Skip to main content
x

‹‹የዓባይ ውኃ ሙግት›› መንስኤና መፍትሔው

በኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ

እ.ኤ.አ. በማርች (መጋቢት) ወር 2015  ካርቱም ከተማ አስር አንቀጾች ያካተተ “የመርህ መግለጫ” በመባል የሚጠራ ስምምነት በኢትዮጵያ በሱዳንና በግብፅ መሪዎች ተፈረመ፡፡ ይህ ስምምነት በቀጥታም ሆነ በሌላ መንገድ ከዚህ በፊት የተደረገውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አይጠቅስም፡፡ የተሐድሶ ግድብ በመገንባቱ የተነሳ በግርጌ በሚገኙት ሱዳንና ግብፅ ላይ ተጽዕኖ ያስከትል እንደሆነ በገለልተኛ የፈረንሳይ ሁለት ኩባንያዎች የሚቀርበውን የጥናት ውጤት ሦስቱ አገሮች በመርህ መግለጫ ስምምነታቸው ለማክበር ቃል ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም የተሐድሶ ግድብ በውኃ የሚሞላበት ሒደትና ዕቅድ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡

በቅርቡ ቢአርኤል (BRL) የተባለ የፈረንሳይ ኩባንያ ባቀረበው የመግቢያ ሪፖርት ላይ መግባባት አልተገኘም በሚል ምክንያት ግብፅ በቴክኒኩ ድርድር ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆኗን በመግለጿ ጉዳዩ መውጫ አጥቶ ይገኛል፡፡ 

ባለፈው ኅዳር ወር የግብፅ መሪ ጄኔራል ሲሲ በአንድ ቀይ ባሕር ዳርቻ መዝናኛ ጣቢያ ባሰሙት ንግግር “የኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና ወዳጆቻችን የልማት ፍላጎት በቀና መንፈስ እንመለከታለን፡፡ የአገራችንን ብሔራዊ ደኅንነት ለመጠበቅ አቅምና ችሎታው አለን፡፡ ውኃ ደግሞ ለእኛ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው፡፡ አራት ነጥብ” ብለዋል፡፡

 

በዚህ ዓመት ብቻ የግብፅ መሪ ሱዳንን፣ ታንዛኒያንና ሩዋንዳን እየተዘዋወሩ በመጎብኘት የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሥራው እንዲቋረጥ የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ እንዳደረጉ ይነገራል፡፡ ታንዛኒያና ሩዋንዳ የትብብር ማዕቀፉን ስምምነት በፓርላማቸው ያጸደቁ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡

በዚህ ሳምንት ደግሞ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰሜህ ሹክሬ አዲስ አበባ ተገኝቶ የግብፅ ምድር 96 በመቶው በረሃ ነውና በሕዳሴው ግድብ ምክንያት የዓባይ ውኃ ሳይቋረጥ መድረሱ የአገሩ ደኅንነት ቁልፍ መሆኑን አሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለግብፅ ጥቅም እንጂ ምንም ጉልህ ጉዳት እንደማያስከትልባት አስምራለች፡፡ ለማንኛቸውም ስለ ግድቡ የሚቀርበው ማናቸውም ሐሳብ ንግግር የሚደረግበት በሁለትዮሽ ሳይሆን በስምምነታችን መሠረት የሱዳንም መገኘት ማስፈለጉን የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ገልጿል፡፡

እንደሚታየው የዓባይ ውኃ ሙግት ዛሬም ፍጻሜው እየራቀ ነው@ ውጥረቱን በቅርብ መከታተል ከጀመርኩ አያሌ ጊዜ መሆኑን ከዚህ በታች ባጭሩ ለማስታወስ እሞክራለሁ::

የዛሬ ሃምሳ ዓመት ገደማ ነበር በፓሪስ ዩኒቨርስቲ ሶርቦን የሕግ ትምህርቴን ካገባደድኩ በኋላ “የዓባይ ውኃ አከፋፈል መዛነፍ” በሚል አርዕስት የዶክተሬት ቲዝስ ለመጻፍ የተነሳሳሁት፡፡ በዚያን ዘመን፣ እንዳሁኑ ኢንተርኔትና ጉግል ስላልነበሩ፣ ያሰብኩትን እቅድ በሚገባ ለመቀጠል የሚቀለው፣ ጉዳዩ የሚያገባቸው አንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚገኙትን ሰነዶች መፈላለግና መመርመር ያስፈልግ ነበር፡፡ ከፓሪስ ሌላ ሮም፣ ካይሮ፣ ለንደን እና አዲስ አበባም ጭምር መዘዋወር ስለሚጠይቅ፣ ይህን ለመፈጸም ግን፣ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ መንግሥት የተመደበልኝ የስኮላርሺፕ ዕርዳታ በቂ አልነበረም፡፡ ይህንኑ በመረዳት በቅድሚያ አዲስ አበባ ለተወሰነ ጊዜ ተመልሼ፣ የዓባይ ውኃ ጉዳይ የአገር ጉዳይ በመሆኑ፣ ጥናቱን ፍጻሜ ለማድረስ የገጠመኝን የገንዘብ እጥረት ለትምህርት ሚኒስቴር አስረድቼ ስኮላርሺፔን እንዲያስተካክልልኝ መጠየቅ አንዱ አማራጭ ነበር፡፡

በዚሁ ጉብኝት ሳቢያ፣ ስለ ዓባይ የሕግ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አቅዋም ምን እንደሆነና ይህንኑ የሚደግፉ ጽሑፎችና ጥናቶች ወይንም ሌሎች ጠቃሚ ሰነዶች ለሥራዬ ስለሚረዱኝ እንድመለከታቸውና በማስታወሻ ለመያዝ እንዲፈቀድልኝ ለመጠየቅም ጭምር አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል በሚል እምነት ነበር ጉዞዬን ያቀድኩት፡፡

ለዚህ ሁሉ፣ የባለሥልጣኖቹን ውሳኔ መተማመኛ ሊሆን ይችላል በማለት፣ የቲዝሱን ዝግጅት በቅርብ ይመሩ የነበሩትን ታዋቂ የኢንተርናሽናል ሕግ ሊቅ፣ ፕሮፌሰር ሻርል ሩሶን በጠየቅኋቸው መሠረት ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርብ የድጋፍ ደብዳቤ ጽፈውልኝ እስከ ዛሬ ዋናው ከእኔ ዘንድ ይገኛል፡፡

እ.ኤ.አ በጃንዋሪ (ጥር) ወር 1964 አዲስ አበባ እንደደረስኩ ሳልዘገይ ትምህርት ሚኒስቴር ስኮላርሺፕ ክፍል ቀርቤ ጉዳዩን ባመለከትኩ ጊዜ፣ ትምህርታቸውን አገባደው የተመለሱ ሌሎች ተማሪዎች ስላሉ፣ ከነሱ ጋር አብረህ ቀርበህ ጉዳይህን በቀጥታ ለግርማዊነታቸው ማቅረቡ ይበጃል የሚል መልስ አገኘሁ፡፡

እንደተባለውም ሳምንት ሳይቆይ፣ በትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ክፍለእግዚ አቅራቢነት ሃያ የማንሞላ ተማሪዎች ንጉሠ ነገሥቱ ፊት ቀርበን፣ ከመካከላችን ልዩ ጉዳይ ያላቸው አቤቱታቸውን በየተራ ለማቅረብ እንደሚችሉ ስለ ተነገረን፣ ለጊዜው ሁሉን በሚገባ ባላስታውስም፣ አንዳንዶቹ ችግራቸውን አሰምተው ውሳኔ ወዲያውኑ እንዳገኙ ነበር፡፡ በተለይ የማይረሳኝ በቅርብ የማውቀው የአንዱ ተማሪ አቤቱታ ነበር፡፡ የተባለው ወጣት በትምህርት ገበታ ላይ በነበረበት ጊዜ የውጭ አገር ሴት አግብቶ፣ በአቅም ማነስ ምክንያት እዚያው ትቷት ስለመጣ የአውሮፕላን ትኬት እንዲታዘዝለት ጠይቆ ወዲያውኑ እንደቀናው ትዝ ይለኛል፡፡

