Skip to main content
x
ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት
ዚምባቡዌያዊያን የወታደራዊ ኃይሉን ዕርምጃ በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋል

ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት

ለ37 ዓመታት በዘለቀው አገዛዛቸው የሚታወቁትና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የመሰላቸውን ያለ ይሉኝታ በመናገር ተጠቃሽ የሆኑት፣ በ93 ዓመት ዕድሜያቻው ፕሬዚዳንት በመሆናቸው የዓለም አንጋፋው ርዕሰ ብሔር በመሆን የዓለም መነጋገሪያ በመሆን የሚታወቁት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ እ.ኤ.አ. በ2008፣ ‹‹ሥልጣን ላይ ያመጣኝ አምላክ ብቻ ነው የሚያወርደኝ፤›› ሲሉ በምርጫ ዘመቻው ወቅት መናገራቸው፣ ከበርካታ ለጥቅስ ከበቁ አባባሎቻቸው መካከል ይታወሳል፡፡ ሮበርት ሙጋቤ እንግሊዝን ጨምሮ በማንኛውም ጉዳይ ሸንቋጭ የሆኑ ቃላትን ከመጠቀማቸው በላይ፣ አወዛጋቢና አነጋጋሪ በሆኑ ንግግሮቻቸውም ይታወቃሉ፡፡ ኢምፔሪያሊዝም፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ እንግሊዝ፣ ሒትለር፣ ክሪኬት፣ ኢኮኖሚ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች፣ የአፍሪካ አኅጉር፣ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችና ተተኪ ማዘጋጀት በመሳሰሉት ጉዳዮች ያሻቸውን ብለዋል፡፡

ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት
የዚምባቡዌ ጦር ኃይሎች ኮማንደር ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤን በቁም እስር እንዳዋሉዋቸው ይነገራል

 

ለእንግሊዝ መሪዎች ከነበራቸው ጥላቻ ይበልጥ አስገራሚ የነበረው ለአዶልፍ ሒትለር የነበራቸው አመለካከት ነው፡፡ ሒትለርን የሚያደንቁት ሙጋቤ ለጀርመን ሕዝብ ፍትሕ ያሰፈነና ሉዓላዊነታቸውን ያስከበረ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በገዛ ሀብታቸው እንዲጠቀሙ መብት የሰጠ ነው ብለው፣ ሒትለር ማለት እንዲህ ያለ ሰው ከሆነ እሳቸው የእሱን አሥር እጥፍ እንዲሆኑ ምኞታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹እኔ ብዙ ጊዜ ሞቻለሁ፡፡ ለዚህም ነው እየሱስ ክርስቶስን የምበልጠው፡፡ እየሱስ አንዴ ብቻ ሞቶ አንዴ ተነስቷል፤›› ያሉትም 88ኛ የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ነበር፡፡ ለግብረ ሰዶማውያን ወሰን የሌለው ጥላቻ ያላቸው ሙጋቤ ከውሻና ከአሳማ ያነሱ ፍጥረቶች ናቸው በማለት በተደጋጋሚ ከመናገራቸውም በላይ፣ እንዲያውም ውሻና አሳማ ተቃራኒ ፆታዎችን የሚመርጡ በመሆናቸው ከግብረ ሰዶማውያን በጣም የተሻሉ ናቸው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ተተኪያቸውን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹ተተኪን ማዘጋጀት? ውርስ ነው እንዴ? በዴሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ መሪዎች በዚህ መንገድ አይመጡም፡፡ በትክክለኛው መንገድ በሕዝብ መሾም አለባቸው…›› ያሉት ባለፈው ዓመት ነው፡፡ አሁን ግን ሙጋቤ ሌላ ምዕራፍ ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ምዕራፍ ደግሞ ጀምሯል፡፡

