይበት መንገድ እያጣ በመምጣቱ ያ ተፅዕኖ የወለደው ሒደት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡

      እነዚህ የተመረጡት ፓርቲዎች የተመረጡት ምን መሠረት ተደርጎ ነው? ማኅበረሰቡን በምን ያህል ደረጃ ይወክሉታል? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ድርድር ምንጊዜም በአቅም ላይ የሚመሠረት ነገር ነው፡፡ በፍላጎት ወይም በይሁንታ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማንን ወክለው ነው የሚደራደሩት? ሲደራደሩስ በማኅበረሰቡ ዘንድ በበቂ ሁኔታ ትኩረት እንዲያገኙ የሚያደርጋቸው ነው ወይ? ኢሕአዴግ እንቢ ሲል የድርድሩን ሒደት በሚፈልጉበት መንገድ ለማስለወጥ የሚችሉት በምን መንገድ ነው? ምንም ዓይነት የማኅበረሰቡ አቅምና ጉልበት በሌለበት ሁኔታ ፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድሩ ተሳትፎ አዳማቂ ሆኖ ከማለፍ ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ጉልበትም ግንዛቤም ያላቸው ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተወክለው ሙያዊ ትንታኔ በሚሰጡበት መልክ አለመሆኑ ድርድሩን ጎዶሎ ያደርገዋል፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለድርድር ሲመጡ አቅማቸው ለድርድር የሚያበቃቸው መሆኑ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም አቅም የላቸውም ብዬ ስለማስብ ኢሕአዴግ የሚሰጠውን ከመቀበል ውጪ ያለፈ ነገር አይኖራቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተገናኘ ከዚህ ቀደም በተለይ የፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅን ሲያሻሽሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ወክለን ነው የምንሳተፈው ብለው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን እኛ እየተደራደርንበት ያለው ጉዳይ ሕግ ሆኖ ስለሚወጣ፣ የአገሪቷን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁን ላሉትም ሆነ ወደፊት ለሚመጡት የሚያገለግል ነው የሚል ክርክር አላቸው፡፡ ይህንን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር እንዴት ያዩታል?

አቶ ሙሼ፡- እንግዲህ ማንኛውም ድርድር ዋጋ አለው፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካ መመራት ያለበት በውይይትና በድርድር ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ በሚፈጠረው አዎንታዊ ውጤት አገርን መምራት ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ድርድር ግን በተመጣጣኝ ኃይሎች መካከልና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ተዋናዮች መካከል መካሄድ የሚገባው ነው እንጂ፣ አንተ የፈለግከውን አንድ ሰው መርጠህ ከእነዚያ ሰዎች ጋር በመፃኢ የኢትዮጵያ ዕድል ላይ ተወያይቼ እወስናለሁ ማለት ኢዴሞክራሲ ነው፡፡ ውጤቱም በጉልበት የሚጫን ነው የሚሆነው እንጂ የሁሉንም ይሁንታ አያገኝም፡፡ ይሁንታ የሌለው አማራጭ ደግሞ አማራጭ ሊሆን አይችልም፡፡ መጀመሪያ የማኅበረሰቡ ይሁንታ ያስፈልገዋል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የማኅበረሰቡ ይሁንታ አላቸው ወይ? ተቀባይነት አላቸው ወይ? ስትል ማኅበረሰቡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ገለል አድርጎ አጀንዳውን በራሱ ይዞ በቁጣ የወጣበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ስለዚህ ምንድነው የእነሱ ይሁንታ የሚለውን ነገር ይመጣብሃል፡፡ ይህ ነገር ከልብ የታመነበትና ለውጡንም ውጤታማ ለማድረግ ታቅዶ ከሆነ ከላይ የገለጽኳቸውን ተዋንያን ማሳተፍ አለበት፡፡

