Skip to main content
x

‹‹ይበልታ›› ሊቸረው የሚገባ ሕዝባዊ ባንክ

በታገል ጎበዜ

ሰው ከእንስሳት የሚለየው ‹‹ባለ አዕምሮ›› በመሆኑ ነው፡፡ አዕምሮውን ተጠቅሞ በአካባቢው የሚፈጠሩ ነገሮችን ማየትና ማመዛዘን ይችላል፡፡ አንድ ነገር ሲጠፋ፣ ሲባላሽ እያዩ በሆድ ውስጥ ብቻ አምቆ ይዞ ከማማትና ከመተማማት ይልቅ የሚያዩዋቸውንና የሚታዘቧቸውን ጉድለቶችን ህፀፆች፣ ድክመቶችና አጓጉል ክንዋኔዎች እንዲታረሙ መናገር፣ መጮህ፣ መዘገብና ማሳሰብ ከሰው ይጠበቃል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በጥሩ ሁኔታ የተከናወኑ ሥራዎች ሲታዩ፣ መልካም አስተዳደር ሲሰፍንና የመሻሻል ዕርምጃዎች ሲንፀባረቁ ሠሪዎቹንና አድራጊዎቹን ማበረታታትና ማመሥገን፣  ውጤቶቻቸውም ለሌሎች መማሪያ እንዲሆኑ በይፋ መግለጽና ማሳወቅ በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ሆኖም በአገራችን ብዙ ሰዎች ጥፋታቸው ወይም ድክመታቸው ሲነገራቸው ‹‹ነቀፌታ›› ብቻ አድርገው የሚመለከቱት ቢሆንም፣ ቁም ነገሩ ለበጎና ለመተራረም እስከሆነ ድረስ ወደኋላ ማለት አይገባም፡፡

በአንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ 23ኛ መደበኛና 20ኛ ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ጸሐፊው ተገኝቶ በጠቅላላ ጉባዔው አካሄድና በተለይም በዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ ላይ ያስተዋላቸውን ድክመቶችና ህፀፆች ‹‹ሆድ ይፍጀው›› ብሎ ሳያደፍጥ በይመለከተኛልና በያገባኛል ስሜት፣ በዚሁ ሪፖርተር ጋዜጣ በልናገር ዓምድ ላይ ረቡዕ ኅዳር 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ዕትም አመለካከቱን ገልጿል፡፡ የጽሑፉ ዓላማ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ስህተቶቹንና ግድፈቶቹን ከድርጅት መልካም አስተዳደር አንፃር አይተው፣ መርምረውና ተረድተው ስህተቶችንና ጉድለጎችን እንዲያርሟቸውና እንዲያስተካክሏቸው በቅን ልቦና የተደረገ ማሳሰቢያ ነበር፡፡

እንደገና ደግሞ ጸሐፊው ኅዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በእናት ባንክ 4ኛ መደበኛ   የባለአክሲዮኖች  ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝቶ የጉባዔውን ሒደትና  የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ምርጫ እንደታዘበው፣ ሕግንና ደንብን ተከትሎ በጥራት የተከናወነ በመሆኑ  ‹‹ይበልታውን›› በጋለ ስሜት ለመግለጽ ይወዳል፡፡ ‹‹ይበልታ›› የሚለው ከሥረ ቃሉ  ከበል፣ ልበል፣ ይበል ይወጣል፡፡ በአገራቸን ደስ የሚያሰኝ ‹‹ማለፊያ ቅኔ›› በተነገረ ጊዜ  አድማጩ ‹‹ይበል!››፣ ‹‹ይበል!›› በማለት የቅኔውን መልካምነት በማረጋገጥ ይሁንታውንና ደስታውን ለተቀኝው እንደሚገልጽ ሁሉ ጸሐፊው ለእናት ባንክም  ‹‹ይበልታ›› ችሮታል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው ቀን የተካሄደው የጉባዔ ክንዋኔ በመልካም አኳኋን የተፈጸ በመሆኑ ‹‹ይሁን፣ በርቱ፣ ቀጥሉበት…›› በማለት ባንኩ እንዲበረታታ፣ በአብነትነቱም ሌሎች እንዲጠቀሙበት ለማሳሰብ ነው፡፡

