Skip to main content
x
አገርን መታደግ የሚቻለው ዘመኑን በሚመጥን መፍትሔ ብቻ ነው!

አገርን መታደግ የሚቻለው ዘመኑን በሚመጥን መፍትሔ ብቻ ነው!

በአገሪቱ በሥራ ላይ ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓት ያፀናው ሕገ መንግሥት 23ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው ሕገ መንግሥት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚረዱ በኩረ ሐሳቦችን የያዘ ሲሆን፣ በፊት የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን በማረም አዲሷን ፌዴራላዊት አገር ዕውን ለማድረግ ዓላማ የሰነቀ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ እንደሚለው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ የሕዝቡ አኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የራስን ዕድል በራስ መወሰንን በመጠቀም በነፃ ፍላጎትና በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት ቁርጠኝነት ተገልጿል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ የየራሱ አኩሪ ባህል፣ የመልከዓ ምድር አሠፋፈር፣ በተለያዩ መስኮች ግንኙነቱ የተሳሰረ መሆኑንና አብሮ የሚኖር ስለሆነ የጋራ ጥቅምና አመለካከት እንዳለውም ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ለመጪው የጋራ ዕድል፣ ጥቅም፣ መብትና ነፃነት በጋራና በተደጋጋፊነት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነት ታምኖበት የፌዴራል ሥርዓቱ ሥራ ጀምሯል፡፡ ጉዞው ቀጥሎም 23 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ በዚህ ጊዜ አገሪቷንና ሕዝቧን የገጠሙ ፈተናዎችን መዳሰስ ተገቢ ነው፡፡

ማንኛውም ዓይነት ሥርዓት ከእንከን የፀዳ ነው ብሎ በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡ አገሪቱ ተግባራዊ ያደረገችው የፌዴራል ሥርዓት በርካታ ጥያቄዎች የሚነሱበትም ከእንከን የፀዳ ባለመሆኑ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር ምን ዓይነት ገጽታ ይኑረው? የትኛው ዓይነት አወቃቀር ይሻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ ራሱን የቻለ ትልቅ አገራዊ መድረክ ስለሚያስፈልገው፣ በዚህ ላይ ለመነጋገር አሁን አመቺ አይሆንም፡፡ ነገር ግን አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ራዕይ ሰንቆ 23 ዓመታት ጉዞ ያደረገ የፌዴራል ሥርዓት ውስጥ፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግጭቶች ገጽታቸውን እየለዋወጡ ይከሰታሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሔርን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች በየሥፍራው እየተቀሰቀሱ በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በርካቶች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ አሁንም ድረስ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለፌዴራል ሥርዓቱ ዋነኛ ዘብ ነን በሚሉት በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ምክንያቱ በግልጽ ያልተነገረ ግጭት ተፈጥሮ ዜጎች ለዕልቂት ተዳርገዋል፡፡ በየቦታው የግለሰብ ግጭቶች የብሔር ገጽታ እየተላበሱ ደም ይፈሳል፣ ንብረት ይወድማል፡፡ አሁንም እዚህም እዚያም የሚያፈተልኩ ግጭቶች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ዜጎች ራቅ ያለ ቦታ በመሄድ ለመሥራትም ሆነ ጉዳያቸውን ለመፈጸም በጣም እየፈሩ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ታቅፎ ተዓምር መጠበቅ አይቻልም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የስታዲዮም ረብሻዎች መልካቸውን በመቀየር የብሔር ሰሌዳ እየተለጠፈ ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ረብሻዎችና ሁከቶች መኖራቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ክስተት ነው፡፡ ምንም እንኳ ውጤትን በፀጋ መቀበል በስፖርት ውስጥ የተለመደ ጽንሰ ሐሳብ ቢሆንም፣ አንዳንዴ ነውጠኞች ሰበብ በመደርደር ብጥብጥና ትርምስ ይፈጥራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ከፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ውጪ ስለማይሆኑም ክስተቱ በተነፃፃሪ ያን ያህል ጥፋት አያስከትልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ክስተት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ አሁን ግን በስታዲዮምና ከስታዲዮም ውጪ በተለይ በእግር ኳሱ አካባቢ እየታየ ያለው ክስተት መረን እየተለቀቀ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋነትና ማስተዋል ጋር የሚቃረኑ ሕዝብን በጅምላ መስደብና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚንዱ ተግባራት እየተፈጸሙ ነው፡፡ የእግር ኳስ አፍቃሪያን የማይታወቁባቸው አደገኛ ባህሪያት እየተስፋፉ፣ የሰላማዊ ሰዎች መብቶች እየተጣሱ ነው፡፡ ከስፖርት መሠረታዊ ፍልስፍና ያፈነገጡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ተቀባይነት የሌላቸው በፖለቲካ አየር የተሞሉ ድርጊቶች፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ በአስቸኳይ መፍትሔ ካልተገኘ ማቆሚያው ይቸግራል፡፡