የኔ ተራ ሲደርስ፣ እቅዴን ንጉሡ በትክክል እንዲረዱልኝ በማሰብ፣ በዓባይ ወንዝ ግርጌ የሚገኙት ግብፅና ሱዳን፣ የወንዙን ውኃ ሙሉ በሙሉ ሁለቱ በመከፋፈል የሌሎቹን ተጋሪ አገሮች በተለይም ዋናዋ የወንዙ መጋቢ የሆነችውን ኢትዮጵያን በድርድሩ እንድትካፈል ሳይጠይቁ፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ኖቬምበር (ኅዳር) 8 ቀን 1959 የፈረሙት ስምምነት፣ ሚዛናዊነት እንደሚጎድለው በማስታወስ አገራችን በውኃው ሀብት ላይ ያላትን መብት በሕግ አንጻር የሚደግፍ ጥናት ለማቅረብ ያለኝን እቅድ እያወሳሁ ሳለ፣ ንጉሡ በቢሮአቸው ጠረጴዛ ላይ የነበረ አልበም ይሁን ሌላ ሰነድ ማገላበጥ ሲጀምሩ ተመለከትኩ፡፡ ትኩረታቸውን ለማሳብ ንግግሬን አቋረጥኩ፡፡ ቀና ብለው ካዩኝ በኋላ “ቀጥል” የሚል ትዕዛዛዛቸውን ሰማሁ፣ ድምፄን አጉልቼ ጉዳዩን እንደገና መዘርዘር በመቀጠል እያለሁ፣ ደግሜ ስመለከት አሁንም ሐሳባቸው ከእኔ ዘንድ አለመሆኑን ስረዳ ድምፄን እንደገና ገታሁት፡፡ እጅግ ድፍረት እንደሆነ ተሰምቶኛል፣ ግን እድሜዬ ገና ሃያዎቹ ገደማ ወጣት ስለነበርኩና የማቀርበው እቅድ እጅግ የማምንበት ስለሆነ ሁኔታው በጣም ከንክኖኝ ስለነበር ነው፡፡ እንደገና ትዕዛዝ መጣ፣ ከጀርባቸው ቆሞ የነበር ልዩ ፀሐፊያቸውም ይገላምጠኝ ጀመር፣ በዚህ ጊዜ ግራ ተጋባሁና አቤቱታዬን አድበስብሼ ጥናቱን ለመቀጠል የሚያስችል ተጨማሪ ገንዘብ መንግሥት እርዳታ እንዲያደረግልኝ በመጠየቅ ንግግሬን አሳጥሬ እንዳከተምኩ፣ በትምህርት ሚኒስቴር አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩ ይታይና ለውሳኔ እንዲቀርብ ንጉሡ ሚኒስትሩን አዘው በዚሁ አሰናበቱኝ፡፡ ከዚያ ሁላችንም እጅ ነስተን ስንወጣ በቤተ መንግሥት ዙሪያ የነበረ አንድ የማውቀው ሰው አግኝቼ የደረሰብኝን አጫውቼው፣ የውሳኔውን ፍቺ ስጠይቀው፣ “አይ ከኛው ጋር እዚህ መክረምህ ነው” የሚል መልስ እንደሰጠኝ ትዝ ይለኛል፡፡ 

እኔም ሌላ አማራጭ እስቲገኝ፣ በዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ አዲስ በተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ፣ እንዳጋጣሚ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሕግ ባለሙያ ሲያፈላልጉ ነበርና የመሥራት እድል ስለ ገጠመኝ፣ እንደተባለውም አዲስ አበባ ከረምኩ፡፡ የዓባይ ውኃ እቅዴ በእንደዚህ ዓይነት ባጭሩ ተቀጭቶ አርባ ዓመታት ያህል የውኃ ሽታ ሆኖ ሰነበተ፡፡ ቢሆንም በተቻለኝ መጠን፣ የዓባይን ውኃ የሚመለከቱ ጽሑፎችና ሰነዶች ማከማቸቱን አላቋረጥኩም ነበር፡፡

ከዚያን ጊዜ አንስቶ ዛሬም ሳይቀር የንጉሡ ለጉዳዩ ትኩረት መንፈጋቸው ሚስጥሩ አልተፈታልኝም፡፡ ምን ይሆን ያሳሳትኩት? አያሌ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ትልቅ ያገር ጉዳይ ማንሳቴ ይሆን? ድንገት በዚያን ዘመን ፕሬዚዳንት ናስርና ንጉሡ መካከል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ቋሚ መኖሪያ አዲስ አበባ እንዲሆን የበለጠ መግባባት ተፈጥሮ፣ የዓባይን ጉዳይ ማንሳት ጊዜው አመቺ አልሆነ ይሆን? ወይም የኤርትራን ችግር ግብፆች እንዳያባብሱ በማሰብ ይሆን? ታዲያ አንድ ተራ ተማሪ  የሚያዘጋጀው ጥናት፣ እዚህ ከፍተኛ ዲፕሎማሲ ውጣ ውረድ ውስጥ ምን ስፍራ ይኖረዋል@ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች እስከዛሬ በአንጎሌ ሲተራመሱ ኖረዋል፡፡ የዛሬ 18 ዓመት ጡረታ ከገባሁ በኋላ፣ ቀድሞ አምባሳደር በመሆን ያገለገልኩበት አገር እንደገና በተማሪነት በመመዝገብ፣ ጉዳዩን በአዲስ አንቀሳቅሼ የምርምር ሥራዬን ለአያሌ ዓመታት ሙሉ ፓሪስና ካናዳ በመመላለስ ፈጽሜ እነሆ የተባለውን ጥናት ተዘጋጅቶ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ምስጋና ይድረሰውና፣ በመጽሐፍ መልክ ለማቅረብ በቅቻለሁ፡፡ ሆኖም ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ፣ ንጉሡ የሰጡት መልስ ባንድ በኩል ረድቶኛል ለማለት የምደፍረው መጽሐፉን የጻፍኩት አርባ ዓመት ያህል በሕግ ሥራ ላይ ችሎታዬን ከማሻሻሌ በኋላ መሆኑ ነው፡፡

ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ ለዶክቶሬት ቲዝስ በፈረንሳይኛ ያዘጋጀሁትን ጥናት በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሜ ማቅረብ ዓይነተኛ ጥቅም ይኖረዋል የሚል ግምት የነበረኝ፣ ከዚህ በፊት ስለ ዓባይ የተዘጋጁ መጣጥፎችም ሆኑ፣ መጻሕፍት ብዙውን ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆናቸው፣ ይህ በአማርኛ የተዘጋጀ መጽሐፍ፣ ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን በወንዙ ውኃ ላይ አገራቸው ላላት መብትም ሆነ ግዴታ የሚነሳውን ሙግት መከታተልና ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳል በሚል ተስፋ ነው፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆን፣ መጽሐፉ የአንባቢዎችን ትኩረት በመሳቡ በየጊዜው የተነሱ አዳዲስ ሁኔታዎችን በማካተትና በማረም እነሆ ለሦስተኛ እትም መብቃቱን በዚህ አጋጣሚ አስታውሳለሁ፡፡

