Skip to main content
x
በአራት ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት ታስቧል
የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

በአራት ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት ታስቧል

ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው የኢንቨስትመንት ኩባንያ ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ከተለያዩ የእስያ ኩባንያዎች ጋር በመተባበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የነዳጅ ማጣሪያ ለመገንባት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ ታወቀ፡፡

የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የነዳጅ ማጣሪያውን የሚገነቡት በእስያ በነዳጅና በመሠረተ ልማት ግንባታ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በመተባበር ነው፡፡ የፕሮጀክቱ የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ የቦታ መረጣ ሥራ መከናወኑን አቶ ዘመዴነህ ተናግረዋል፡፡

የነዳጅ ማጣሪያው በዋነኝነት ለኢትዮጵያ የሚያገለግል ሆኖ ለሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፣ ‹‹ጂቡቲን ጨምሮ የተለያዩ ቦታዎችን ካጠናን በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የነዳጅ ዴፖ በሚገኝበት አዋሽ ከተማ እንዲገነባ መርጠናል፤›› ብለዋል፡፡

በአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው የነዳጅ ማጣሪያ በቀን 120,000 በርሜል ነዳጅ የማጣራት አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ እስካሁን ከእስያ ባለሀብቶች ጋር ሲሠራ መቆየቱን የገለጹት አቶ ዘመዴነህ፣ በቅርቡ የአሜሪካ ባለሀብቶችም በነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክቱ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን አስረድተዋል፡፡

ፌርፋክስ ከማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ጋር የመጀመርያ ደረጃ ንግግር ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ዘመዴነህ፣ በቀጣይ ዝርዝር የሆነ የሥራ ዕቅድ ለመንግሥት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ የኢነርጂ ዋስትና ለማረጋገጥ ፕሮጀክቱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመርያውን የነዳጅ ማጣሪያ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1959 ዓ.ም. በአሰብ ወደብ የገነባች ሲሆን፣ በወቅቱ በሩሲያዊያን ባለሙያዎች የተገነባው የነዳጅ ማጣሪያ በዓመት 500,000 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ የማጣራት አቅም ነበረው፡፡ የደርግ መንግሥት በነዳጅ ማጣሪያው ላይ ባካሄዳቸው የማስፋፊያ ሥራዎች የማጣራት አቅሙ ወደ 800,000 ሜትሪክ ቶን ደርሶ ነበር፡፡

በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት የነዳጅ ማጣሪያውን በመውሰዱ፣ ኢትዮጵያ የአገልግሎት ክፍያ በመፈጸም ስትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ ሆኖም የነዳጅ ማጣሪያው በማርጀቱና የሁለቱን አገሮች የነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት ባለመቻሉ፣ ኢትዮጵያ በ1989 ዓ.ም. የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ መጠቀሟን አቁማ የተጣራ የነዳጅ ውጤቶችን ማስገባት ጀመረች፡፡

በተለያዩ ጊዜያት የነዳጅ ማጣሪያ ለመሥራት ጥናቶች ቢካሄዱም ከወረቀት በዘለለ የተገነባ የነዳጅ ማጣሪያ የለም፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ የተጠነሰሰው ውጥን ‹‹ይበል የሚያሰኝ ነው›› ብሏል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም፣ የነዳጅ ማጣሪያ ግንባታውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር የተጀመረ ድርድር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የተጣራ ነዳጅ ከማስመጣት ድፍድፍ ነዳጅ አምጥቶ አጣርቶ መጠቀም እንደ ሬንጅ፣ ቡታ ጋዝና ፔትሮ ኬሚካል የመሳሰሉ ምርቶች የሚገኙ በመሆናቸው ለአገር ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አዋጪነት የኢንቨስትመንት መመለሻ ጊዜ በአግባቡ ተጠንቶ ሥራ ላይ ከዋለ ለአገር ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ኢንዱስትሪ የነዳጅ ማጣሪያዎች ከፍተኛ የዋጋ ፉክክር እንዳለ የሚናገሩት አቶ ታደሰ፣ በህንድና በሳዑዲ ዓረቢያ ግዙፍ የነዳጅ ማጣሪያዎች መገንባታቸውንና እነዚህ ማጣሪያዎችም ለደንበኞች አነስተኛ ዋጋ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡

‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ በመጣው የዋጋ ፉክክር ምክንያት ዘመናዊና ግዙፍ የሆኑ ማጣሪያዎች አነስተኛ የሆነ ዋጋ የሚሰጡ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ የታሰበው ማጣሪያ ከእነዚህ ማጣሪያዎች ያነሰ ዋጋ ሊሰጥ ይችላል ወይ?›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

‹‹እኛ ሁልጊዜም የተሻለ ዋጋ ወደሚሰጠን ነው የምንሄደው፡፡ ከህንድ የሚመጣው የተጣራ ነዳጅ የሚቀንስ ከሆነ ከህንድ ነው የምናስገባው፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ በዋጋና የአገሪቱን የነዳጅ ጥራት መመዘኛዎች የሚያሟላ ከሆነ የታቀደው የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ለአገር ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

‹‹በዋጋና በጥራት ተወዳዳሪ መሆን ከቻለ ፕሮጀክቱን በደስታ እንቀበለዋለን፤›› ብለዋል አቶ ታደሰ፡፡ አቶ ዘመዴነህ በበኩላቸው ኩባንያቸው ተገቢውን ጥናት ማካሄዱን፣ ሊገነባ የታሰበው የነዳጅ ማጣሪያ ግዙፍና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚጠቀም በመሆኑ፣ የአሜሪካና አውሮፓን የነዳጅ ጥራት መሥፈርት የሚያሟላ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዝርዝር የሆነ የፋይናንስ ጥናት ሠርተናል፡፡ የተጣራ ነዳጅ ከሚገዛበት ዋጋ ባነሰ ማቅረብ እንደምንችል በሠራነው ጥናት አረጋግጠናል፤›› ብለዋል፡፡

የነዳጅ ማጣሪያው የፕሮጀክቱ የመጀመርያ ክፍል መሆኑን የገለጹት አቶ ዘመዴነህ ማጣሪያው ቡታ ጋዝ፣ ናፍጣ፣ ቤንዚን፣ ነጭ ጋዝ፣ የአውሮፕላን ነዳጅና ፔት ኮክ የሚባል ለፋብሪካዎች በነዳጅነት የሚያገለግል ግብዓት እንደሚያመርት ተናግረዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል የፔትሮ ኬሚካል ማምረቻ ኢንዱስትሪ እንደሚቋቋም አስረድተዋል፡፡

ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በሁለት መስኮች ተባብሮ መሥራት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በሚቋቋመው የነዳጅ ማጣሪያ የአክሲዮን ድርሻ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁለተኛ ከነዳጅ ማጣሪያው የሚመረቱ የነዳጅ ውጤቶችን በብቸኝነት ገዝቶ ለኩባንያዎች ሊያከፋፍል ይችላል፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ የፕሮጀክቱን ዝርዝር የሥራ ዕቅድ በቅርቡ ለመንግሥት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዕቅድ በ2010 ዓ.ም. ይፋ እንደሚደረግ፣ የነዳጅ ማጣሪያው ግንባታ በ2011 ዓ.ም. ተጀምሮ በ48 ወራት ይጠናቀቃል የሚል ዕቅድ መያዙን አቶ ዘመዴነህ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡

‹‹አራት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በጣም ትልቅ በመሆኑ ነገሮችን መልክ ማስያዝ፣ የፋይናንስና የሕግ ጉዳዮች ጥናት ረዥም ጊዜ ወስዷል፤›› ብለዋል፡፡

ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በቴክኖሎጂ፣ በመሠረተ ልማትና በሪል ስቴት ፕሮጀክቶች ኢንቨስት የሚያደርግ ሲሆን፣ አዋጭ ለሆኑ ቢዝነሶች በተለያዩ መንገዶች ፋይናንስ ያቀርባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሄሎ ካሽ ላይ ኢንቨስት ያደረገ ሲሆን፣ በቅርቡ ኩስቶ ከተባለ የሲንጋፖር ኩባንያና ከመሰቦ ሲሚንቶ ጋር በመተባበር የግንባታ ግብዓቶች የሚያመርት ኩባንያ በ70 ሚሊዮን ዶላር ለመመሥረት ተስማምቷል፡፡ በቀጣይ ሁለት አምራች ኩባንያዎች ለማቋቋም በመሥራት ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘመዴነህ፣ ኩባንያቸው ወደፊት በአምራች ኢንዱስትሪና በመሠረተ ልማት ላይ በስፋት መሰማራት እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