Skip to main content
x
‹‹አንድ ልጅ ሲደመር አንድ ላፕቶፕ አንድ ትልቅ ቢዝነስ ይሆናል››

‹‹አንድ ልጅ ሲደመር አንድ ላፕቶፕ አንድ ትልቅ ቢዝነስ ይሆናል››

 

 

አቶ ቴድሮስ ታደሰ፣ የሴንተር ፎር አፍሪካ ሊደርሺፕና

የኤክስ ሀብ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አቶ ቴድሮስ  ታደሰ የሴንተር ፎር አፍሪካ ሊደርሽፕ ስተዲስና የኤክስ ሀብ አዲስ መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ሴንተር ፎር አፍሪካን ሊደርሽፕ ስተዲስ የተቋቋመው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ የማማከር አገልግሎት፣ የወጣቶችና የሴቶች አመራር ብቃት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥልጠናዎችንም ያከናውናል፡፡ የድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴና በወጣቶች የፈጠራ ሥራዎች የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ቴድሮስ ታደሰ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ኤክስ ሀብ ምን ላይ ነው የሚሠራው?

አቶ ቴድሮስ ፡- ብዙ ጊዜ ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስጓዝ ሀቦችን አያለሁ፡፡ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ አይስ አዲስ ሥራ ጀምሮ ስለነበር እንድሠራ ያነሳሳኝ ሞራል ይሰጠኝ ነበር፡፡ ሌሎች ከተሞችም ስሄድ ፈጥኜ የቴክኖሎጂ ሀቦች አሊያም ሶሻል ኢንተርፕሩነርሺፕና ኢኖቬሽን ላይ የሚሠሩ ሀቦችን አያለሁ፡፡ እኛ ማኅበረሰቡን ከትርፋችን እንዴት ነው ማጋራት የምንችለው እያልኩ በማስብበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ሀቦችን ስመለከት ለአገራችን የምንሰጠው ስጦታ ትልቁን ስጦታ መሆን አለበት ብዬ ወሰንኩ፡፡ ይህ ትልቁ ስጦታ ደግሞ ሰው ነው፡፡ ከሰው በላይ ምንም ስጦታ የለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሚወጡበት ፕሮግራም ቢኖረን እነዚያ ሰዎች ደግሞ ተመልሰው ወደ ማኅበረሰቡ ቢቀላቀሉ ሰው ሰጠን ማለት አይደለም? ከዚያ በኋላ ለረዥም ጊዜ እንቅልፍ አልተኛም ነበር፡፡ ይህንን ጉዳይ ሳስብ ነበር የማድረው፡፡ ልጅ ሆኜ ብዙ ሐሳቦች ነበሩኝ፡፡ ሐሳቦቼ በሙሉ ግን ከምናብ ሳያልፉ ውኃ ይበላቸዋል፡፡ መንገዱን የሚያሳየኝ ስላልነበር አንዳንዶቹን በማስታወሻዬ ላይ አሠፍር ነበር፡፡ እያደግኩ ስመጣ ግን ሁሉም ነገር በአንድ ወቅት ሐሳብ እንደነበር ይገባኝ ጀመረ፡፡ ሰማይና ምድር፣ ተራራና ወንዙ ሳይቀር በአንድ ወቅት በአምላክ ውስጥ የነበሩ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ የሰው ልጅ በራሱ አምላክ ውስጥ የነበረ ሐሳብ ነው፡፡ ሐሳብ ክቡር ነው፡፡ ሐሳብ የማያከብር አገር ሁሌም ደሃ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ሐሳብ የሚከበርበት፣ ሰው የሚሠራበት ቦታ ‹‹ሀብ›› ነው፡፡ እነዚህን ልጆች የሚቀበላቸው ከባቢ ከተፈጠረ የማኅበረሰብ ተሃድሶ ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ማኅበረሰብ የሚቀየረው በሐሳብ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፋው ትልቁ ነገር በተለይም በፖለቲካው የሚያስታርቅ ሐሳብ ነው፡፡ ያ ሐሳብ እስከሚገኝ ድረስ አገር ይረበሻል፣ ድህነት ይስፋፋል፣ ብጥብጥ ይበዛል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በሐሳብና በሰዎች መካከል ጋብቻ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ደግሞ የኢንኪዩቤሽንና የኢንተርፕሩነርሺፕ ማዕከል መፍጠር ግድ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮች ምንድናቸው? ምን ዓይነት ሐሳቦችስ ይፈቷቸዋል የሚለውን ለመለየት ዳሰሳ (ሰርቬይ) መሥራት ጀመርን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በየዕለቱ ላፕቶፓቸው ላይ ከአራት እስከ ሰባት ሰዓታት ድረስ ጊዜ የሚያጠፉ በትንሹ ከ7,000 እስከ 10,000 የሚሆኑ ወጣቶች መኖራቸውን ተመለከትን፡፡ እነዚህ ወጣቶች በየቀኑ 49,000 ሰዓታት ያጠፋሉ፡፡ ችግሩ እነዚህ ወጣቶች ላፕቶፖቻቸው ላይ የሚያጠፉት ጊዜ ሳይሆን ልጆቹ ተበታትነው ስለሚሠሩ እንዱ ከአንዱ መማር አይችልም፣ መንገዱን የሚያሳያቸው አያገኙም፡፡ ስለዚህ የሚችሉትን ያህል ይሠራሉ ውጤታማ ግን አይደሉም፡፡ ነገ መጥተው የሚከፍቱት ትላንት ካቆሙበት ሳይሆን፣ ከጀመሩበት ነው፡፡ ትምህርት ከባቢ ይፈልጋል፡፡ አቅጣጫ ያስፈልገዋል፡፡ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡፡ ይህ ባለመኖሩ አገሪቱ ከእነዚህ ወጣቶች ላይ በትንሹ 49,000 ሰዓታት ታጣለች፡፡ እነዚህ ወጣቶች ምን መሥራት እንደሚፈልጉ ገና አልለዩም፡፡ የየራሳቸው የሆነ ግራፊክ ዲዛይንም ይሁን ሌላ ነገር የሚሞክሩ ናቸው፡፡ ሐሳባቸውን መስመር የሚያሲዝላቸው ሰው ባለመኖሩ አገሪቱ  ከልጆቹ በየዓመቱ የምታጣው ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ሰዓት ተበታትኖ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ የአይቲ ዘርፍ ይሻሻላል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህም እነዚህን ልጆች እንሰብስብ፣ የቴክኖሎጂ ሀብ እንክፈት የሚል ውሳኔ ላይ ደረስን፡፡ እነዚህ ወጣቶች የሞባይል አፕሊኬሽን፣ ኢንተርኔት ቤዝድ ሶሉዊሽን ወይም ሶፍትዌር ሶሉዊሽን እንዲያመጡ እናግዛቸዋለን፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላም ሰባት ልጆች ያሉበት፣ አምስት ወጣቶች ያሉበት፣ ሁለት ልጆች ያሉበት፣ በሦስት ግሩፕ የተከፋፈሉ ወጣቶችን ጥሩ ኢንተርፕሩነር አደርገን አበቃናቸው፡፡ እነዚህን ልጆች ካየን በኃላ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ሥርዓት ለመዘርጋት ወስንን፡፡ በዚህም ኤክስ ሀብ ተወለደ ማለት ነው፡፡ ኤክስ ሀብ ከተመሠረተ ወደ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኤክስ ሀብ ከተመሠረተ በኋላ አበረታች ለውጥ ማየት ችላችኋል?