በሌላ በኩል መጽሐፉ በፈረንሳይኛም ቋንቋ ብራሰልስ ከተማ መታተሙ በተለይ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ስለ ዓባይ የሕግ ሁኔታ (ሬጅም) ያላቸውን ግንዛቤ እንደሚያዳብርና በተጨማሪም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎች ለሥራቸው እንደሚረዳ ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በአንዲት እንግሊዛዊት ባለሙያ ተሳትፎ ተዘጋጅቶ፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ፈቃዱ ሆኖ፣ እንዲያትምልኝ ማቅረቤንና ሟቹው ታዋቂ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት መጽሐፉን ካነበቡ በኋላ የሰጡትን አስተያየት በእንግሊዝኛ በሚታተመው መጽሐፍ በመቅድም መልክ እንደሚካተት አስታውቃለሁ፡፡

መጽሐፉን ለማዘጋጀት ባጠቃላይ የተጠቀምኩባቸው፣ 62 መጻሕፍት፣ 51 ያህል መጣጥፎች፣ 8 ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች፣ 11 የዓለም ፍርድ ቤትና ሌሎች የአገሮች ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች፣ በየመንግሥታት የቀረቡ ኦፊሺያል አቋሞች፣ 14 የኢንተርናሽናል መጽሔቶችና የልዩ ልዩ አገር ጋዜጦች ጭምር ናቸው፡፡

 

በዚህ የተነሳ መጽሐፉ ለኢትዮጵያ አዳልቷል የሚል ዝንባሌ እንዳይነሳ የአገራችንን አቋም ጭምር የሚደግፉ የሕግ ሊቃውንትን አስተያየቶች የሚያካትቱ፣ ቁጥራቸው 600 የሚጠጋ የግርጌ ማስታወሻዎች ተጠቅሰዋል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህ ቀጥሎ ስለ መጽሐፉ ቅደም ተከተልና ዋና ዋና ክፍሎች ባጭሩ ይቀርባሉ፡፡

የዓባይ ውኃ መልክዓ ምድርና ሃይድሮሎጂ እንዲሁም የተፋሰሱ አካባቢ የዓየር ንብረት ጠባይ በመንደርደሪያው ምዕራፍ ከተተነተኑ በኋላ፣ መጽሐፉ ሦስት ዋና ክፍሎች አሉት፡

በመጀመሪያው ዋና ክፍል፡- የዓባይን ሁኔታ በሚገባ ለመረዳት እንዲቻል በቅድሚያ የዓለም አቀፍ ሕግ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማወቁ ተገቢ በመሆኑ፣ የድንበር ዘለል ወንዞች ኢንተርናሽናል ሕግ ከመነሻው እስካሁን ያሳየውን አቅጣጫ በመመርመር፣ የኢንተርናሽናል ወንዝ ጽንሰ ሐሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሒደት መገንባቱን፣ አጠቃቀሙም ከመጓጓዣ ወደ ኢኮኖሚ ልማት ማምራቱን፣ በቅርቡ ደግሞ የወንዝ ተፋሰስና ሌሎችም ጽንሰ ሐሳቦች ተቀርጸው፣ የእያንዳንዱ ድንበር ዘለል ወንዝ የራሱ የሆነ ልዩ ባሕሪ ስላለው፣ ለሚፈጠረው የአጠቃቀም ችግር የተለያየ መፍትሔ ማስፈለጉን ያስረዳል፡፡ የወንዙ ተጋሪ አገሮች እንደ መልክዓ ምድር አቀማመጣቸው ከግዛት ፍጹም ሉአላዊነትና (absolute territorial sovereignty) በግዛት ፍጹም አንድነት (absolute territorial integrity) መርሆች በመመሥረት ስለተከፋፈሉ፣ ሊገላግላቸው ይረዳል ብሎ በማሰብ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ኒው ዮርክ ላይ ከ20 ዓመታት ድርድር በኋላ እ.ኤ.አ. በ1997  የጸደቀው ኮንቬንሽን በዚሁ ክፍል ይጠናል፡፡

ሁለተኛው ዋና ክፍል፡- በመጀመሪያ የዓባይን ወንዝ የዛሬውን የሕግ ሁኔታ የገነቡ የፖለቲካ ስልትና ሽኩቻዎችን እንዲሁም ጄኦፖለቲክስ፣ ስለ ዓባይ ውኃ አከፋፈል በመንግሥታት የተፈረሙ ልዩ ልዩ ስምምነቶች ያስነሱትን ክርክሮችና እንዲሁም በዓባይ ውኃ ለመጠቀም በተናጠል የተፈጸሙ ዕርምጃዎች፣ በመንግሥታት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ያስከተሉትን ውጥረቶች ጭምር ያቀርባል፡፡

ሦስተኛው ዋና ክፍል፡- በዓባይ ወንዝ ከላይ የሚገኙ መንግሥታትና እንዲሁም የኢንተርናሽናል ሕግ ሊቃውንትም ጭምር፣ አሁን ያለው የዓባይ የሕግ ሁኔታ፣ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙ ስምምነቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ሕጋዊነቱን ጥያቄ ውስጥ እንዳስገቡ በሰፊው ካቀረበ በኋላ፣ በተፋሰሱ ያለው ሚዛን አልባ የሆነ የውኃ አከፋፈል ተቀባይነቱ እየመነመነ በመሄዱ በአንድ አዲስ ድርድር የሚወሰን ይዘት ተተክቶ፣ በሀብቱ በእኩልነት መጠቀም የሚያስችለውን ሕጋዊ ሂደት በቅርብ ይመረምራል፡፡

የዓባይን ውኃ ጉዳይ በተመለከተ የተነሱት ሁለት ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ይሆናሉ፡፡ መጀመሪያ፣ የዓባይ ውኃ አከፋፈል በአሁኑ ወቅት የተዛባ መሆኑንና፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ የጋራ ሀብት የሆነውን የዓባይ ውኃ በትብብር ማልማት የማይታለፍ መፍትሔ መሆኑን ማስገንዘብ ነው፡፡

1. የተዛባው የዓባይ ውኃ አከፋፈል

እንደሚታወቀው ሁሉ፣ የዓባይ ተፋሰስ የተለያዩ የአየር ጠባዮች ስለሚያንዣብብበት፣ ለወንዙ በውኃ መጋቢነት የሱዳን ድርሻ እጅግ መጠነኛ ሲሆን፣ ግብፅ ደግሞ አንድም ጠብታ አታበረክትም፡፡ እነዚህ ሁለት አገሮች፣ በተለይ ግብፅ፣ ለመስኖ የሚያስፈልጋቸውን ውኃ የሚያገኙት ከዓባይ ወንዝ ብቻ ሲሆን፣ የወንዙ ምንጮችም ከግዛት ክልላቸው ውጭ መሆናቸው መታወስ አለበት፡፡ በሌላ በኩል፣ ደግሞ  በዓባይ ትራስጌ ያሉ አገሮች፣ በተለይ ኢትዮጵያ፣ የወንዙ ውኃ ዋና አቅራቢዎች  በተደጋጋሚ የሚከሰተው የድርቅ ሁኔታ ሕዝቦቻቸውን ለመመገብና የእርሻ ልማታቸውን ለማስፋፋት በዓባይ ሀብታቸው መጠቀም  እንደሚገደዱ ግልጽ ሆኖ በመቅረቡ ነው፡፡  

በ19ኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ፣ ግብፅን በቁጥጥሯ ካስገባች በኋላ፣ እንግሊዝ የተረዳችው አንድ ነገር ቢኖር፣ ግብፅን አረጋግቶ ለመግዛት ዋናው ቁልፍ የዓባይ ውኃ መሆኑ ነው፡፡ ግብፅ ውስጥ ለመደርጀትና በስዊዝ ቦይ ላይ ያላቸውን ስትረቴጂክ ስፍራ ይዘው መቀጠል ከፈለጉ፣ የዓባይ ውኃ ያላንዳች እክል ወደ ግብፅ ግዛት እንዲዘልቅ ማድረግ ዋናው ዘዴ እንደሆነ እንግሊዞች በማያወላውል መንገድ ሊረዱ የቻሉበት ሁኔታ ነበር፡፡

