Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትር አንድ በጣም ከተገመገመ ባልደረባቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

ክቡር ሚኒስትር አንድ በጣም ከተገመገመ ባልደረባቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አርፍዶ ሲገባ አገኙት]

  • ለመሆኑ ሰዓቱን አይተኸዋል?
  • አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • እና ምን እየሠራህ ነው?
  • ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ይቅርታ ከመጠየቅ ሰዓትህን ማክበር አይሻልም?
  • ትንሽ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡
  • ምን ሆነህ ነው ደግሞ የምታነክሰው?
  • ስትራፖ ይዞኝ ነው፡፡
  • የምን ስትራፖ?
  • ትናንት ምን እንደነበረ አያውቁም እንዴ?
  • ምን ነበረ ትናንት?
  • ታላቁ ሩጫ፡፡
  • እና ሮጠህ ነው?
  • ያው ሕዝቡ የሚያደርገው ነገር አይደለ፡፡
  • አንተ ሕዝብ በነፈሰበት አትንፈስ አላልኩሁም?
  • እኔማ የሮጥኩት የሕዝቡን የልብ ትርታ ለመስማት ነው፡፡
  • ሌላ ቦታ የሕዝቡን የልብ ትርታ መስማት አይቻልም?
  • ሕዝቡ ብቸኛ መተንፈሻው ይኼኛው ሩጫ ነው፡፡
  • እንዴት? እንዴት?
  • ያው ሕዝብ በግልጽ የሚሰማውን የሚናገርበት ቦታ ነው፡፡
  • ምን ሰማህ ታዲያ?
  • ኧረ ብዙ ነገር ነው የታዘብኩት፡፡
  •  እኮ ምን?
  • የተከለከሉ ኮንሰርቶች ሲካሄዱ ነበር፡፡
  • ማለት?
  • ሕዝቡ የቴዲን ዘፈን ከፍቶ ሲደልቅ ነበር፡፡
  • ምን?
  • በቃ የጎዳና ኮንሰርት ተካሂዷል ማለት ይቻላል፡፡
  • ሕገወጥ ኮንሰርት ተካሂዷል እያልከኝ ነው?
  • እንዲያውም መንግሥት ሰላማዊ ሰልፍ ስለከለከ ሕዝቡ ይኼን ፕሮግራም ልክ እንደተፈቀደ ሰልፍ እያየው ነው፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • በቃ ሰው የሚሰማውን ስሜት፣ ቅሬታ፣ ብሶትና ተቃውሞ የሚያሰማበት መድረክ ሆኗል፡፡
  • ስለዚህ የሕዝቡን ቁጣ በዚህች በዚህች ማስተንፈስ ከቻልን ጥሩ ነው፡፡
  • እ…
  • አየህ አገሪቷ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም ለሚሉ እንደ መከራከሪያ እናነሳዋለን፡፡
  • ካሉ እሺ፡፡
  • በነገራችን ላይ አሁን ስለሩጫው ስታወራ አንድ ነገር በራልኝ፡፡
  • ምን ክቡር ሚኒስትር?
  • በሩጫው ላይ  ሰዎች ሞተዋል አይደል?
  • ሁለት ሰዎች ሞተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • በምን ምክንያት ነው የሞቱት?
  • ትክክለኛ ምክንያት ባላውቅም ሩጫው ከብዷቸው ይመስለኛል፡፡
  • አየህ ምንም እንኳን ሕክምናው ላይ ብዙም ባልሆንም፣ ለሩጫው ግን ሰው ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት፡፡
  • እሱማ ልክ ነው፡፡
  • በዛ ላይ ለሁላችንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠቅማል፡፡
  • ምን አስበው ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • አየህ የሞቱት ሰዎች እኮ የእኛም ባልደረቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
  • እሱማ ልክ ነው፡፡
  • ስለዚህ መጀመርያ በራሳችን ሠራተኞች መጀመር እንችላለን፡፡
  • አልገባኝም?
  • ከዛ ደግሞ የሌሎች የመንግሥት ሠራተኞችንም ማካተት እንችላለን፡፡
  • ምኑ ላይ?
  • በቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን፡፡
  • የምን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ?
  • በቃ ሁሉም ሠራተኛ ጠዋት ጠዋት ግቢያችን ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርግ፡፡
  • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • በሰው ሕይወት የምን ቀልድ አለ?
  • ዓላማውን ግን ምንድነው ክቡር ሚኒስትር?
  • የራሳችንን ሩጫ ለማዘጋጀት ነዋ፡፡
  • የምን ሩጫ?
  • ቅድም ታላቁ ሩጫ ላይ ሕዝቡ ተቃውሞውን ከማስማቱ ባለፈ የተከለከሉ ኮንሰርቶችን እያደረገ ነው አላልከኝም?
  • ብያለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ስለዚህ እኛም ጎን ለጎን ሌላ ሩጫ ማካሄድ አለብን፡፡
  • እሺ፡፡
  • በዚሁ ሩጫ ላይ የሚሰሙት መፈክሮች ልማቱን የሚያበስሩ፣ አገሪቱም ለዓለም ተምሳሌት መሆኗን የሚያሳዩ መፈክሮች ብቻ ይሆናሉ፡፡
  • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • መጀመርያ የኢሕአዴግ ካድሬዎችን ሰብስበን ስለህዳሴ ግድባችን፣ ስለባቡራችንና ስለመንገዶቻችን ድጋፍ እንዲሰጡና እንዲዘምሩ እናደርጋለን፡፡
  • ስለ ስኳር ፕሮጀክታችንስ?
  • እሱ ይቆይ?
  • እሺ፡፡
  • በቃ እነዚህን ካድሬዎች አሰባስበን ሩጫ ማካሄድ ነው፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር ሩጫ ማዘጋጀት እኮ ከፍተኛ ወጪ አለው፡፡
  • የምን ወጪ?
  • በትንሹ የቲሸርትና የሜዳሊያ ወጪ፡፡
  • ምን ችግር አለው ታዲያ?
  • ቲሸርት መከልከላችንን ረሱት እንዴ?
  • ይኼ ለልማቱ ስለሆነ ችግር የለውም፡፡
  • እርስዎ ካሉ እሺ፡፡
  • እንደውም ለሩጫው ጥሩ ስም አግኝቼለታለሁ፡፡
  • ምን ሊሉት ነው?
  • ታላቁ የልማት ሩጫ!

