Skip to main content
x

የኮምፒዉተር ፕሮግራም የኮፒራይት መብቶችና ግዴታዎች

በውብሸት ሙላት

የኮምፒውተር ፕሮግራም (ሶፍትዌር) እና ዳታቤዝ (በሥርዓትና በዘዴ የተሰደሩ የመረጃ ግብዓቶች) በአዋጅ ቁጥር 410/1996 መሠረት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅጅ መብት ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡

ይህ ጽሁፍ ፍተሻ የሚያደርገው ለኮምፒውተር ፕሮግራምና ለዳታቤዝ በሕጎቻችን የተሰጣቸውን ጥበቃ በመዳሰስ ክፍተታቸውንም ለማሳየት ሲሆን፣ እግረ መንገዱን መፍትሔዎቹንም ለማሳየት ይሞክራል፡፡ በቅድሚያ ግን የሕጎቹን ይዘት በመመልከት፣ በተከታዩም ሕጎቹ ላይ መጠነኛ ግምገማ እናድርግ፡፡ ለግምገማ የሚቀርቡት ጭብጦች ጽንሰሐሳቦቹን በማብራራት ከሕግ አኳያ የታዩበትን ሁኔታ በትችት ይቀርባል፡፡ ከዚያም ለወደፊቱ ምን ማድረግ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ሐሳቦችም ይቀርባሉ፡፡

ስለኮፒራይት ጥቂት የመንደርደሪያ ነጥቦች

የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ እንደሁም ሳይንሳዊ ፈጠራዎች የአንድን አገር ሁለንተናዊ  ልማት በማፋጠን በኩል ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው እሙን ነው፡፡ ይህንን ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት ሥራ ፈጣሪዎች የሚበረታቱበትን እና ጥበቃ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር የግድ ነው፡፡

ለማበረታቻ፣ ጥበቃ ለማድረግ ብሎም የሥራውን ባለቤትም ሆነ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚያግዙት የሕግ ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቅጅ መብት ጥበቃ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም ለኮምፒውተር ፕሮግራምና ዳታቤዝ ጥበቃ ለማድረግ የወጣው ሕግ ነው፡፡

 የዚህ ሕግ ዋና ዓለማ የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ሌሎችም የፈጠራ ሥራዎች ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ዕውቅናመስጠትና ጥበቃማድረግ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበራታቱ፣ የፈጠራ ባለቤቶቹም ከሥራቸው እንዲጠቀሙ ማድረግ አንዱ ዓላማው ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ልማት በማበርከት ለባህላዊ፣ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ሳይንሳዊናቴክኖሎጂያዊ ዕድገት እገዛ እንዲያደርጉ መደላድል መፍጠር ሌላኛው ነው፡፡

ለዚህም ይመስላል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 91(3) ውስጥ መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ኪነ ጥበብን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ግዴታ እንዳለበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ያስቀመጠው፡፡ ይህንንም ከግብ ለማድረስ የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር ይቻል ዘንድ፣ ቀድሞ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ውስጥ የነበሩትን ውስን ድንጋጌዎች ያስፋፋና ለአዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችም ጥበቃ የሚሰጥ አዋጅ ቁጥር 410/1996 የተሰኘ ሕግ ወጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ሁልጊዜ እያደጉ፣ መብቶቹም  እየተለዋወጡ ስለሚሔዱ፣ አዋጅ ቁጥር 872/2007 የተሰኘው ተጨማሪ ሕግ ሥራ ላይ ውሏል፡፡

