Skip to main content
x

ማኅበራዊ ንቅዘትን የተፋለመው ወጣት

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በሰለሞን ኃይለማርያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› በሚል ርዕስ (ተዛማጅ ትርጉም ማኅበራዊ ንቅዘትን በወኔ የተፋለመው ወጣት) በእንግሊዝኛ ተደርሶ በ2003 ዓ.ም. በኮድ ኢትዮጵያ ለኅትመት የበቃው መጽሐፍ በጀርመንኛ ተተርጉሞ ባለፈው ጥቅምት ወር  ለጀርመንኛ አንባቢዎች ቀርቧል፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፉ ከሰባተኛ ክፍል በላይ የሚገኙ እንግሊዝኛ አንብበው ለመረዳት የሚችሉ ታዳጊ ወጣቶችና ወጣቶች ትምህርታዊ ቢሆንም፣ ከአማርኛ በፊት ጠቃሚነቱ ታውቆ ወደ ጀርመንኛ መተርጎሙ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህም ሆኖ በኢትዮጵያዊ ደራሲ የተጻፈ በመሆኑና የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ውጤት በመሆኑ ከዚህም በላይ ትምህርታዊ በመሆኑ ጽሑፉን መገምገም አስፈላጊ ሆኗል፡፡

በዚህ ግምገማዊ ጽሑፍ፣ መጽሐፉ እንዴት ሊጠነሰስ እንደቻለ፣ እንዴት እንደተጻፈ፣ ለምን እንደተጻፈ መጠነኛ የዳሰሳ ጥናት የተደረገ ሲሆን፣ መጽሐፉንም በማንበብ ፍሬ ሐሳቡን ለማቅረብና ከወጣቶች ሥነ ባህሪ ዕድገት አኳያ የሚያበረክተው ገንቢ አስተዋጽኦን በሚመለከት አስተያየት ለመስጠት ጥረት ተደርጓል፡፡ የግምገማው መሠረታዊ ዓላማ ይኸው በአማርኛ ሳይተረጎም፣ በአገር ውስጥ አድናቆት ሳያገኝ በውጭ አገር የተሸለመውና የተተረጎመው መጽሐፍ ምን እንደሚተርክ በአጭሩም ቢሆን ቃኝቶ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ድርጅቶች በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ለማካተት ይችሉ እንደሆነ ሐሳብ ለመሰንዘር ነው፡፡

መጽሐፉ መጠንሰስ

በነሐሴ ወር 2003 ላይ ኮድ ኢትዮጵያና ኮድ ካናዳ የተባሉ አጋር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 18 ለሆኑ ወጣት አንባቢያን የሚመጥን የሥነ ጽሑፍ ውድድር አዋጅ ያስነግራሉ፡፡ በወቅቱ በውድድሩ የሚሳተፉ ደራስያን ለውድድር የሚያቀርቡት ልቦለድ ከዘመኑ ማኅበራዊ ሕይወት ጋር የተዛመደ፣ ወጣቶች የማኅበረሰቡ አባላት በመሆናቸው በአፍላ ዕድሚያቸው ፊት ለፊት የሚጋፈጡት የማኅበራዊ ሕይወት ቀውስና ፈተና ምን እንደሆነ የሚያንፀባርቅ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ለውጥ የሚመጣበትን አቅጣጫ የሚጠቁም ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት ተመልክቷል፡፡

ደራሲው ሰለሞን ይህንን የውድድር መመርያ ከመረመረ በኋላ ተልዕኮው የማኅበረሰቡን ቁስል ማወቅና የማኅበራዊ ጠንቁ ዓይነት፣ ምንነት፣ ስፋት፣ ጥልቀት መጠቆም ብቻ ሳይሆን መፍትሔው ምን እንደሆነ ለማቅረብ ያ ውድድር መልካም አጋጣሚ የሆነለት ይመስላል፡፡ በዚያ ወርቃማ አጋጣሚም በደራሲው ውስጥ ሲብሰለሰል የኖረው ማኅበራዊ ንቅዘት አድማሱ ሥዩም ብሎ በቀረፀው ዋነኛ ገጸ ባህሪው አማካይነት ምንጭ ሆኖ ይፈስ መፍሰስ እንደጀመረ ከጅምሩ መረዳት ይቻላል፡፡