      ለምሳሌ አሁን እነዚህ እንደ ድርድር መነሻ ሆነው የቀረቡት ነገሮች ከሙያ አኳያ እንዴት ነው የሚታዩት? በዓለም ላይ ያለው የምርጫ ሥርዓት በትልልቅ አሥራ ሁለት ክፍሎችና በሦስት ዋና ዋና መሥፈርቶች የሚከፈል ነው፡፡ ብዙ ዓይነት የምርጫ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚያ ምርጫዎች ቀርበው መጀመርያ በትክክል ተተርጉመው፣ አማራጮች በትክክል ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚሄዱ መሆናቸው ተመዝኖ፣ ሙያዊ ትንታኔ ተሰጥቶባቸው ነው የተጀመሩት? ኢሕአዴግ የራሱን የቤት ሥራ ሠርቶ መጣ፡፡ ሌሎች አማራጮች ሳይሆኑ የቀረበት ቁጥሩ ነው፡፡ ስንት ሰው በአብላጫ ስንት ሰው በተመጣጣኝ ይወከል የሚል ክርክር ነው የተደረገው እንጂ፣ ለምን ይህ ሆነ የሚል ነገርም አልነበረም፡፡ ስለዚህ ከሙያ ድጋፍ አንፃር ኢሕአዴግን የሚቃወም ሆነ የሚደግፍ ገለልተኛ የሆነ ሰው መሳተፍ ነበረበት፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ይወስናል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ይህ አለመደረጉ ስህተት ነው፡፡ አሁንም ይህ ዕድል በሌለበት ሁኔታ ይህ ውሳኔ ለእኔ የኢሕአዴግ ፍላጎት ውጤት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስቲ ወደ ምርጫ ሥርዓቱ ማሻሻያ እንምጣና ባለፈው ሳምንት ከረዥም ድርድር በኋላ አብላጫና ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ለመተግበር ተስማምተዋል፡፡ ኢሕአዴግ መጀመርያ 10 በ90፣ ከዚያ 15 በ85 መጨረሻ ላይ ደግሞ 20 በ80 እንዲሆን አቅርቧል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ መጀመርያ 50 በ50 ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን 40 በ60 ብለው ኢሕአዴግ አልተቀበለውም፡፡ ኢሕአዴግ ያቀረበውን 20 በ80 ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ቅይጥ ትይዩ የሚባለው የምርጫ ሥርዓት ትከተላለች ማለት ነው፡፡ ለአንድ ኢትዮጵያዊ በቀላሉ እንዲገባው ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት ምን ማለት ነው?

አቶ ሙሼ፡- ቅይጥ ትይዩ የምትለው ምንድነው? ሁለት የምርጫ ሥርዓቶችን መቀየር የምንለው ነው፡፡ ይህን የምታደርገው በአንድ በኩል የምርጫ ብዝኃነትን ለማሳየት ነው፡፡ ይህ ማለት አብላጫ ማለት አብዛኛውን የማግኘት ነገር የሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዝኃነት ማለት አካታችነትን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ አንዳንዶች አገር ላይ ያለው ልምድ ምንድነው ለሁለቱም ነው ድምፅ የምትሰጠው፡፡ ብዝኃነት ማለት ውክልና ነው፡፡ አንድ ፓርቲ ባገኘው ድምፅ ልክ የሚሳተፍበት አሠራር ነው፡፡ ይህ አሠራር ደግሞ ድምፆች እንዳይባክኑ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አብላጫ ድምፅ የሚያገኘው ከአጠቃላይ ትልቁን ድምፅ ወይም ትልቁን ድርሻ ወስዶ መንግሥት የሚመሠርትበት ይሆናል፡፡ ይህ የውክልና ጉዳይ ነው፡፡ የተወሰነ አካል ድምፁ እንዳይባክንና እንዲወከል የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ወረዳ ላይ ጉልበት ያላቸው ፓርቲዎች ትልቅ ድምፅ ይኖራቸዋል፣ ግን 50 በመቶ አያመጡም፡፡ መንግሥት የመመሥረት አቅም ስለሌላቸው ባገኙት ድምፅ ልክ እንዲወከሉ ታደርጋቸዋለህ፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በርካታ ፖለቲካዊ ችግሮች አሉ፡፡ ይህን ከመፍታት አንፃር የሚኖረው ጠቀሜታ ምንድነው?