ጸሐፊው ለመታዘብ ዕድል ባገኘባቸው ሁለት ኩባንያዎች ጉባዔዎች መካከል አትኩሮት ሊቸራቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመርያው ነገር አንዱ ኩባንያ ዕድሜ ጠገብ ሆኖ ለ23ኛ ዓመት ዘንድሮ ጉባዔውን ያካሄደ ነው፡፡ በቀዳሚው ጽሑፍ ላይ እንደተመለከተው ከአጀማመሩና ከዕድሜው አንፃር እያደር የግል ጥቅመኝነት ችግር  በኩባንያው ‹‹የድርጅት አመራር (corporate governance)›› ላይ ለመንሰራፋቱና    የአክሲዮን ባለቤትነት መሠረቱም ሆነ የካፒታል ዕድገቱ ከተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች መዳፍ ያልተላቀቀ መምሰሉ ነው፡፡

ሁለተኛው ኩባንያ ደግሞ ዘንድሮ ገና 4ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደ፣ ታዳጊና በአመራሩ ላይ የግል ጥቅመኝነት ችግር ያልተጠናወተውና በአመሠራረቱም  ‹‹እናትነትን›› ማዕከል ያደረገና ‹‹አካታች (inclusive)›› የሆነ የባንክ አገልግሎት  በአገሪቱ ውስጥ የሚያስፋፋ፣ በተለይም ሴቶች ወገኖቻችንን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን በጎ ዓላማ ያነገበ፣ የሁሉንም የባለድርሻ አካላት ጥቅም በቅን ልቦናና በታማኝነት ለማስቀደም የሚጥር፣ ብሎም በባንክ አገልግሎት የበኩሉን ኢኮኖሚያዊ አስተዋጸኦ በግምባር ቀደምትነት ለማበርከት የተነሳሳ መሆኑ ነው፡፡

የንግድ ሕጉና ‹‹የመድንና የባንክ ሥራን ለመደንገግ የወጡት አዋጆች››   እንደሚገልጹት የመድንና የባንክ አገልግሎቶች የሚቋቋሙት በአክሲዮን ማኅበርነት ብቻ ነው፡፡ በግልና በሌሎች የንግድ ማኅበራት ዓይነት ሊቋቋሙ አይችሉም፡፡ ከሕግጋቱ ዓላማዎች መካከል መሠረታዊ ነው ሊባል የሚችለው፣ ኩባንያዎቹ ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖራቸውና በተቻለ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአቅሙ የአክሲዮን ባለቤት እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ዓላማ አንፃር እናት ባንክ የአክሲዮን ባለቤትነት መሠረቱን ያሰፋና እያሰፋም የሚሄድ ሲሆን፣ 4ኛ ጉባዔው ድረስ 14.000 (አሥራ አራት ሺሕ) ኢትዮጵያንን የአክሲዮኖች ባለቤቶች አድርጓል፡፡ በሥራ እንቅስቃሴውም እስካሁን ድረስ በጸሐፊው ግንዛቤ ‹‹ከመላሾ›› ፅዱ ነው ቢባል ስህተት አይመስለውም፡፡ ‹‹መላሾ›› ሥረ ቃሉ መላስ፣ ‹‹ስኳር መላስ፣ ወይም ሌላውን ለማባባል ማላስ››  እንዲሉ፡፡

‹‹ካፒታል›› በስፋት እንዲሰባሰብና በሥራ ላይም እንዲውል፣ ብሎም የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ፣ እንዲዳብርና የሥራ ዕድልም እንዲፈጠር መሠረተ ብዙ የአክሲዮን ማኅበራትን ማቋቋም ወሳኝ ነው፡፡ ይህንንም ለማበረታታት የበለፀጉትና ወጤ ኢኮኖሚዎች (Developed and Emerging Economies)፣ እንዲሁም በማደግ ላይ ያሉት ጭምር ከሚጠቀሙባቸው ሥልቶች መካከል አንዱ ‹‹የአክሲዮን ልውውጥ ገበያ (Stock Exchange Market)›› እንደሆነ ይታወቃል፡፡