በአዋጅ የተደነገጉት የኮምፒውተር ፕሮግራም ምንነት

የኮምፒውተር ፕሮግራም (ሶፍትዌር) በመሣሪያ የሚነበብ ጽሑፍ ነው፡፡ የሚያነበው መሣሪያ የሚገኘውም ኮምፒውተር ውስጥ ነው፡፡ የኮምፒውተሩ አካል ነው፡፡ ሲያነበውም ኮምፒውተሩ ተግባሩን ማከናወን ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለሌላ የታለመለትን ውጤት ወይም የሚፈለግበትን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራም በቃላት፣ በኮዶች፣ በተለያዩ የሥራ ትዕዛዞችና ዘዴዎች ወይም በሌላ አኳኋን የተቀነባበሩ መመሪያዎች ስብስብ ነው፡፡ መመሪያነታቸውም ለኮምፒውተሩ ነው፡፡ ኮምፒውተሩን ይመሩታል፡፡

የኮምፒውተር ፕሮግራም የሚባለው በመሣሪያ የሚነበበው እንጂ በኮምፒውተሩ ላይ የምንመለከተው ወይም የምንሰማው ወይም የምናገኘው ውጤት አይደለም፡፡ የሕግ ጥበቃውም ውጤቱ እንዲመጣ ኮምፒውተሩን ለሚያዙት የመመሪያዎች ስብስብ ነው፡፡

የሕግ ጥበቃ የሚያስገኙ መሥፈርቶች

አንድ ሰው ለሥራው የቅጅ መብት ጥበቃ የሚያገኘው እንደሁኔታው በሥነ-ጽሑፍ፣ኪነ-ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ መስክ ፈጠራዊ የሆነ ሥራ የሠራ እንደሆነ፣ የሥራ አንጪው የአዕምሮ ውጤት እስከሆነ ድረስ፣ የሥራው ዓላማና ጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ወጥ (ኦርጅናል ) ከሆነ እና የተቀረጸ ወይም ግዙፍነት ካገኘ፣ ሥራው በመውጣቱ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሕግ የመብት ጥበቃ ያገኛል፡፡

በመሆኑም የሥራው አመንጪ ለሥራው ጥበቃ ለማግኘት ከፈለገ የሠራው ሥራ በመጀመሪያ ወጥ (ኦርጅናል) መሆን ይኖርበታል፡፡ ወጥ (ኦርጅናል) መሆን ሲባል፣ በሥራ አመንጪው የተሠራው ሥራ ከሌሎች ሥራዎች ያልተቀዳ መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ሐሳብ ነው፡፡ ይህም ማለት ሶፍትዌሩ ፕሮግራሙን የሠራው ሰው የአእምሮ ውጤት መሆን አለበት እንደማለት ነው፡፡

ሁለተኛው የጥበቃ መሥፈርት ደግሞ ሥራው ግዙፋዊነት ያገኘ መሆን አለበት የሚለው ነው፡፡ ግዙፋዊነት (የተቀረፀ) መሆን ማለት፣ አንድሥነ-ጽሑፍ፣ኪነ-ጥበብ ወይም የሳይንሳዊ ሥራ አመንጪው ሰው የሠራው ነገር፣ የአእምሮው ውጤት የሆነ፣ ወጥነት ያለው ሆኖ ግዙፍ በሆነ ነገር ላይ መሥፈር የሚችል ሥራ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡

ይህም ማለት የአእምሮ ውጤት የሆነው ሥራ በሐሳብ ደረጃ የቀረበ ሳይሆን፣ ግዙፍ በሆነ ዕቃ ላይ የሰፈረ መሆን አለበት፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራሙም በወረቀት ወይንም ዲጂታል በሆነ ኮምፒውተር ውስጥ መቀመጥ አለበት እንደማለት ነው፡፡ ጥበቃ የሚሰጠውም ሐሳቡ በመገለጹ ነው፡፡ ስለዚህ የአእምሮ ውጤት የሆነውን ይህንን ፕሮግራም በወረቀት ካሰፈረው ወይም በኮምፒውተር ከጻፈው ነው ጥበቃ የሚያገኘው፡፡

