Skip to main content
x
ለፍልሰት የተዘየደው መላ

ለፍልሰት የተዘየደው መላ

ትንሿ ስልኩን ከሊስትሮ ሳጥኑ ጎን በስክሪኗ ደፍቶ መሬት ላይ አስቀምጧታል፡፡ መደበኛውን የስልክ አገልግሎት ከመስጠት፣ እንደ ነገሩ በሆነው ስፒከሯ ኩርኩር የሚል ሙዚቃ ከማሰማት ባለፈ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን መስጠት የምትችል አትመስልም፡፡ ከገበያ ከወጣችም የከራረመች ትመስላለች፡፡

ለ15 ዓመቱ ባንታየው (ስሙ ተቀይሯል) ግን በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ከሚገኙ ወላጆቹ ጋር የምታገናኘው ብቸኛ የቴክኖሎጂ ውጤት ነች፡፡ በአብዛኛው የባንታየው ውሎ ስልኩ አብራው አለች፡፡ ከናፈቁት ዘመዶቹ ታገናኘዋለች፣ በሙዚቃም ታስጨፍረዋለች፡፡ አሁን ላይ ግን ወደ ሚኖርበት ቀዬ የሚመለሰው ከቀናት በኋላ ነውና በቂ ገንዘብ አጠራቅሞ ለመሄድ ትግል ገጥሟል፡፡ እንኳንስ በስልኩ የከፈተውን ሙዚቃ ሊያዳምጥ ደንበኞቹ የሚሉትን እንኳ በወጉ ማድመጥ ተስኖታል፡፡ በምናቡ የሚመላለሰው ምን ያህል ብሠራ ምን ያህል ማግኘት እችላለሁ? የሚል በምኞትና በዕውነታ መካከል ያለ ምናባዊ ስሌት ነው፡፡ 

በግብርና ከሚተዳደሩ ወላጆች የተገኘው ባንታየው ትውልዱና ዕድገቱ በወላይታ ሶዶ ነው፡፡ የአፍሪካ መዲና ስለሆነችው አዲስ አበባ ሲባል የሚሰማው ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች በተለየ በከተማዋ ኑሮ ምቹና አጓጊ እንደሆነ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የስድስተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ቀዬውን ለቆ አዲስ አበባ የመጣው፡፡ እዚህ ከመጣ በኋላ ኑሮ እንደጠበቀው ቀላል አልሆነለትም፡፡ ይሁንና ከነበረበት የተሻለ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡

በቀን እስከ 100 ብር ድረስ እንደሚሠራ በኩራት ይናገራል፡፡ አንድ ጫማ ሲጠርግ ከአምስት እስከ ስምንት ብር ይከፈለዋል፡፡ ክፍያው ይኖርበት በነበረው ወላይታ ሶዶ ከተማ ሠርቶ ከሚያገኘው ጋር ብዙም ልዩነት ባይኖረውም አዲስ አበባ ድረስ ከመምጣት አላገደውም፡፡ በቀን ገቢው መካከል ያለው ልዩነት ለሱ ቦሌ አካባቢ ያሉትን ዘናጭ ቤቶች፣ ሕንፃዎች፣ ሆቴሎች፣ ዘመናዊ ሰዎች አጠቃላይ የአካባቢው ድባብ ይኖርበት ከነበረው የገጠር ከተማ እያነፃፀረ ከመደመም አይበልጥበትም፡፡ አዲስ አበባ በቀዬው ለሚገኙ የዕድሜ እኩዮቹ አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ነበር የምሠራው ብሎ ማውራትም የሚያኩራራው ታሪክ ይሆናል፡፡