‹‹የአክሲዮን ልውውጥ ገበያ (Stock Exchange Market)›› በአገራችን የሌለና በቅርቡም ይኖራል ብሎ ለመገመት ይቸግራል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በአገሪቱ ውስጥ የተቋቋሙት የገንዘብ ደርጅቶችም ሆኑ ሌሎች ዓይነቶች የአክሲዮን ማኅበራትም ቢሆኑ፣  በመሥራቾች የእርስ በርስ ዕውቅና፣ በአገርና በወንዝ ልጅነት፣ እንዲሁም በሌሎች የመሳሳቢያ ግንኙነቶች የተጠራቀመ ካፒታል መሆኑ አይስተባበልም፡፡ የአክሲዮን ማኅበራቱ ካፒታል ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያድግም ሕዝብ እንዲሳተፍባቸው ክፍት የሚደረጉ ሳይሆን፣ እንዳመሠራረታቸው በውስጥ ለውስጥ ካሉት ባለአክሲዮኖች መዳፍ አይወጣም፡፡  በቅርቡ ትውልደ ኢትዮጵያን ከሆኑ የውጭ አገር ዜጎች ላይ ብሔራዊ ባንክ ያስመለሳቸው የባንክና የመድን ኩባንያዎች አክሲዮኖች ለጨረታ ሲቀርቡ፣ ከመደበኛ ዋጋቸው በላይ እጅግ በናረ ዋጋ ለመግዛት ሕዝብ ያደረገው መረባረብ ስለአገሪቱ የአክሲዮን ልውውጥ ፍላጎት ሰሚ ቢገኝ ጸሐፊው የማንቂያ ደወል ነው ይላል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ዕድሜ ጠገቡ ኩባንያ ሰፊ የባለአክሲዮን መሠረት አለው ብሎ ለመናገር ጸሐፊው አይደፍርም፡፡ ምክንያቱም እ.ኤ.አ. ኅዳር 30 ቀን 2017 በኩባንያው ድረ ገጽ ላእንደተጻፈው፣ ኩባንያው በሥራ ላይ በቆየባቸው ባለፉት 23 ዓመታት ውስጥ የባለአክሲዮኖቹ ብዛት ያደገው ሲጀመር ከነበረው 26 ወደ 124 ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በኩባንያው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ባለአክሲዮኖች የበዙበት፡፡ የኩባንያው ካፒታል ከጊዜ ወደጊዜ ሲያድግም፣ ባለፈው ጸሑፍ ላይ እንደተገለጸው በተመጣጥኖ (proportionately) ክፍፍል በአንበሳው ድርሻ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ባለአክሲዮኖች እንደፋፉበት ከዚህ በላይ ማስረጃ አይገኝም፡፡

ሁለተኛው የሚጠቀስ ነገር ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ባለፈው ዓመት (2009 ..)  የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ ግልጽነትን የተላበሰ እንዲሆንና ለመልካም አስተዳደር ዋነኛ መርሆችም አጽንኦት ለመስጠት ስለምርጫ ጥቆማና አሠራር የወጣው ደንብ፣ ‹‹በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጠቅላላው የተፈረመ ካፒታል ውስጥ ሁለት በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሆነውን ድርሻ የያዘን ሰው ወይም ደርጅት ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮን (Influencial shareholder)››፣ እንዲሁም ‹‹በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከጠቅላላው የተፈረመ ካፒታል ከሁለት በመቶ ወይም ከዚያ በታች አክሲዮን የያዘን ሰው ወይም ደርጅት ተፅዕኖ ፈጣሪ ያልሆነ ባለአክሲዮን (Non-influencial shareholder›› በማለት ባለአክሲዮኖችን በሁለት ጎራ የሚከፍል ሲሆን፣ በእናት ባንክ ውስጥ ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች የሌሉበትና ሁሉም የባንኩ ባለአክሲዮኖች በአንድ መደብ ሥር የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡

 በተቆጣጣሪው ባለሥልጣን መመርያ መሠረት ተፅዕኖ ፈጣሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ ያልሆኑ ባለአክሲዮኖች ባሉበት ደርጅት ውስጥ ሁለቱ ምድቦች ድምፅ የሚሰጡት  በተለያዩ ሁለት ድምፅ መስጫ ሳጥኖች ለየብቻቸው ነው፡፡ በእናት ባንክ የዳይሬክተሮች ለቦርድ አባልነት በባለአክሲዮኖች የተጠቆሙት ሃያ ሁለት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ድምፅ የተሰጣቸው በአንድ የምርጨ ሳጥን ሳይከፋፈሉ ነው፡፡