የሙጋቤ አዲሱ ምዕራፍ ከመነሻው ወታደራዊ ግልበጣ ቢመስልም፣ አሁን ግን መልኩን ቀይሮ ከፓርቲያቸው ዛኑ ፒኤፍ፣ እንዲሁም በፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግሉ ግንባር ቀደም ተዋጊዎች ከነበሩ (Veterans) እና ከደጋፊዎቻቸው ጭምር ‹‹በቃዎት!›› ተብለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የዋና ከተማዋን ሐራሬ ዋና ዋና ጎዳናዎች ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መሣሪያ ደግነው ሲርመሰመሱባቸውና ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያውን በዚምባቡዌ ጦር ኃይሎች ኮማንደር ጄኔራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ የሚመሩ ወታደሮች ሲቆጣጠሩ፣ በሙጋቤ ላይ ግልበጣ የተካሄደ ነበር የመሰለው፡፡ ቆየት ብሎም ሙጋቤ በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ መዋላቸው ሲሰማና ጄኔራሉ ‹‹መረጋጋት ለመፍጥር›› ጦሩ መንቀሳቀሱን ሲናገሩ ያመነም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከቀናት በኋላ ሥልጣናቸውን በሰላም እንዲያስረክቡ የተነገራቸው ሙጋቤ እያንገራገሩ ነው መባሉ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ሳበ፡፡

ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት
ሕዝቡ ሙጋቤን ይበቃዎታል ብሏል

 

በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በሥልጣን ላይ እንዳሉ የሚነገርላቸው ሙጋቤ፣ እሑድ ኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ሥልጣናቸውን አስረክበው ሕዝባቸውን እንደሚሰናበቱ ቢታሰብም፣ እሳቸው ግን አሻፈረኝ በማለታቸው በማግሥቱ ሰኞ እኩለ ቀን ድረስ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን ወይ ፍንክች በማለታቸው በፓርላማ አማካይነት ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ሒደት መጀመሩ እየተሰማ ነው፡፡ በቴሌቪዥን ቀርበው ሥልጣናቸውን ያስረክባሉ ተብለው የተጠበቁት ሙጋቤ እንቢታቸውን ሲገልጹ፣ በካፌዎችና በሬስቶራንቶች ውስጥ ተስፋ ሰንቀው የጠበቁ ወጣት ዚምባቡዌያዊያን ብስጭታቸው በግልጽ ይታይ ነበር፡፡ የሚወዱት የእግር ኳስ ቡድን አጥቂ ጎል አፍ ላይ ማግባት የሚችለውን የሳተ ያህል ነበር በንዴት የጦፉት፡፡ ይኼ ብስጭት የወጣቶቹ ብቻ ሳይሆን፣ የእሳቸው ደጋፊ የነበሩ የገዢው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ አባላትና የቀድሞ የነፃነት ታጋዮች ጭምር ነበር፡፡ ለዚህም ነው የነፃነት ተዋጊዎቹ መሪ፣ ‹‹ሙጋቤ ሥልጣን በቃህ!›› ሲሉ፣ ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ደግሞ ከአመራር ያስወገዳቸው፡፡ እሳቸውን ለመተካት ሲዘገጃጁ የነበሩት የ52 ዓመት ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤም ከዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ የሴቶች ሊግ መሪነት ተወግደዋል፡፡

ግሬስ ሙጋቤ 41 ዓመት የሚበልጧቸው ባለቤታቸው ሮበርት ሙጋቤ እንዲተኳቸው እያዘጋጇቸው የነበሩ ወይዘሮ ሲሆኑ፣ ለዚህም ሲባል ሙጋቤ ምክትላቸው የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋግዋን ከሥልጣን አባረው ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሰደዱ አድርገዋል፡፡ ከነፃነት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትርነትና በፕሬዚዳንትነት ከ42 ዓመታት በላይ ዚምባቡዌን እየመሩ ያሉት ሙጋቤ፣ ወታደራዊ ኃይሉ ጣልቃ ገብቶ በሰላም የቀረበላቸውን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ አለመቀባቸው ለብዙዎች ገረሜታን ፈጥሯል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ በአፍሪካ አኅጉር ታይቶ የማይታወቅ ወታደራዊ ኃይል የተሳተፈበት ሰላማዊ ጥሪ የመጨረሻ ውጤቱ ምን ይሆን የሚለው አጓጊ ሆኗል፡፡ እስካሁን የአንድም ሰው ሕይወት ሳይጎዳ መቀጠሉም አስገራሚ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በአፍሪካ ወታደሮች ጣልቃ የገቡት ወይም ግልበጣ ያካሄዱበት አገር መሪው  ተገድሏል፣ ወይም ወደ ስደት አቅንቷል፡፡ ሙጋቤ በዚምባቡዌ የነፃነት ትግል ‹‹ጀግና›› መሆናቸው? ወይስ ሌላ ታሪካዊ አጋጣሚ? የሚለው እስካሁን ግልጽ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1960 ጀምሮ ከ200 በላይ ወታደራዊ ግልበጣ ባጋጠማት አፍሪካ የዚምባቡዌ ጉዳይ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡

ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት
ፕሬዚዳንት ሙጋቤን ይተካሉ ተብለው የሚጠበቁት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ደቡብ አፍሪካ በስደት ላይ ናቸው

 

ከዚምባቡዌ የሚወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ደቡብ አፍሪካ ያሉት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ምናንጋግዋ ሙጋቤን በአስቸኳይ ሥልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ነግረዋቸዋል፡፡ በሙጋቤ ግፊት በቅርቡ ከምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው የተነሱት ምናንጋግዋ በሴራ ሊገደሉ እንደነበረ ያውቁ እንደነበር ተናግረው፣ አሁን የሙጋቤ የመጨረሻው ሰዓት ነው ብለዋል፡፡ በሌላ ዘገባ ደግሞ ሙጋቤና የቀድሞ ምክትላቸው በስልክ መነጋገራቸውን ጄኔራል ቺዌንጋ ማረጋገጣቸው ተሰምቷል፡፡ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ወደ ዚምባቡዌ የሚመለሱት ደኅንነታቸው ተረጋገጦ መሆኑን ለሙጋቤ መናገራቸውም ተዘግቧል፡፡ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ከሥልጣናቸው የተባረሩት የሙጋቤ ባለቤት ያለተቀናቃኝ የባላቸውን ሥልጣን እንዲረከቡ ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ወታደራዊ ኃይሉና የዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ አባላት በመስማማት በሙጋቤ ላይ ተነሱባቸው እየተባለ ነው፡፡ ወታደራዊ ኃይሉ ግን ዕርምጃውን የገፋበት ከሙጋቤ ጋር በመሆን የአገሪቱን ‹‹የወደፊት ፎኖተ ካርታ›› ለማዘጋጀት ነው ብሏል፡፡ ይህ ዕርምጃው ደግሞ የአብዛኞቹን ዚምባቡዌያዊያን ድጋፍ አግኝቷል ቢባልም፣ ጥርጣሬ የገባቸው አሉ፡፡

ሰኞ እኩለ ቀን ላይ ያበቃው ቀነ ገደብ ባለመከበሩ አሁን የቀረው የሙጋቤን ያለ መከሰስ መብት ማንሳትና ክሱን መጀመር ነው ተብሏል፡፡ ከገዥው ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ስብሰባ በኋላ ሰኞ ዕለት መግለጫ የሰጡት የፓርላማ አባሉ ፖል ማንግዋና፣ ‹‹ሙጋቤ በጣም ግትር ሰው ናቸው፡፡ የሕዝቡን ድምፅ እየሰሙ ቢሆንም፣ ለማዳመጥ ግን ፈቃደኛ አልሆኑም፤›› በማለት፣ ይህ ደግሞ በቀጥታ ወደ ክስ ለመግባት ፈሩን ይቀዳል ብለዋል፡፡ በዚምባቡዌ በአገር መሪ ላይ ክስ የሚመሠረተው ከፍተኛ የሆነ ጥፋት ሲፈጸም፣ ሕገ መንግሥት ሲጣስ፣ ለሕገ መንግሥቱ አለመታተዝ ወይም አለማስፈጸም፣ ወይም በብቃት ማነስ ወይም ድክመት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የፓርላማ አባሉ ማንግዋና ሙጋቤ ባለቤታቸውን ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ሥልጣን ላይ ለማቆናጠጥ ያደረጉት ተግባር ሕገወጥ ነው ይላሉ፡፡ ግሬስ አገር ለመምራት መብት የሌላቸው ሴት ናቸው ብለዋል፡፡ ሴትየዋ የመንግሥት ሠራተኞችንና የቀድሞውን ምክትል ፕሬዚዳንት በአደባባይ ሲሳደቡ የነበሩ ናቸው ሲሉም ያክላሉ፡፡ በዚህ መሠረት የሙጋቤ ክስ በአመዛኙ ከሕገ መንግሥቱ ጥሰት ጋር ሊገናኝ ይችላል ማለት ነው፡፡

