Skip to main content
x
የለገሃሬው ሐውልት
የለገሃሬው ሐውልት ይህ ሐውልት በምሥራቃዊቷ ድሬዳዋ ከተማ ለገሀሬ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ጣቢያ ፊት ለፊት የሚገኝ ነው፡፡ በብረት ቱቦዎች ቅጥልጥል ሐውልቱ የተሠራው በ2006 ዓ.ም. የተካሄደውን የከተሞች ፎረም ተከትሎ ነው፡፡

ማንባት ነው ያሰኘኝ

ማንባት ነው ያሰኘኝ
ማልቀስ ነው ያማረኝ

ከቁጭቴ ጋራ፤ ወትሮ ከመታገል
የንባ ማድጋዬን፤ ሰብሮ መገላገል
ማልቀስ ነው ያማረኝ፡፡

ያደራ ሳንዱቄ፤ ሲሰበር ክዳኑ
የባልንጀርነት፤ ሲጣስ ቃልኪዳኑ
መጋኛ ሲመታው
ዝምድና ሲከፋ
ፍቅር መሬት ከድታው
ባፍጢሙ ሲደፋ
የዳመነ ፊቴን፤ መዳፌ ውስጥ ልቅበር
የንባ ጋኔን ልስበር፡፡

እኔ
እንደበሬ ያረስሁ
እህል የጎመጀሁ፤ ዝማምን የጎረስሁ
አዝመራ ያደረስሁ
ፍሬውን ያልቀመስሁ፤
እኔ
መከራን በበርሚል
መጽናናትን በእፍኝ
ከዘመን ያተረፍሁ
እንቧይና ሙጃ፤ የወረሰው ሳሎን
ሳልፈልግ የታቀፍሁ

ቀስተደመናየ፤ ምድጃ ሥር ወድቆ
እፍኝ አመድ ዝቆ፤
እፍኝ ትቢያ ቅሞ
ጥላሸቱን ጠግቦ
ትቢያ ተሸክሞ
ኖህ ከነ ታሪኩ
ከነ ታይታኒኩ
እባህር ውስጥ ሰጥሞ
ለማየት የበቃሁ
ፊቴን እየፈጀሁ፤ ደረት እየደቃሁ
ማልቀስ ነው ያማረኝ፡፡

- በዕውቀቱ ሥዩም

* * *

ጥቁሩ ቁራ

ቁራ በአንድ ወቅት ሼኪ ወይም ቄስ ስለነበረ ቀለሙም ነጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ አዕዋፋት ሁሉ አቤቱታ አሰሙበት፡፡ እንደዚህም አሉ ‹‹አንድ ወገን ሥጋ ይበላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፍራፍሬ ይበላል፡፡››

ከዚያም ሁሉም አዕዋፋት ተሰባስበው ‹‹አንተ ሼኪ ወይም ቄስ ነህ! ነገር ግን የምትሠራው ነገር ስህተት ነው፡፡ ትንንሾቹ አእዋፋት ሥጋ መመገብ አለባቸው፡፡ ትልልቆቹ ደግሞ ፍራፍሬ ይብሉ፡፡ አንተ ግን ከሁለቱም ወገን ትበላለህ፤›› አሉት፡፡

በሱማሌ ብቻ ሳይሆን በኩሽ ባህል በአጠቃላይ ቁራ የፀሐይ አምላክ የሆነው የዋቅ ተወካይ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ኦሮሞዎችም ጭምር በፀሐይ አምላክ ያምናሉ፡፡ ቁራ የፀሐይ አምላክ ዋቅ የተናገረውን ለሰዎች የሚተረጉምና የሰዎችንም መልዕክት ወደ ፀሐዩ አምላክ የሚያደርስ መሆኑን ያምናሉ፡፡

ቁራውም ሲናገር ‹‹ዋቅ! ዋቅ!›› እያለ ነው፡፡

ሆኖም ቁራው እምነት በማጉደል ሁለቱንም ነገሮች ማለትም ፍራፍሬና ሥጋ ስለበላ ቅጣት ተጣለበት፡፡ ረግመውትም ጥቁር ሆኖ ቀረ፡፡

  • አህመድ መሃመድ ዓሊ

* * *

ዋጋ ስጥ

እውነተኛ ማንነትህን ማወቅ፣ እውነተኛ ፀጋህን በማወቅ መከተል አለበት፡፡ ከብቃቶች ሁሉ የላቀችዬቱ ብቃት፣ ብቃትን የማወቅ ብቃት ነች፤ ይላሉ ጠቢባን፡፡ ይህ የሌሎችን ብቃት ስለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ የገዛ ራስህንም ብቃት ስለማወቅ የተባለ እውነት ነው፡፡ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ግን፣ እውነተኛ ኃይልህና ፀጋህ እምንህ ላይ እንደሁ ለማወቅ አይሳንህም፡፡