ይህንን ሁኔታ አዋጁአንቀጽ 2(1) ሥር ማብራሪያ አስቀምጦለታል፡፡ መቅረጽ ወይም ግዝፈት እንዲያገኝ ማድረግ ማለት አንድ ሥራ፣ ምስል፣ ድምጽ ወይም የአንደኛቸው አምሳያ ምትክ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ መሳያ አማካኝት እንዲታይ፣ እንዲባዛ፣ ወይም እንዲሰራጭ ማድረግ ማለት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራምም በተለያዩ መንገዶች ግዙፍነት ሊያገኝ ይችላል፡፡

የኮምፒውተር ፕሮግራም የሥራ አመንጭ (Author) እንደሆነ ሕጉ ዕውቅና የሚሰጠው ለፕሮግራሙ ፈጣሪ ነው፡፡ ይህ የሥራ አመንጭ ወይንም የኮምፒውተር ፕሮግራመር እንደሌሎች የቅጅ መብት ባለቤቶች የኢኮኖሚና እና የሞራል መብቶች አሉት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአዋጁ አንቀጽ 5 ሥር እንደተገለፀው፣ ማንኛውም ሐሳብ፣ የአሠራር ሂደት፣ ሲስተም፣ የአሠራር ዘዴ፣ ጽንሰ ሐሳብ፣ ቀመር፣ ለአጠቃላይ ሥራ የሚያገለግል የቁጥር ሰንጠረዥና ቅፅ፣ መርኅ፣ በአንድ ሥራ ውስጥ የተተነተነ ወይም የተብራራም ሆነ ያለተብራራ ግኝት ወይም ዳታ፣ የሕግ ባሕርይ ያላቸው ማናቸውም ይፋ የሆኑ የሕግ እና የአስተዳደር ሰነዶችና ይፋ የሆኑትርጎሜያቸው በቅጅና ተዛማጅ መብቶችሕግ ጥበቃ አይደረግላቸውም፡፡ 

ከኮምፒውተር ፕሮግራም አኳያ ጥበቃ የተደረገው በመሣሪያ የሚነበበውን የመመሪያዎች ስብስብ እንደሆነ ተመለክተናል፡፡ እዚህ ላይ ሕጉ ጥበቃ ሳያደርግ የዘለለውና የዘነጋው አንድ ትልቅ የአእምሮ ፈጠራ አለ፡፡ ‹‹አልጎሪዝም››፡፡

አልጎሪዝም፣ አንድን የኮምፒውተር ፕሮግራም ለመጻፍ መነሻና መሠረት ነው፡፡ ፕሮግራሙን ከመጻፍ በፊት በርካታ ጥናቶችን አድሮጎ መፍትሔዎቹን በሒሳብ፣ በዲያግራም ወይም በሌላ መልክ ካዘጋጀ በኋላ የኮምፒውተር ቋንቋ የሚችል ሰው ለኮምፒውተሩ እንዲስማማ በማድረግ ይጽፈዋል፡፡ ከዚያም ኮምፒውተሩ የሚፈለግበትን ተግባር ይከውናል፡፡ ለእዚህ ግን መሠረቱና ትልቁ የአእምሮ ውጤት አልጎሪዝም ነው፡፡ አልጎሪዝም ግን የአሠራር ሒደት ነው፡፡ የአሠራር ሒደት ደግሞ ጠበቃ እንደማያገኝ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራም አካል ነው እንዳይባልም፣ ኮምፒውተር የሚያነበው አልጎሪዝሙን አይደለም፡፡ አልጎሪዝሙን ያገኘና በኮምፒውተር ቋንቋ (ለምሳሌ ሲፕላስ ፕላስ፣ ጃቫ ወዘተ) መጻፍ የሚችል ማንኛውም ሰው የኮምፒውተር ፕሮግራሙን ይሠራዋል፡፡

በመሆኑም፣ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጁ ለአልጎሪዝም ጥበቃ አለመስጠቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ሌሎች አገሮች አልጎሪዝምን ለፕሮግራሙ እንደሚሰጡት ሁሉ የሕግ ጥበቃ ያደርጉለታል፡፡ ጥበቃ ለማድረግ ግን ምዝገባን እንደቅደመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡ እንዴት እንደሚመዘገብ የሚደነግግ ዝርዝር ሕግ አላቸው፡፡

ጥበቃ ለኮምፒውተር ብቻ?