ታሪኩ

220 ገጽ ካለው መጽሐፍ የምንረዳው አድማሱ የተባለው ዋነኛ ገጸ ባህሪ፣ ገና ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ወደ ሥራ ዓለም እስከተሰማራበት ጊዜ ድረስ ሙሰኝነትን የተዋጋ ቅን ዜጋ ነው፡፡ ታሪኩ የታሪክ ጥንጥኑን እየተረተረ የሚሄደው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ሰዎች የተፈጨ በርበሬን ከደቀቀ ጡብ ጋር እየቀላቀሉ ለሽያጭ ሲያዘጋጁ ይመለከተትና ይህንን አስከፊ ሥራ ለፖሊስ ያስታውቃል፡፡ ይህም በጓደኞቹ ዘንድ እንዲታወቅና መልካም አርአያ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ጉቦ እየተቀበሉ የሚፈጽሙትን ሕገወጥ ተግባር ይገነዘብና ያንን አሳፋሪ ተግባር ያጋልጣል፡፡ ርዕሰ መምህሩም በአድማሱ ጥቆማና ክትትል ጉዳዩ ወደ ወላጅ ኮሚቴ ቀርቦ ይባረራል፡፡ አድማሱ የ12ኛ ትምህርቱን ጨርሶ በአንድ ዕቃ መለዋወጫ መሸጫ መደብር ሲቀጠርም አጭበርባሪዎች ይገጥሙትና ፊት ለፊት ተጋፍጦ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል፡፡

ይሁንና በሕይወት የሚገጥምን ፈተና ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማለፍና በአሸናፊነት የመወጣት ሒደት  አልጋ በአልጋ ሊሆን የማይችል በመሆኑ ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ተግባር በጀግንነት በመታገሉ ምክንያት መሸለም፣ መመስገን፣ ትልቅ ማኅበራዊ ደረጃ መያዝና ክብር ሊሰጠው ሲገባ ጥሩ ሥራን በመጥፎ በሚተረጉሙ ብላሽ በሆኑ ሰዎች የሐሰት መረጃ ይወነጀላል፡፡ በመወንጀሉም አስፈላጊ ያልሆነ መንገላታት ይደርስበታል፡፡ እንግልቱን አልፎ በዕውቀትና በፍቅር ሕይወት ያልፋል፡፡ የሚገጥመውን ፈተና በከፍተኛ ጥረት ይወጣዋል፡፡ ማኅበራዊ ንቅዘት አስከፊና አስጸያፊ ቢሆንም እንኳን ጸሐፊው የተጠቀመበት የሥነ ጽሑፍ ጥበብ ገንቢ ሐሳብ የያዘ ታሪኩን እንድናደንቀው እያደረገ ከዳር ዳር እንድናነበው ያደርጋል፡፡

በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ አፍራሽ አዝማሚያዎችን እንደምን ሥነ ጽሑፋዊ ውበቱ በተላበሰ መንገድ ለተደራሹ ማቅረብ እንደሚገባ ያስተምረናል፡፡ የፈጣሪና አምራች ኅብረተሰብ እንደ ምን መገንባት እንዲቻል ይገልጽልናል፡፡ በተለይም በብዙ የሕይወት መስክ ዕውቀታቸውን የሚያከፍሉት የገነተ ልዑሉ የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሽማግሌው አቶ ንጋቱ በአድማሱ ሕይወት ከፍተኛ ሥፍራ ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ያለማቋረጥ በመለወጥ ላይ በምትገኘው ዓለም ራስን ከለውጡ ጋር አስማምቶ መጓዝ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ንፁህ ግዴታ መሆኑን ከምሁሩ አንደበት እንገነዘባለን፡፡ ለአንዲት በዘመነ ግሎባላይዜሽን ውስጥ የምትጓዝ አገር አስፈላጊውን መረጃ መያዝ እንዳለባትና በዚህ መረጃም መመራት እንደሚገባት በጣፈጠ መንገድ ከታሪኩና ከባለ ታሪኩ እንድንገነዘብ እንደረጋለን፡፡ ስለቤተሰብ ምጣኔ፣ ርዕይ ስላላቸው ወጣቶችና ፊት ለፊት የሚጠብቃቸውን የሕይወት ፈተና እንደምን ተጋፍጠው ድል እንደሚያደርጉት ይመራቸዋል፡፡ መጽሐፉን ልማታዊ የሥነ ጽሑፍ ሥልትን በተዋበ መንገድ እንደምን ማቅረብ እንደሚቻል ያመለከተ ነው ማለት ይቻላል፡፡ መጽሐፉ መካከለኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰቡ ክፍሎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ቢሆንም እንኳን መላውን መደብ እንዲያካትት ተደርጎ የተደረሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡

 የመጽሐፉ መቼትና ይዘት

ታሪኩ የሚፈጸመው በመዲናችን አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ሥፍራዎች ሲሆን ዘመኑም ያለንበት ነው፡፡ የታሪኩ ምንጭም በማኅበራዊ ንቅዘት የተዘፈቀው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ታሪኩ የሚገመገመውም ከዚህ አኳያ ነው፡፡

በመቼቱ ላይ እንደተጠቀሰው የመጽሐፉ ዋነኛ ጭብጥ ማኅበራዊ ንቅዘት ለዕድገታችን ፀር ነውና እንዋጋው፣ ወደዚህም የውጊያ መስክም ነገ ኃላፊነትን የሚረከበው ወጣት ትውልድን አስገብተን በለጋ ዕድሜው በማሠልጠን በደመነፍስ ሳይሆን በስልት እንዲዋጋው እናስችለው በሚል መሠረታዊ ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ የሚስተዋለውን ማኅበራዊ ንቅዘት በልዩ ልዩ አጋጣሚዎችና ምክንያቶች የሚጠቁመው መጽሐፍ ጋናዊው አርማህ ‹‹ዘ ቢዩቲፉልስ አር ኖት የት ቦርን›› (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1968 በመጻፍ በወቅቱ የነበረውን ማኅበራዊ ንቅዘት እንዳቀረበውና ካሜሩናዊው ደራሲ ፈርዲናንድ ኦዮኖ «ቦይ» ወይም «ዘ ሐውስ ቦይ» እየተባለ በሚጠራው መጽሐፍ የፈረንጆች ደካማ አስተሳሰብ እያዋዛ እንደሚተቸው ሰለሞንም እያዋዛ ማኅበራዊ ሕፀፃችንን ይነግረናል፡፡ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ ሴኔጋላዊው ዑስማኔ ሰንባኔ እንደ «ኒዮርክ ታይምስ» እና «ታይምስ» የመሳሰሉ መጽሔቶችም በቀረበለት ቃለ መጠይቅም «ያደረግሁት ነገር ቢኖር አፍሪካውያን ያልተገሰሰ ድንግል የኪነ ጥበብ ሀብት በውስጣቸው እንዳላቸው ማሳየት ነው፤» ካለ በኋላ፣ «መቼም አንድ ሰው ሲፈጥር አገሩን እንጂ ዓለምን እያስተነተነ አይፈጥርም፡፡ በመሠረቱም በአፍሪካ ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ አፍሪካውያን እንጂ አሜሪካውያን ወይም ፈረንሣውያን ወይም ሩሲያውያን ወይም ቻይናውያን ሊሆኑ አይችሉም፤» በማለት የገለጸውን አቅጣጫዊ አገላለጽ በተግባር የሚያሳይም ነው፡፡ ሰለሞን በተጠቀሰው መጽሐፉ ኡስማኔ ሰንባኔ «ዘ መኒይ ኦርደር» በተሰኘው መጽሐፉ ዘመናዊ ተብዬ የሴኔጋላውያን ሕይወት ምን ያህል በቢሮክራት፣ በጉቦኞች፣ ታማኝነት በጎደላቸው፣ በሙስና በተዘፈቁ ተወላጆች እንደተበላሸ ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳየን ሁሉ፣ በዋነኛው ገጸ ባህሪ በአድማሱ አማካይነት ያለንን ማኅበራዊ ንቅዘት እንድንመለከትና እንድንገመግመው ያደርገናል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ በርካታ ገጸ ባህሪያት ቢኖሩም ዋነኛው ገጸ ባህሪ ማኅበራዊ ንቅዘቱ የኅብረተሰቡ በመሆኑ ዋናው ገጸ ባህሪ ብቻውን መጥፎ ድርጊት እንዴት እንደሚፈጸም፣ በማን እንደሚፈጸምና ለምን እንደሚፈጸም ተመልክቶ፣ ለማኅበራዊ ፍርድ አቅርቦ፣ ተርኮ፣ ታግሎ የሚወጣው አይደለም፡፡ ምን ለማለትና ለማድረግ እንደፈለገ የሚያዳምጠውንና ሐሳብ የሚጋራውን ይፈልጋል፡፡ ይህም ሆኖ በከፍተኛ መኮንንነት ካገለገሉ በኋላ በጡረታ የተገለሉትና በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት በጥበቃ የሚሠሩት አባቱ ቁጡና ብቸኝነት የሚሰማቸው ዓይነት በመሆናቸው የልጃቸው አድማሱ ስሜት የሚያጤኑ ዓይነት ሰው አይደሉም፡፡ ስለሆነም አድማሱ ከአባቱ ይልቅ ከእናቱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ያዘወትራል፡፡ ይህም ማኅበራዊ ችግር መፈታት እንዳለበት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ እንድንገነዘብ ይቀሰቅሰናል፡፡ ይልቁንም ከፍተኛ የጦር መኮንን የነበሩት አባቱ የመጀመርያ ሚስታቸውና ልጆቻቸው በኤርትራ ጦርነት ስለሞቱ በውስጣቸው ታምቆ ከሚኖረው የመረረ ሐዘን በኋላ ትውስታው እየመጣ እንከን እንደሆናቸው በመግለጽ፣ ለሰው ልጅ ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያቀርብልናል፡፡ ሌሎችም ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን መልዕክቶች በመጽሐፉ ውስጥ ማግኘት ይቻላል፡፡

