Skip to main content
x
‹‹መንግሥት ፖለቲካዊው ሽኩቻ የልማት ጠንቅ ከመሆኑ በፊት ሊቆጣጠረው ይገባል››

‹‹መንግሥት ፖለቲካዊው ሽኩቻ የልማት ጠንቅ ከመሆኑ በፊት ሊቆጣጠረው ይገባል››

ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ከፍተኛ አማካሪ

ፕሮፌሰር ኬኒቺ ኦህኖ እ.ኤ.አ. በ1987 ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በበርካታ የኢኮኖሚ ልማትና የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ላይ በማማከርና በማስተማር፣ እንዲሁም በርካታ የምርምር ሥራዎችን በማሳተም ይታወቃሉ፡፡ በማኅበራዊ ሳይንስ መስክ ላበረከቷቸው አስተዋፅኦዎች ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታትም በጃፓን መንግሥት ተወክለው ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት ይበጃሉ ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦች ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን በልማታዊ ኢኮኖሚና በኢንዱስትሪ ፖሊሲ መስኮች ከበርካታ እስያ አገሮች ልምድና ተሞክሮ በመነሳት እያማከሩ ይገኛሉ፡፡ በጃፓን ‹‹ናሽናል ግራጁዌት ኢንስቲትዩት ፎር ፖሊሲ ስተዲስ›› ተቋም ውስጥ በፕሮፌሰርነት እያገለገሉ የሚገኙት ኦህኖ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመመላለስ የኢንዱትሪ ፖሊሲ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ላይ እየተገኙም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ይመክራሉ፡፡ ሰሞኑን ለዚሁ ስብሰባ አዲስ አበባ በመገኘት ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መክረዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ስለወቅታዊው የሠራተኞች ጉዳይ፣ እንዲሁም ስለምንዛሪ ለውጡና ስለሌሎችም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የመከሩት ኦህኖ፣ በአገሪቱ ስለሚታዩ መሠረታዊ የኢንዱስትሪ ችግሮችና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች ከብርሃኑ ፈቃደ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን በተካሄደው ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምክክር መድረክ ወቅት የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከስሪላንካ ሲያወዳድሩ ነበር፡፡ ስሪላንካ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ስትሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ተርታ ትመደባለች፡፡ በሁለቱ መካከል ሌሎችም ልዩነቶች አሉ፡፡ ከስሪላንካ ጋር ለምን ማወዳደር አስፈለገ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ከሌሎችም በርካታ አገሮች ጋር ማወዳደር ይኖርብሃል፡፡ ኢትዮጵያን ከሌሎች አገሮች ጋር ስናወዳድር ቆይተናል፡፡ እስካሁን 15 ይደርሳሉ፡፡ ስሪላንካ ለኢትዮጵያ ምሳሌ ሆኖ ስትቀርብ ብቸኛዋ አገር አይደለችም፡፡ በዚህ ወቅት ስሪላንካን ከኢትዮጵያ አኳያ ማየት የፈለግነው ከስሪላንካ የመጡ ልብስ አምራች ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሥራ ስለጀመሩ ነው፡፡ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ኢዛቤላ የተባለው ካልሲ አምራች፣ ሃይድራማኒ ሸሚዝና ሌሎችንም የሚያመርተውና ሔላ የተባለው ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም እየመጡ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደርን አነጋግሬ አምስት ኩባንያዎች ከስሪላንካ መምጣታቸውን ነግረውኛል፡፡ አንዳንዶቹ በእሽሙር ሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) የሚመጡ ቢሆንም፣ በራሳቸው ለመሥራት የሚመጡ፣ ወደ መቐለና ሌሎችም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመግባት የሚፈልጉ አሉ፡፡ የኢዛቤላ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሌሎችም ኩባንያዎች እንዲመጡ እያደረጉ ነው፡፡ ስለዚህ አልባሳት የሚያመርቱ የስሪላንካ ኩባንያዎች ለምን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንደ ጀመሩ ማጥናት ስለፈለግንም ጭምር ነው፡፡ በምን ተስበው እንደሚመጡ፣ ምን ዓይነት ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸውና የመሳሰሉትን ለማየት እንፈልግ ነበር፡፡ ስሪላንካ ከዝቅተኛው መካከለኛ ገቢ ደረጃና ወደ ከፍተኛው መካከለኛ ገቢ ደረጃ እየተጓዘ የሚገኝ ኢኮኖሚ አላት፡፡ የሕዝቡ የነፍስ ወከፍ ገቢ 4,000 ዶላር ገደማ ነው፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ በእጅጉ ይበልጣል፡፡ እንደ አልባሳት አምራችና ለውጭ ገበያ አቅራቢነታቸው በጣም የመጠቀ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

ምናልባትም በዓለም ላይ ዋነኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እንደ ጃፓን፣ ሲንጋፖርና ሌሎች አገሮች አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ አምራችነታቸውን እየተጠቀሙ ነው፡፡ ደቡብ ኮሪያ አሁንም ያመርታሉ፡፡ ስሪላንካዎች ግን ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ያለምንም መዛነፍ የአሜሪካና የአውሮፓ የሠራተኛ ሕጋግትን በማክበርና የሚፈለግባቸውን ሁሉ በማሟላት ጭምር ያመርታሉ፡፡ የአካባቢ ጥበቃና መሰል መሥፈርቶችንም ያሟላሉ፡፡ የደረሱበትን ይህንን ደረጃም ለሌሎ አገሮች ያስተምራሉ፡፡ ለዚህ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ቬትናም ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከስሪላንካ መቅሰም የምትችላቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ምርቶችን በማምረት ረገድ ትልቅ ብቃት አላቸው፡፡ እንደ ጂአይዜድ፣ የስዊድን መንግሥት፣ የእንግሊዝ ተራድኦ ድርጅት፣ እንዲሁም የዓለም የሥራ ድርጅት (አይኤልኦ) ያሉት ተቋማት፣ እንደ ኤችኤንድኤምና ፒቪኤች ያሉት ትልልቅ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ መሠረታዊ የአመራረት፣ የአካባቢ ጥበቃና የሠራተኞችን ደኅንነት በመጠበቅ ጥራት ያላቸው ምርቶች እንድታቀርብ እያገዙ እንደሚገኙ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተቋማት በኩባንያዎቹ የውስጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚታዩት ነባራዊ ሁኔታዎች ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው፡፡ ጃፓን ስለጥራትና ስለካይዘን ልታስተምር ትችላለች፡፡ ስለስታንዳርድ በተለይም ስለሠራተኛ ጉዳይና ስለአካባቢ ጥበቃ ስታንዳርዶች ከሌሎች አገሮች መማር ይጠበቅባችኋል፡፡

ሪፖርተር፡- የስሪላንካ ኩባንያዎች በጣም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን አልባሳት አምራች ከሆኑ፣ በውድድር ሳቢያ ወደ ሌሎች አገሮች ለመሰደድ እየተገደዱ ነው ማለት ይቻላል?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- በከፍተኛ ደረጃ አድገዋል፡፡ በዚህም ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ እኛ ባየነው መሠረት ግን ችግራቸው ውድድር አይለደም፡፡ እንደ ቻይና፣ ህንድ አሊያም ቬትናም ዓለምን አያዳርሱም፡፡ ከዓለም የአልባሳት ገበያ የአንድ በመቶ ድርሻ ቢኖራቸውም ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ያለቀላቸው ምርቶችን ያመርታሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ፣ ወደ ባንግላዴሽና ወደ ሌሎችም አገሮች እየሄዱ የሚገኙት በሠራተኛ እጥረት ምክንያት ነው፡፡ ከፍተኛ የሥራ ለውጥ ስላለ ሠራተኞችን ማቆየት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ የተለየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚቀጠሩ ሰዎች ያን ያህል ለፋብሪካ የሚያበቃ ዕውቀት አልቀሰሙም፡፡ በፋብሪካ ውስጥ እንዴት መሥራት እንዳለባቸውም አያውቁም፡፡ ስለዚህ የተሻለ ነገር ለማግኘት በየአቅጣጫው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በስሪላንካ ግን ምንም እንኳ የሠለጠኑም ቢሆኑ በፋብሪካ መሥራት