አዋጁ የኮምፒውተር ፕሮግራም በማለት ዕውቅና የሚሠጠው ለኮምፒውተር ብቻ በመወሰን ነው፡፡ ጥያቄው ግን ኮምፒውተር ማለት ምን እንደሆነ ትርጓሜ አለመስጠቱ ነው፡፡ ለአብነት ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች፣ የኮምፒውተር ፍላጮች (ማይክሮችፕስ) ኮምፒውተር መሆናቸውን የሚያመለክት ፍንጭ በአዋጁ ውስጥ አናገኝም፡፡ ሶፍትዌር ወይም የኮምፒውተር ፕሮግራም ግን እነዚህንም መሣሪያዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡም ሆነ በእነሱ አማካይነት የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን የግድ ሶፍትዌር አስፈላጊ ነው፡፡ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ እነዚህን ጨምሮ ነው ኮምፒውተርን የተረጎመው፡፡ ስለሆነም፣ የእጅ ስልክ (ሞባይል) እና ሌሎች መሣሪያዎች ላይ የሚሠሩ ሶፍተዌሮች ጥበቃ አልሰጠም፡፡

የኮምፒውተር ፕሮግራመር መብቶች

የኮምፒውተር ፕሮግራም ንብረት ነው፡፡ የማይታይ፣ የማይጨበጥና የማይዳሰስ ሀብት ነው፡፡ ለንብረቱ ባለቤትም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 40 እና 41 ሥር የሰፈሩት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ የንብረቶቹ መሠረት የሥነ ጽሑፍ፣ኪነጥበብ ወይም ሳይንሳዊፈጠራ ሥራዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኮምፒውተር ፕሮግራምም በእነዚህ ሥር የሚመደብ በመሆኑ፣ የተለያዩ የኢኮኖሚና የሞራል መብቶችን ያስገኛል፡፡

የፕሮግራመሩ ኢኮኖሚያዊ መብት ማለት ከፈጠራ ሥራው የሚያኘው፣ በገንዘብ ሊለካ የሚችል መብት ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ መብቶች የሚባሉት በአዋጁ አንቀጽ 7 ሥር እንደተገለፀው ሥራውን የማባዛት፣ የመተርጐም፣ የማመሳሰል፣ የማቀናበር ወይም ወደ ሌላ ዓይነትመቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦርጅናል ሥራን ወይም ቅጂውን የማከፋፈል፣ ኦርጂናል ሥራውን ወይም ቅጂውን ለሕዝብ የማሳየት፣ በይፋ የመከወን፣ ብሮድካስትማድረግ እና በሌላ መልክ ማሥራጨትን የመሳሰሉት መብቶች እንደተሰጡት ይገልፃል፡፡ እነዚህ መብቶች የሥራ አመንጪውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኝ የሚደግፉት ናቸው፡፡

አንድ የሥራ አመንጪ በሥራው ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ መብት ለሌላ ሰው በውል አሳልፎ መስጠት ይችላል፡፡ የአንድ ወጥ የሥነ-ጥበብ ሥራ ወይም የአንድ ደራሲ ወይም የዜማ ደራሲ ኦርጅናል ጽሑፍበሥራው አመንጪ ከተላለፈ በኋላ ከሚደረገውድጋሚ ሽያጭ ዋጋ ላይ የሥራ አመንጪው ወይም ወራሹ የተወሰነ ድርሻማግኘት መብት እንዳለውም አዋጁ ይገልጻል፡፡