የእንግሊዝ መሪዎች ትልቁ እምነት፣ የዓባይን ሸለቆ በሙሉ ቁጥጥሩ ሥር ያላስገባ ማናቸውም መንግሥት ግብፅን ይዞ የመቆየት እድሉ የመነመነ በመሆኑ፣ የዓባይ ምንጮች በተቀናቃኝ ወይንም በግድየለሽ መንግሥት እጅ መውደቅ፣ ከባድ አደጋ መጋበዝ ሆኖ ይቆጠር ነበር፡፡

በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ፣ ብቸኛ ተሰሚነቱንና ሥልጣኑን ለመረጋገጥ፣ የእንግሊዝ መንግሥት የሌሎች የአውሮፓ ኃያላን ቅኝ ገዢ መንግሥታትን ትብብር ማግኘት ወሳኝ በመሆኑ፣ ከነዚሁ አገሮች ጋር ስለ ዓባይ ውኃ ዋስትና ሌሎች ስምምነቶች መፈራረም አስፈላጊ ሆኖ ነበር፡፡

በክፍለ አህጉሩ የነበራቸውን የጥቅም ክልል ለማጠናከር ያቀዱ እንደ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ቤልጂግና ፈረንሳይ ያሉ አገሮችም ሆነ፣ የግዛቷን አንድነት ከአደጋ ለማዳን በማሰብ የአፄ ምኒልክ ነፃዪቱ ኢትዮጵያም ጭምር፣ ስምምነቶቹን ከእንግሊዝ ጋር ከመፈራረም ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የገባችበት የ1902 ስምምነት ስለ ሱዳን ድንበር ሲሆን፣ በጣልቃ እንግሊዝ ያስገቡት 3ኛው አንቀጽ የዓባይን ውኃ ይመለከታል፡፡

ከኢትዮጵያ በስተቀር፣ የዓባይ ተፋሰስ ተጋሪ ግዛቶች በቅኝ አገዛዝ ሥር ይገኙ ስለነበር፣ የስምምነቶቹ ዋና ግብ፣ በዓባይ ውኃ ለመጠቀም የሚመለከታቸው መንግሥታት ያላቸውን እቅድ መግታትና ማናቸውም በአካባቢው ያለ አገር ግብፅን በሚበድል መልኩ በዓባይ ውኃ የመጠቀም ችሎታ እንዳይኖረው ማድረግ ነበር፡፡

እነዚህን ስምምነቶች የእንግሊዝ መንግሥት ሲፈርም፣ ዋና ስትራቴጂው ወደ ህንድና አውስትራሊያ የሚዘልቀው የባህር መንገድ መተላለፊያ ጣቢያዎችን በተለይ የስዊዝን ቦይ መቆጣጠርና በተጨማሪ የጣናን ሐይቅ፣ የጥቁር ዓባይን፣ የባሮ ኦኮቦን አካባቢ በቅርቡ በመከታተል የግብፅን የውኃ ዋስትና ማስጠበቅ ነው፡፡

የዛሬውን የዓባይን ውኃ አከፋፈል ለመረዳት ይህ ታሪካዊ የቅኝ ግዛት መንግሥት አቋም ምን ጊዜም መዘንጋት የለበትም፡፡

ባሁኑ ጊዜ የዓባይን የኢንተርናሽናል ሕጋዊ ሁኔታ በዋናነት የሚወስኑ ሁለት ስምምነቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው በፈረንጆች አቆጣጠር ሜይ (ግንቦት) 7 ቀን 1929  በታላቋ ብሪታንያና በግብፅ መካከል የተፈረመው ስምምነት ሲሆን ከሠላሳ ዓመት በኋላ ደግሞ ኖቬምበር (ኅዳር) 8 ቀን 1959 ግብፅ እና ሱዳን የፈረሙት ስምምነት ነው፡

በመጀመሪያው ስምምነት ግብፅ በዓባይ ውኃ ላይ “ተፈጥሮአዊና የባለንብረትነት ታሪካዊ መብት” እንዳላት እንግሊዝ ያረጋገጠችላት መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም በመሆኑ፣ ማናቸውም ሌላ የተፋሰሱ አገር፣ ሱዳንም ጭምር፣ በውኃው ለመገልገል የሚወጥነውን እቅድ ሊፈጽም የሚችለው ግብፅ በቅድሚያ ስትስማማበት ብቻ እንደነበር በግልጽ ተቀምጧል፡፡

 

በስምምነቱ እንደተመለከተው

“ወደ ግብፅ መሬት የሚፈሰውን የውኃ መጠን ሊቀንስ የሚችል፣ ከዚያው የሚደርስበትን ቀን ሊለውጥ ወይንም የውኃውን ከፍታ ዝቅ የሚያደርግና በግብፅ ጥቅም ላይ ጉት የሚያስከፍል፣ ሱዳን ውስጥም ሆነ በእንግሊዝ ሥር የሚተዳደሩ ቅኝ ግዛቶች (ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንጋኒካ) ውስጥ ዓባይ ላይ ወይንም መጋቢዎቹ ወንዞችም ሆነ ወንዙ የሚመነጭባቸው የተለያዩ ሐይቆች ላይ የግብፅ መንግሥት በቅድሚያ ካልተስማማ ለመስኖ ወይንም የኃይል ማመንቻ የግንባታ ሥራ መሥራት አይቻልም” ይላል፡፡

ይህም ለግብፅ የማገጃ ድምፅ መብት እንደተሰጠ ይቆጠራል፡፡ ግን ይህን ዓይነቱን ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ የሰጠቻትን መብት በመተው ግብፅ ከሱዳን ጋር በ1959 ደግሞ፣ በ1929 ውል መሠረት ነባር መብት (Acquired Rights) የሚባለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁለቱ አገሮች የዓመት ድርሻቸውን ውኃ መጠን በአዲስ ድልድል፣ ማለትም 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለግብፅ፣ 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ለሱዳን ተከፋፍለው ሌሎቹን ተዋሳኝ አገሮች ሳያካትቱ ብቸኛ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ የተፋሰሱ የበላይ አገሮች ግን ድርድሩ ላይ ለመካፈል እድሉ ቢነፈጋቸውም፣ ውኃውን አካፍሉን የሚል ጥያቄ ካቀረቡ ግን ከግብፅና ከሱዳን ድርሻ በእኩል ተቀንሶ ሊሰጣቸው እንደሚችል ስምምነቱ ይገልፃል፡፡ ግን ይህ አንቀጽ እስከዛሬ በተግባር ተሞክሮ ባይታወቅም፣ ከዓባይ ውኃ አንዲት ጠብታም ቢሆን መቀነስ የለበትም ከሚለው የግብፅ አቋም ጋር በግልጽ መጋጨቱን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡

የዓባይ ውኃ ከሌሎች ድንበር ዘለል ወንዞች ለየት የሚያደርገው፣ በወንዙ ከታች በኩል ከሚገኙ አገሮች ይልቅ፣ ከበላይ ያሉት ተጋሪ አገሮች በውኃው አከፋፈል የተበደሉ በመሆናቸው ነው፡፡ በተጨማሪ ስለወንዙ ውኃ አከፋፈል ያሉት ስምምነቶች በተፈረሙበት ወቅት ኢትዮጵያና ዘግየት ብለው ነፃ የወጡት የውኃ መጋቢ አገሮች የድርድሩ ተከፋዮች እንዳልነበሩ ከላይ ተጠቅሷል፡፡