የመገምገሚያ ዓውድ

በመሠረቱ፣ በአገራችን ያለው ማኅበራዊ ንቅዘት ምን እንደሆነ ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ አንድ ሕፃን ልጅን ለመላክ መደለያ ሲሰጥ ይጀመራል፡፡ በትምህርት ቤት ‹‹ካስኮረጅከኝ ይህን አደርግልሃለሁ›› በሚል ይቀጥላል፡፡ የሚያስፈራራኝን ከመታህልኝ ገንዘብ ከየትም አምጥቼ እሰጥሃለሁ ወደ ሚባል የሚታለፈው በልጅነት ዘመን ነው፡፡ በቤት ብቻ ሳይሆን በጎረቤት፣ በመንደር፣ በቀበሌ፣ በትምህርት ቤት በመደለያ፣ በጉቦ፣ በሸፍጥ፣ አስመስሎ በመንገርና በማስመሰል የሚታዩ፣ የሚሰሙና የሚደረጉ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች አሉ፡፡  ዕድሜ ከፍ እያለ በሄደ መጠን የማኅበራዊ ቀውሱ ዓይነትና መጠን እያደገ እንደሚሄድም አያጠያይቅም፡፡ ጉዳዩ ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን ‹‹ይህን ከሰጠኸኝ ይህን አደርግልሃለሁ›› እየተባሉ ከሚመለኩ ነገሮችም ጋርም ይገናኛል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ባቀረበው አንድ የታተመ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደጠቆመው፣ «ጉቦ» ለሚለው ቃል አዲስ የኣማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ፍርድን ለማጣመምና ሐሰትን እውነት ለማስመሰል ለሐሰተኛ ዳኛ የሚበረከት መማለጃ ነው፤›› ይላል፡፡ ስለሆነም ጉቦ በስጦታም ሆነ በበረከት፣ በእጅ ማራሻም ሆነ በጉርሻ፣ በምልጃም ይሁን በደጅ ጥናት፣ በማሞገስም ሆነ በማሞካሸት፣ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስም ሆነ የብፁዐን ሁሉ ብፁዕ አድርጎ በግልም ሆነ በጋራ ማቅረብ የማይገባን ጥቅም ለማግኘት ከሆነ  ዞሮ ዞሮ ሕገ ወጥ ድርጊትን ለመሸፋፈንና ፍርድን ለመገምደል የሚያገለግል ማኅበራዊ ንቅዘት ከመሆን አያልፍም፡፡

ይህንኑ ቃል ዌብስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርብር፣ ማታለል፣ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን ዳኛ ወይም ባለሥልጣን ኃላፊነቱን እንዲዘነጋ የሚሰጥ ሽልማት ስጦታ ውለታ፣ ወዘተ. በማለት ያፍታታዋል፡፡ ብላክስ ሎው የተበላው የታወቀ መዝገበ ቃላት ደግሞ (አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ) በሕጋዊ ኃላፊነት ያለን ባለሥልጣንን (በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን) አመለካከት፣ አስተሳሰብ በተፅዕኖ ለማሳመን ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ነባር በስጦታ፣ በበረከት፣ በድርጎ፣ ወይም በሌላ መልክ መስጠትና መቀበል እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡ እንደዚሁ በሌላ መዝገበ ቃላት ትንታኔ «የራስ ያልሆነን ሀብትና ንብረት በተለያየ መልኩ መውሰድ» ማለት እንደሚሆን፣ በቀጥታ ኪስ ውስጥ ዘው ብሎ ባይገባ፣ ቤት ሰርስሮ ሳጥን ሰብሮ በድፍረት ባይሰርቅ፣ አሳቻ ቦታ ቆሞ ባይነጥቅ፣ የዚያን ከዚህ አምጥቶ የማይሆነውን «ይሆናል» የሚሆነውን «አይሆንም» በሚል ወይም ልብን አፍዝዞና አደንግዞ ባይወሰድ፣ ጉቦ የራስ ሀቅ ያልሆነን ሀብት፣ ንብረት ወይም ሌላ መንፈሳዊ ስጦታን በሥልጣን ተጠቅሞ መቀበል፣ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበርና ማታለል መሆኑን እንረዳለን፡፡