አቶ ሙሼ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጫ ሥርዓታችን ትልቁ ፈተና ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ የማካሄድ እንጂ የመወከል ጉዳይ ነው ብዬ አላምንም፡፡ መጀመሪያውኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መደረግ ያለበት ነፃ፣ ገለልተኛ የሆነና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ የሚያካሂድ ተቋም መገንባት ነው ያለብን፡፡ መጀመሪያ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ችለናል ወይ? ይህንን የሚያካሂደው ተቋም በማኅበረሰቡ ዘንድ ተዓማኒነት አለው ወይ? ተቃዋሚዎች ወደ ምርጫ ሲገቡ መጀመርያ በተቋሙ ላይ ጥርጣሬ ይዘው ነው፡፡ ወደ አሁኑ ዓይነት ድርድር የምታመጣው መጀመርያ የምናካሂደው ምርጫ ፍትሐዊ ሆኖ፣ በዚ ፍትሐዊ ምርጫ ተገቢውን ወንበር ማግኘት እንደማትችል በተግባር ሲረጋገጥ ነው፡፡ ያ ገና አልተረጋገጠም፡፡ ምክንያቱም ይህን ከሚያካሂደው ተቋም ጋር ፀብ ላይ ነው ያለነው፡፡ ይህ ተቋም ባለበት ሁኔታ በዚህ መንገድ የሚሰጥህ ወይም የሚቀርብልህ ወንበር የሕዝቡ ይሁንታ አለው አልልም፡፡ ችሮታ ነው፡፡ ለምንድነው መጀመርያ ችሮታ ውስጥ የምንገባው? በነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ አማካይነት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውድድር አካሂደው ከዚያ በሚገኘው ውጤት ላይ ተመርኩዘን፣ አሁን ወደምትለው የምርጫ ሥርዓት ልናመጣ እንችላለን፡፡ ግን ያ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተሞከረም፡፡ ይህ ለእኔ ያኛውን ሥርዓት አልፎ ለመሄድ የማደረግ ጥረት ነው የሚታየኝ፡፡ ምርጫ ቦርድ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ የሚነሳበትን ጥያቄ እንዴት አድርጌ ተጣጥፌ ላሳልፈው ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ገለልተኝነቱ ጥያቄ ላይ የወደቀ ተቋም ነው፡፡ እሱ የሚያካሂደው ምርጫ ነፃም፣ ገለልተኛም አይደለም፡፡ ተዓማኒነት የሚጎድለው ነው እየተባለ ነው፡፡

      የሚዲያ አጠቃቀማችን ገለልተኝነት የሚጎድለው ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ የሚዲያ አጠቃቀም ላይ እንደዚህ ነው የሚካሄደው፡፡ እነዚህ ሁሉ ካልተፈቱ ችሮታ ምን ያደርጋል፡፡ ከሕዝቡ በስተጀርባም የሚያስነሳው ጥያቄ አለ፡፡ ሕዝቡስ በችሮታ ለተቃዋሚዎች ወንበር ስጡልኝ የሚል ጥያቄ መቼ አነሳ? ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ይካሄድልኝ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ መጀመሪያውኑ እንደ ጥያቄ ሊነሳ የሚገባው ነገርም አይደለም፡፡ ከገጠመን ችግር አንፃርም መውጫ መንገድ አይደለም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ እዚያ ላይ እንነጋገር፡፡ ይህንን የሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ገለልተኛ ነው ብለው ያመኑ ናቸው ማለት ነው፡፡ በነፃና ገለልተኛ ምርጫ ሥርዓት ውስጥ ማሸነፍ ስላቃተን ውክልና የምናገኝበት ሁኔታ ይመቻችልን የማለት ያህል ነው፡፡ መጀመርያ ያኛው ስላልተሞከረ እርሱ ተሞክሮ ቢሆን ኖሮ እየተጠየቀ ያለው ይህንን እረዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተከፈቱ አማራጭ መድረኮች ተጠቅመው ማሸነፍ ስላልቻሉ፣ ሕዝቡ ደግሞ መወከል ስላለበት በምንም ይሁን በምንም መንገድ ይወከል ልትል ትችላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ደግሞ ከዚህ አንፃር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር? በተለይ ድርድር ሲባል ሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ ይህን እሰጥሃለሁ ይህን እቀበላለሁ የሚባል ነገር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ማድረግ ነው ያለባቸው?

