Skip to main content
x

የትምህርት ሚኒስቴር አወዛጋቢ አሠራርና ተጠያቂ አልባነት

በመላኩ ገድፍ

ዘላቂነት ያለው፣ አስተማማኝ፣ ጥራትና ፍትሐዊነቱ የተረጋገጠ ትምህርትና ሥልጠና በቀጣይነት በመገንባት ተወዳዳሪ የሆነ ብቁ ዜጋ በማፍራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳለጥ የሚል ራዕይ ሰንቆ የሚንቀሳቀሰው የትምህርት ሚኒስቴር  ዓላማን ከማሳካት አንፃር ሲታይ በብዙ ርቀት ላይ ሆኖ እየተንደፋደፈ፣ ‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ› ዓይነት ፖሊሲዎችን በየጊዜው ሲያወጣ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ትምህርት በኢትዮጵያ ባለፉት አሥርት ዓመታት በመንግሥት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ቢሆንም፣ ዘርፉ ይኼ ነው የሚባል ተጫባጭ እመርታ ሊያሳይ ግን አልቻለም፡፡ በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ‹በሁሉም ቅድመ ምረቃ ትምህርት መስኮች ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የብቃት መለኪያ አጠቃላይ የምዘና ፈተና ወስደው አጥጋቢና ከዚህ በላይ ውጤት ማስመመዝገብ ይጠበቅባቸዋል በማለት ያወጣው መመርያ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላየ ጌቴ እንደሚሉት፣ ይህ መመርያ በውጤታማ ትግበራ ስኬት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በቅርቡ ከተነደፉ መርሐ ግብሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ተመራቂ ተማሪ በተማረበት የትምህርት ዘርፍ በቂ ዕውቀትና ክህሎት ሊኖሩት እንደሚገባና ይህንን ለማረጋገጥም መመዘኛ ፈተና መሰጠቱ አያከራክርም፡፡ ነገር ግን ከመውጫ ፈተናው በፊት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ሒደት ይህንን መመርያ ከግብ ያደርሳል ወይ? የሚለው በቅድሚያ መታየት አለበት፡፡ ‹የትም ፍጪው ዱቀቱን አምጪው› እንዲሉ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ሒደቱ ላይ ከመሥራት ይልቅ ውጤቱ ላይ ያተኮረ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ አካሄድም የተፈለገውን የትምህር ጥራት ከማምጣት  አንፃር ሲታይ ዉጤታማነቱ አጠያያቂ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በመማር ማሰትማር ሒደት ውስጥ ለትምህርት ጥራት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት መምህራን ናቸው፡፡ ተማሪዎች የሚማሯቸውን የትምህርት ዓላማዎች በጥሩ ሁኔታ ለመገንዘብም በቂ የማስተማር፣ ልምድና ክህሎት ባላቸው መምህራን መማር እንዳለባቸው የማያከራክር ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚመደቡ መምህራን የማስተማር ክህሎትና ብቃት ከላይ ከተጠቀሰው መርህ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡

መምህር አንተነህ በላይ (ስማቸው ተቀይሯል) በአገራችን ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በአንዱ የምህንድስ ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው፡፡ መምህር አንተነህ፣ ‹‹በሕይወቴ አስተማሪ እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፤›› ይላሉ፡፡ መምህር የሆኑበትን አጋጣሚም እንደሚከተለው አስረድተውኛል፡፡ በተማሩበት ዩኒቨርሲቲ አመርቂ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ለመምህርነት ይመለመላሉ፡፡ ‹‹እኔም አጥጋቢ ውጤት ስለነበረኝ  ከተመረጡት ውስጥ አንዱ ነበርኩ፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር አሁን በማስተምርበት ዩኒቨርሲቲ መደበኝ፡፡ መሥሪያ ቤቱ ለሦስት ሳምንት ያህል ከመምህርነት ሥራ ውጪ የሆነ ሥልጠና ከሰጠን በኋላ በቀጥታ ወደ ማስተማር ሥራ አሰማራን፡፡ እኔም በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሥራ ዕድል እጥረት በመፍራት በማልፈልገው የሙያ ዘርፍ ለመቀጠል ተገደድኩ፤›› ይላሉ፡፡