አይፈልጉም፡፡ በዚህ ምክንያት ኩባንያዎቹ ወደ ኢትዮጵያና ሌሎች አገሮች ለመምጣት እየተገደዱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ፖሊሲው ከፍተኛ ምክክር መድረክ የሰሞኑ ውይይት ትኩረቱ ምርታማነት ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ርካሽ የሰው ጉልበት አለ ቢባልም፣ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሠለጠነና የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለባቸው ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ይህም ሆኖ ኩባንያዎቹ ሥልጠናና ማበረታቻ በመስጠት ሠራተኞቻቸውን ለማቆየት ሲጣጣሩም ይታያሉ፡፡ እርስዎ ለዚህ መትፍትሔ የሚሆነው ምንድነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ከስሪላንካ ጋር ስናወዳድረው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሠራተኛ እጅግ ይቀረዋል፡፡ በጣም ኋላቀር ነው፡፡ ከ40 ዓመታት በፊት የስሪላንካ ሠራተኞች ማንበብና መጻፍ የሚችሉ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ መናገር የሚችሉ ነበሩ፡፡ ጥሩ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን ያሟሉ እንዲሁም የሠለጠኑ ነበሩ፡፡ እንደ አገር ይህን ይዘው ነው የተነሱት፡፡ ኢትዮጵያውያን ክህሎት እንዳላቸው ቢታመንም መሠልጠን አለባቸው፡፡ በመፀዳጃ አጠቃቀም ሳይቀር ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ችግር ሲኖር ለአለቆቻቸው እንዴት ሪፖርት እንደሚያደርጉም መማር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያለ ፈቃድ ከፋብሪካ ረዘም ላለ ጊዜ ጠፍቶ መቅረት አይቻልም፡፡ እንደነዚህ ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ገና አልዳበሩም፡፡ እንዴት እንደሚቆርጡና እንደሚሰፉ ከመማራቸው በፊት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ አስተሳሰባቸው መታረቅ አለበት፡፡ በፋብሪካ ሠራተኛነት መቃኘት አለባቸው፡፡ ዲሲፒሊን ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከፋብሪካ ኃላፊ ጋር እንዴት እንደሚነጋገሩና እንደሚግባቡ ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህ ረጅም ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ከስሪላንካ ጋር ለማገናነኘት የሞከርኩት፡፡ ከ40 ዓመታት በፊት እነሱም ይች ችግር ነበረባቸው፡፡ የገጠር ሴቶች ወደ ኤክስፖርት ማቀነባበሪያ ዞን በመግባት እንዲሠሩ ያደርጉ ነበር፡፡ እነዚህ ሴቶች ግን በፋብሪካ መሥራት እንዴት እንደሆነ አያውቁም ነበር፡፡ ገንዘብ ሲያጠፉ የጤና አልነበረም፡፡ ቁጠባ አያውቁም፡፡ ከማኅበረሰቡ ሞራላዊ እሴት ያፈነገጡ ባህርያትን ያሳዩ ስለነበር ነዋሪዎች ፋብሪካዎቹን ይወቅሱ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ግን ከረጅም ጊዜ በፊት አልፈዋቸዋል፡፡ እንዴት አለፉት የሚለውን እናንተ ከእነሱ እንድትማሩ ያስፈልጋል፡፡ ከስሪላንካውያኑ ሦስት ነገሮችን መማር ትችላላችሁ፡፡ አንዱ ግን ሠራተኞችን ዲስፕሊን ማስተማር፣ ሕግ እንዲያከብሩና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ይገባል፡፡ እነሱ ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ 40 ዓመታት ሊወስድባት አይገባም፡፡ በሁለትና በሦስት ዓመታት ውስጥ ጥሩ የሥራ ባህል ያዳበሩ ሠራተኞች ይኖሯችኋል ለማለትም ይከብዳል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ስለሚያራምዳቸው እንደ ቤስት ስኮር ካርድ ያሉ የማኔጅመንት አካሄዶች ሥጋት እንዳደረብዎ ሲገልጹ ነበር፡፡ መንግሥት ቢፒአር ብሎ ጀመረ፡፡ ካይዘንም ይጠቀሳል፡፡ አሁን ደግሞ ዴሊቨርሎጂ የሚባለውንም መከተል ጀምሯል፡፡