[ክቡር ሚኒስትር አንድ በጣም ከተገመገመ ባልደረባቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

  • ምንም አልተረፍኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ሆንክ?
  • ስንት ጊዜ በግምገማ አልፌያለሁ እንደዚህ ግን የከበደኝ የለም፡፡
  • ምን እያልክ ነው?
  • በቃ ዘነጣጥለው ነው የበሉኝ፡፡
  • ምን?
  • አንዴ ሳይሆን ሁለት ሦስቴ ነው ስብሰባው ውስጥ የወደኩት፡፡
  • ይኼን ያህል?
  • ክቡር ሚኒስትር ነፍሰ በላ ሆነዋል ስልዎት፡፡
  • ግን ይኼ እኮ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
  • አሁን ገን አስፈርቶኛል፡፡
  • ምኑ ነው ያስፈራህ?
  • መውደቂያ ነዋ ክቡር ሚኒስትር
  • ማን ሲወድቅ አይተህ ነው?
  • ክቡር ሚኒስትር እኔ በሙስናው ብዙም እንደሌለሁበት ያውቃሉ?
  • ታደያ በምንድነው የተገመገምከው?
  • በኪራይ ሰብሳቢነት ነው የተገመከምኩት?
  • የምታከራየው ሕንፃ አለ እንዴ?
  • የኪራይ ሰብባቢ አመለካከት አለህ ተብዬ ነው እንጂ፡፡
  • እኔ የሚገርመኝ ገምጋሚዎቹ ሁሉ ሕንፃ እያከራዩ ሌላውን ኪራይ ሰብሳቢ ሲሉ አያፍሩም?
  • ምን ይደረጋል?
  • ይኼ ግን ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡፡
  • እንዴታ ክቡር ሚኒስትር?
  • እኔን ሲገመግሙ እኮ ሥጋ ያየ የተራበ አንበሳ ነው የሚመስሉት፡፡
  • እንዴት ነው ግን የሚችሉት?
  • ግምገማው ሲብስብኝ እኔም ጉርሻዬን አጠነክረዋለሁ፡፡
  • የምን ጉርሻ ነው?
  • ኮሚሽኔን ነዋ፡፡
  • እ…
  • እሱ ነው እንደዚህ የአዞ ቆዳ እንዲኖረኝ ያደረገው፡፡
  • አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ትለምደዋለህ ስልህ?
  • ክቡር ሚኒስትር በአሁኑ ግምገማ ግን መነሳቴ አይቀርም፡፡
  • ከተነሳህ ምን ትሆናለህ?
  • ምንም እኮ የለኝም ክቡር ሚኒስትር?
  • ምርጫህን ብቻ ማስተካከል ነው፡፡
  • የምን ምርጫ ነው?
  • ከሁለቱ ‹‹አ›› አንዱን መምረጡ ላይ ነዋ፡፡
  • ከየቱና ከየቱ?
  • ከአምባሳደርና…
  • እ…
  • ከአማካሪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ኢንቨስተር ጋር ተገናኙ]