መምህሩ የማስተማር ሥራ ሲጀምሩ በጣም ተቸግረው እንደነበርና ለዚህም ዋናው ምክንያት የመምህርነት ሙያ ሥልጠና አለመውሰዳቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህ ባለመሆኑ የመጀመርያ ተጎጂዎች ተማሪዎች እንደሆኑና በቂ የማስተማር ክህሎትና ዕውቀት በሌላቸው አስተማሪዎች የሚማሩ ተማሪዎች፣ የሚማሩትን የትምህርት መስክ ዓላማዎች በደንብ ይገነዘባሉ የሚል እምነት እንደሌለ በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡ መምህር አንተነህ ከላይ በተጠቀሱትና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው የምዘና ፈተና መመርያ ትክክለኛ ጊዜውን የጠበቀ አይደለም ይላሉ፡፡ ከመውጫ ፈተናው በፊት በዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማር የሚመደቡ ጀማሪ መምህራን ስለመምህርነት ሙያ ሥልጠና በመስጠት በቂ ፍላጎት፣ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ኅዳር 22 ቀን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ከመጪው 2011 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ምዘና ተግባራዊ መደረጉ እርግጥ መሆኑን በድጋሚ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በመግለጫው ላይ መሥሪያ ቤቱ የመውጫ ፈተናውን መመርያ ከመተግበሩ በፊት፣ የመመርያው ተግባራዊነትና ጠቀሜታ በሚመለከተው አካል ተጠንቷል ወይ? በትምህርት ማኅበረሰቡና ለባለ ድርሻ አካላት ላይስ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ተሠርቷል? የምዘና ፈተናውን የሚያወጣው አካልስ ምን ያህል ገለልተኛና ብቃቱ የተረጋገጠ ነው? በመመርያው መሠረት ምዘናውን የማያልፉ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆናል? እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች የሰጡት መልስ የለም፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው ምዘናው በብዙ አገሮች የተለመደና ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት በገለልተኛ አካል የተዘጋጀውን ምዘና ወስደው ብቃታቸውን የሚያረጋግጡበት አሠራር መሆኑን እንጂ፣ ምዘናው በወቅቱ በአገራችን ካለው የትምህርት አሰጣጥና ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ተገቢነቱ ምን ያህል እንደሆነ በመረጃ ለማረጋገጥ አልደፈሩም፡፡

በ2009 የትምህርት ዘመን መጨረሻ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የአራተኛ ዓመት የምህንድስና ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ ወደ ኢንዱስትሪዎች በሚወጡበት ጊዜ፣ በሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ (ሆሊስቲክ) ፈተና መውሰድ ላይ አለመስማማት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከ1,400 በላይ ተማሪዎች  ፈተናውን አንወስድም በማለታቸው፣ በዩኒቨርሲቲው ግፊት በፖሊስ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው አዲሱን የአጠቃላይ ፈተና የውጤት አሠራር በመተው ቀድሞ ወደ ነበረበት የምዘና ሥርዓት መመለሱን በመግለጽ፣ ተማሪዎች ወደ ግቢው ተመልሰው የመማር ማስተማሩ ሒደቱ እንዲቀጥል  አድርጓል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ዩኒቨርሲቲው አዲስ የምዘና አሠራር ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት፣ የምዘናውን አስፈላጊነት በተማሪዎች ዘንድ የግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ካለማሠራቱም በላይ ተማሪዎች ለምዘናው የሥነ ልቦናና የዕውቀት ዝግጅት እንዲያደርጉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል በመምህራን ካለመኖሩ በተጨማሪ፣ በአገሪቱ ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉም ተመመሳሳይና ወጥ የሆነ አሠራርም ሆነ የምዘና ሥልት እንደሌላቸው የሚያሳብቅ ነው፡፡

በያዝነው የትምህርት ዘመን የመውጫ ፈተናውን (Exit Exam) በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን በመግልጹ፣ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሒደቱን እንዳስተጓጎለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት እንኳን በአምቦ፣ በመቱ፣ በሐረማያና በወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች መመርያውን በመቃወም ትምህርት አቋርጠዋል፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሰቲዎች ውስጥ ያለውን ያለመረጋጋት ሁኔታ እንዳያባብሰው፣ የሚመለከተው አካል የወጣውን መመርያ አስፈላጊነት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ ባላድርሻ አካላት ላይ ግንዛቤ መፍጠር ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት አሰጣጥ ሒደትን እንዲኖር፣ ‹በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ዘንድ የትምህርት ቁሳቁሶች አቅርቦት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋማዊ አደርጃጀት፣ በተግባር የተደገፈና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት፣ ወዘተ. መሰል ለምዘናው አፈጻጸም እንቅፋት የሚሆኑ አሠራሮችን በቅድሚያ ማስተካከል  አስፈላጊ  ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸሻለ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በቀደሙት ዓመታት ከትምህርት ተደራሽነት አኳያ የነበረው ተሳትፎ ኢትዮጵያን ከዓለም ዝቅተኛ ደረጃ  ላይ ከሚገኙ አገሮች ተርታ አሠልፏት ቆይቷል፡፡ የነበሯት ትምህርት ቤቶችም በከተሞች ዙሪያ ያሉ ዜጎችን ያማከሉ፣ በፆታ ስብጥርም ቢሆን ሚዛናዊነት የጎደላቸው ነበሩ፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዛት 4,000፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህትር ቤቶች ቁጥር ደግሞ 278 ብቻ ነበሩ፡፡ አጠቃላይ የተማሪዎች ብዛትም ከሁለት ሚሊዮን አይበልጥም ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ከበፊቱ አንፃር ሲታይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ከ39 ሺሕ በላይ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ከ3,300 በላይ ደርሷል፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶችም በአጠቃላይ ከ27 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ማሰተናገድ እየተቻለ ነው የከፍተኛ ትምህርት  ማዘጋጃ በሆነው የመሰናዶ ትምህርት ፕሮግራም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ተገድቦ የቆየውን የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥርም አሁን 36 ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህ መረጃ  በአገሪቱ ያለው የትምህርት ሽፋን ጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡

ነገር ግን የትምህርት ሽፋንን  ከማስፋፋት እኩል የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት እየተደረገ አለመሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡ በዋነኛነት የመውጫ ፈተናውን ተግባራዊነት አጠራጣሪ የሚያደርገውም ይኸው በዩኒቨርሲቲዎችና በእያንዳንዱ የክፍል ደረጃ ያለው የትምህርት ጥራት አመርቂ ዉጤት አለማስመዝገቡ ነው፡፡ ‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ› እንዲሉ፣ ተማሪዎች ለ17 ዓመትና ከዚያ በላይ የክፍል ደረጃውን ይመጥናሉ ተብለው የመጡበትን ሒደት በአንድ ቀን የምዘና ፈተና ከማረጋገጥ ይልቅ፣ ከጅምሩ በየክፍል ደረጃው አግባብነት ያለው የትምህርት አሰጣጥና የምዘና ሒደት ላይ ጥልቅ የሆነ ፍተሻ በማድረግ ተማሪዎች በቂ ዕውቀት፣ ክህሎትና በራስ የመተማመን ችሎታ ይዘው እንዲዘልቁ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላየ ጌቴ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከተቀረፁ መርሐ ግብሮች ውስጥ የመውጫ ፈተና አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ፣ የዓመታት ትምህርትን ውጤትን በአንድ ቀን የመውጫ ፈተና መመዘን በየትኛውም ሁኔታ የትምህርት ጥራትን ሊያሻሽል እንደማይቻል ተገንዝቦ በእያንዳንዱ የክፍል ደረጃ ላይ ያለውን የትምህርት ጥራት በአንክሮ በመፈተሽ ችግሩን ከምንጩ  ማድረቅ ይቻላል፡፡ የትምህርት ጥራትን ከመሠረቱ ለማሻሻልም በመጀመርያ ለመማር ማስተማር ሒደት አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ተገቢ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ሕዝብን እወክላለሁ የሚል አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን በቪላ ቤትና በቅንጡ መኪና ዘመናዊ ሕይወት በሚኖርባት ደሃዋ አገር ኢትዮጵያ፣ በገጠር ለሚገኙ ተማሪዎች ለመማሪያ የሚሆን ደሳሳ ጎጆ እንኳን ባለመኖሩ ዛፍ ሥር ሲማሩ ከማየት በላይ ምን የሚያም ነገር አለ? እዚህ መዲናችንስ ቢሆን ተማሪዎች ያለ በቂ መማሪያ መጻሕፍት አቅርቦት የመጀመርያ ሴሚስተር ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ ምን ቀራቸው? በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የግል ትምህርት ቤቶች በኮምፐርሳቶ በተከፋፈሉ ትንንሽ የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ተማሪዎች ታግተው ሲማሩ፣ ዓይቶ ባላየ የሚያልፈው የትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ጥራትን እያሻሻልኩ ነው ቢል ታማኝነት የለውም፡፡

