Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ደወሉላቸው

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ደወሉላቸው

[ክቡር ሚኒስትሩ ግምገማ ላይ ተቀምጠዋል]

-    ክቡር ሚኒስትር እንኳን ደህና መጡ፡፡

-    እንኳን ደህና ቆያችሁኝ፡፡

-    ይኼ እንግዲህ ለአምስተኛ ጊዜ ስንገመግምዎት ነው፡፡

-    እኔ ግን በጣም እየሰለቸኝ ነው፡፡

-    ምኑ ነው የሰለችዎት?

-    ለአምስተኛ ጊዜ እኮ ነው ግምገማ ያስቀመጣችሁኝ፡፡

-    ታዲያ ምን ይደረግ?

-    እናንተ ግን ሥራ ፈታችኋል እንዴ?

-    ክቡር ሚኒስትር ግምገማ እኮ የሥራችን ዋነኛ አካል ነው፡፡

-    እኔ ላይ ግን በዛ፡፡

-    ጥፋቱም እርስዎ ላይ ስለበዛ ነዋ፡፡

-    እናንተ ግን ከእኔ ውጪ የሚገመገም የላችሁም እንዴ?

-    ለምን እርስዎ በተደጋጋሚ እንደሚገመገሙ አያውቁም?

-    በሚገባ ነው እንጂ የማውቀው፡፡

-    እኮ ለምንድነው?

-    ጥላቻና ምቀኛ ስለበዛብኝ ነዋ፡፡

-    ምን?

-    በውስጣችንም ፀረ ልማትና ፀረ ሰላም ስለበዛ ነው፡፡

-    ወደው አይስቁ አሉ፡፡

-    ምንም የሚያስቅ ነገር የለም፡፡

-    ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ ታጥበው ጭቃ ነዎት፡፡

-    ብንከባበር አይሻልም?

-    የምንከባበርበት ጊዜማ አልፏል፡፡

-    ምን አድርግ ነው የምትሉኝ?

-    በእርስዎ ላይ የብቃት ማነስ ችግር እየተነሳ ነው፡፡

-    የምን ችግር?

-    የብቃት፡፡

-    ይኼን ያህል ዘመን አገር ሳስተዳድር የነበረው ብቃት እያነሰኝ ነው?

-    ይኼን ያህል ጊዜ ያገለገሉት ለፓርቲው ታማኝ ስለነበሩ እንጂ የብቃት ጥያቄ ከመጀመርያ ጀምሮ ሲነሳብዎት ነበር፡፡

-    ስለዚህ የአካሄድ ችግር አለ እያላችሁኝ ነው?

-    የምን የአካሄድ ችግር?

-    ከዚህ በፊት የታላቁ መሪያችንን ራዕይ እናስቀጥላለን አላላችሁም?

-    እሱማ ተብሏል፡፡

-    ታዲያ ታላቁ መሪ በፓርቲያችን ውስጥ ታማኝነት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል አላሉም?

-    አሁን ባለው ሁኔታ ግን ለፓርቲያችን ታማኝነት ብቻ አያዋጣም፡፡

-    ስለዚህ የታላቁ መሪ ራዕይ ተበርዟል ማለት ነው?

-    ክቡር ሚኒስትር ያልሆነ ቦታ ለመደበቅ ባይሞክሩ ጥሩ ነው፡፡

-    እኔ ድብብቆሽ እየተጫወትኩ ሳይሆን በግልጽ እየተናገርኩ ነው፡፡

-    ያልገባዎት የብቃት ችግር አለብዎት እየተባሉ ነው፡፡

-    ብቃት ቢያንሰኝም ለፓርቲዬ ደም እሰጣለሁ፡፡

-    ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ወቅት ደም መስጠት ያለብዎት ለደም ባንክ ነው፡፡

-    እየቀለዳችሁብኝ ነው?

-    ጊዜው የቀልድ እንዳልሆነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

-    ምን አድርግ ነው የምትሉኝ?