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- መንግሥትን በጥቅሉ ስናየው በዕቅድ ሥራ ላይ የተጠመደ (ፕላን ማይንድድ) ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሁሉም ነገር ፖሊሲ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ የተጻፈ ፖሊሲና ሕግ መኖር አለበት፡፡ አዋጅና ደንብ ያስፈልጋል፡፡ ኩባንያዎችና ሠራተኞችም በእነዚህ መመራት አለባቸው፡፡ ይህ ክፋት የለውም፡፡ ሆኖም ነፃነቱ ሊኖር ይገባል፡፡ ሠራተኞች የት መሥራት እንዳለባቸው፣ እንዴት መሥራት እንዳለባቸውና እንዴት መማር እንዳለባቸው ነፃነቱ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የኩባንያ ኃላፊዎችም ሠራተኞቻቸውን ለመምረጥ፣ ለማሠልጠንና ለመሳሰሉት ፍላጎታቸው መጠበቅ አለበት፡፡ ለጋሾች ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና እየሰጡ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ መሠረታዊ ሥልጠና በመስጠቱ ላይ ማለትም እንደ ንፅህና አጠባበቅ፣ የፋብሪካ ሥነ ምግባርና የመሳሰለው ላይ ሥልጠና ቢሰጡ ምንም አይደለም፡፡ ጥቅል በሆነው ጉዳይ ላይ ያግባባል፡፡ ወደ ዋናው የቴክኒክ ጉዳይ ሲመጣ ግን እያንዳንዱ ኩባንያ የሚያራምደው የየራሱ ፍልስፍና ስላለው፣ እነሱ ለሠራተኞቻቸው የሚሰጡት ሥልጠናና ልምምድም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በጃፓን የቶዮታና የሆንዳ ሥርዓቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ሁለቱም መኪና አምራቾች ቢሆኑም፡፡ ፓናሶኒክ የሚከተለው የምርት ሥርዓት ፍልስፍና ከሶኒ በጣም ይለያል፡፡ የኮርፖሬት ባሕላቸው የተለያየ ነው፡፡ የቴክኒኩን ጉዳይ ለኩባንያዎቹ መተው የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ቀላል የሚባሉት ላይ ሥልጠና መስጠቱ የመንግሥት ትኩረት ቢሆን ይበጃል፡፡

ሪፖርተር፡- በየጊዜው የሚለዋወጠው የማኔጅመት ሥርዓትና የሚጠይቀው ወጪ በመንግሥት ላይ የዘለቄታዊነት ጉዳይና የሀብት ብክነት ጥያቄ አያስከትልበትም?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- መንግሥቱ በሙከራ የሚያምን ነው፡፡ በርካታ ጉዳዮችን በንቃት ይሞክራል፡፡ በርካታ ጉዳዮችም እንደታሰበው ውጤት ሳያመጡ ይቀራሉ፡፡ ካይዘንም እንደ ሌሎች እንደማይከሽፍ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በተወሰነ ደረጃ ካይዘን እየሄደ ነው፡፡ ቢፒአር፣ ቤንች ማርክ፣ ቢኤስሲ የተባሉት በአንድ ወቅት በጣም ሲነገርላቸው  ነበር፡፡ ምን ያህል ውጤት እንዳስገኙ አላውቅም፡፡ አዳዲስ ነገሮችን መሞከሩ ክፋት የለውም፡፡ በወደቀ ሥርዓት ላይ የሙጥኝ ማለት አይገባም፡፡ ይሁንና ነገሮችን በፍጥነት መቀያየርና ደጋግሞ ይህንኑ ማድረግ ብዙዎችን ያሰለቻል፡፡ አንዳንዶቹ ኩባንያዎች በዚህ አሠራር ዝለዋል፣ ደክሟቸዋል፡፡ በዋናው የምርት ሥራቸው ላይ እንዳያተኩሩ እያደረጋቸው ነው፡፡ ለእኔ በሙከራ የተሞላ አስተሳሰብ መኖሩ ክፋት አይኖረውም፡፡ ሆኖም መንግሥት ዝግ ማለት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተኛው ወይም ‘አድቫንስድ’ የሚባለው የካይዘን ትግበራ መቼ ነው የሚጀመረው?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ሥልጠናው እኮ ባለፈው ዓመት ተጀምሯል፡፡ እስካሁን ስድስት ኩባንያዎች በአድቫንስድ ሥርዓት መመራት ጀምረዋል፡፡ የሚከተሉት ሥርዓት የቶዮታ፣ የሆንዳ አሊያም ቶታል ኳሊቲ ማኔጅመንት የሚባለው ስለመሆኑ ገና አላረጋገጥሁም፡፡ ከፍተኛ ውስብስበነት ያለበትን የካይዘን ደረጃ ለመተግበር እየተሞከረ ነው፡፡ ከዚህ ጎን እስከ ዶክትሬት ደረጃ በካይዘን ሥርዓት ትምህርት መስጠት ተጀምሯል፡፡ በከተማ ደረጃም የካይዘን አተገባበር ሒደት ተጀምሯል፡፡ ባለፈው ወር በየዘርፉ የሚተገበረው የካይዘን ሥርዓት (ሴክተር ካይዘንም) መተግበር ተጀምሯል፡፡ የቆዳና ጨርቃ ጨርቅ፣ የብረትና ሌሎችም የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩቶች በሴክተር ካይዘን ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ስለካይዘን በደንብ የሚያውቅ ሰው እንዲኖር ማድረግ ይገባል፡፡ ቢያንስ መሠረታዊውን ካይዘን ማስተማር የሚችሉ ሰዎች በእነዚህ ተቋማት ቢገኙ፣ በየጊዜው የካይዘን ኢንስቲትዩትን እየጠሩ አስተምሩን የሚለውን ጥያቄ ማስቀረት ይቻላል፡፡ መንግሥት በራሱ እየሄደበት የሚገኝ ነው፡፡ የጃፓን መንግሥት ድጋፍ አላደረገም፡፡ ሌላው በጥቂት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ወደ ራሱ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዋና መሥሪያ ቤትነት ባሻገር የሥልጠና