በጂኦግራፊ እንደተለመደውና እንደሚጠበቀው፣ በወንዙ ከታች በኩል ያሉ አገሮች በውኃው ሲጠቀሙ ከበላይ የሚገኙት አገሮች ላይ ጉዳት እንደማያደርሱ ስለተገመተ በአጠቃላይ ሲታይ፣ የወንዞች ግልጋሎት ኢንተርናሽናል ሕግ፣ በመልክዓ ምድር አቀማመጣቸው በወንዙ በታች በኩል የሚገኙ የተፋሰሱ አገሮች ከላይ ያሉትን አገሮች ሊጎዷቸው ይችላሉ በሚል እምነት የተቀረፀ ነበር፡፡  ይህም የሆነበት የሕንድና የፓኪስታን እንዲሁም ቱርክና ሶሪያ፣ ኢራቅ መካከል የነበረውን የግንኙነት ውጥረት በማስታወስ ይመስላል፡፡

በዓባይ ግን ሁኔታው ለየት ብሎ፣ ከታች በኩል የሚገኙት አገሮች በተለይ ግብፅ ከላይ ያሉትን ተጋሪዎች ኢትዮጵያን ጭምር የልማት እቅድ እንዳያከናውኑ ለረዥም ጊዜ አግደው በግዛታቸው የሚፈሰውን ውኃ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዳይቃጡ ትብብራቸውን ነፍገው መቆየታቸውን ያመለክታል፡፡

በዚህም የተነሳ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ የሚያስከትለውን የፍጥረት ደንብን በመሻር፣ በወንዙ ግርጌ የሚገኙ አገሮች በወንዙ ትራስጌ በሚገኙ አገሮች ላይ ጉዳት ማድረስ ችለዋል፡፡

ሁለተኛው ዓባይን ለየት የሚያደርገው ሁኔታ፣ ኢትዮጵያን የመሰለ በውኃ መጠን ከፍተኛውን ድርሻ ለወንዙ የሚያበረክት አገር (86%) ከውኃው የሚያገኘው ግልጋሎት እጅግ ያነሰ ሲሆን (1%) አንዲት ጠብታ እንኳን የማታቀርበው ግብፅ ግን በዓባይ ሀብት በከፍተኛ ደረጃ ቢያንስ 75% ያህል መጠቀም መቀጠሏ ነው፡፡

 

ይህም በመሆኑ፣ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የውኃ ግልጋሎት አንድወጥ ሕላዊነት የሚወሰነው በጆኦግራፊ አቀማመጥና በሃይድሮሎጂ ሳይሆን፣ በታሪክ የተመሠረተ መብት መሆን አለበት በሚል አቅዋም ሚዛናዊነት የጎደለውን የዓባይን ውኃ አከፋፈል በቅኝ ግዛት ዘመን ከዛሬ 90 ዓመት በፊት የወረሰችውን የሕግ ሁኔታ እንዳይደፈር እስከዛሬ ግብፅ ስትሟገት ቆይታለች፡፡

በሌላ በኩል በዓባይ ትራስጌ የሚገኙ ቡሩንዲ፣ ኮንጎ ኪንሻሳ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ታንጋኒካ፣ በነፃነታቸው ማግስት በየበኩላቸው በቅኝ ገዢዎቻቸው የተፈረሙት ስምምነቶች (የ1929 ስምምነት ለምሳሌ) ግዴታ ውስጥ እንደማያስገቧቸውና እንደገና መታየት እንዳለባቸው ካመለከቱ በኋላ፣ ስምምነቶቹን በእኩልነትና የሁሉም የወንዙ ተጋሪ አገሮች ጥቅም ተጠብቆ በአዲስ ለመፈራረም ዝግጁ መሆናቸው በየመግለጫዎቻቸው አረጋግጠዋል፡፡ ግብፅ፣ በወቅቱ ለቀረበው ሐሳብ መልስ ባለመስጠቷ ጉዳዩ እስካሁን ተንጠልጥሎ ከርሟል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የ1929  ስምምነት በቀጥታ የማይመለከታት ስለሆነ፣ የ1902 ስምምነትን ግን በእንግሊዝ ተጽእኖና ጥቅም ብቻ ተመሥርቶ የተፈረመ ለኢትዮጵያ በለውጡ ምንም ዓይነት ማካካሻ የማይሰጥ በመሆኑ ኢትዮጵያን እንደማያስገድዳት የሕግ ሊቃውንት አሳስበዋል፡፡ ኢትዮጵያም በበኩሏ የስምምነቱን አንቀጽ 3 እንደማትቀበል በመደጋገም አስታውቃለች፡፡ በተጨማሪ አፄ ምኒልክ የተስማሙት የዓባይን ወንዝ “ተዳር እዳር የሚሸፍን ሥራ” እንዳይሠሩ ነው እንጂ በውኃው ሀብት፣ ኢትዮጵያ አትጠቀምም አላሉም፡፡

ባጠቃላይ በዓባይ ውኃ ላይ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ መብት ለግብፅ ያበረከተው የ1929 ስምምነት የግብፅን መንግሥት ወዳጅነት ለማፍራትና የእንግሊዝን የፖለቲካ ጥቅም ለማዳበር የታቀደ እንጂ በተለመደው የኢንተርናሽናል ሕግ ውስጥ ዋጋ እንደሌለው የሕግ ሊቃውንት በወቅቱ አስገንዝበዋል፡፡

 

በተጨማሪም ግብፅና ሱዳን የፈረሙት የ1959 ስምምነት የዓባይን ውኃ ሀብት ከአሥር የተፈሰሱ ተጋሪ አገሮች ለሁለቱ ብቻ የሚያከፋፍል በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ስምምነት ሆኖ ሌሎቹን ተጋሪ አገሮች ለማስገደድ እንደማይችል የሕግ ሊቃውንቱ አረጋግጠዋል፡፡

ስለዚህ የዓባይ ወንዝ በርዝመት በዓለም የመጀመሪያውን ስፍራ መያዙ ቢታወቅም፣ ከቀሩት ሌሎች የአፍሪካ ወንዞች የሚለየው፣ የውኃውን ሀብት በጋራ ለማስተዳደርና ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም የውኃውን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል የተፋሰሱን አገሮች በሙሉ የሚያካትት ስምምነት እስከዛሬ ተነፍጎት በመቆየቱ ነው፡፡

አሁን እንደሚታየው ሁሉ፣ የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች በየፊናቸው የሚጠይቁትን የተለያዩና የማይጣጣሙ የውኃ ፍላጎቶችን ለማርካትና ለማስማማት እንደሚያዳግት ግልጽ በመሆኑ፣ በወንዙ ከታችና ከላይ ክፍሎች የሚገኙ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት ማሳየቱ ማስገረም የለበትም፡፡

በግብፅ የቀረቡት የመከራከሪያ ነጥቦች ክብደት እንደሌላቸው ማሳያ ከዚህ በታች በመጽሐፉ የተገለጸውን በሚከተለው እንዘረዝራለን፡-

  1. የዓባይ ወንዝ ግብፆች እንደሚሉት የአገራቸው ብቸኛ ሀብት አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ እንደሁም ለኬንያ፣ ለዩጋንዳ፣ ለታንዛኒያ፣ ለሩዋንዳ፣ ለቡሩንዲ፣ ለኮንጎ፣ ለሱዳን፣ ለደቡብ ሱዳንና ለኤርትራም ጭምር ፍጥረት ያበረከተላቸው የጋራ ፀጋ መሆኑን ማወቅ ይገባል፡፡

 

በዚህም ሳቢያ የዓባይ ውኃ የማናቸውም ተጋሪ አገር፣ በወንዙ ከትራስጌም ይሁን ከግርጌ፣ የግል ንብረት ሳይሆን፣ በዓባይ ተፋሰስ የሚኖሩ ሕዝቦች በሚዛናዊና በተመጣጠነ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚገባ የጋራ ሀብት መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ ግብፅ የዓባይ ውኃ ላይ በቅኝ ገዢዎች ስምምነቶች የነበራትን የበላይነት ይዤ ልቀጥል ማለቷ ማንም ሊረዳው አይችልም፡፡

