Skip to main content
x
የፌዴሬሽኑ የምርጫ ጊዜ ዳግመኛ ተራዘመ
አቶ ዘሪሁን መኰንን የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ

የፌዴሬሽኑ የምርጫ ጊዜ ዳግመኛ ተራዘመ

  • የሥራ አስፈጻሚ ምርጫው ‹‹ውክልና›› ወይስ ‹‹ምርጫ›› የሚለው ጉባዔው እንዲወስን ተላልፏል

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሁን ያለው አመራር የአገልግሎት ዘመኑን ካጠናቀቀ ወራት አስቆጥሯል፡፡ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከምርጫ ሥርዓት ጋር አያይዞ ለፌዴሬሽኑ ያስተላለፈውን የምርጫ ሥነ ምግባር ኮድ ተከትሎ ምርጫው ተራዝሞ ሒደቱን የሚከታተልና የሚያስፈጽም አስመራጭ ኮሚቴ እንዲሰየም መደረጉ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ መሠረት ታኅሣሥ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡

ከዕጩ ተወዳዳሪዎች ግለ ታሪክ ጀምሮ የምርጫውን አጠቃላይ ዝርዝር ጉዳይ እንዲከታተልና እንዲያስፈጽም በጉባዔው የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ እንዳስታወቀው፣ ምርጫው ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲሆን የተወሰነው በፈረንጆቹ ገና ምክንያት ነው፡፡

አስመራጭ ኮሚቴ ጉባዔው ከሰጠው ኃላፊነት አኳያ ብቻም ሳይሆን ከደንብና መመርያ አንፃር ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዳላደረገ እየተተቸ ይገኛል፡፡ ዓርብ ታኅሣሥ 6 ቀን በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የዕቅድ ክንውኑን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ ኮሚቴው በኃላፊነት የተሰጠውን ሥራ ያከናወነው ከመርሕ ይልቅ በመቻቻልና በእጅ ብልጫ እንደነበርም አስረድቷል፡፡

በብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ በፊፋ እንዲሁም ጉዳዩ በአንድም ሆነ በሌላ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ምርጫን ጨምሮ መሰል ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የሚጠቀሟቸው አሠራሮች እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመነሳት በምርጫ ሳይሆን በውክልና የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ያደረገው ጥረት ደንብና መመርያዎችን መሠረት አድርጎ ከመሄድ ይልቅ ድምፅ ብልጫን እንደ አማራጭ መውሰዱ ተገቢ እንዳልሆነ የሚተቹ አሉ፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው ተነጋግሮ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ከሚጠበቅበት ድርሻ መካከል ክልሎች ለፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ ዕጩ አድርገው ያቀረቧቸው ተወዳዳሪዎች ወደ አመራር ሲመጡ መሥፈርቱ ‹‹ውክልና›› ወይስ ‹‹ምርጫ›› የሚለውን የመለየትና የማጥራት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ያሳለፈው ውሳኔ ግን ‹‹ጉባዔው ይወስን›› የሚል መሆኑ ታውቋል፡፡