በመሆን ጎዳና ላይ፣ ብዙ ተጓዦች፣ ነፍሳቸውን ወይም መንፈሳቸውንና ኃይሏን እውነተኛ ማንነታቸውና ኃይላቸው እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ነፍስ ወይም መንፈስ በምንለው የቃል ዣንጥላ ውስጥ የትየለሌ ልዩ ፀጋዎች ታምቀዋል፡፡ ይህ በሰው መንፈስ ውስጥ ብቻም አይደለም፤ በባህልና በተፈጥሮ መንፈስም ውስጥ እንጂ፡፡

አንተ ፈጣሪ በሰም ያሸገህ ህቡዕ መጽሐፍ ነህ፡፡ በነፍስህ ግምጃ ቤት ውስጥ የተቀመጡቱ ሚስጥራት ሊገለጡ የሚችሉት ባንተ ብቻ ነው፡፡ በባህልህ ካዝና ውስጥ የተቆለፈባቸው የጥበብ ዕንቁዎች ተከፍተው ሊወጡ የሚችሉት ባንተ ብቻ ነው፡፡

ሁለንተና አብዝቶ ይወድሃልና፣ ያንተን በገዛ ራስ መንቃት አብዝቶ ያፈቅራልና፣ ከቶም ሊያስገድድህ አይሻም፡፡ በፈቃድህ ጉበን ላይ እሚያሻህን እገዛ ሊሰጥህ ብቻ ይጠብቃል፡፡

ላለህና እቅርብህ ለሆነው ዕውቅናና ዋጋ ስጥ፡፡ እጓሮአቸው ፍጹም ንፁህ ሉል እያለላቸው፣ ከአድማስ ባሻገር ድብቅ ፀጋ ፍለጋ ከሚማስኑትን አትሁን፡፡ ሁዋላ፣ ለውድቀትህ የሆነን ነገር መኮነን ካለብህ፣ እጦትህን ሳይሆን፣ ማየት አለመቻልህን ኮንን፡፡ አንተ ግን፣ ከኮናኞች ወገን አይደለህም፡፡

  • ኦ’ታም ፑልቶ ‹‹የፈላሱ መንገድ›› (2006)

* * *

ጃፓን የቪዲዮ ጨዋታ ለሚከተሉ አሽከርካሪዎች ሕግ አወጣች

‹‹ማርዮ ካርት›› በጃፓን የሚወደድ የቪዲዮ ጌም (ጨዋታ) ሲሆን፣ ብዙዎች የጨዋታውን ገጸ ባህሪዎች የሚወክሉ ልብሶች ለብሰው መጠነኛ መኪና (ስኩተር) ያሽከረክራሉ፡፡ አሽከርካሪዎቹ ገጸ ባህሪያቱን ለማስመሰል ሲሞክሩ ደኅንነታቸው በሚጠብቅ ሁኔታ አይደለም፡፡ በጃፓን ጎዳናዎች አደጋ መከላከያ ቆብ (ሔልሜት) ሳያደርጉና የደኅንነት ቀበቶ ሳያስሩ የሚያሽከረክሩ ሰዎች በዝተዋል፡፡

የጃፓንን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ችግሩ ያሳሰባት ጃፓን አዲስ የአሽከርካሪዎች ሕግ አውጥታለች፡፡ ስኩተር የሚነዱ ጃፓናውያን ያለ አደጋ መከላከያ ቆብና የደኅንነት ቀበቶ እንዳይንቀሳቀሱ አግዳለች፡፡

የጨዋታው ገጸ ባህርዎችን የሚያስመስሉ ልብሶች ከቆብና ከቀበቶ ጋር ጥቅም ላይ እንዲውሉም ሕጉ ይደነግጋል፡፡ የ‹‹ማርዮ ካርት›› ጨዋታ ገጸ ባህሪን የተከተሉ አለባበሶች በጃፓን ታዋቂ ሲሆኑ፣ ቱሪስቶቹንም በመሳብ ይታወቃሉ፡፡

ጃፓን የቪዲዮ ጨዋታ ለሚከተሉ አሽከርካሪዎች ሕግ አወጣች

* * *