  1. በወንዙ ከበላይ የሚገኙ አገሮች ለመስኖ እርሻቸው የሚውል የተትረፈረፈ የዝናብና ሌላ የውኃ ሀብት ባለቤት ሲሆኑ፣ ግብፅ ግን ከዓባይ ሌላ ምንም የውኃ አቅርቦት እንደሌላት ሆና መቅረብ መርጣለች፡፡ በእርግጥ ግብፅ የዓባይ ውኃ ጥገኛ መሆኗን ማንም አይክድም፡፡ ሆኖም በከርሰ ምድሯ የተከማቸውን የውኃ ሀብቷን እያለ እንደሌለ አድርጋ መቁጠር የለባትም፡፡ ዋናው ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ግን ዝናብ አስተማማኝ አማራጭ ለመሆን እንደማይችል ነው፡፡ ይህም የሆነበት በተለይ በከፊል ሞቃታማ ስፍራዎች የዝናቡ መጠን ውጣ ውረድ ያለው ከመሆኑም በላይ ዝናቡን በማጠራቀሚያ ይዞ ለማቆየት ከፍተኛ ወጪን በማስከተሉ ነው፡፡ ዝናብ ለእርሻ ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች ከመጣሉም ሌላ ባልሆነ ወቅት መጥቶ የተመረተውን የእርሻ ሰብል ጎርፍ ሲያወድመው ታይቷል፡፡

ኢትዮጵያን በተመለከተ አንዱ አካባቢ ዝናብ ሲያገኝ ሌላው ሲያጣ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ድርቅ እንደሚያጠቃቸው ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ዝናብ ይምጣ አይምጣ በማይታወቅበት ሁኔታ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የዘወትር ሥጋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ዝናብን አማራጭ አድርጎ መቁጠር ያስቸግራል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ አገር ዝናብ እንደልብ ያገኛልና፣ በግዛቱ በሚፈሰው የወንዝ ውኃ በተለይ በኃይል ማመንጫ ብቻ ተወስኖ ልጠቀም ብሎ ሲወጥን፣መብት አይሰጠውም የሚል የዓለም አቀፍ ሕግ እንደሌለ መታወቅ አለበት፡፡

  1. በግብፅ መሪዎች አስተያየት የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በሞላ ስለ ዓባይ ውኃ አጠቃቀም በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረሙ ስምምነቶች መመራት አለባቸው ይላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አቋም ስለ ድንበር ዘለል ወንዞች ውኃ አጠቃቀም የተባበሩት መንግሥታት ሜይ (ግንቦት) 1997  ካጸደቀው ኮንቬንሽን ጋር አለመጣጣሙን መጽሐፉ በሰፊው ማስረዳቱን ያመለክታል፡፡
  2. በዓባይ ውኃ ላይ ግብፆች ነባር መብት እንዳላቸው ይከራከራሉ፡፡ ግን ይህ አቋም ትክክል አለመሆኑ የሚታወቀው የድንበር ዘለል ወንዞችን አጠቃቀምን በተመለከተ በወቅቱ የዓለም አቀፍ ሕግ (CUSTOMARY INTERNATIONAL LAW) ውስጥ ቋሚ ወይም ነባር መብት የሚል ጽንሰ ሐሳብ ስፍራ የለውም፡፡ ይህ የቀደምትነት መብት ይጽና ከተባለ ለረዥም ጊዜ በወንዙ ውኃ የተጠቀመ መንግሥት፣ ሌሎች ዘግይተው በመድረስ በጋራ ውኃው ሊጠቀሙ የሚፈልጉ የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች መብታቸውን ሊገፈፉ ነው ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ያለው ሁኔታ ደግሞ በዓለም አቀፍ ሕግ፣ መንግሥታት መካከል መኖር የሚገባውን የመብት እኩልነት መርሆ ስለሚሽረው ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

2. ለችግሩ መፍትሔ አፈላለግ

ባሁኑ ጊዜ ስለ ዓባይ ከዚህ ቀደም ብሎ የተፈረሙት ስምምነቶች የገነቡት የውኃው አጠቃቀም ያስከተለውን እክሎች በኢንተርናሽናል ሕግ አንፃር መገምገምና የሚመለከታቸውን አገሮች የወደፊት መብትና ግዴታ ከሌሎች ድንበር ዘለል ወንዞች ሁኔታ ጋር በማስተያየት በዓለም አቀፍ ደረጃ በየጊዜው እየዳበረ የመጣውና በቅርቡ በተደነገገው ሕጋዊ መመሪያ በመመሥረት የአገሮችን መብትና ግዴታ ለይቶ ማቅረብ የመጽሐፉ ዋና ተግባር ነው፡፡

 

የኢንተርናሽናል ሕግ ሒደት በወንዙ በላይ በኩል ያሉ አገሮች ግዛት ፍጹም ሉአላዊነት በግዛታቸው በሚፈሰው ውኃ ያላንዳች ገደብ መጠቀም ሲሆን (የሀርሞን ዶክትሪን)፣ በወንዙ ከታች በኩል የሚገኙ አገሮች ደግሞ በግዛት ፍጹም አንድነት መርሆ መሠረት የወንዙ ውኃ ያለምንም መሰናክል ወደ ግዛታቸው እንዲገባ፣ በመባል የታወቁት ሁለት የሙግት አቋሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከሙ መጥተው፣ ባሁኑ ጊዜ አዝማሚያው የጋራ ወንዙን ውኃ በሚዛናዊና በተመጣጣኝ መንገድ ሁሉም ተጋሪ አገሮች እንዲጠቀሙበት የሚያስችለው መርሆ ሰፊ ተቀባይነት ለማግኘት በመብቃቱ ነው፡፡

በዚህም ረገድ ግንቦት 21 ቀን 1997  ኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ስለ ደምበር ዘለል ወንዞች በተለያዩ ግልጋሎቶች፣ ማጓጓዣን ሳይመለከት፣ ስለ መጠቀም ሕጋዊ መብት የጸደቀው ኮንቬንሽን ዓይነተኛ ምስክር ነው፡፡ የቬየትናም መንግሥት 35ኛውን የማጽደቂያ ሰነዱን በማቅረቡ ኮንቬንሽኑ እ.ኤ.አ. ከኦገስት (ነሐሴ) 2014 ጀምሮ በተግባር ላይ ውሏል፡፡

ድንበር ዘለል ወንዞችን የሚመለከቱ ቀደም ብለው የተፈረሙ ስምምነቶች ውስጥ የተዘረዘሩትን መብትም ሆነ ግዴታዎች ኮንቬንሽኑ በቀጥታ ባይለውጣቸውም የተባሉትን ስምምነቶች ከኮንቬንሽኑ መሠረታዊ መርሆች ጋር ማጣጣም ተገቢ መሆኑንም የሚያመለክት አንቀጽ ይገኛል፡፡

በተጨማሪ ይህ ኮንቬንሽን ሁለት መርሆችን ያካትታል፡፡ በአንድ በኩል፣ የያንዳንዱ ተጋሪ አገር በውኃው ሀብት ያለውን ሚዘናዊና ተመጣጣኝ የግልጋሎት መብት ሲመሠርት፣ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የወንዙ ተጋሪ ማናቸውም አገር በውኃው ሲጠቀም ሌሎች ተዋሳኝ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ አሠራር መወሰን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ የመጀመሪያው መርሆ በግዛታቸው በሚፈሰው ውኃ ለመገልገል የወጠኑትን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ መንግሥታትን መብት ያስክብራል፣ ሁለተኛዋ ደግሞ ከዚህ በፊት በውኃው ሲጠቀሙ የቆዩትን እንደ ግብፅ ያሉ መንግሥታትን አቋም የሚደግፍ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የኮምፕሮማይዝ (የማመቻመች) አስታራቂ ሰነድ በመሆኑ፣ ሁሉም ወገን እንደ አተረጓጐሙ የሚፈልገውን ያሰኘዋል፡፡ ኮንቬንሽኑ ጉድለት ቢኖረው ይህ ዋናው ነው፡፡