ከትምህርት ሚኒስቴር አፍንጫ ሥር እዚሁ በመዲናዋ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ታከው በቅርብ ርቀት ላይ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እየሠሩ የሚገኙ ጫት ቤቶች፣ የመጠጥ ቤቶችና የሺሻ ቤቶች በመማር ማስተማር ሒደት ላይም ሆነ በትምህርት ጥራት ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ መሥሪያ ቤቱ ሳይገነዘብ ቀርቶ ሳይሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ያለው ቁርጠኝነት በእጅጉ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በመማር ማስተማሩን ሒደት ላይ ምልከታ እንዲያደርጉ ወደ ትምህርት ቤቶች የሚልካቸው ባለሙያዎች በየትምህርት ቤቶች ያሉት የመማሪያ ክፍሎች ምን ያህል ምቹ ናቸው? ትምህር ቤቱ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎች በቂ የሆነ ቤተ መጻሕፍት፣ ላቦራቶሪ፣ የኮምፒውተር ክፍል፣ መፀዳጃ ቤትና መሰል ጉዳዮች ዝቅተኛውን መሥፈርት ማሟላታቸውን የመፈተሽና ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ የሚመለከተው አካልም መሥፈርቱን በማያሟሉ ትምህርተ ቤቶች ላይ የማዳግም ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ከትምህርት ቤቶች ጋር እጅና ጓንት ሆነው የትምህርት ጥራትን እያሰተጓጎሉ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸውን ባለሙያዎችም ላይ ተመጣጣኝ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

በእርግጥ ትምህርት ሚኒስቴር በመማር ማስተማር ሒደት ላይ ችግር የሚፈጥሩ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ሲወስድ አይስተዋልም፡፡ እንደ ማሳያም በ2009 ዓ.ም. በ12ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት የመግቢያ ፈተና ወረቀቱ ኃላፊነት በጎደላቸው የተቋሙ ሠራተኞች እጅ በመግባቱና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመለቀቁ ምክንያት፣ ፈተናው ተቋርጦ መራዘሙ ይታወሳል፡፡ ይህ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተከሰተ በመሆኑ በተማሪዎችና በወላጆች ላይ ድንጋጤን ከመፍጠሩም በላይ፣ የተማሪዎችን ሥነ ልቦና በመጉዳት በቀጣይ ለተዘጋጀው ፈተና በራስ የመተማመን ችሎታቸውን በመሸርሸር ውጤታማነታቸውን ቀንሷል፡፡ አንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸው ሠራተኞች የተፈጠረው ድርጊት በተማሪዎችና በወላጆች ላይ ከፈጠረው የሥነ ልቦና ቀውስ በተጨማሪ፣ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ፣ ለፈተና ወረቀቶች ዝግጅት፣ ለትራንስፖርትና መሰል ሥራዎችን ለማከናወን ሲባል አገሪቱን በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ አሳጥቷል፡፡

ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ግዙፍና አገር አቀፍ ስህተት የሠሩ አካላትን አጣርቶ ዕርምጃ አለመውሰዱ ነው፡፡ ካለፈው ስህተቱ የማይማረው ትምህርት ሚኒስቴር  በ2009 ዓ.ም በአማራ ክልል በተወሰኑ የፈተና ጣቢያዎች በ10ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋና በ12ኛ ክፍል የሥነ ዜጋና የታሪክ ትምህርት ፈተናዎች ላይ ታሪካዊ ስህተቶች  ተስተውለዋል፡፡ በአንድ የፈተና ጥራዝ ውስጥ የዓመተ ምሕረት፣ የፈተና መለያ ኮድ መለያየትና መዘበራረቅ፣ እንዲሁም የጥያቄ ተራ ቁጥር መዘለልና መደገም በዋነኛነት የሚጠቀሱ ስህተቶች ነበሩ፡፡ ከሁሉም በለይ አስቂኙ ነገር በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥነትና ፍፁም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ የሚዘጋጀው ፈተና፣ በተወሰኑ የአማራ ክልል የፈተና ጣቢያዎች ላይ ብቻ መከሰቱ መልስ አልባ ጥያቄ መሆኑ ነው፡፡

በወቅቱ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የአማራ ቴለቪዥን የአገር አቀፍ ትምህርትና የፈተናዎች ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያን በስልክ ጠይቆ ነበር፡፡ በባለሙያው ችግሩ መፈጠሩን አምነው የተከሰቱት ጥቃቅን ስህተቶች በመሆናቸው፣ በቀላሉ ተስተካክለው ይታረማሉ በማለት ችግሩን አድበስብሰው አልፈዋል፡፡ በአጠቃላይ በ2008 ዓ.ም. እና በ2009 ዓ.ም. ለተፈጠሩት ግዙፍ ስህተቶች በይፋ ይቅርታ የጠየቀም ሆነ ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም፡፡ ይህም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ተጠያቂ አልባ የሆነ አሠራር ምን ያህል የተንሰራፋና ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ መንገድ በአገር ሀብትና በተማሪዎች፣ በመምህራንና በወላጆች ሥነ ልቦና ላይ በአጠቃላይ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ እደፈለጉ ስህተት እየሠሩ ያለ ተጠያቂነት እስከ መቼ ይቀጥላሉ? የሚለው ጥያቄ የሚመለከተውን አካል ምላሽ ይሻል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