አቶ ቴድሮስ ፡-  ሦስት ዓመታት ከሠራን በኋላ ውጤታችን ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ ቢያንስ በአራት ግሩፖች ውስጥ የሚገኙ ወጣቶቸን ጥሩ አድርገን ቀርፀናል፡፡ በርካቶችን ደግሞ ለጥሩ ነገር እንዲነሱ ማድረግ ችለናል፡፡ የአይሲቲው ማኅበረሰብ የሚሰባሰብበት ከባቢም መፍጠር ችለናል፡፡ የአይቲውን ማኅበረሰብ ማገናኘት ቻልን፡፡ በመጀመርያው ሳምንት ከጉግል ሰዎች መጥተው በቢሯችን ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሚመሩ ተማሪዎች መምጣትም ችለዋል፡፡ ማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ የሚማሩ ተማሪዎችም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ያስተማሩት እዚህ ነው፡፡ ከአየርላንድ፣ ከአውትራሊያ፣ ከፈረንሣይና ከተለያዩ አገሮች ሰዎች እዚህ እየመጡ እንማማራለን፡፡ ሀብ የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ሰዎች ከተለያየ ቦታ መተው የሚገናኙበት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በኤክስ ሀብ ምንምን ዓይነት ባለሙያዎች ይሰባሰባሉ?

አቶ ቴድሮስ ፡-  ሀቡ የተለያዩ ሰዎች መጥተው የሚገናኙበት ቦታ ነው፡፡ የእኛ አሠራር ምን ይመስላል ብለን ስናስብ ሦስት ነገሮች እንዲገናኙበት አደረግን፡፡ ዲዛይን የሚሠሩ፣ ኮደሮች፣ ሶፍትዌር የሚሠሩና በአራተኛ ደረጃ ገንዘብ ያላቸው ኢንቨስተሮች የሚገናኙበት እናድርገው ብለን ነው የፈጠርነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ሰዎች የሚገናኙበት ሀብ ፈጥረን፣ ነገር ግን ማውጣት የቻልነው አራት ቡድን ብቻ ነው፡፡ የአይቲ ኢንተርፕሩነርስን ለመፍጠር እኛ ብቻ በቂ አይደለንም፡፡ ዲዛይኑን ከሚሠሩ፣ ከኮደሮች፣ ሶፍትዌሩን ከሚሠሩና ከኢንቨስተሮች በተጨማሪ ኢንተርኔቱን የያዘው አካል መንግሥት፣ የንግድ ምዝገባ ላይ ፈቃድ የሚሰጠው አባልና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉበት ይገባል፡፡ እኛ ግን በጣም የተበታተንን ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአይቲ በተጨማሪ በሌሎች የሥራ ፈጠራ መስኮችስ ትሠራላችሁ?

አቶ ቴድሮስ ፡- አዎ እንሠራለን፡፡ ሦስት ዓመታት ያህል ከሠራን በኋላ ነው ለምን አይቲ ብቻ ላይ እንሠራለን ወደ ሶሻል ኢንተርፕሩነርሽፕ፣ ቢዝነስ ኢንኪዩቤሽን እንግባ ያልነው፡፡ ቆሎ መሸጥ የምትፈልግ ወጣት ትምጣና ቆሎዋን ፈጠራ በታከለበት፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ችግር በሚፈታ መንገድ ትሥራው፡፡ ፎቶግራፈር፣ ልብስ ሰፊ ከሆነም ይምጣ፣ ለአይቲ ግን የተለየ ትኩረት እንስጠው ብለን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- አይቲ ላይ ብቻ የተለየ ትኩረት ማድረጉን የመረጣችሁት ለምንድነው?