እነዚህ ሁለት መርሆ የማይጣጣሙ መስለው ቢታዩም አያሌ የሕግ ሊቃውንት ለሚዛናዊና ተመጣጣኝ ግልጋሎት ቅድሚያ መስጠት እንደሚበጅ በጥናታቸው ማስገንዘባቸውን መጽሐፉ ያመለክታል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ያጠናክረዋል ማለት ነው፡፡

የድንበር ዘለል ወንዝ የውኃ ሀብት የያንዳንዱ ተጋሪ አገር የግል ንብረት፣ ሳይሆን በሚዛናዊና በተመጣጠነ መንገድ በጋራ የመጠቀም መብት መሠረታዊ መርሆ መሆኑ ይመረጣል፡፡ መንግሥታት መካከል የእኩልነት መርሆ እንዲከበር ከተፈለገ፣ በታወቁ መስፈርያዎች በመመራት፣ ለምሳሌ ያህል ያካበቢው ሕዝብ የውኃው ሀብት ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነ ወይንም የማኅበርና የኢኮኖሚ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት በሚያግዝ መንገድ እያንዳንዱ አገር በሀብቱ መጠቀም እንዲችል ማድረግ ነው፡፡

ባጠቃላይ የዓባይ ውኃ በወንዙ ከግርጌም ሆነ ከራስጌ የሚገኙ የተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች የግል ንብረት ሳይሆን በጋራ በሚዛናዊና በተመጣጠነ መንገድ ለየሕዝቦቻቸው የኢኮኖሚ ልማት እንዲያውሉት ማድረጉ አማራጭ የሌለው አሠራር መሆን ይገባዋል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የሕግ ሁኔታ ስፍራ ሊኖረው ስለማይችል በአዲስ ስምምነት መተዳደር እንደሚገባው የብዙዎቹ እምነትና ፍላጎት ነው፡፡

 

ግብፅና ሱዳን አሁን ያለው የሕግ ሁኔታ ይቀጥል የሚል አቋማቸው ከ2003  ጀምሮ፣ በናይል ቤስን ኢንሼቲቭ ጥላ ሥር አንድ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ለማፅደቅ የተከናወነው ድርድር በእጅጉ እንዲያዘግምና ቢቻልም እንዳይፈረም በብርቱ ጥረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ድርድሩ እንዲሳካ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አርኪ ውጤት ለማግኘት አስችሏል፡፡ ሆኖም በድርድሩ ወቅት አከራካሪ የሆኑት ጉዳዮች ሙሉ መፍትሔ አላገኙም፡፡ አከራካሪ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

መጀመሪያ ነጥብ፡- በውኃው ለመጠቀም ሲል እቅዶችና ግንባታዎች የወጠነ አንድ ተጋሪ አገር በጽሑፍ ለሌሎች የወንዙ ተጋሪ አገሮች በቅድሚያ ማስታወቅ፣ ግዴታን ይመለከታል፡፡ የኢትዮጵያ መልእክተኛ በጊዜው እንዳሳሰበው ሁሉ፣ ለአገሮቹ የሚመደብ የውኃ ድርሻ በቅድሚያ ሳይወሰን እቅድ አውጥቶ የማሳወቅ ጉዳይ ላይ መከራከሩ ፋይዳ እንደማይኖረው ያስገነዘበበት ጊዜም ነበር፡፡

ሁለተኛው ነጥብ፡- ስለ ዓባይ ውኃ ከዚህ በፊት የተፈረሙት ስምምነቶች የትብብር ማዕቀፉ አንቀጾች ጋር የሚጋጩ ሆነው ከተገኙ ውድቅ ይሁኑ አይሁኑ፣ የሚል ላይ ሲሆን፣

ሦስተኛው ነጥብ፡- ያሉት ስምምነቶች ውድቅ ይሁኑ ከተባለ በውኃው የሚጠቀመው አገር የያንዳንዱን ተጋሪ አገር የውኃ ዋስትና (Water Security) የማክበር ግዴታ አለበት የሚል አዲስ አንቀጽ (14ለ) እንዲጻፍ በግብፅና በሱዳን የቀረበው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የሆነበት፣ በወንዙ ከላይ የሚገኙ አገሮች ኢትዮጵያም ጭምር፣ በወንዙ ውኃ የሚጠቀም አገር “የሌላውን ማናቸውንም ተጋሪ አገር የውኃ ዋስትና ባለመጉዳት መሥራት አለበት” ሲሉ፣ በግብፅና በሱዳን በኩል የቀረበው ረቂቅ ደግሞ በወንዙ የሚጠቀም አገር “የሌላውን ተጋሪ አገር የውኃ ዋስትናና እንዲሁም ወቅታዊውን ግልጋሎትና የነበረ መብቱን በማይፃረር መልኩ መከናወን አለበት” ስለሚል፣ ነባር ስምምነቶች እንዳሉ ዘልቀው የተደለደለው የውኃ ድርሻ ፈጽሞ እንዳይነካ ማለት ነው፡፡

እ.ኤ.አ. ጁን (ሰኔ) 2007  በኢንቴቤ (ኡጋንዳ) የተሰበሰበው የውኃ ሚኒስትሮች ጉባዔ፣ አስታራቂ ሐሳብ ለማቅረብ ባለመቻሉ፣ ጉዳዩ ወደ መሪዎቹ ተላልፎ አዲስ መመሪያ እንዲሰጥበት ተወስኖ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ እርምጃ ውጤት ባለማስገኘቱ አከራካሪው ጉዳይ እንደገና በሚኒስትሮች ጉባዔ በአስቸኳይ እንዲመረመር ግንቦት 29 ቀን 2009 ኪንሻሳ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ የአካባቢ ሚኒስትር ሚስተር ዦዜ ኤንዱንዶ ባሳሰበው መሠረት ቀረበ፡፡ ሚስተር ኤንዱንዶ በተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች ዋና ከተሞች ተዘዋውሮ በመመካከር አከራካሪው አንቀጽ 14ለ ውሳኔ ሳይወስድበት የስምምነቱ አባሪ ሆኖ እንዲቆይና፣ በልዩ ባለሙያዎች ተጠንቶ እስኪቀርብ ድረስ፣ እስካሁን የተስማሙበትን አንቀጾች ያሰፈረው ኮንቬንሽን ባጠቃላይ በድምፅ ብልጫ እንዲፀድቅ ተወሰነ፡፡ ግብፅ የተቃውሞ ድምፅዋን ስትሰጥ የሱዳን መልዕክተኛ በበኩሉ አዳራሹን ረግጦ መውጣቱ ይታወሳል፡፡