-    እርስዎ የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡ እየመለሱ አይደለም፡፡

-    ምን ይፈጠር ታዲያ?

-    መጀመርያ ሂስዎን ይዋጡ፡፡

-    ለዚሁ ነው እንዴ?

-    እንዴት ማለት?

-    የምትሉትን ሂስ ከፈለጋችሁ በስፕራይት፣ ካልሆነም በውኃ፣ አይሆንም ካላችሁ በውስኪ ለመዋጥ ዝግጁ ነኝ፡፡

-    ይህን የግምገማ ሥርዓት እንደ ቀልድ እያዩ መጡ ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?

-    የምን ቀልድ ነው? ጊዜው የሚቀለድበት አይደለም አላላችሁም እንዴ?

-    ይኼው ሂሴን አንዴ በስፕራይት ወይም በውኃ ካልሆነም በውስኪ እውጣለሁ እያሉ አይደል እንዴ?

-    እስከ ዛሬ በርካታ ሂሶችን ውጫለሁ፡፡

-    እሱማ ልክ ነው፡፡

-    ከዚያም ባለፈ ስንት የስኳርና የደም ግፊት መድኃኒት ውጫለሁ፡፡

-    ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?

-    ሁሉን ነገር ውጫለሁ ለማለት ነው፡፡

-    አንድ ያልዋጡት ነገር ግን አለ፡፡

-    ምን?

-    ጥይት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ እንደገቡ ከአማካሪያቸው ጋር ይገናኛሉ]

-    ምነው ክቡር ሚኒስትር ፊትዎ ጠቁሯል?

-    ኧረ ተወኝ ተወኝ፡፡

-    ፀሐዩ ነው?

-    ፀሐይዋ ብትሆን በስንት ዕድሌ?

-    ምን ሆኑ ታዲያ?

-    እኔ እኮ የዓላማ ጽናት ስላለኝ ነው እንጂ ድሮ ነበር የምሞተው፡፡

-    ለምን ክቡር ሚኒስትር?

-    ጨጓራዬ ተላጠ፡፡

-    ማን ነው የላጠው?

-    አጉል እናውቃለን የሚሉት ናቸዋ፡፡

-    አልገባኝም ለመሆኑ የት ነበሩ?

-    ግምገማ ምናምን የሚሉት ጊዜ ያለፈበት ስብሰባ ላይ ነዋ፡፡

-    እ. . .

-    ስንትና ስንት ቢዝነስ የሚሠራበትን ጊዜ በከንቱ ያቃጥላሉ፡፡

-    ስንትና ስንት ምን?

-    ስንትና ስንት ሥራ፡፡

-    ስንትና ስንት ቢዝነስ ያሉ መስሎኝ ነው?

-    ቢዝነስስ ቢሆን ሥራ አይደለም እንዴ?

-    ለነገሩ እውነትዎን ነው፡፡

-    ግን ጊዜዬን በሉት፡፡

-    ምንድነው ግን ነገሩ?

-    ሂስህን ዋጥ አሉኝ፡፡

-    እንደዚያ ተባሉ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?

-    አዎ ምነው?

-    አይ አንድ ነገር ልነግርዎት ፈልጌ ነበር፡፡

-    ምንድነው የምትነግረኝ?

-    ስምዎ በጣም እየተነሳ ነው፡፡

-    በምን በክሬን ነው?

-    እየቀለድኩ ሳይሆን በየመድረኩና በየኮሪደሩ ስምዎ በጣም ይነሳል፡፡

-    መቼም በመልካም ነው የሚነሳው አይደል?

-    ለነገሩ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው ይባላል፡፡

-    ምን እያልክ ነው?

-    ስምዎ የሚነሳው በመጥፎ ነው፡፡

-    እንዴት ማለት?

-    ሥራዎን ትተው ጭልጥ ብለው ገብተዋል እየተባለ ነው፡፡

-    የት?