የክስ ሒደቱን ለመጀመር በብሔራዊ ሸንጎውም ሆነ በሴኔት ድምፅ መሰጠት አለበት፡፡ እነዚህ የዚምባቡዌ የፓርላማ አካላት የክስ ሒደቱን ለማስጀመር ወሳኝ ናቸው፡፡ ከሁለቱ ምክር ቤቶች በሚገኝ አብላጫ ድምፅ መሠረት የጋራ ኮሚቴው (የሁለቱ ምክር ቤቶች) ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን የሚያስወግደውን ምርመራ ይጀምራል፡፡ በግኝቱ መሠረት ኮሚቴው ክስ እንዲመሠረት ምክረ ሐሳብ ካቀረበና ሁለቱ ምክር ቤቶች በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ካፀደቁ፣ ሙጋቤ ከሥልጠነ መንበራቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይኼንን ዓይነቱን ሒደት ሞክረው አልተሳካላቸውም ነበር፡፡ አሁን ግን ፕሬዚዳንት ሙጋቤ የገዛ ራሳቸውን ፓርቲ ድጋፍ በማጣታቸው፣ በሁለቱ ምክር ቤቶች ከመጠን በላይ ድጋፍ ድምፅ ተገኝቶ እንደሚወገዱ እምነት አለ፡፡ ይህም በስደት ላይ ያሉትን ምክትል ፕሬዚዳንት በቀላሉ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ወደ ሥልጣን ያመጣል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለወደፊቷ ዚምባቡዌ ‹‹ፍኖተ ካርታ›› እያዘጋጀሁ ነው እያለ ያለው ወታደራዊ ኃይል ፍላጎት መሆኑ የተረጋገጠ ነው ተብሏል፡፡ ወታደራዊ ኃይሉ ግን ለጊዜው ‹‹ምን መደረግ እንዳለበት›› ማረጋገጫውን ለመስጠት አልፈለገም፡፡ ውስጥ ውስጡን ግን ሽግግሩ ሰላማዊ እንዲሆንና ደም መፋሰስ እንዳይከተል ሁለቱን ባላንጣዎች በስልክ እያነጋገረ መቀጠሉ ሌላው ተመራጭ ዘዴ ነውም እየተባለ ነው፡፡

ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት
ፕሬዚዳንት ሙጋቤ በ41 ዓመት ከሚበልጧቸው ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ጋር ከቤተ መንግሥት ሊባረሩ ተቃርበዋል

 

ፕሬዚዳንት ሙጋቤ 93ኛ የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ በሚቀጥለው ምርጫ እወዳደራለሁ ማለታቸውና ባለቤታቸው ደግሞ ሙጋቤ ቢሞቱም አስከሬናቸው ይወዳደራል ማለታቸው፣ በዚምባቡዌያዊያን ዘንድ ከመጠን ያለፈ ብስጭት ፊጥሮ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት የአፍሪካ ‹‹ፈርጥ›› የምትባለው ዚምባቡዌ በኢኮኖሚዋ መውደቅ ሳቢያ ዜጎች ለአስደንጋጭ የዋጋ ግሽበት ተጋልጠው መከራ የሚገፉበት አገር ናት፡፡ ሙጋቤ ከነጮች ላይ መሬት ወስደው ለጥቁሮች በማከፋፈላቸው ከፍተኛ ድጋፍ ቢያገኙም፣ በእንግሊዝ መሪነት በምዕራባውያን ማዕቀብ አገራቸው መከራ አይታለች፡፡ እሳቸው ደግሞ ሥልጣን ላይ ጥምጥም ብለው አልነቃነቅ ማለታቸው ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ዚምባቡዌያዊያን አሁን ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ አዙረውባቸዋል፡፡ የሚያምኑት ወታደራዊ ኃይልም ከፓርቲያቸው ጋር ሆኖ በቃ እያላቸው ነው፡፡ ሠራዊቱ ግዳጁን ጨርሶ ወደ ጦር ሠፈሩ ይመለሳል ቢባልም፣ ሙጋቤ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲያስረክቡ ተጠይቀው ዝም ቢሉም፣ አሁን እርግጠኛው ነገር ዚምባቡዌ ውጥረት ውስጥ ናት፡፡ ሠራዊቱ በሙጋቤ ዙሪያ ያሉትን በቁጥጥር ሥር አውሎ እሳቸውን ለድርድር ቢጋብዝም፣ ሙጋቤ በመጨረሻው ሰዓት ላይ መሆናቸው ግን እርግጠኛ ይመስላል፡፡ ዚምባቡዌያዊያን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ብዛት አደባባይ ወጥተው ‹‹ሙጋቤ በቃዎት!›› ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ ‹‹ሙጋቤ ታሪክ ሆነዋል›› እያሉ ነው፡፡