ከኪንሻሳ በኋላ ለዚህ ሁኔታ መፍትሔ ለማግኘት እንዲቻል ግብፅ በተከታታይ ሦስት የሚኒስትሮች ጉባዔ በአሌክሳንድሪያ፣ ካይሮና በመጨረሻም ሻርም ኤል ሼክ ሚያዝያ 13 ቀን 2010 እንዲሰበሰብ አድርጋ ነበር፡፡ ሆኖም ለችግሩ ምንም ዓይነት መፍትሔ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ የዑጋንዳዋ የውኃ ሚኒስትር ሚስዝ ማርያ ሙታጋምባ በጉባዔው ፍጻሜ ላይ “ላለመስማማት መስማማት ላይ ደርሰናል” ስትል ያቀረበችው ማጠቃለያ አስተያየት የጉባዔውን ጠቅላላ መንፈስ ይገልጻል፡፡ በበኩሉ የግብፅ የውኃ ሚኒስትር መሐመድ አላም በዚያው ዓመት ሚያዝያ 20 ቀን በግብፅ ፓርላማ ፊት ባሰማው መግለጫ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች “የዓባይ ውኃ ጉዳት የፀጥታችን መሠረት” በመሆኑ፣ ግብፅ የማትቀበለውን ስምምነት የወንዙ ተጋሪ አገሮች ከመፈረም እንዲቆጠቡ አስጠንቅቆ ሳለ፣ ግንቦት 14 ቀን 2010  ተዘጋጅቶ የቀረበውን በአብላጫ ድምፅ የፀደቀውን ሰነድ ስድስት ከላይ የሚገኙ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዑጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ታንዛንያ ፈርመዋል፡፡ ስለዚህ በየፓርላማቸው የማፅደቁ ተግባር ከተፈፀመ ስምምነቱ ፀንቶ፣ የቀድሞቹ የቅኝ ግዛት ተጽእኖ ያረፈባቸው ስምምነቶች ይሻራሉ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ በመከታተል ስምምነቱን ሲያፀድቁ ከሁሉ የማይጠበቀው ኬንያን የመሰለ የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር፣ ቡሩንዲና ዑጋንዳ ተመሳሳይ ውሳኔ ላይ አለመድረሳቸው ነው፡፡ ይህም የሆነበት አንዱ ምክንያት ግብፅ ባካሄደችው የዲፕሎማሲ ተፅዕኖ ይሆናል፣ ወይንም የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ኢትዮጵያ ተለይታ ከግብፅና ከሱዳን ጋር በግንቦት ወር 2015 ካርቱም ከተማ ሌላ የመርህ መግለጫ (Declaration of Principles) ሰነድ መፈረም ቅር አሰኝቷቸው ይሆን@

Cooperation Framework Agreement ስምምነት በተፈረመ በዓመቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ያወጣል ተብሎ የተገመተው ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የድንጋይ ማኖሪያ ሥነ ሥርዓት በመጋቢት 2003 ዓ.ም. (2011) በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲፈፀም በዚሁ ወቅት ባሰሙት ንግግር፡-

“በገዛ ወንዛችን የውኃ ሀብት የመጠቀም መብታችንን የሚያግድ ምንም ነገር አይኖርም፤ ውኃችን ላይ ያለንን መብት ሥራ ላይ ስናውል ዋናው ግባችን በአገራችን ውስጥ የሰፈነውን ድህነትን ለመቋቋም ነው፡፡ ይህም ምንም ዓይነት ተንኮል ጎረቤቶቻችን አገሮች ላይ እንደማንሰነዝር ያመለክታል፤ ምንም ዓይነት አሉታዊ ውጤት ጎረቤት አገሮች ላይ ካለማስከተሉም በላይ ገንቢ ውጤት ለሁሉም የሚያቀርብ እቅድ ነው፤” ብለዋል፡፡

 

በግብፆች በኩል የነበረው ተቃውሞ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን ውኃ ሊቀንሰው ስለሚችል ለወደፊቱ የግብፅን አርሶ አደሮች ይጎዳል የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የግብፅ የሃይድሮሎጂ ምሁሮች ሳይቀሩ በግንባታ ላይ የሚገኘው ግድብ ሰፊ የውኃ ማጠራቀሚያ (63 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ) ከመሆኑም በላይ፣ ቀድሞ በግብፅና በሱዳን ግዛቶች በመትነን የሚባክነውን ውኃ በእጅጉ በመቀነስ ዓመቱን ሙሉ ሳያቋርጥ የውኃ ፍሰት ለሁለቱ አገሮች እንደሚያበረክትላቸው አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪ በግርጌ ለሚገኙት ሕዝቦች ግድቡ የሚያመነጨው የኃይል ጥቅም ተካፋይ ለመሆን ያስችላቸዋል፡፡

በእርግጥም ግድቡ በውኃ እስኪሞላ አንዳንድ እክል እንደሚገጥም አይካድም፡፡ ግን መዘንጋት የሌለበት ሱዳን ውስጥ የተገነባው የሜሮዌ ግድብ ሥራው አያሌ ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ስለሆነም ውኃ እስኪሞላው ድረስ ያስከተለው የውኃ ቅነሳ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የግብፅ አርሶ አደሮችም የናስር ሰው ሠራሽ ሐይቅ (162 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ) በዓባይ ውኃ እስኪሞላ ድረስ ለዓመታት ታግሰዋል፡፡ ተመሳሳይ ትዕግሥትና ትብብር ለኢትዮጵያ ግድብ ግንባታ በማሳየት ሥራው ተከናውኖ የአካባቢው አገሮች ሊጠቀሙ መቻላቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ኤክስፐርቶች እንዳሳሰቡት የሕዳሴ ግድብ፣ በግብፅ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ አናሳ ነው፡፡ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በትብብር ከሠሩና የመረጃ መለዋወጥ ካደረጉ፣ የኢትዮጵያን ግድብ በውኃ የመሙላቱ ተግባር በቁጥጥር ከተካሄደ የናስር ሰው ሠራሽ ሐይቅ ውስጥ ባለው የውኃ መጠን (162 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ) የሕዳሴ ግድቡ እስኪሞላ ድረስ ግብፅ ልትጠቀም መቻሏን ጭምር አመልክተዋል፡፡

 

በጠቅላላው ሲታይ ሱዳን ጥቅሟ ላይ በመመሥረት አቋሟን ለውጣ በግድቡ መሠራት ኢትዮጵያ ለአካባቢው ልማት ላደረገችው አስተዋጽኦ ሙሉ ድጋፍ ከመለገሷም በላይ፣ ከዚህ በፊት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ጅላሚኒ ዙማ በበኩላቸው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በፓን አፍሪካኒዝም አዲስ መንፈስ በመመራት ስለወንዙ አጠቃቀም የሚፈጠሩትን ልዩነቶች መፍታት የሚችሉት በቅኝ ግዛት ዘመን፣ በተፈረሙ ጊዜው ያለፈባቸው ስምምነቶች ሳይሆን፣ በድርድር በሚገኘውና በአብዛኛው ተጋሪ አገሮች በድምፅ ብልጫ በተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መሆን ይገባዋል ሲሉ ማሳሰባቸውን በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ቢባል በካይሮ በኩል በቅርቡ በባለሥልጣኖች የሚሰነዘረው አቋምና ዛቻ የተለመደ ቢሆንም፣ በ2015 ካርቱም በገቡት ስምምነት ተመርተው ያለመግባባት ቢከሰትም ችግሩን ለሸምጋይ ዳኝነት አቅርቦ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጉዳዩን ወደ ዓረብ ሊግ ጉባዔ መውሰዳቸው በቀላል የሚታይ ዕርምጃ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ለመጽሐፉ የሰጠሁት አርእስት “ሙግት” የሚለው ቃል ጉዳዩ መቼም የማያልቅ ትርጉም ይሰጠዋል በሚል ለመለወጥ አመንትቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ግን በእጅጉ የሚያሳስበው ከአያሌ ዓመታት በኋላ፣ ሙግቱ ሳይለወጥ እስከ ዛሬ መቀጠሉ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፓሪስ የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ ሲሆኑ፣ በፈረንሣይ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደርም ነበሩ፡፡ ስለአፍሪካና ስለኢንተርናሽናል ሰብአዊ መብት ጥበቃ ጉዳዮች የታተሙ አያሌ መጣጥፎችን በማበርከትና በዓለም አቀፍ መድረኮች በማቅረብ ከመሳተፋቸውም በላይ፣ በሕግና በዲፕሎማሲ መስኮች በተለይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በዋና የሕግ አማካሪነት፣ ቀጥሎም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በረዳት ሚኒስትር ደረጃ የአፍሪካ አንድነት መምርያ ኃላፊነትና በሕግ አማካሪነት፣ በመጨረሻም ለሁለት አሠርታት በካናዳ የኬቤክ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምርምር ክፍል ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