የምርጫ አስፈጻሚ ሆኖ ኃላፊነቱን የተቀበለው የዚሁ ባንክ አስመራጭ ኮሚቴ በባለአክሲዮኖች ከተጠቆሙት ከመቶ በላይ ዕጩዎች መካከል የምርጫ ደንቡ በሚያዘው መሠረት፣ እያንዳንዱን ለመመረጥና ባንኩን ለማገልግል ፈቃደኛ የሆነን ባለአክሲዮን ዕጩ ተጠቋሚ በትምህርት ዝግጅቱና በሥራ ልምዱ በማመዛዘን፣ የባንኩን ጥቅሞች ከሁሉም ተጠቋሚዎች በበለጠ ይሰጣሉ፡፡ የባንኩንም ሥራ ሊመሩና ሊቆጣጠሩ  ይችላሉ፡፡  እንዲሁም የመሪነት ብቃት አላቸው ብሎ አስመራጭ ኮሚቴው ያመነባቸውን 22 ዕጩዎች የእያንዳንዳን ዕጩ ስም፣ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የምዘና ውጤትና  የሥራ ልምድ የያዘ ሰንጠረዥ ለጉባዔተኛው ከተበተነ በኋላ ኮሚቴው ሊቀመንበር ዝርዝር ሪፖርታቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡  

የተጠቆሙት ዕጩዎችም በመድረክ ላይ ወጥተው በጉባዔተኛው በይፋ እንዲታዩ ሲደረግ፣ የቀረቡት 21 ዕጩዎች ብቻ በመሆናቸውና አንድ ዕጩ ተደጋግመው ቢጠሩም ስላልቀረቡ ኮሚቴው በተጠባባቂነት ከያዛቸው መካከል በደረጃ የሚመጥኑትን አንድ ዕጩ  ወዲያውኑ እንዲተኩ አድርጎ፣ 22ቱ ዕጩዎች ስለየራሳቸው ለጉባዔተኛው አጭር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ አካሄድ መሠረት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ያወጣውን የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ደንብ የአስመራጭ ኮሚቴው በአግባቡ በሥራ ላይ አውሎ፣ ግልጽነትን በተላበሰና ለድርጅት መልካም አስተዳደር (Corporate Governance) ዋነኛ መርሆች አጽንኦት በመስጠት ምርጫው በመከናወኑ፣ ሁሉም ባለአክሲዮኖች ‹‹ይበልታቸውን›› በደማቅ ጭብጨባ አረጋግጠዋል፡፡

ከዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት ምርጫ በፊት የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔው በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ተወያይቶ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡ ጉባዔተኛው እንዲወያይባቸው በቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በሁለቱም ኩባንያዎች መካከል ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን በውይይቱ አመራርና ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የጎላ ልዩነት ጸሐፊው ተገንዝቧል፡፡ ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን በሁለቱም ኩበንያዎች ጉባዔዎች ላይ የራሱን ተወካይ በታዛቢነት የላከ ስለሆነ የተሟላ ሪፖርት እንደሚቀርብለት አይካድም፡፡ የእናት ባንክ የጉባዔ ሒደት ግን በሥርዓት ስለመከናወኑ ጸሐፊው የበኩሉን ምስክርነት ይሰጣል፡፡

የጉባዔ ተሳታፊ ቁጥር ብዛት ያለውና ድምፅ ለመቁጠርም አስቸጋሪ ሲሆን፣ ጊዜ ለመቆጠብ ሲባል ጉባዔተኛው ውሳኔዎችን ለመቀበሉ እጅ በማውጣት ወይም በማጨብጨብ እንዲገልጽ መጠየቅ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በዚያ ሁኔታ የተካሄደ  ውሳኔ ፍፁማዊ እንደሆነ ለመቁጠር ያስቸግራል፡፡ የድምፅ አሰጣጡን ሕጋዊነት ለመጠበቅ የጉባዔው ሰብሳቢ በጭብጨባም ሆነ እጅ በማውጣት በተሰጠው ውሳኔ ላይ ተቃውሞ ወይም ድምፀ ተዓቅቦ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ጉባዔተኛውን መጠየቅና ከተገኘም እንዲመዝገብ፣ ካልተገኘም አለመኖሩ ታውቆ እንዲመዘገብ ማድረግ  ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም እጁን ያላወጣ ወይም ያላጨበጨበን ሰው እንደተስማማ መቁጠር አይቻልም፡፡ የውሳኔ ተቃዋሚ ወይም ድምፀ ተዓቅቦ ስለመኖሩ መጠየቅና መመዝገብ ሊነሳ የሚችለውን የቅራኔ ክፍተት ይዘጋል፡፡

የእናት ባንክ 4ኛ መደበኛ ጉባዔ የውሳኔዎች አሰጣጥና በመጨረሻም የዕለቱ ቃለ ጉባዔ በንባብ መደመጥ የጉባዔውን በአግባቡ መመራት የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ጸሐፊውን በእጅጉ ደስ አሰኝቶታል፡፡ ስለዚህ ለዚህ ታዳጊ ባንክ ‹‹ይበልታ›› ያንሰዋልን?  ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