ከቁመቱ ያጠረ ሱሪው፣ ያለቀ ካናቴራው፣ አመድ የመሰለ ፊቱ ኑሮ እንዳልተመቸው ይመሰክራሉ፡፡ ከወንድሙና ከሌሎች ይኖርበት ከነበረው አካባቢ አብረውት ከመጡ  የአገሩ ልጆች ጋር አራት ሆነው ለሚኖሩበት ቤት በወር 1,000 ብር ይከፍላሉ፡፡ ይህም ሥራውን በሚሠራበት ቦሌ አካባቢ ያሉ ቅንጡ ሕንፃዎችን ከማየት ባለፈ እንኳንስ እንደሱ ላለ ምስኪን የተሻለ ኑሮ ይኖራሉ ለሚባሉ ሰዎችም በውስጡ ለመኖር የህልም ያህል የራቀ ምኞት መሆኑን እንዲረዳ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ወደ ወላይታ ሶዶ ተመልሶ ትምህርቱን ካቋረጠበት ለመቀጠል ወስኖ ተመዝግቧል፡፡

ለፍልሰት የተዘየደው መላ

 

በአዲስ አበባ ቆይታው ኑሮ መኖር ችሎ እንደነበር ለጓደኞቹ ማሳየት፣ መዘነጥ አለበት፡፡ ስለዚህም ከመሄዱ በፊት ልብስ፣ ጫማ፣ ደብተርና ሌሎችም የሚያስፈልጉትን የትምህርት ግብዓቶች መግዛት አለበት፡፡ ይኼንንም ለማድረግ 3,000 ብር እንደሚያስፈልገው ይናገራል፡፡  ችግሩ እስካሁን ማጠራቀም የቻለው 1,500 ብር ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ለትራንስፖርት የሚያወጣውን ችሎ የሚቀረው ከዩኒፎርም፣ ደብተርና እስክሪፕቶ አልፎ የሚያዘንጠው አይደለም፡፡

ስለዚህም ትምህርት ከተጀመረ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ተቀማጩ 3,000 ብር እስኪሞላለት ትንሽ ቆይቶ ለመሥራት ወስኗል፡፡ በቀን 100 ብር ድረስ ቢሠራም ዓመት ሠርቶ ማጠራቀም የቻለው 1,500 ብር መሆኑን ላጤነ ስንት ጊዜ ቢሠራ ተቀማጩ 3,000 ብር ይደርስለታል? የሚለውን መመለስ አይከብደውም፡፡ በአዲስ ተስፋ እቀጥላለሁ ያለውን ትምህርት ጉዳይስ የት ይደርስ ይሆን የሚለው ደግሞ ሌላው የታዳጊው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማቅናት አልያም ጥያቄ ውስጥ የሚከተው አሳሳቢው ጉዳይ ነው፡፡

ይህ እንደ ባንታየው ያሉ የተሻለ ነገር ይኖራል በሚል ባልተጨበጠ ተስፋ ተነሳስተው ቀያቸውን ለቀው ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ በርካታ ታዳጊዎች ችግር ነው፡፡ አዲስ አበባ ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች አንፃር የተሻለ መሠረተ ልማት፣ የተሻለ ሥልጣኔ፣ የተሻለ የአገልግሎት ጥራት ይኖራል በሚል እዚህ ለመኖር የሚደረገውን ከሞት ሽረት ያልተናነሰ ትግል ሳያጤኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በየጊዜው ወደ አዲስ አበባ ይፈልሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ ድርቅና ሌሎችም መሠል ጉዳዮች ብዙዎች የሚኖሩበትን  ቀዬ ትተው ወደ ከተሞች እንዲፈልሱና ከተሞችለልክ በሰው እንዲጨናነቁ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ከ10 እስከ 19 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ወደ ከተሞች የሚፈልሱት የመማር ዕድል ለማግኘት ሲሆን፣ 28.6 በመቶ የሚሆኑት ወንዶችና 32.4 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለሥራ ፍለጋ ይፈልሳሉ፡፡ በሌሎች የተለያዩ ግፊቶች ቀያቸውን ትተው ወደ ከተሞች የሚኮበልሉም ብዙ ናቸው፡፡ ይሁንና ለምን ያህሉ ይሳካላቸዋል? የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡

13 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና 21 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች አስበው የመጡለትን የትምህርት ዕድል አያገኙም፡፡ የሥራ ዕድል ለማግኘት ወደ ከተማ የሚፈልሱት ሴቶችም በቤት ሠራተኝነት፣ በካፊቴሪያ አስተናጋጅነት አልያም በቡና ቤት ሠራተኝነት ተቀጥሮ ከመሥራት ባለፈ የተሻለ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው የጠበበ ነው፡፡ 19 ከመቶ የሚሆኑት ሥራ ፈላጊ ሴቶች የተባሉትን የሥራ ዓይነቶች እንደማያገኙ በከተማ ጤና ማጠናከሪያ ፕሮግራም የተሠራው ጥናት ያመለክታል፡፡ ይህም በከተሞች አካባቢ ድህነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲስፋፋ እያደረገው ይገኛል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገሪቱ በተለያዩ ከተሞች በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 11 በመቶ ነበር፡፡ ይኼ ቁጥር ..አ. 2011 ወደ 14 በመቶ አድጓል፡፡  ያለው የከተሞች መስፋፋት ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት ምጣኔም በልጧል፡፡ ይኼ ድህነት የበለጠ እንዳይስፋፋ፣ የከተሞች የማስተናገድ አቅምና የነዋሪዎቹ ቁጥር የሚያድግበት ምጣኔ የተራራቀ እንዳይሆን ከባድ ሥራ መሠራት እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡

መሰል አጋጣሚዎችና ሌሎችም በከተሞች ያለው የሥራ አጦች ቁጥር በተለይም ወጣት ሥራ አጦች 15 በመቶ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በሚፈልሱበት አዲስ አበባ ያለው የሥራ አጦች ቁጥር ደግሞ 32.5 በመቶ ደርሷል፡፡ ሁኔታው በአገር አቀፍ ደረጃ በድህነት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥርን 29.6 በመቶ እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ከፍተኛ የድሆች ቁጥር ካላቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባና ድሬዳዋ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ 28.1 በመቶ የሚሆኑት አዲስ አበቤዎችም በድህነት የሚኖሩ ናቸው፡፡

70 እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ከተሜዎች የሚኖሩት በተጨናነቁና ለኑሮ በማይመቹ አካባቢዎች ነው፡፡ ሁኔታው ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጡ እያደረጋቸውም ይገኛል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የንፁህ ውኃ ተደራሽነት፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና ጉዳይም አደጋ ውስጥ ነው፡፡  ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ከባድ ጫና እያሳደረ ያለውም በአዲስ አበባ ነው፡፡ የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. ከ2013 ወደዚያ ባሉ ተከታታይ አምስት ዓመታት 40 በመቶ የሚሆኑ ከገጠር ወደ ከተማ የፈለሱ ዜጎች አዲስ አበባን መምረጣቸውን ያሳያል፡፡

ይህም በከተማዋ ያለው የድህነት መጠን እንዲስፋፋ ከማድረግ ባለፈ ከንፅህና ጋር የተያያዙ የጤና ችግሮች እንዲበራከቱ እያደረገ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት በከተሞች አካባቢ ይበዛል፡፡ በአዲስ አበባ 24 በመቶ የሚሆነው ሞት እየተከሰተ የሚገኘው ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ለዚህም በከተሞች አካባቢ የሚታየው ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ሥርዓት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡

ከገጠር ወደ ከተሞች የሚደረገውን ፍልሰት ለማስቀረትና ጤናማ ያልሆነውን የከተሜነት መስፋፋትን መስመር ለማስያዝ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የሁለተኛ ከተሞች ልማት ላይ አተኩሮ መሥራት ወሳኝ ነው፡፡ የሁለተኛ ከተሞች መስፋፋትም ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን አብዛኛውን ፍልሰት መቀነስ የሚችል ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ጉራማይሌ የሆነውን የከተሞች ዕድገት ወጥነት እንዲኖረው በማድረግ ከተሞች ሊያስገኙ የሚችሉትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ከፍ እንዲላ ማድረግም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የሚያበረክቱት ድርሻ 38 በመቶ ነው፡፡ ይኼ አነስተኛ የሚባል ባይሆንም ለአገሪቱ የሰው ኃይል የፈጠሩት የሥራ ዕድል ግን ከ15 በመቶ አይበልጥም፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱ የተለያዩ ችግሮች መካከል የሁለተኛ ከተሞች ልማት ደካማ መሆን አንዱ ነው፡፡ የሁለተኛ ከተሞች የዕድገትና ሥራ ፈጠራ ሞተሮች መሆን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከተሞች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ብዛት ያለው የሰው ኃይል በሥራ ማሰማራት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉባቸው ዕድል መፍጠር ግድ ይላል፡፡ ይህም የተሻለና ከቦታ ቦታ ተመጣጣኝ የሆነ ልማትን ለማስፈን እንዲሁም በየጊዜው ወደ አዲስ አበባ ለሚፈልሱ ዜጎች ሌላ አማራጭ እንደመስጠት ነው፡፡

ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገው የዓለም ባንክ የአጋርነት ማዕቀፍ፣ ኢትዮጵያ የታችኛውን መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ምድብ ለመቀላቀል በምታደርገው ጉዞ ሁለት መሠረታዊ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚጠበቅባት አመልክቷል፡፡ እነዚህ ፈተናዎች በዋነኛነት በአገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች የተመጣጠነ ልማት ማምጣትን የተመለከቱ ናቸው፡፡

ባንኩ አዲስ ባዘጋጀው የትብብር ማዕቀፍ ከቦታ ቦታ ያለውን የልማት ልዩነት ለማጥበብ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ ይኼንንም የሚያስፈጽመው ሁለተኛ ከተሞችና የትራንስፖርት ኮሪዶሮች ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን በመደገፍ አዳዲስ ገበያዎች እንዲጎለብቱና ለገበሬው ተደራሽ እንዲሆኑ፣ እንዲሁም በከተሞቹ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማድረግ ነው፡፡ የትብብር ማዕቀፉ በክልሎችና በወረዳዎች መካከል የተመጣጠነ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች መካከል ሁለተኛ ከተሞችን በስፋት መገንባት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም አስምሮበታል፡፡

ማዕቀፉ አገር አቀፍ የሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ክልላዊ የዕድገት ማዕከላትና ዘመናዊ ሁለተኛ ከተሞችን በማልማት ከታች ያለውን 40 በመቶ ደሃ ማኅበረሰብ አቅም ለመገንባት ይሠራል፡፡ ይሁንና በፍጥነት እያደገ የሚገኘው የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር በውኃ አቅርቦትና በከተሞች ፅዳት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የፅዳት አገልግሎት በከተሞች ዕድገትና ሁለተኛ ከተሞችን የማበልፀጉ ሥራ ላይም ከፍተኛ ማነቆ መሆኑን ከአጋርነት ማዕቀፉ ጋር ተያይዞ የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡  ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ ግን ከምንም የተሻለ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በከፍተኛ መጠን መቀነስ እንደሚችል የታመነበት ሌላ አዲስ ፕሮጀክት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መጀመሩን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ስምንተኛውን አገር አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሽልማት በከፈቱበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚተገበረውና አስፈላጊው መሠረተ ልማቶች ከአገልግሎቶች ጋር ተሟልተው የሚገነቡ ዘመናዊ የገጠር መኖሪያ መንደሮች እንዲገነቡ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የመንደሮች አጠቃላይ ዲዛይን የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በግንባታ ሒደቱም በየአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታስቧል፡፡

‹‹እዚያው ያሉ ወጣቶችን አሠልጥነን እነሱን ኮንትራክተር አድርጎ መሥራት የሚያስችል አካሄድ ነው የምንከተለው፡፡ ግንባታው ግን ከፍተኛ ወጪ ርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነ የክልል መንግሥታት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካለት ሊሳተፉበት ይገባል፤›› ያሉት ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ እነዚህ የገጠር መንደሮችና ሁለተኛ ከተሞች ልማት ግንባታ አንገብጋቢ የሆነውን ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ እንደሚችል ዕሙን ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ፕሮጀክቶቹ ከውጥን ባለፈ ምን ያህል ዕውን መሆን ይችላሉ? እንደ ባንታየው ላሉ አዲስ አበባ መኖርን እንደ ትልቅ ስኬት ለሚቆጥሩ ታዳጊዎችስ ከቀያቸው እንዳይፈናቀሉ ምን ዋስትና ይሰጣል? የሚለው ነው፡፡