አቶ ቴድሮስ ፡- በአይቲ ላይ የተለየ ትኩረት የምናደርገው አንደኛ ወደፊት ሁሉም ነገር በአይቲ ላይ ጥገኛ እየሆነ ስለሚሄድ ነው፡፡ ሁለተኛ ከድህነት መውጫ ቀላሉ መንገድ አይሲቲ በመሆኑ ነው፡፡ ለመንግሥት እንዴት ማሳየት እንደምንችል ግራ የገባኝ ነገር መንግሥት ግን ያላየው፣ ከድህነት ማምለጫ መንገድ ነው፡፡ አስፈላጊው የመሠረተ ልማት አውታር ዝርጋታ ከተሻሻለ፣ የኢንተርኔት አቅርቦት ጥሩ መሆን ከጀመረና ጥቂት ድጋፍ ከተደረገበት፣ አንድ ልጅ ሲደመር አንድ ላፕቶፕ አንድ ትልቅ ቢዝነስ ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ወጣት ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልዩ ፍቅር አለው፡፡ 70 በመቶ  የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ወጣት ነው፡፡ ኮምፒዩተር፣ ላፕቶፕና ሌሎች የቴክኖሎጂ ዕቃዎች በቀላሉ የሚገኙበት መንገድ ቢፈጠር፣ የኢንተርኔት አቅርቦት ቢሻሻል ይህችን አገር ከድህነት ማውጣት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት ወርቅም ውኃም አሊያም ሌላ ውድ ማዕድናት አይደሉም፡፡ አዲሱ ኃይል ወጣቱ ነው፡፡ ይህንን አምኖ መቀበል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ካመነችና በየትኛው ሴክተር ላይ ትኩረት ላድርግ ካለች አይሲቲ ከሁሉም ቀላሉ ነው፡፡ ይህንን መንገድ ተከትለው ብዙ አገሮች መቀየር ችለዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ደግሞ የቻሉት በፖሊሲ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያሉ ሀቦችን በመፍጠር ነው፡፡ መንግሥት ሀቦችን አይፈጥርም መፍጠርም አይጠበቅበትም፡፡ ነገር ግን ለተፈጠሩት ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ አይሀብ ናይሮቢ ላይ ሲቋቋም ለአምስት ዓመታት ያህል በሰከንድ 100 ሜጋ ባይት ያለው የኢንተርኔት ኮኔክሽን በነፃ ነበር ተሰቶት ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ የመንግሥት አካላት ቢሯቸው ቁጭ ብለው የሚሠሩትን ነገሮች ይመለከታሉ፡፡ እኔም የምፈልገው በተለያዩ የመንግሥት አካላት ተወክለው የሚመጡ ሰዎች እኛ ጋር ሲሠሩ ማየት ነው፡፡ 100 ሚሊዮን ነን ግን ብዙ ሀብ ያስፈልገናል፡፡ ብዙ ሥራ አለን፡፡ አብረን መሥራት መቻል አለብን፡፡ አብሮ ለመሥራትም ከባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በራችንን ክፍት አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶቹን ከማስተባበር ጋር ተያይዘው ያጋጠሟችሁ ችግሮች አሉ?

አቶ ቴድሮስ ፡- መጀመርያ ያጋጠመንና ያስደነገጠን ችግር ወጣቶቹ ተባብሮ ለመሥራት ፍላጎት አልነበራቸውም ነበር፡፡ ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ መበላለጥን ነበር የሚፈልጉት፡፡ ኮድ ከማድረግና ሶፍትዌር መጻፍ እስካቻሉ ድረስ ጎበዝ ነኝ ብለው ያስባሉ፡፡፡ ጎበዝ ግን አይደሉም፡፡ ኮዱን መጻፍ ለሥራ ፈጣሪው ስኬት በጣም ትንሹ የቤት ሥራ ነው፡፡ እሱ የጻፈውን ኮድ ዲዛይን አድርጎ ለተጠቃሚው እንዲቀለው አድርጎ የሚያዘጋጀው ሌላ ሰው ነው፡፡ ለገበያ እንዴት መቅረብ አለበት፣ የቢዝነስ ምዝገባውን፣ የሕግ ጉዳዩንና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮችን የሚሠሩት ሌሎች ባለሙያዎች ናቸው፡፡፡ እነዚህ ወጣቶች ይህንን አያውቁም፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ ጎበዝ ተብለው የተሸለሙት ኮድ ማድረግ ስለቻሉ ነው፡፡ እስከ ኮሌጅ ድረስ የደረሱትም ጎበዝ ጎበዝ እየተባሉ ነው፡፡ ስኬታማ ለመሆን ግን የአንቺ ጉብዝና ካሉት የቤት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው፡፡ እንዴት ተደርጎ ነው ከእኔ እኔ ወደ እኛ እኛ ማምጣት የሚቻለው? የሚለው ቀላል አልነበረም ከባዱ ሥራ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩ ሁሉም  ብቻቸውን ውጤታማ መሆን እንደማይችሉ ገብቷቸዋል፡፡ ሌላው ለእነዚህ ወጣቶች ያሳየው እናንተ በግል ነው ደፋ ቀና የምትሉት ከእናንተ ጋር የሚወዳደሩ ሌሎች ግን ከተማ አላቸው፡፡ በአሜሪካ ሲሊኮን ቫሊ አለ፡፡ ህንድም፣ ናይጄሪያም ሌሎችም አገሮች ለቴክኖሎጂ ለአይሲቲ ልማት ብቻ ተብለው የተዘጋጁ ከተሞች አሏቸው፡፡ እኛ ጋር ግን የአይሲቲው ማኅበረሰብ የሚገናኝበት ቦታ እንኳን የለውም፡፡ ሌላው በጣም የሚያሳዝነው ነገር ይህቺ አገር ለሶፍትዌር ብዙ ወጪ ታወጣለች፡፡ የእኛ ፍላጎትም ይህንን ወጪ ማስቀረት የሚችሉ ወጣቶችን መፍጠር ነው፡፡ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የሚጠቀሙባቸው ከውጭ አገር የሚገዙ ሶፍትዌሮች ለግዥ ከሚወጣው ከፍተኛ ወጪ ባሻገር አሠራሩን ተላምዶ ማሠራት አስቸጋሪና ብዙ ዓመታት ይፈጃል፡፡ ምክንያቱም በእኛ ሰዎች የተሠራ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በእኛ ሰዎች የተሠራ ቢሆን የተሻለ ይሆናል እያሉ ነው?