አቶ ሙሼ፡- መጀመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስንል ትናንትናና ዛሬ ይለያሉ፡፡ ዋናው ነገር እሱ ነው፡፡ ትናንትና ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በቂ የሆነ የሕዝብ ይሁንታና ድጋፍ አግኝተው መንግሥትን በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ማስገደድ የቻሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ምክንያቱም ይህ ጉዳይ የኃይል ሚዛን ጉዳይ ነው፡፡ ድርድር የኃይል ሚዛን ጉዳይ ነው፡፡ ዝም ብለህ እርቃንህን መጥተህ የአገሪቱን ሀብት ከያዘ ፓርቲ ጋር ልትደራደር አትችልም፡፡ የሚልህን ተቀብለህ ነው መሄድ ያለብህ፡፡ ስለዚህ እኔ እንደሚመስለኝ መጀመሪያ ሥራው መሠራት ያለበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደዚህ ነገር ከመግባታቸው በፊት ምን ዓይነት ውክልና ነው ያለን? ያለን አቅም ምን ያህል ነው? በሚሉት ላይ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ስለዚህ አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቅሙ አላቸው ወይስ የላቸውም የሚለው ላይ ነው የሚጥለን፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ላይ ነው የሚጥለን፡፡ መጀመርያ ሥራቸውን ሠርተዋል ወይ? ምን ያህል አባል አላቸው? ምን ያህል ደጋፊ አላቸው? የሕዝቡንስ ጥያቄ ይወክላሉ ወይ? ተቃዋሚዎች ቆመው መጠየቅ ያለባቸው ይህን ነው፡፡

      ይህ የምርጫ ሥርዓት ዕውን የሆነው በውክልና ሳይሆን በቀጥታ ተሳትፎ ነው፡፡ እንዴት ነው በቀጥታ ተሳትፎ የተወሰነን ውሳኔ አጥፈህ፣ አቅምህ ደካማ እንደሆነ እያወቅህ፣ የኢሕአዴግ ተፅዕኖ እንደሚኖርብህ እየገባህና ይህንን በባለቤትነት ወስደህ ለመደራደር ቁጭ የምትለው? ይህ መብት የላቸውም፡፡ ኢሕአዴግ ከፈለገ በምክር ቤት ተወያይቶ ማፅደቅ ነው ያለበት፡፡ ይህንን የድርድር ገጽታ መስጠትም አግባብ አይደለም፡፡ በቀጥታ ተሳትፎ በሕገ መንግሥቱ የተካተተን ነገር እየለወጥህ ነው፡፡ ያንን ለመለወጥ የሚያስችል ሥልጣን ያለው ማን ነው? ኢሕአዴግ አነሰም በዛ ቁጥሩ ሊያከራክረን ቢችልም በምርጫ አሸንፎ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ካሸነፈ ውክልና ምንድነው? ምርጫ ቦርድ ስለመዘገባቸው ብቻ ነው? አንዳንዶቹ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂደው አያውቁም፡፡ አንዳንዶቹ አባል እንዳላቸውም እግዚአብሔር ይወቅ፡፡ አንዳንዶቹ ከቤታቸው የተጠሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ግለሰብ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ መፃኢ ዕድል በሚወስን ነገር ላይ ቁጭ ብለህ ስትነጋገር እንዴት ነው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያየኸው? እውነት ይህ መብት አለኝ ወይ? ይህንስ ለማድረግ እኔ ኃላፊቱ አለብኝ ወይ? ግዴታው አለብኝ ወይ? ብለህ ማሰብ አለብህ፡፡