አንድ የሥራ አመንጭ በሥራው ላይ በገንዘብ የማይተመን የሞራል መብትም አለው፡፡ ይህም ለሠራው ሥራ ተገቢው ዕውቅና እንዲሰጠው የሚያደርግ መብት ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 8 ሥር እንደተገለፀውም፣ የሥራ አመንጪው የኢኮኖሚ መብት ባለቤት ቢሆንም ባይሆንም፣ የሥራ አመንጪቱ እንዲታወቅ የመጠየቅ፣ ሳይታወቅ የመቆየት ወይም የብዕር ስም የመጠቀም፣ ክብሩንና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መባዛት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም እና ሥራውን የማሳተም መብቶቹ የሞራል መብቶቹ ናቸው፡፡ በሌላ አገላለፅ የሞራል መብት የፈጠራ ሥራው ባለቤት ደራሲ (የሥራው አመንጪ) የመባል፣ ሥራዎቹ እንይዛቡ የማድረግና መሰል መብቶችን የሚያካትት ነው፡፡

ከዚህ አኳያ አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራመር በነጻ ለሕዝብ የሚሠራጩ ሶፍትዌሮችን (open source software) ቢያቀርብም እንኳ፣ ማለትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባያስገኙለትም፣ የሞራል መብቱ እንዲጠበቅለት ግን ሕግ ያስገድዳል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሶፍትዌሮችን ፕሮግራመሩ ተጠቃሚዎች እንዳሻቸው እንዲለዋውጧቸው ሊፈቅድ ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈቃድ የታከለባቸው ከሆኑም ፕሮግራመሩ የሞራል መብቶቹን በራሱ ጊዜ ስለቀነሳቸው ወይም ስለተዋቸው፣ ኃላፊነትን አያስከትሉም፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት መብቶች በሕጉ መሠረት ለወሳሾች ወይም ለስጦታ ተቀባዮች ካልሆነ በቀር የሥራ አመንጪው በሕይወት እያለ ወደ ሦስተኛ ሰው ሊተላለፉ አይችሉም፡፡ የሞራል መብት ከኢኮኖሚያዊ መብት በተቃራኒ መልኩ ወደ ሦስተኛ ወገን በውል ሊተላለፍ አይችልም፡፡

የዳታቤዝ ምንነትና ጥበቃ

ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ መሠረት ዳታቤዝ የመረጃ፣ የቁጥር፣ የዲያግራም እና የመጣጥፍ ስብስብ ነው፡፡ ስብስቡ ግን ሥርዓት ባለው አኳኋን ተሰድሮ/ተደራጅቶ በመቀመጥ እንጂ እንደው ተዘባርቆ የተከማቸ አይደለም፡፡ ይህ ስብስብ/ክምችት ደግሞ ሊፈለግም ሊገኝም የሚችለው በኮምፒውተር አማካኝነት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ የራሱ የተለየ አሰዳደር፣ አከመቻቸትና አቀማማመጥን ተከትሎ የተቀመጠ ከላይ የተጠቀሱትን ስብስቦች የሠራ ሰው፣ የቅጅ መብት ባለቤት እንደሆነ ተቆጥሮ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ከዚህ አንጻር ጥበቃ የተደረገው ተሰብስቦ ለተከማቸበት ሥርዓት እንጂ፣ ለእያንዳንዱ መረጃ፣ ቁጥር፣ መጣጥፍ ወይም ዲያግራም አይደለም፡፡ አዋጁ በማብራሪያ መልክ አንቀጽ 4 ሥር ስለምንነቱ ፍንጭ ይሰጣል፡፡ እንደውም በኮምፒውተር ብቻ ሳይሆን፣  ‹‹በሚነበብ መሣሪያም ይሁን በሌላ መልክ ያለ›› ሊሆን እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ትርጉም ከተሠጠበት አንቀጽ በሰፋ እና በተሻለ መንገድ፣ የዳታቤዝን ምንነት ገልጾታል፡፡