አቶ ቴድሮስ ፡-  አይሲቲ ላይ እኛ መሥራት ያለብን ትልቁ ምክንያት የእኛ ችግሮች ለአሜሪካና ለአውሮፓ ችግሮች አይደሉም፡፡ እነሱ የእኛን ችግሮች ካለፉ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የእነሱ ቴክኖሎጂ የእኛ ችግር አይፈታውም፣ አያውቀውምም፡፡ እኛም የምንሞክረው እነሱ የጻፉትን ፕሮግራም ወይም ሶፍትዌር ጥሩ ተጠቃሚ ለመሆን ነው፡፡ እኛ ገና ፈጣሪ አልሆንም፡፡ ጎበዙ ልጅ እንኳን ጎበዝ የሚባለው ጥሩ ተጠቃሚ ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህም ነው ትልልቅ ሶትዌሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ግርታና ጭንቀት የሚታየው፡፡ የሚጻፉትም በእኛ ቋንቋ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም ያለብንን ችግር በማቅለል ፈንታ ሌላ ችግር ይሆናሉ፡፡ የእኛ ፍላጎት ያላትን የሶፍትዌር ፍላጎት የራሷ ልጆች የሚፈጥሩላትን ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአይሲቲ ጋር ተያይዘው ከሚነሱ ችግሮች መካከል የደኅንነት ጉዳይ አንዱ ይባላል፡፡ በዚህ ረገድ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር ችግሩ ሳይፈጠር አስቀድሞ ለመከላከል የምትሠሯቸው ሥራዎች ካሉ ቢያብራሩልኝ፡፡

አቶ ቴድሮስ ፡-  ከእያንዳንዱ ሶፍትዌር ጋር አብሮ የሚመጣ የደኅንነት ችግር አለ፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች የወደፊት ችግር ደኅንነት ነው፡፡ እኛ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ ሃኪንግ ነው፡፡ ነገር ግን አንድም ባንክ እኛ ጋር መጥቶ እስቲ የእኔን አሠራር ሀክ አድርጉ ያለ የለም፡፡ እስቲ እኛ ጋር ኑና የእኛ ወጣቶች ድርጅታችሁን ሀክ ያድርጉና ከደኅንነት አንፃር ያለባችሁን ክፍተት ገምግሙ እንላቸዋን፡፡ ሌላ ሰው ከውጭ ሀክ ከሚያደርጋችሁ የእኛው ልጆች ሀክ ያድርጓችሁ ብለን ብዙ ጊዜ ለምነናቸዋል፡፡ የአገሪቱ የወደፊት ችግር የሳይበር ደኅንነት ነው፡፡ የሳይበር ደኅንነት በደመወዝተኛ አይደለም የሚረጋገጠው፡፡ የሳይበር ደኅንነት የሚረጋገጠው በነርዶች (በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምጡቅ በሆኑ) ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለድርሻዎች ጋር የመሥራቱ ነገርስ እንዴት ነው?

