Skip to main content
x
ሐሩር አስጣዩ የራስ ጃንጥላ

ሐሩር አስጣዩ የራስ ጃንጥላ

በአፋር መዲና ሰመራ በኅዳር መገባደጃ የተከበረው 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ልዩ ካደረጉት አንዱ፣ በስታዲየሙ ለተገኙት ታዳሚዎች የቀኑን ሐሩር ለመቋቋም የሚያስችላቸው ጃንጥላ መታደሉና የበዓሉ ማድመቂያ መሆኑ ነው፡፡ በራስ ላይ የሚጠለቀው ኮፍያ መሳይ ጃንጥላ በኢትዮጵያና በአፋር ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ተጊጧል፡፡ ፎቶዎቹ የስታዲሙን ታዳሚ ባንድ በኩል፣ በአፋር ባህላዊ ልብስ የተዋበችው ታዳጊዋን በሌላ በኩል ያሳያሉ፡፡

  • ፎቶ በታምራት ጌታቸው

***

‹‹ሳታመኻኝ ብላኝ››

አያ ዥቦ ልጁ ሞተበትና ለነ እንኮዬ አህዩትልጄ ሞቷልና አላቅሱኝሲል መርዶ ነጋሪ ላከ።

ተረጅዎቹምእንግዲህ ሰምተን ብንቀር ይጣላናል ብንሄድም ይበላናል። እንዴት ብናደርግ ይሻላል?” በማለት ምክር ዠመሩ። ነገር ግንቀርተን ከሚጣላን ሄደን ቢበላን ይሻላልብለው ተነስተው ልብሳቸውን አሸራርጠው ሄዱ።

ከለቅሶውም ቦታ እንደ ደረሱ አንደኛዋ ብድግ አለችና፣

ምን አጥንት ቢሆን ይሰብራል ጥርስዎ

ምን ጨለማ ቢሆን እሾኽ አይወጋዎ

ምን ጥቍር ቢበሉ ነጭ ነው ኩስዎ

ያንን ጐራ ዞሮ ይሰማል ድምጥዎ

አሁን የርስዎን ልጅ ምን አገኘብዎ?” እያለች ሙሾ ታወርድ ዠመር።

እሱ ደግሞ ቀበል አለና፣

አንችስ ደግ ብለሻል መልካም አልቅሰሻል

ይህ ሁሉ አዘንተኛ ምን ይብላ ብለሻል?” ሲል መለሰ።

እንዳልማራቸው ባወቁ ጊዜ እንግዲህ አለቀቀንም ምን ማድረግ ይሻለናል ብለው እነ እንኮዬ አህዩት ምክር ዠመሩ። አንዲት እናቷ የሞተችባት ውርንጭላ ከነርሱ ጋር ነበረችና ይህችን እንስጥና እንገላገል ብለው ሲነጋገሩ ግልገሏ አህያ ሰምታ፣

ምነው እኔ ውርንጫ

ይዞኝ በሩጫብላ ተነስታ እልም አለች።

ከዚህ በኋላ ጭንቅ ያዛቸውና መቼስ ምን ይደረግ ለንቦጫችንን ሰጥተነው እንሂድ ብለው ተማከሩ። ወዲያው በል እንግዲህ የላይ የላይ ለንቦጫችንን ውሰድ አሉት። እሱም እንዳመለከቱት ለንጨጭ ለንጨጫቸውን ገነጣጠለና ለቀቃቸው።

በሦስተኛው ቀን ደግሞ እስቲ ዛሬ ሣልስቱ ነውና እመቃብሩ ላይ ደርሰን አያ ዥቦን ጠይቀን እንምጣ ብለው ቢሄዱ አያ ዥቦ ቀድሞ ከመቃብሩ ላይ ሲያለቅስ ደረሱ።

አያ ዥቦም ድዳቸውን ገልፍጠው ባየ ጊዜ፣

ለካ የኔ ሐዘን ለናንተ ሰርግና ምላሽ ሆኖላችኋልና የኔ ልጅ ትላንትና ሞቶ ዛሬ እናንተ እየተሳሳቃችሁ የመጣችሁት በምን ምክንያት ነው?” ብሎ ተቆጣና ለወገኖቹኧረ በሉ አንድ አንድዋን እየዘረጠጣችሁ ጣሉልኝአላቸው።

ከዚህ በኋላ የዥብ ወገን ያህያን ልጅ እየገነጣጠለ ጣለ ይባላል።

አያ ዥቦ ሳታመኻኝ ብላኝ

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደመስቀል  ‹‹እንቅልፍ ለምኔ›› (1952 )

‹‹ሳታመኻኝ ብላኝ››

***

ኢትዮጵያዊ ነኝ!