-    ጭልጥ ብለው ገብተዋል ብቻ ሳይሆን ተዘፍቀውበታል እየተባለ ነው፡፡

-    ገንዳ ውስጥ ነው?

-    እየቀለድኩ እኮ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?

-    ስለምንድነው የምታወራው?

-    እንዲያውም አንዳንድ አመራሮች እንኳን ታድሰው ፈርሰው ቢሠሩም ለውጥ አያመጡም እየተባለ ነው፡፡

-    ምን እያልክ ነው ታዲያ?

-    እርስዎም ከእነሱ መካከል መሆንዎን ሰምቻለሁ፡፡

-    እኔ ጠፋሁ?

-    ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡን መምራት አልቻሉም፣ በቦታውም ቁጭ ያሉት በታማኝነት እንጂ በብቃት አይደለም እየተባለ ነው፡፡

-    ይቺ ደግሞ ሰሞኑን ያመጣችኋት ዝማሬ ናት?

-    የቷ ክቡር ሚኒስትር?

-    አቅም አንሶሃል ምናምን የምትሏት?

-    እንዲያውም ክቡር ሚኒስትሩ ጥልቅ ተሃድሶ ያደረጉት በራሳቸው ላይ ሳይሆን በሌላ ነገር ላይ ነው ተብሏል፡፡

-    በሌላ በምን ላይ?

-    በባንክ አካውንትዎ ላይ፡፡

-    ይቺን ይወዳል?

-    ለማንኛውም በጊዜ ይዘጋጁ፡፡

-    ለምንድነው የምዘጋጀው?

-    ሁለት ነገር ለማስረከብ፡፡

-    ምንና ምን?

-    ሥልጣንዎትንና. . .

-    እ. . .

-    ቤትዎን!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ከሚስታቸው ጋር ተገናኙ]

-    ምነው ዛሬ ፊትህ ጥሩ አይደለም?

-    ዛሬ ቀኑን እንዴት እንዳሳለፍኩ ስለማታውቂ ነው፡፡

-    ምን ሆንክ ደግሞ?

-    ጠዋት ይኼ የማይረባ ግምገማ ነበር፡፡

-    ከዚያስ?

-    በቃ እንዲሁ ሲያስደነግጡኝ አረፈድኩ፡፡

-    እሺ፡፡

-    ከዚያ ደግሞ ይኼ አማካሪዬ የማይሆን ነገር ነገረኝ፡፡

-    ምን?

-    እኔ ግን እሱ ሊያማክረኝ የመጣ አይመስለኝም፡፡

-    ለምንድነው የመጣው ታዲያ?

-    ሊሰልለኝ ነዋ፡፡

-    ይኼን ዛሬ ነው ያወቅከው?

-    ምን እያልሽ ነው?

-    ያየሁት ቀን ሰላይ መሆኑ ገብቶኛል፡፡

-    ለምን አልነገርሽኝም ነበር?

-    ታውቃለህ ብዬ ነዋ፡፡

-    በቃ ተይኝ ጉድ ሆኛለሁ፡፡

-    እንዴት?

-    ስንት ነገር ፊቱ ስቀባጥር እኮ ነው የምውለው፡፡

-    ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ነው?

-    ሂሴን ሲያስወጡኝ ነው የዋሉት አልኩሽ እኮ?

-    ስቅ አለህ እንዴ ታዲያ?

-    የምን ስቅታ አመጣሽ?

-    ለነገሩ አንተ ከሂስ ጀምሮ እስከ ደም ግፊት መድኃኒት የመዋጥ ልምድ ያለህ ሰውዬ አይደለህ እንዴ?

-    እሱማ ስንት ትልልቅ ኮሚሽንም ውጫለሁ፡፡

-    ምን አስጨነቀህ ታዲያ?