አቶ ቴድሮስ ፡-  ትልቁ ችግር የሆነብን ነገር መንግሥትን እዚህ ቤት ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ መንግሥት ለወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ሥራ ለመፍጠር ይደክማል፡፡ በዚህ በጣም ተሳክቶለታል፡፡ ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡ ይህንን ለማሻሻል ወጣቶቹ የሚደራጁባቸውን የሥራ ዝርዝሮች በየጊዜው ማሻሻል አለበት፡፡ ለምሳሌ እኛ ጋር የሚሠሩ ሥራዎች አዳዲስ ፈጠራዎች ናቸው፡፡ 80 በመቶ የሚሆኑት ፈጠራዎች በአነስተኛና ጥቃቅን ከተያዙ የሥራ ዘርፎች ዝርዝር ውስጥ የሉበትም፡፡ መንግሥት ከእነሱ እኩል መሄድ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን እየሄደ አይደለም፡፡ የማደራጃችሁ ዝርዝሩ ውስጥ ባሉ የሥራ መስኮች ነው ይላል፡፡ ይህ መሆን የለበትም፡፡ ለወጣቶች ካሰበ ከእነሱ ጋር አብሮ ይሥራ፡፡ ከእኛ ዓይነት ማዕከሎች ብዙ መማር ይችላል፡፡ ሌላው ጉዳይ መንግሥት ወጣቶቹን ካደራጀ በኋላ አነስ ያለ ሥልጣና ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ የገበያ ትስስር ይፈጥርላቸዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ መነሻ ካፒታል ገንዘብ ያበድራቸዋል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ላልተለወጡ ሥራ ፈጣሪ ላልሆኑ ወጣቶች ገበያና ገንዘብ ሲሰጣቸው ማንነታቸው ሊሸከመው ስለማይችል ዕዳ ውስጥ ይገባሉ፡፡ መጀመርያ ሥራው መሠራት ያለበት ሥራ ፈጣሪው ላይ ነው፡፡ ዕድሉ አይደለም መቅደም ያለበት፡፡ እኛ ደግሞ ወጣቶቹን መቀየር ላይ ተሳክቶልናል፡፡ ነገር ግን መነሻ ካፒታል የሚያገኙበትን፣ የሥራ ትስስር የሚፈጠርበትን መንገድ ማመቻቸት ላይ የመንግሥትን ያህል አቅም የለንም፡፡ ሁለታችን አብረን ብንሠራ ግን ጥሩ ይሆናል፡፡ የጋራ አገር እስከሆን ድረስ ደግሞ አብረን መሥራት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ከባለሀብቱ ጋር አብሮ በመሥራት ረገድ ያለው ነገር ምን ይመስላል?