ማዕከል ስለሚሆን፣ የተማሪዎች ማደሪያና የባለሙያዎች ቢሮዎችም በዚህ ሕንፃ ውስጥ እንደሚኖሩ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ነገሮች በጥሩ ደረጃ እየተጓዙ ነው፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎችም ኃላፊዎች ከፍጥነቱ ባሻገር የሰው አስተሳሰብ ለውጥም እያሳሰባቸው ነው፡፡ የካይዘን ፍልስፍና የሚተገበርበት ፍጥነት ባይጠላም የሚፈለገውን ያህል ሥርፀት ማስገኘቱ ግን ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም በሁለቱ መካከል ያለውን ሚዛን ማስጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ሚዛኑን የጠበቀ አካሄድ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፡፡ የጃፓን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ጉዳዩን እንዲከታተለውም ይፈልጋሉ፡፡ ካይዘን በኢትዮጵያ ሲተገበር ከዘጠኝ ዓመታት ያላነሰ ቆይታ አለው፡፡ ድንገት ይተናል ብዬ አላስብም፡፡ ጥያቄው ግን መካከለኛና ከፍተኛ የካይዘን ሥርዓት እንዴት ይተገበራል የሚለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ ከእርስዎ ጋር በተነጋገርንባቸው አጋጣሚዎች የፖለቲካ አመራሮች በአገሪቱ የልማት ጉዳይ ላይ ጠንካራና ቁርጠኛ አካሄድ እንዳላቸው ሲናገሩ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይም በልማት ሥራዎች ላይ ያላቸውን ትኩረት እንደሚያሳጣቸው ይገመታል፡፡ ይህ ሥጋት ይፈጥራል?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- እውነት ነው፡፡ ሆኖም እኔ የፖሊቲካ ሳይንስ ሰው አይደለሁም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ በዝርዝር ልናገር አልችልም፡፡ ሆኖም ስለአገሪቱ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በምንነጋርበት ወቅት መንግሥት በፖለቲካ ጉዳይ እንደተወጠረ የሚያሳዩ ነገሮችን እንታዘባለን፡፡ በመንግሥት ውስጥም የኢንዱስትሪ ፓርክ ሕንፃዎች በፍጥነት እንዲገነቡ የሚፈልጉ ቡድኖች አሉ፡፡ ሌላኛው ቡድን ደግሞ በፍጥነት የሚካሄደው ግንባታ ሥጋት ፈጥሮበታል፡፡ ይፍ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልልቅ አገሮች በርካታ ቁጥር ያላቸው ልዩ ልዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ስብስብ በመሆናቸው የተለያየ ሐሳብና አመለካከት ይኖራቸዋል፡፡ እነዚህን በሙሉ ሰጥ ለጥ ላድርግ ብትልና አንድ ዓይነት አመለካከት ይኑር ብትል ግን የሚሆን አይደለም፡፡ አምባገነንነት ነው፡፡ መንግሥት ፖለቲካዊው ሽኩቻ የልማት ጠንቅ ከመሆኑ በፊት ሊቆጣጠረው ይገባል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የዚህን መንግሥት የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ ቢያቆሙት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አንዳንድ ሠራተኞች የሚገባቸውን እንደማያገኙ እየተናገሩ ነው፡፡ በተለይ ከደመወዝና ከሥራ ዕድል አኳያ ማለት ነው፡፡ የሥራ ኃላፊዎች የሠራተኞችን ደመወዝ ያላግባብ ማሳነስ  የለባቸውም፡፡ ይህም ሲባል ግን የሠራተኛ ማኅበራትም ከሚገባው በላይ ደመወዝና ሌላውም ጥቅማ ጥቅም ቶሎ ቶሎ እንዲመጨምር ማድረግ የለባቸውም፡፡ በእስያ እንዲህ ያለው ነገር ሲደረግ በማጋጠሙ የውጭ ኩባንያዎች ጥለው ለመሄድ ተገደዋል፡፡ እንደማስበው አንድ መሪ እንዲህ ያለውን ነገር አጣጥሞ ማስኬድ ከቻለ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም በአመራሩ ውስጥ ሁለት ጎራዎች ተፈጥረው አንደኛው በፍጥነት ይስፋፋ ሲል ሌላኛው የለም ዝግ እንበል እያለ ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ በእስያ ጃፓን፣ ታይዋንና ሲንጋፖር ናቸው እንዲህ ያለውን ሚዛን በማስጠበቅ በቅጡ ማስተዳደር የቻሉት፡፡ ሲንጋፖርና ጃፓን በግልጽ እንዳስቀመጡት ማኔጅመንቱ፣ ሠራተኛውና መንግሥት ከምርታማነት የተገኘውን ፍሬ ይካፈላሉ፡፡ ማንም ማንንም አይጫንም፡፡ ሚዛኑ የተጠበቀ ነው፡፡ ከፍተኛ የምርት ዕድገት ሲኖር ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ሆኖም እንደ ፊሊፒንስ፣ ቬትናም፣ ካምቦዲያና ኢንዶኔዥያ ያሉት አገሮች በፖለቲካዊ ምክንያት የደመወዝ መጥንን በፍጥነት እያሳደጉ መጥተዋል፡፡ በመሆኑም በመካከለኛ ገቢ አገሮች አንድ የሚያጋጥም ችግር ውስጥ ገብተዋል፡፡ እርግጥ ሌሎች ችግሮችም አሉ፡፡ ሠራተኞችን መጨቆን ትክክል አይደለም፡፡ ተቃዋሚዎችንም እንዲሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ስንነጋገር የኢንቴርነት መዘጋትና ሌሎችም ዕርምጃዎች በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ ሊያሳድር ስለሚችለው ተጽዕኖ አንስተው ነበር፡፡ አሁን ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ አኳያ ያነጋገሯቸው ኩባንያዎች ምን ይላሉ? ሥጋታቸውስ ምንድነው?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- እርግጥ ሁሉን አቀፍ ጥናት አላካሄድንም፡፡ የጃፓንና የስሪላንካ ኩባንያዎችን ለማነጋገር ሞክረናል፡፡ መንግሥትና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበርም የውጭ ኩባንያዎች ደስተኛ ያልሆኑባቸውን አንዳንድ ነገሮች ያውቃሉ፡፡ ለጃፓን ኩባንያዎች ትልቁ ፈተና ባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈጠረባቸው አለመረጋጋት ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም፣ የጃፓን ኩባንያዎች የነበራቸውን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት ቀንሶታል፡፡ የኢንተርኔት አለመኖር፣ ሲኖርም ፍጥነቱ ደካማ መሆን ብሎም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ቢያሳስባቸውም፣ ዋናው ችግር ግን ይኼ አይደለም፡፡ የጃፓን ኩባንያዎችን ከመምጣት እየጎተታቸው ያለው የመንግሥት ግንዛቤ ችግር ነው፡፡ እንደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ወይም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያሉ መንግሥታዊ ተቋማት ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ ያላቸውን (ሃይቴክ) ኩባንያዎች ፍላጎት በቅጡ የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ በመሆኑም ማስረዳት፣ መደራደርና ማስተማር አስፈልጎናል፡፡ ለምሳሌ መንግሥት ትልልቅ ፋብሪካዎች ብዙ ሰዎችን እንዲቀጥሩለት ይፈልጋል፡፡ የጃፓን ሃይቴክ ኩባንያዎች ምናልባት 50 ሰዎችን ይፈልጉ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ 50 ብቻ ለምን፣ ብዙ ሰዎችን ለምን አትቀጥሩም ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሃይቴክ ኩባንያዎች ከታች ጀምሮ ያለውን የምርት ሰንሰለት ተከትለው ላያመርቱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የፕላስቲክ ፋብሪካዎች ቢኖሩ፣ ሁሉንም የምርት ሒደት ከመነሻ እስከ መድረሻ በመከተል አያመርቱም፡፡ መንግሥት ግን ሁሉም የምርት አካሄዶችን እንዲከተሉ ይጠይቃቸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ለጃፓን ሃይቴክ ኩባንያዎች ማቅረቡ ልክ አይመስለኝም፡፡

የጀርመንና ሌሎችም የአውሮፓ ኩባንያዎች ተመሳሳይ ችግር እየገጠማቸው ይመስለኛል፡፡ ትንንሽ ኩባንያዎች ቢሆኑም በሌሎች ኩባንያዎች ኔትወርክ ውስጥ ሆነው የሚያመርቱና የምርት ትስስራቸው ከጫፍ እስከ ጫፍ የማይገናኝ ናቸው፡፡ ሆኖም እነዚህ ኩባንያዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ይህም ቢባል ግን የመንግሥትን የተረጋጋ ፖሊሲ ይፈልጋሉ፡፡ ፖሊሲው የሚተገበርበት አቅጣጫም ተዓማኒነት እንዲኖረው ይሻሉ፡፡ ሁሉንም ነገር እያበላሹና እየሞከሩ መሥራት ክፋት ባይኖረውም፣ በየዓመቱ የፖሊሲና የሕግ ለውጥ የሚደረግ ከሆነ ግን ከፍተኛ ኩባንያዎች ይቸገራሉ፡፡ እንደ ቱርክ፣ ቻይናና ህንድ ያሉ ኩባንያዎች ይህ ዓይነቱ ነገር ላያሳስባቸው ይችላል፡፡ ሥጋት አይፈሩም፡፡ አስቸጋሪ የቢዝነስ ከባቢ አየር ይመቻቸዋል፡፡ ጃፓኖች ምርት ላይ ማተኮሩን ይመርጣሉ እንጂ በየመሥሪያ ቤቱ ባለው ቢሮክራሲና መሰል ምክንያት መቸገርን አይፈልጉትም፡፡ ይሁንና ምናልባት ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ ከሄደ በሚቀጥለው ዓመት በዚህ ወቅት ለጃፓኖች በኪራይ የሚውል አነስተኛ የኢንዱስትሪ ዞን  ይገነባል፡፡ ለጃፓኖች በሚስማማ አደረጃጀት፣ አረንጓዴ ሥፍራ፣ የውኃ ኩሬ ያለውና የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጥበት፣ ከሐዋሳና ከመቐለ ፓርኮች የተለየ ፓርክ ይገነባል፡፡ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ፋብሪካዎችን ከመክፈት ባሻገር ከአውሮፓም ከጀርመንም የሚመጡ፣ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ ያላቸው ኩባንያዎችም የሚስተናገዱበት ዕድል ሊመቻች ይገባል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ጽፌላቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ቆይታዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን የማግኘት ዕድል ነበረዎት?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- አዎን ተገናኝነተናል፡፡ ከአንድ ሰዓት ዘለግ ላለ ጊዜ ተነጋግረናል፡፡ እኛ ስለምንሠራው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ስለሚገነቡት የኪራይ ፋብሪካዎችም ግንዛቤው አላቸው፡፡ ሥጋት የሆነባቸው የሠራተኛ ጉዳይ እንዳለ አጫውተውኛል፡፡ በካይዘን አተገባበርና ሥርፀት ላይ ያላቸውንም ሥጋት ተነጋግረናል፡፡ ለመንግሥት የፖሊሲ ሐሳብ የሚያመነጩ (ቲንክ ታንክስ) ተቋማትን እንደገና የማደራጀት ፍላጎት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም የምርምር ተቋማት አሉ፡፡ ሆኖም ብዙ ዕምነት የሚጣልባቸው፣ መንግሥትን ሊደግፉ የሚችሉ የቲንክ ታንክ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ በሠራተኛ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማኅበራዊና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ አገሪቱ በማክሮ ኢኮኖሚ መስክ፣ በውጭ ምንዛሪ፣ በበጀት ጉድለትና በመሳሰሉት መስኮች ያሉባትን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚቻል ሐሳብ የሚያመነጩ ምርጥ ጭንቅላቶች ያስፈልጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለየገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ዕርምጃው እርስዎ ምን ይላሉ? ወደ ውጭ የሚላክ በቂ ምርት ሳይኖር ለማበረታታት ተብሎ የተወሰደው ዕርምጃ ተገቢ አይደለም ብለው የሚተቹ አሉ፡፡

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተወሰደው ዕርምጃ ደስተኛ ናቸው፡፡ ሆኖም የምንዛሪ ለውጥ የረጅም ጊዜ ችግር መፍቻ መሣሪያ አይደለም፡፡ እንዲያውም የአጭር ጊዜ ችግሮችንም ሊፈታ የሚችልበት አቅም ጠባብ ነው፡፡ ጊዜያዊ መፍትሔ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር የምንዛሪ ለውጡ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ የምርት እሴት መፍጠር መቻል ነው፡፡ እነዚህ እሴቶች ሲፈጠሩ የፍጆታ ዕቃዎችን በገፍ ማስገባት ይቀንሳል፡፡ እንደ ብረት ያሉትን የኢንዱስትሪ ግብዓችንም ከውጭ ከማስገባት በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ጫና ይቀንሳል፡፡ እንዲያውም ወደ ውጭ የመላክ አቅምንም ይፈጥራል፡፡ ጥራት፣ ወጪና በወቅቱ የማቅረብ አቅም ሲፈጠርም የአገር ውስጥ እሴት ፈጠራን ይበልጥ ያነቃቃል፡፡ የምንዛሪ ለውጡን ብዙ መተቸት ባልፈልግም ጊዜያዊ መፍትሔ ነው የሚያመጣው፡፡ በዚህ ዕርምጃ መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት አይቻልም፡፡ ኢንዱስትሪ ሊኖር ይገባል፡፡ ግብርናው ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ የወጪ ንግድ ሊያድግ ይገባዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረተው ምርት ከውጭ የሚገባውን መተካት መቻል አለበት፡፡ ሠራተኞችን ማሠልጠንና ምክንያታዊ የታክስ መዋቅር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የዓለም ባንክ በሚያወጣው የቢዝነስ መመዘኛ ሪፖርትም ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቃል፡፡