      ምንም ዓይነት አባል የሌላቸው፣ በሕጉ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔ ያላካሄዱ፣ ሒሳባቸውን ኦዲት ያላስደረጉ፣ ምርጫ በወቅቱ የማያካሂዱ ፓርቲዎች በሕጉ መሠረት ሠርተፊኬታቸውንም መነጠቅ አለባቸው፡፡ እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝቡን ወክሎ ቁጭ ብለው በኢትዮጵያ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሊደራደሩ ህልውናቸውም መክሰም የሚገባው ነው፡፡ እነዚህን ይዘህ በኢትዮጵያ ሕዝብ ህልውና ላይ ድርድር እያደረግኩ ነው ሲባል፣ ኢሕአዴግም እንደ ድርጅት ተቃዋሚ ነን የሚሉትም እንደ ፓርቲ ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር አለው፡፡ እና ምንድነው ማድረግ ያለባቸው ከተባለ እውነትም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታማኝ ከሆኑና ይህ ድርድር መካሄድ ካለበት ፎርምም፣ ቅርፅም ይዘትም እንዲለወጥ ነው ትግል ማድረግ ያለባቸው፡፡

      ኢሕአዴግ ቀድመው የተዘጋጁ ነገሮች ይዞ ነው የመጣው፣ ያስታውቃል፡፡ እነርሱ ግን ከ50 ሲነሱ ለምንድነው ከ50 የተነሱት? 50 ይዘው ተነስተው እንዴት ነው ከግማሽ በላይ የሚወርዱት? በድርድር ያቀረብከውን አጀንዳ ጥለህ ድርድር ላይ ነኝ የምትለው፡፡ ሰጥቶ መቀበልም እኮ አንድ ነገር ነው፡፡ 50 በመቶ ትወርዳለህ፡፡ ከዚያ በታች እኮ ተሸናፊነት ነው፡፡ 50 በመቶ ይዘህ መጥተህ 20 በመቶ ይዘህ ቤትህ ስትገባ ድርድሩ እኮ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሽፏል፡፡ ሰጥቶ መቀበል ማለት 50/50 ጉዳይ ነው መሆን ያለበት፡፡ ሲጀመር አማራጮችን ይዘው አልመጡም፡፡ ስንት አማራጮች? እነዚህ አማራጮችስ ቀርበው ነበር ወይ? ማን ነው ይህንን ይዞ የመጣው? ይህንን ይዞ ሲመጣ ምን አጀንዳ ይዞ ነው? ለራሱ እንዲመቸው ነው? እውነትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ ነው? በዚህ መንገድ ተቃዋሚዎች ማድረግ የነበረባቸው የሕዝብ ውክልና የለንም፡፡ ታማኝነት የለንም፡፡ እንደሚባለው በቂ የሕዝብ ውክልና የለንም፡፡ አንዳንዶቻችንም ግለሰቦች ነን፡፡ ስለዚህ ይህ መድረክ ውክልናው መስፋት አለበት፡፡ ሌሎቹ እንዲሳተፉ ዕድሉ መሰጠት አለበት ማለት ነበረባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ድርድር የተጀመረው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ ሕዝቡ ያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ በዚህም ሳቢያ ነው ፕሬዚዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ነገሮችን እንደሚያስተካክሉ ቃል የገቡት፡፡ አሁንም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ተቃውሞዎች እንደ ቀጠሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ምንድነው ታዲያ መፍትሔው?