አቶ ቴድሮስ፡- መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሲደክም የነበረው ኢንቨስተሮች ላይ ነበር፡፡ አንድን ኢንቨስተር ለማበረታታት መንግሥት ታክስ ከመቀነስ አንስቶ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ያደርጋል፡፡ እንዲህ ተለፍቶለት የሚወጣ አንድ ኢንቨስተር ለዜጎች የሚፈጥረው የሥራ ዕድል ቢበዛ ከ30 አይበልጥም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ትልቁ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ያለው የቱ የሥራ መስክ ነው ቢባል እንደ ታክሲ ያሉ የትራንፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ከተማ ውስጥ 16,000 ታክሲዎች አሉ ቢባል 16,000 ሾፌሮችና ረዳቶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ታክሲ 32,000 ሰዎች ይዟል ማለት ነው፡፡ ቡና ቤቶች፣ ሻይ ቤቶች፣ ዳቦ ቤቶች፣ እንዲህ ያሉ አነስተኛ ንግዶች ናቸው ከፍተኛውን የሥራ ዕድል እየፈጠሩ የሚገኙት፡፡ ነገር ግን አነስተኛው ድጋፍ የሚያገኙት እነዚህ ናቸው፡፡ ትልቁ ድጋፍ የሚሄደው ለኢንቨስትመንት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ትኩረት መሆን ያለበት ለእንደኛ ዓይነት ትንንሽና መካከለኛ ቢዝነሶች ነው፡፡ ለመንግሥት ማሳየት የምንፈልገው እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች ነው፡፡ ሌላው ባለሀብቱን በተመለከተም ትልቅ ችግር አለ፡፡ አቅሙ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሶፍትዌር ኢንጂነሮች ሥራ ከመስጠት ይልቅ ለአንድ ለማያውቀው የህንድ ኩባንያ መስጠት ይመርጣል፡፡ ለዚያውም ለጻፉት ሶፍትዌር አፕዴትና ጥገና በእነሱ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ነው፡፡ ሶፍትዌር ከውጭ በገዛሽ ቁጥር ለሸጠልሽ ኩባንያ ተገዥ ነሽ፡፡ ድርጅቱ በየዓመቱ አፕዴት ሲያስፈልገው ክፈል የተባለውን ከፍሎ ነው የሚያገኘው፡፡ ሥራ አቁሞ መደራደር አይችልም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ለኢትዮጵያዊ ከመስጠት ለእነሱ መስጠት ይመርጣሉ፡፡ አሁን ግን ይህንን ነገር እየቀየርን ነው፡፡ ከእኛ ጋር የሚሠሩ ዕድሜያቸው ከ21 እስከ 24 የሆኑ ወጣቶች ለአንድ ድርጅት የሰው ሀብት፣ ጥሬ ዕቃ፣ ገንዘብና የመሳሰሉትን ነገሮች አንድ ላይ ማስተሳሰር የሚችል ሶፍትዌር ሠርተዋል፡፡ ድርጅቱ ሶፍትዌሩን ውጭ ካሉ የሶፍትዌር ኩባንያዎች ለመግዛት ሞክሮ ብዙ ሚሊዮን ብር ነበር የተጠየቁት፡፡ የእኛ ልጆች ግን በተመጣጣኝ ዋጋ ነው ሠሩለት፡፡ ባለሀብቶቹ በራሳቸው አገር ተወላጆች ማመን አለባቸው፡፡ ብዙ ባለሀብቶች አሉ፡፡ የእኛ ሕልም እነዚህን ወጣቶች ከባለሀብቱ ጋር ማገናኘት ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ያለበትን ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል እንዴት መጠቀም ይቻላል ይላሉ?

አቶ ቴድሮስ፡-  ያልገባን ነገር አለ፡፡ ይኼ ሁሉ ሕዝብ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ እያለ በዘር ተከፋፍሎ ይብላላል፡፡ አዲሱ ዘር ግን ኦሮሞ፣ ትግሬ ወይም ሌላ ጎሳ አይደለም፡፡ አዲሱ ዘር ስሙ ወጣት ይባላል፡፡ 70 በመቶ የአገሪቱ ሕዝብ አማራ ወይም አፋር አይደለም ወጣት ነው፡፡ ስሙም ደስ ይላል እንደዘርም የሚዘራ ዘር ነው፡፡ እንደ ቡድንም የሚጠራ ነው፡፡ የእኛ ምኞት እዚህ ውስጥ መግባትና መሥራት ነው፡፡ የራሳቸውን አገር መምራት ያለባቸውም እነሱ ናቸው፡፡ የዚህች አገር ሀብት ሰው ነው፡፡ ሰው ላይ የሚሠራ ከተገኘ እያንኳኳች መሄድ አለባት፡፡ አሁን ኤክስሀብ ቢሮ ውስጥ ወርቅ ተገኘ ቢባል መንግሥት ሮጦ አይመጣም? ይኼው ሰው ተገኘ ወጣት ተገኘ ለምን አይመጣም?