  • ምን ዓይነት አገር ውስጥ ነው ያለነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ምን ሆንክ ደግሞ?
  • እኔ እዚች አገር ላይ ኢንቨስት አድርጌ በሰላም መኖር አልችልም?
  • ምንድነው የምታወራው?
  • እንደሚያውቁት እዚህ አገር ላይ አንቱ የተባልኩ ባለሀብት ነኝ፡፡
  • እሱማ ልክ ነው፡፡
  • በዛ ላይ በርካታ ዜጎችን ቀጥሬ የማሠራ ኢንቨስተር ነኝ፡፡
  • ይኼም ትክክል ነው፡፡
  • አገሪቷ ላይ ስንትና ስንት ሀብት ነው ያፈሰስኩት፡፡
  • እውነት ነው፡፡
  • ከዛ ውጪ የፓርቲያችሁም አጋር ነኝ፡፡
  • እሱማ የክፉ ቀን ደራሻችን ነህ፡፡
  • ክቡር ሚኒስትር አንዱ ድርጅቴ ከሰረ፡፡
  • በሚዲያ ሰምቻለሁ፡፡
  • አዬ ክቡር ሚኒስትር ወሬው ሚስጥር ነበር፡፡
  • ሚስጥሩን ነው ሚዲያዎቹ ያጋለጡት?
  • አንድ ሁሌም ለእኛ ጠላት የሆነ ስላለ እሱ እንደሚጽፈው ገብቶን ነበር፡፡
  • እሺ?
  • የሚገርምዎት ክቡር ሚኒስትር አንዳንድ ከእኛ ጎን የቆሙ ሚዲዎች ድርጅታችን መክሰሩን ሲሰሙ እንዳልሰሙ ነው የሆኑት፡፡
  • ለምን?
  • ለእነዚህ ሚዲያዎች የምንሰጠው ማስታወቂያ በእጥፍ እንጨምርላቸዋለን፡፡
  • በጣም ይገርማል፡፡
  • አንዳንድ ሚዲያዎች ደግሞ ጭራሽ ድርጅታችን አተረፈ ብለው ነው የጻፉት፡፡
  • ምን?
  • ለእነዚህማ ሽልማት ሁሉ ነው የሚገባቸው፡፡
  • ድርጅታችሁ ከስሮ ግን እንዴት አተረፈ ብለው ጻፉ?
  • ጥሩ ነገር መመኘት ጥሩ ነው እኮ፡፡
  • ዜና ከመቼ ጀምሮ ነው ምኞት የሆነው?
  • ለነገሩ እንደዛ የጻፉት ሚዲያዎች የእኛው ልሳኖች ናቸው፡፡
  • እሺ ቀጥል፡፡
  • አንዳንዶች ደግሞ አጉል በሕዝብ እንወደድ ብለው ከስሯል ብለው ጽፈዋል፡፡
  • ታስሯል ነው ያልከኝ?
  • ከስሯል ብለው የጻፉ፡፡
  • ታዲያ እናንት ከስሯችኋል አይደል እንዴ?
  • ቢሆንም እኛ ልማታዊ ባለሀብቶች ነን እኮ፡፡
  • ምን ይደረግ እያልክ ነው?
  • ሚዲያዎቹ በሙሉ ይዘጉ፡፡
  • ለምን ሲባል?
  • ለነገሩ እኛ ከመንግሥት ይኼን አንጠብቅም፡፡
  • እና ምን ልታደርግ ነው?
  • የእኛ ሠራተኞችና ደንበኞች እንዳያነቧቸው ከልክለናል፡፡
  • አንተም ሆነህልኛል ማለት ነው?
  • ምን?
  • ትንሹ አምባገነን!

[ክቡር ሚኒስትሩ እየተገመገሙ ነው]

  • ክቡር ሚኒስትር የእርስዎ ጉዳይ እያንገሸገሸን ነው፡፡
  • ምኑ ነው ያንገሸገሻችሁ?
  • ይቺን አገር እንደ ሸንኮራ እኮ ነው የመጠጧት፡፡
  • መጀመርያ አገሪቷ ውስጥ ሸንኮራ መቼ ኖሮ ያውቃል?
  • እ…
  • ስኳር ፋብሪካ ሳይገነባ ስለሸንኮራ ታወራላችሁ?
  • ክቡር ሚኒስትር ማን አለብኝነትዎ ምን ያህል እንደደረሰ እያየነው ነው፡፡
  • ምን እያላችሁ ነው?
  • አሁን ለእርስዎ ሂስና ግለሂስ አያዋጣም፡፡
  • እና ምን ልታደርጉ ነው?
  • ዕርምጃ ከመውሰዳችን በፊት የሕዝብ ሀብት ይመልሱ፡፡
  • ምን?
  • አሁን ያፈሩት ሀብት በሙሉ በሙስና የተገኘ ስለሆነ ለመንግሥት ይመልሱ፡፡
  • ሙሉ በሙሉ?
  • አዎን፡፡
  • ሙሉ በሙሉ አልመልስም፡፡
  • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ባይሆን እንደ ሳውዲዎቹ እንደራደር?
  • በምን?
  • በ70/30!