አቶ ሙሼ፡- መፍትሔው ለእኔ ቀላል ነው፡፡ መጀመርያ ኢትዮጵያ ውስጥ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ ይቋቋም፡፡ ከዚያ በሚገኘው ውጤት ላይ መንግሥት የሚሆነው አካል የሚሠራውን ሥራ ለሚቀጥለው አምስት ዓመት መቀበል ነው፡፡ አሁን እኮ ሁልጊዜ የማያቋርጥ ጥያቄ የሚነሳው ኢሕአዴግ በእውነተኛ ምርጫ አላሸነፈም የሚል ጥያቄ ስላለ ነው፡፡ ሲጀመር የሁሉ ነገር ማዕቀፍ ይኼ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በተቃዋሚዎችም በተለያዩ መንገዶች ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ጥያቄው ነፃና ገለልተኛ ነኝ በሚለው ሚዲያ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ አሁን ያ በሙሉ ተጠራርጎ ስለጠፋ ነው ሕዝቡ ራሱ ተዋናይ ሆኖ የመጣው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ገለል አድርጎ ራሱ ተዋናይ ሆኖ መጣ፡፡ አሁን ችግሩ እየሰፋና ውስብስብ እየሆነ የመጣው ደግሞ ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ፍልስፍና የለውም፡፡ ይህንን የተቃውሞ ኃይል የሚመራው የራሱ አመራር፣ ግብና አቅጣጫ ስለሌለው ነው፡፡ ቁጣ፣ ብስጭትና ተስፋ መቁረጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ለእኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ገለልተኛ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ የሁሉም ነገር መፍቻ እሱ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ነገር በየአካባቢው የተነሳው ቁጣ መልስ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የተባለው ነገር አሁንም ለሌላ ቁጣና አለመረጋጋት ሊጋብዝ በሚችል መንገድ እየሄደበት ያለው ምክንያት አንድ ነው፡፡ ድርድሩ የማኅበረሰቡን ውክልና እንዳገኘ አድርገህ ስለጀመርከው፣ ማኅበረሰቡ ደግሞ እነዚህ ሰዎች አይወክሉኝም ብሎ ስለሚያስብ፣ ማኅበረሰቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች አይደሉም አሁን ድርድር እየተካሄደባቸው ያሉት፡፡ ስለዚህ ሐሰት ነገሮች ነው መቅረብ የነበረባቸው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸው አጀንዳ አላቸው፡፡ መድረክ ማጣት፣ ትግላቸውን ለማካሄድ አፈናው፣ እንግልቱ፣ እስሩና መሰደዱ የፈጠረባቸውን ተፅዕኖ ለማስለወጥ የሚያደርጓቸው ትግሎች አሉ፡፡ ይህ በአብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝባዊ ጥያቄዎችም ነበሩ፡፡ የአስተዳደር፣ የአገልግሎት፣ የፍትሕ እጦት፣ የሥራ አጥነት ችግር፣ ወዘተ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በዚህ ድርድር ላይ በትይዩ መቅረብ ነበረባቸው፡፡ አሁን በአብዛኛው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የግል ፍላጎቶች ናቸው እየቀረቡ ያሉት፡፡ የፖለቲካ፣ የፋይናንስ፣ ሚዲያ የማግኘት በከፊል የሕዝቡ አጀንዳ ቢሆኑም፣ የምርጫ ሥርዓቱና የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ግን ከዚያ ውጪ መሠረታዊ የተባሉ ሕዝቡን ወደ ቁጣ የወሰዱት ጥያቄዎች አልቀረቡም፡፡ በውይይቱም አልተካተቱም፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ ይጠበቅብሃል፡፡ ያንን ካደረግክ አሁን የምትለው ችግር ይፈታል፡፡ ሁለት የባዕድ አገር ሕዝቦች አይደሉም ትግል ላይ ያሉት፡፡ አንድ አገር ውስጥ የተሻለ አስተዳደር የሚፈልግ ሕዝብ ትግል እያካሄደ ነው ያለው፡፡ የኢፍትሐዊነት ጥያቄ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ የመብት ጥያቄ፣ የነፃነት ጥያቄ፣ የተጠቃሚነት ጥያቄ ነው አገሪቷ ውስጥ እየተነሳ ያለው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለመፍታት መጀመርያ መንግሥት ያስፈለገው ለዚህ ነው፡፡ መንግሥት ሌላ ዓላማ የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሄድ ብዙ ችግሮች ይፈታሉ ብለዋል፡፡ ይህንን ነገር ለማድረግ አልተቻለም፡፡ በተለይ ከከ1997 ዓ.ም. በኋላ ያለው ሒደት እየታየ ነው፡፡ ግለሰብ አስተያየት ሰጪዎችም የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ኢሕአዴግ እንኳ ሳይቀር እያለ ያለው ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት ነው፡፡ ሲሆን ግን አይታይም፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚታረቁት መቼ ነው ታዲያ? ሁልጊዜ ይባላል፡፡ ግን አይደረግም፡፡ ምርጫው ገለልተኛ፣ ነፃ፣ ታማኝ ነው ይላል ኢሕአዴግ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ አይደለም ይላሉ፡፡ ችግሮች እየሰፉ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሐሳቦች አስታርቆ ፍትሐዊ፣ ገለልተኛና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መቼ ነው የሚካሄደው?