ኢትዮጵያዊ ነኝ!
በላሊበላ አስቀድሼ፣ ሸህ ሁሴን ባሌ የተገኘሁ፤
በአባ ገዳ ተመራርቄ፣ መካ ላይ እርስቅ ያገኘሁ፡፡
ይርጋለም ያጋጥኳትን ላም፣ ወለጋ ላይ አሰርሬ፤
ትኩስ እንገርዋን የጠጣሁ፣ አክሱም ላይ ጥገት አስሬ፤
ሰሜን ያለብኩትን ወተት፣ በአርሲ ጮጮ የሞላሁ፤
ጋምቤላ ወተቱን ንጬ፣ የሀረሪ ቆንጆ የቀባሁ፡፡
ወሰን የለሽ እግረ ፌንጣ፣
ሞተ ሲሉኝ ብን - ትር የምል፣ ሄደ ሲሉኝ የምመጣ፤
የቅዠት ምች፣ ህልም ፈቺ . . . ዳነ ሲሉኝ የማገረሽ፤
ወሰን አልባ እግረ ሞረሽ፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ!!

  • በድሉ ዋቅጅራ

***

ሰው እንዴት ነው?

ውብ ድምፅ ያላቸው ወፎች በረሃ ሃገራቸው ነው፡፡ ቃና ባለው ዜማ ከተዋበ ድምፃቸው ጋራ ሲዘምሩ ግን በረሃውን ገነት ያደርጉታል፡፡ እንዳዘነም ልብ የነበረውን ምድረ በዳ የገነት ያህል ሊለውጡት ችሎታ ሲኖራቸው አዳኞች አይተዋል፡፡ እንዲሁም የላባው ውበት ሊያኮራው የሚችል የቁራ አሞራ ደግሞ በዜማውና በድምፁ ክፋት እንደገነት ያማረችውን አገር በረሃ ያደርጋታል፡፡

ሰውም በሚኖርበት ርስቱ ላይ እንዲሁ ነው፡፡ የተዋጣ ቅያስ ባላቸው መንገዶች መጓዝ አይታው ሁሉ ደስ ያሰኘዋል፡፡ አበቦችም በተተከሉበት ቦታ መጠለል አዲስ ስሜትና ዕረፍት ይሰጠዋል፡፡ ቅርፁ እጅግ አምሮ በታነፀ ቤት መኖርም ይመቸዋል፡፡ በሰገነት መቀመጥም እጅግ ክብር ያለው ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ነገር ግን የነፍስን አሥራው በማንቀሳቀስ ሰውን ደስ ሊያሰኘው የሚችል ጣዕም ያለው ሙዚቃና ባህል ያለው ዘፈን ባይኖር የማንኛውም የሚታይ ውበት ሁሉ ግምቱ አባይ ይሆናል፡፡

ተመስገን ገብሬ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› (ኅዳር 1935)

*****

ማንነትን ፍለጋ

‹‹ኢትዮጵያ በዌስት ኢንዲስ ሥነ ጽሑፍ›› በሚለው የገዛኸኝ ጌታቸው መጣጥፍ ውስጥ

እንደተገለጸውዌስት ኢንዲያንስ ምንጫቸው አፍሪካ እንደሆነች ያምናሉ፡፡ የማንነታቸው መገኛ እንደምትሆንም ይገምታሉ፡፡ በአ.አርዳቶርኔ መጽሐፍ ‹‹The scholar Man›› ውስጥ ያለው የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ አዳም ኩየስተስ የማንነቱን ጉዳይ አንስቶ ሲናገር ‹‹የራሴ ታሪክ ኖሮኝ  እንዳደገ ሰው ስለራሴ ምንም ነገር አላውቅም፡፡ የማውቀው ያልሆንኩትን ብቻ ነው፡፡ እንግሊዛዊ አይደለሁም እንደምገምተው እንዲያውም ዌስት ኢንዲያንም አይደለሁም›› ይላል፡፡ ትግሉ ማን እንደሆነ ለማወቅ ነው፡፡

በዚህ የማንነት ፍለጋ ውስጥ ነው አፍሪካ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የማንነታቸው ተምሳሌት ሆና በየድርሰቶቻቸው ውስጥ የምትገለፀው፡፡ በሲልቪያ ዋይንተር በተጻፈው ‹‹The Hills of Hebron›› በሚለው ድርሰት ውስጥ ፀጉሩ የተንዠረገገውና ፂማሙ ራስታ ሲታሠር በፖሊስ መኪና ፊት ተንበርክኮ በጥልቅ ስሜት፤

ኢትዮጵያ ንቂ የልጆችሽንም ጩኸት አድምጪ

ኢትዮጵያ ዛሬ ነፃ ናት፤ የኛም ለቅሶ በምድሪቱ ያስተጋባል

ኢትዮጵያ ንቂ፣ ንጋታችን በእጃችን ናትና፡፡ እያለ ይዘምራል፡፡