-    ይኼኛው ግን ትንሽ አስፈርቶኛል፡፡

-    ሰውዬ ብዙ ጊዜ ሊያባርሩኝ ነው፡፡ ሊያስሩኝ ነው ስትል ነበር፡፡

-    አሁን ግን ከጉድ ያውጣህ ብቻ በይኝ፡፡

-    እናንተ እኮ አትጨካከኑም፡፡

-    እሱስ እውነት ነው፡፡

-    ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

-    ለምንድነው?

-    ያልበላና ያልተጨማለቀ የለማ፡፡

-    ፍራቻዬ እኮ የመስዋዕት በግ እንዳያደርጉኝ ነው፡፡

-    ይኼን ያህል ካስፈራህ አዲስ ዕቅድ መንደፍ ነው፡፡

-    የምን ዕቅድ?

-    መንግሥት ራሱ ዕቅድ አለው አይደል እንዴ?

-    የምን ዕቅድ ነው የምታወሪው?

-    የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነዋ፡፡

-    እሺ፡፡

-    እኛም የራሳችንን ዕቅድ እናቅዳለና፡፡

-    ምን የሚሉት ዕቅድ?

-    የመጦሪያና የማምለጫ ዕቅድ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ደላላ ይደውልላቸዋል]

-    አንተ ሰውዬ አሁን ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም፡፡

-    ክቡር ሚኒስትር ወሳኝ ሥራ ይዤ ነው፡፡

-    የምን ሥራ?

-    እስከዛሬ ከሠራሁት ሥራ ይኼኛው ሕይወቴን የሚቀይር ነው፡፡

-    ምን ዓይነት ሥራ ነው?

-    በቃ በጣም ከባድ ሥራ ነው፡፡

-    ንገረኛ ታዲያ?

-    ይኼ ሥራ ምናልባትም ለእርስዎም መጦሪያዎ ሊሆን ይችላል፡፡

-    ምን አልከኝ?

-    መጦሪያዎ ይሆናል፡፡

-    እስኪ ንገረኝ፡፡

-    ክቡር ሚኒስትር ሥራው እርስዎን በአገር አቀፍ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ያደርግዎታል፡፡

-    ምንድነው የምትዘባርቀው?

-    እኔ ከእርስዎ የምፈልገው አንድ ነገር ነው፡፡

-    ምንድነው እሱ?

-    ፊርማዎን ብቻ፡፡

-    ከዚያስ?

-    ከዚያማ ሕይወትዎ ይለወጣል፡፡

-    ሕይወቴማ ተለውጧል እኮ፡፡

-    ከዚህም በላይ ይለወጣል፡፡

-    ምን እሆናለሁ?

-    አይነኬ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

-    ምን ፈለክ?

-    ክቡር ሚኒስትር ተረጋግተው ያውሩኝ እንጂ?

-    ቅድም ግምገማ ላይ ያደረጋችሁኝ ታውቋችኋል?

-    የፓርቲያችንን ባህል መቼም ጠንቅቀው ያውቁታል?

-    አሁን ለምን ደወልክ?

-    አንድ ሪፖርት ስለምልክልዎት ዓይተው በጠዋት እንዲልኩልኝ ነው፡፡

-    እኔ ጠዋት ላይ ሥራ ስላለኝ የአንተን ሪፖርት ማየት አልችልም፡፡

-    ይኼ ነው ችግርዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡

-    የምን ችግር ነው?

-    ቅድም የብቃት ማነስ የተባለው፡፡

-    እናንተ የትኛው ብቃት ኖሯችሁ ነው?

-    ለማንኛውም ከሰሞኑ ዕርምጃ ይወሰድብዎታል፡፡

-    የምን ዕርምጃ?

-    መነሳትዎ አይቀርም፡፡

-    ማን ወንድ እንደሚነካኝ አያለሁ፡፡

-    ለነገሩ በቀላሉ እንደማይነሱ አውቃለሁ፡፡

-    እንዴት ማለት?

-    ሰሞኑን ቅፅል ስምም ወጥቶልዎታል፡፡

-    ምን የሚል?

-    ሙጋቤ!