 ከላይ ከተገለጸው አንጻር ሲታይ፣ ዳታቤዝ መጀመሪያ የተሠራን ሥራ መሠረት አድርጎ እንደተዘጋጀ የፈጠራ ሥራ (Derivative works) ተቆጥሮ ጥበቃ ተደረገለት እንጂ፣ በራሱ ወጥ ሥራ አይደለም፡፡ ሕጉም እንዲህ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ወጥ የሚሰኘው ነገር የስብስቡ ይዘት፣ የተቀናበረበት ሁኔታና አመራረጡ ነው፡፡ ጥበቃ እንዲሰጠው ያደረጉትም እንዚህ ጥረቶችና የአእምሮ ውጤቶች ናቸው፡፡

ዳታቤዝን ለኮምፒውተር ፕሮግራም እንደተሰጠው ትርጓሜ ከመሆን ያዳነው አንቀጽ 4 ነው ብለናል፡፡ ስለዚህ ዳታቤዝ በተለያዩ በኮምፒውተር ብቻ ሳይሆን፣ በተንቀሳቃሽ የስልክ ቀፎዎች (ሞባይል ስልክ) እና በሌሎች መሣሪያዎችም ሊፈለግና ሊገኝ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ዳታቤዙ የሚፈለገውና የሚገኘው በመሣሪያ እስከሆኑ ድረስ ጥበቃ አለው ማለት ነው፡፡

አንድ ዳታቤዝ ያዘጋጀ ሰው እንደማንኛው የቅጅ መብት ሕግ ጥበቃ የሚያደርግለት የሥራ መብት ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያ ሥራን መሠረት አድርጎ ለተሠራ ሥራ የሚሰጥ ጥበቃ ከተነሳ አይቀር ሊወሳ የሚገባው ቁም ነገር አለ፡፡ አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራምን በአንድ የኮምፒውተር ቋንቋ (ለምሳሌ በጃቫ) አንድ ሰው ቢያዘጋጅ እና ሌላ ሰው ደግሞ በሌላ የኮምፒውተር ቋንቋ (ለምሳሌ በሲፕላስ ፕላስ) ቢጽፈው፣ በቅድሚያ የጻፈው ሰው ምን ዓይነት የሕግ ከለላ አለው የሚለው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በመጻፉ የትርጉም (translation) ሥራ ሊመስለን ይችላል፡፡ የትርጉም ሥራ እንደሆነ ከተቆጠረ ሁለተኛው ፕሮግራመር የመጀመሪያውን ማስፈቀድ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡

ነገር ግን በተለያየ የኮምፒውተር ቋንቋ ቢጻፍም፣ ተመሳሳይ አገልግሎት ስለሚሰጥ የመጀመሪያውን ፕሮግራመር ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይጋፋል፡፡ በተለይም ለአልጎሪዝም ጥበቃ ካልተሰጠ፣ ለአንድ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተዘጋጀን አልጎሪዝም በመውሰድ በሌላ የኮምፒውተር ቋንቋ ሶፍትዌር ቢጽፍ የሁለቱን ሰዎች የሕግ ግንኙነት ለመፍታት የእኛ ሕግ ብዙም እርዳታ አይሰጥም፡፡ ስለሆነም ለዚህ መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ ነው፡፡ ይኸውም ሕጉን መከለስ ነው፡፡

በማጠቃለያው የኮምፒውተር ፕሮጋራምም ሆነ ሌሎች ተያያዥ የአእምሮ ውጤቶችን በተገቢው መንገድ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች አማካይነት በሕግ ዕውቅና መስጠትና ጥበቃ ማድረግ አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበራከቱ እና የሚጠበቅባቸውን በህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲያመጡ እንዲሁም የፈጠራው ባለቤቶች ከሥራቸው እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የሶፍትዌር ኢንዱስትሪው ደግሞ በአገር ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና ባህላዊ ዕድገት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አይደለም፡፡ ይህንን ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችለው፣ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ከሥራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ የሚበረታቱበትን ሁኔታ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የቅንጅትና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጅ ያሉበትን ጉድለቶች ጥቂት ምሳሌዎችን በማንሳት ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ እነዚህን እና ሌሎች ክፍተቶችን መሙላት ዘርፉን ለማዳበር ስለሚያግዝ፣ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