ዘንድሮ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ተረጋግተው መማር አልቻሉም፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች ትምህርት አለመጀመራቸው፣ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ተማሪዎች በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ለመማር በመፍራታቸው እንደገና ምደባ መካሄዱ ሌላው የአገር ራስ ምታት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ብሔር እየለዩ የሚካሄደው የቃላት መቆራቆስ አልበቃ ብሎ፣ በኃይል የታጀበ ማስፈራራትና ሥጋት ሲፈጠር በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ለሕይወት መጥፋትና ለመፈናቀል ምክንያት ናቸው የተባሉ ግለሰቦች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ያወጣው የመውጪያ ፈተና መመርያ እንዲሰረዝ የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በዩኒቨርሲቲዎቹ የመማር ማስተማር መርሐ ግብር ተቋርጧል፡፡ የተማሪዎች ቤተሰቦችም ጭንቅ ውስጥ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ አንድ ክስተት ተፈጠረ ሲባል ብዙዎች እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከዛሬ ነገ ምን ይፈጠራል የሚለው የብዙዎች ጭንቀት ነው፡፡ መፍትሔ መፈለግ ይሻላል? ወይስ እየቆዘሙ በማዝገም የባሰ ችግር መፍጠር?

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ የሚስተጋቡ ጽንፍ የረገጡ አቋሞች ወጣቶችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ነውጠኛ እያደረጉ ናቸው፡፡ አገራዊ ራዕይ የሌላቸውና የአስተዋዩን ሕዝብ የጋራ እሴቶች የሚጋፉ ግድየለሾች የሚለቋቸው ሐሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች፣ ስሜት ኮርኳሪ በመሆናቸው በአገር ላይ ትልቅ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በእልህ፣ በቂም፣ በጥላቻና በግትርነት የተሞሉ መልዕክቶች ከግንባታ ይልቅ አፍራሽነታቸው የጎላ በመሆኑ፣ አገሪቷን ቋፍ ውስጥ እየከተቱ ነው፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ለትልቁ ኢትዮጵያዊነት ምሥል ግድ የማይሰጣቸው ደግሞ ብሔርተኝነትን ከመጠን በላይ እያለጠጡ ችግር እየጠፈሩ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያዎች መረጃ መለዋወጫ፣ ዕውቀት መገባበያ፣ በነፃነት ሐሳብን ማስተላለፊያና መዝናኛ መሆን ሲገባቸው የጽንፈኝነት ማስተናገጃ መሆናቸው ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከሚፀየፉ ጀምሮ አርቆ ማሰብ የተሳናቸው ጭምር ከፍተኛ የሆነ ጥፋት እየፈጸሙ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ወደ መልካም ጎዳና ለመመለስ ካልተረባረቡ ውጤታቸው አውዳሚ መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ ወጣቱን ትውልድ መታደግ የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ አሁን ጥድፊያው መሆን ያለበት በተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ መፍትሔ ለማግኘት ነው፡፡

አገር በማስተዳደር ላይ ያለው ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት እጅግ በጣም አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ እየገባ ያለውን የአገሪቱን ሁኔታ መታደግ ካልቻሉ አገሪቱን የሚጠብቃት ጥፋት ነው፡፡ አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ይገነባባታል ተብላ ትጠበቅ በነበረበች አገር ውስጥ፣ በየሥፍራው የሚፈነዱ ሁከቶች የህልውና ሥጋት ሆነዋል፡፡ በስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችም ሆነ በዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ እየታዩ ያሉ አደገኛ ክስተቶች የመንግሥትን ችግር ነው የሚያሳዩት፡፡ ለፌዴራል ሥርዓቱ እንቅፋት የሆኑትን መሠረታዊ ጉዳዮች መለስ ብሎ ለማየት ፈቃደኝነት ማጣት ውጤቱ ኪሳራ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ባለማክበር ትልቅ ጥፋት ደርሷል፡፡ ሕዝብ ላቀረባቸው ሕጋዊና ትክክለኛ ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ አለመስጠት በጥፋት ላይ ሌላ ጥፋት መደረብ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ራሱን በራሱ እያረመ እንደሚሄድ የበርካታ አገሮች ልምድ ያሳያል፡፡ ራሱን በራሱ የማያርም ሥርዓት ይዞ መንገታገት ደግሞ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ሕዝብ መብቶቹ ተከብረውለት በነፃነት መኖር እንደሚችል ማረጋገጫ ይፈልጋል፡፡ በተለይ የዚህ ዘመን ትውልድ ለጥያቄው ፈጣን መልስ ካላገኘ ትዕግሥት የለውም፡፡ በግምገማና በተሃድሶ ሰበብ አድበስብሶ ማለፍ የማይቻልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርት መሸንገል እንደማይቻል ተረጋግጧል፡፡ ያለፈውን ዘመን ገድል እያነበነቡ ለወቅቱ ጥያቄ ምላሽ መንፈግ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ አሮጌ ወይን በአዲስ አቁማዳ ማስቀመጥ እንደማይቻል ሁሉ፣ ያረጁና ያፈጁ አስተሳሰቦች ለዘመኑ መፍትሔ መሆን አይችሉም፡፡ ስለዚህ አገርን መታደግ የሚቻለው ዘመኑን በሚመጥን መፍትሔ ብቻ ነው፡፡