አቶ ሙሼ፡- መጨረሻ ካልከው ጋር ብዙም አልስማማም፡፡ ጨለምተኝነት ነገር አለው፡፡ ለእኔ ይህ የሚመጣው ከኢሕአዴግ ባህሪ ነው ብዬነው የማምነው፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን የሚያህል ግዙፍ መንግሥት ከትንሽ ጥንስስ ተነስቶ አሸንፎ ስለመጣ፣ በውስጡ ልዩ ተልዕኮ የተሰጠው ድርጅት አድርጎ ራሱን ይቆጥራል፡፡ ይህ አመለካከት ለሌሎች ዕውቅና መስጠት ላይ ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡ ስለዚህ ሁሌ እንደምትሰማው የ40 እና የ50 ዓመት ዕቅድ ይዞ ነው የሚናገረው፡፡ አንድን መንግሥት 40 ዓመት ማቀድ በአንድ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ዕድል ገጥሟል፡፡ የተለየ አዲስ ነገር አይደለም ሙከራ የምናደርገው፡፡ ምርጫ 97 ለኢሕአዴግ የሚኮመጥጥ ጊዜ ነበር፡፡ ወደዚያ መመለስ አይፈልግም፡፡ የ40 ዓመት የተሰጠውን ዕቅድ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ከዚያም 60 ዓመት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ኢሕአዴግ እያለ ያለው እየሞከርኩ ነው፣ እየጣርኩ ነው፣ ካልገባኝም መታገስ አለባችሁ ነው እያለ ያለው፡፡ አዲስ ነገር ሁልጊዜ መምጣት ያለበት ከኢሕአዴግ ነው፡፡ ለውጥ መምጣት ያለበት ከኢሕአዴግ ነው፡፡

      በአገራችን ጉዳይ ከዚህ የበለጠ ንግግር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ቦታ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ሥራ እፈልጋለሁ የሚል ሕዝብ እየመጣ ነው፡፡ ሕዝቡ የራሱን መብት ለማስከበር እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ሕዝቡ በሰላማዊ መንገድ አማራጩን እየወሰደ የሚሄድበት ዕድል እስከተከፈተ ድረስ አንተ የምትለው ነገር ዕውን ይሆናል፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ግን አይደለም፡፡ ምድር ላይ የመጣሁት አንዳች ኃይል ለማውረድ ነው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያንን እስከማወርድ ድረስ እየወደቅኩም፣ እየተነሳሁም፣ እየተሳሳትኩም፣ እያፈርስኩም፣ እየገነባሁም እቀጥላለሁ ካለ ቅድም አንተ ያልከው ነገር ሊከሰት አይችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊና በሕዝብ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ይህ የአንድ ሃይማኖት ዓይነት ነገር ነዋ፡፡ ከዚህ አስተሳሰቡ ካልወጣ አሁን የምትለው ነገር ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