ሌላው የምገነዘበው ነገር በመንግሥት ውስጥ ያለው የሐሳብ ልዩነት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስፈለጉ እርግጥ ነው፡፡ ሆኖም ለወጪ ንግዱ ማበረታቻ እየተሰጠ በአገር ውስጥ እየተመረቱ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን ለሚተኩ ምርቶችም ማበረታቻ የማይሰጥ ከሆነ ግን አካሄዱ የማይመስል ነው፡፡ አንዳንዶቹ አስመጪዎች ምንም ዓይነት የውጭ ምንዛሪ አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው የውጭ ምንዛሪን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ እዚህ የሚመረቱት ነገሮች ከውጭ በሚመጡት ላይ እሴት ካልተጨመረባቸው በቀር፣ በውጭ ምንዛሪ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ አይኖራቸውም፡፡ በቬትናም ጉዳይ ለ22 ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ በንግድ ሚዛን ጉድለት በጣም ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ለዓመታት የቆየው ይህ ችግራቸው ግን አሁን ተፈቷል፡፡ 20 ዓመታት ወስዶባቸዋል፡፡ እንደ ሳምሰንግ ጋላክሲ ያሉ ኩባንያዎች በቬትናም ብዙ ያመርታሉ፡፡ ምንም እንኳ ብዙ ዕቃዎችን ከውጭ ቢያስገባም ሳምሰንግ ጋላክሲ በአገር ውስጥ እሴት እየጨመረ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚያደርገው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ ሌሎችም በማኑፋክቸሪንግ፣ በፍጆታ ዕቃዎችና በማሽነሪዎች መስክ ብዙ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች ስለሚያመርቱ በቬትናም የወጪ ንግድ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ቬትናም በአሁኑ ወቅት ሚዛኑ የተመጣጠነ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቀሴ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከውጭ በሚመጣውና በአገር ውስጥ በሚመረተው መካከል የተጣራ ልዩነት ወይም ብልጫ መኖር አለበት፡፡ ሌላው ደግሞ መንግሥት የምንዛሪ ለውጥ የሚያደርግበትን ጊዜ ማስተካከል ይኖርበታል፡፡ ለተወሰኑ ዓመታት የምንዛሪ ለውጥ ሳይደረግ እየቆየ ድንገት ተነስቶ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፣ በየጊዜው ለውጥ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህም ቢሆን የአጭር ጊዜ መፍትሔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምክክር መድረኩ መካሄድ ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከምክክሩ የተገኘው ትሩፋት ምንድነው ይላሉ?

ፕሮፌሰር ኦህኖ፡- በጣም በግልጽ ከሚታዩት የፖሊሲ ምክክር መድረኩ ውጤቶች አንዱ ካይዘን ነው፡፡ የመንግሥት የጥራት፣ የተወዳዳሪነትና የምርታማነት አሠራሮችን የማምጣት ፍላጎት መፈጠርም ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህን ችግሮች እንዴት እንደሚቀርፏቸው ገና መፍትሔዎቹን አላገኙም፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ስንመጣ ብዙ ሠራተኛ በሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ያጠነጠነ አቅጣጫ ነበር፡፡ በወቅቱ ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ የሚባለው ላይ ነበር ውይይቱ ሲደረግ የነበረው፡፡ የወጪ ንግድ ማስፋፊያና የመሳሰሉት ጉዳዮች ይነሱ ነበር፡፡ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ መለኪያ ሥልታዊ ሥርዓት ግን አልነበረም፡፡ ከውይይቱ መጀመር በኋላ ከመጡት ውስጥ ካይዘን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ይጠቀሳሉ፡፡ ምንም እንኳ የኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተዳደር ላይ ችግሮች ቢኖሩም፣ የውጭ ኩባንያዎች የሚያስተዳድሯቸው መሆናቸውም ጥሩ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡ ስለአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት አንነጋገርም ነበር፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የሚደረገው ውይይት ከእስያ አገሮች በተለይም ለቬትናም፣ ለታይላንድና ለኢንዶኔዥያ የቀረበ አካሄድ በኢትዮጵያ እየታየ ነው፡፡