በእርግጥም መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ዘንግቶ ሥልጣኑን ለሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ማዋል ሲገባው የራሱን ጥቅም የሚያሳደድ ከሆነ፣ በቢሮ ውስጥ ከመቀመጡ በስተቀር ጫካ ከገባ ወንበዴ፣ ጨለማን ተገን አድርጎ ቤት ከሚሰረስር ሌባ፣ አካባቢውን በቁጥጥር ሥር አድርጎ ከሚዘርፍ ነጣቂ፣ የሰው ኪስ ከሚገባ ሞሽላቃ ሌባ ሊለይ አይችልም፡፡ ጉቦ በጉልተኛው ሥርዓት መተያያ፣ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ፣ ጉርሻ፣ ወዘተ. የወግ ስሞቹ ሲሆኑ፤ መደለያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ ወዘተ. የሐሜት መጠሪያዎቹ ነበሩ፡፡ የማዕረግ ስሞቹ ደግሞ አመኃ፣ ገፀ በረከት፣ ሙገሳ፣ ውደሳ፣ ቅደሳ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ የሐሜት ስሞቹ መደለያ፣ ማለዘቢያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ የማይነጥፍ የቅቤ ማሰሮ ቢሆኑም ማስታወሻ፣ መታሰቢያ፣ ስጦታ፣ የሚሉት ደግሞ ከቁልምጫ ስሞቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ «የመንግሥት ገቢን የሚሰበስብ ባለሥልጣን ማር የፈሰሰበት ምላስ» የሚል የህንዶች ተረት ይጨመርበታል፤ «ተሹሞ የማይበላ ተጥዶ የማይፈላ የለም» የሚል የአገራችንን አባባልም ይጠቀሳል፡፡ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» ተብሎም እንደ ትልቅ ነገር አዋቂ ተብዬዎች በምክር ስም የሚሰጡት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡

የመጽሐፉ ቅርጽ

ማኅበራዊ ንቅዘትን የሚያጋልጥ ጽንሰ ሐሳብ በባህሪው ጠንካራና መረር ያለ ቢሆንም ዋነኛ ዓለማው እውነቱን ማንፀባረቅ ብቻ ሳይሆን ሥነ ጽሑፋዊ ውበትን ተላብሶ ታሪኩም ከምዕራፍ አንድ ተነስቶ 29ኛው ምዕራፍ እስኪደርስ ውብ በሆነ ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በዚህ ረገድ ጸሐፊው የተደራሲዎችን ሥነ ባህሪ ጊዜ ወስዶ በማጥናት ከትቦት ከሆነ ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህም በላይ አወዳዳሪዎቹም ሆኑ ገምጋሚዎቹ የማኅበራዊ ኑሮና የሥነ ባህሪ ሊቃውንት ስለሆኑ የእነሱን ሚዛን መድፋት ይጠበቅበት ነበርና በነሱም ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን እንገነዘባለን፡፡ ካለበለዚያ ‹‹ደረቅ በደረቅ አላህም አይታረቅ› እንዲሉ ግዴታ ከሌለ የማይነበብ በሆነ፣ ለሽልማትም በሌላ ቋንቋ ለመተርጎምም ባልታደለ ነበር፡፡ በእርግጥም የታዳሚውን ስሜት ጨምድዶ እስከ መጨረሻዋ ገጽ ካልያዘ የታሰበለትን ግብ ከቶ ሊመታ አይችልም፡፡ ስለዚህም መጽሐፉ ሥነ ጽሑፋዊ ውበትና የማኅበራዊ ቀውስን ተመራማሪዎች በሚገመግሙትና ገምግመውም በሚቀበሉት መልኩ ማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የተጻፈ ነው ማለት እንችላለን፡፡

መጽሐፉ በአጭሩ የተጠቀሰውን ይመስላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት ግን በቅድሚያ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ቢጻፍ ያም ባይሆን በቅድሚያ በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ቢተረጎም መልካም ነበር፡፡  አልሆነም፡፡ ነገር ግን አሁንም ጠቃሚነቱ ግምት ተሰጥቶት በአገር ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በሥርዓተ ትምህርቱ ቢካተት ጥሩ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