Skip to main content
x
ለቂሊንጦ ቃጠሎ ዓቃቤ ሕግ የቆጠራቸው 28 ምስክሮች እንዳይሰሙ ትዕዛዝ ተሰጠ

ለቂሊንጦ ቃጠሎ ዓቃቤ ሕግ የቆጠራቸው 28 ምስክሮች እንዳይሰሙ ትዕዛዝ ተሰጠ

‹‹የምስክሮቹ አድራሻ ስለማይታወቅ በመላው አገሪቱ ተፈልገው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ይሰጥልኝ››

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ

‹‹ጥያቄው የተከሳሾችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላገናዘበ ነው››

ፍርድ ቤት

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ዓቃቤ ሕግ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ዓቃቤ ሕግ ክስ ለመሠረተባቸው እስረኞች በምስክርነት ከቆጠራቸው 85 ምስክሮች ውስጥ 28 ሳይሰሙ እንዲታለፉ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ለትዕዛዙ መነሻ የሆነው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ ያቀረበውን የወንጀል ክስ ክደው በመከራከራቸው፣ ምስክሮች ቀርበው እንዲሰሙ ችሎቱ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ፣ የመጀመርያ ቀጠሮ ከግንቦት 14 እስከ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ምስክሮች ተሰምተዋል፡፡ ቀሪ ምስክሮች እንዲቀርቡለት ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ በቂ ምክንያት መኖሩን አረጋግጦ ቀሪ ምስክሮች ለመስማት ከነሐሴ 1 እስከ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ችሎቱ በተከታታይ ቀጠሮ የቀረቡት ምስክሮች ተሰምተው እንዳበቁ፣ ዓቃቤ ሕግ ነሐሴ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በነበረው ቀጠሮ ቀሪ ምስክሮችን ለማቅረብና ለማሰማት ተለዋጭ ቀጠሮ መጠየቁን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከዓቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት በማግኘቱ ለሦስተኛ ጊዜ ቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ለመስማት ከታኅሳስ 23 እስከ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም፣ መስማት የቻለው አምስት ምስክሮች ብቻ ነው፡፡ ቀሪ 28 ምስክሮች አልቀረቡም፡፡ ፍርድ ቤቱ ለሦስተኛ ጊዜ በያዘው ቀጠሮ ይቀርባሉ ከተባሉት ምስክሮች እስከ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የቀረቡት አምስቱ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ፣ ከታኅሳስ 27 እስከ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአምስት ተከታታይ ቀናት ምስክሮች አለመቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው መጉላላት እንደደረሰባቸው፣ ከአምስት ወር በኋላ ዓቃቤ ሕግ የተሰጠውን ጊዜ እየተጠቀመበት እንዳልሆነ፣ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ሌላ ረዥም ቀጠሮ በመጠየቅ የሚደርስባቸውን እንግልትና ጉዳት ለመጨመር ስለሆነ፣ ፍርድ ቤቱ ምስክር ሊቀርብ ያልቻለ መሆኑን ተገንዝቦ በተሰሙት ምስክሮችና በቀረቡ ማስረጃዎች ብቻ ብይን እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ ይህንን የሚያልፈው ከሆነ መዝገቡን ዘግቶ ያሰናብተን በማለት አመልክተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ የተያዘለት ቀጠሮ ከምስክሮች ብዛት አንፃር ተከታታይ ሆነ እንጂ፣ እንደ አንድ ቀጠሮ የሚታይ መሆኑን ገልጿል፡፡ ቀጠሮው ሳያበቃ ከወዲሁ ምስክር አልቀረበም ተብሎ የሚሰጥ ትዕዛዝ ሊኖር እንደማይገባ አክሏል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በተከታታይ ቀጠሮዎች ምስክሮቹን እንደሚያቀርብ ያቀረበው አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት በማግኘቱ የተያዘው ቀጠሮ የተጠበቀ ቢሆንም፣ የቀረበ ምስክር ባለመኖሩ ዓቃቤ ሕግ ቀሪ 28 ምስክሮች እንዳሉት በድጋሚ በመግለጽ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ከምስክሮቹ ውስጥ በተራ ቁጥር 3ኛ እና 28ኛ ምስክሮች የፍርድ ቤት መጥሪያ በፖሊስ በኩል ደርሷቸው ለመቅረብ መተማመኛ ፈርመው የቀሩ በመሆኑናቸው ተገደው እንዲቀርቡ እንዲታዘዝለት፣ ሌላ አንድ ምስክር ደግሞ መቐለ ከተማ የሚገኙና ፖሊስ በስልክ አግኝቷቸው በሕመም ላይ በመሆናቸው መቅረብ እንዳልቻሉ ስለተገለጸለት፣ ምስክሩ በተለዋጭ ቀጠሮ በመጥሪያ እንዲቀርቡ እንዲታዘዝለት መጠየቁንም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ሌሎቹ ምስክሮች በማረሚያ ቤት በነበሩበት ጊዜ የሰጡት አድራሻ የማረሚያ ቤቱን በመሆኑ በማረሚያ ቤት የነበራቸውን ቆይታ ጨርሰው ሲወጡ ያሉበትን አድራሻ አፈላልጎ ለማቅረብ ፖሊስ የተቸገረ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ አፈላልጎ ማቅረብ ይቻል ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ባቀረበው አቤቱታ ላይ ተከሳሾቹ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው በችሎት በቃል መከራከሪያቸውን እንደገለጹት፣ ለዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በቂ ጊዜ ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ዓቃቤ ሕግ እየጠየቀ ያለው የቀሪ ምስክሮችን አድራሻ እንኳን ሳያውቅ፣ በመላ አገሪቱ እንዲፈለጉለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነሱ በተከሰሱበት ጉዳይ ዋስትና ተነፍገው በእስር ላይ ያሉ በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብታቸውን የሚያጣብብ ነው፡፡ ክርክሩ ለረዥም ቀጠሮ ከመቆየቱ አንፃር የት እንዳሉ የማይታወቁ ምስክሮችን በእስር ሆነው የሚጠብቁበት ምክንያት ስለሌለ፣ በወንጀል መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 94 መሠረት ዓቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት ከሌለው ተለዋጭ ቀጠሮ እንደማይሰጠው የተደነገገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ሕግ መሠረት ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም፡፡

በሌላ በኩል 3ኛ እና 28ኛ ተራ ቁጥር የተገለጹት ምስክሮች ለመቅረብ መተማመኛ ፈርመው ያልቀረቡትን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በያዘው የመጀመርያ ቀጠሮ ላይ አሳስቦ ቀርበው እንዲሰሙ ማድረግ ሲችል፣ ፍርድ ቤቱ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሥራ ፈትቶ እንዲቀመጥ ካረደገ በኋላ፣ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በተራ ቁጥር 30 የተጠቀሱ ምስክር የተባሉትና ከመቐለ ከተማ ይቀርባሉ ተብለው ያልቀረቡት በሕመም ምክንያት እንደሆነ ቢገለጽም፣ የቀረበ የሕክምና ማስረጃ ስለሌለና ይህም ዓቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት እንደሌለው የሚያሳይ በመሆኑ፣ ቀሪ ምስክሮችን የማሰማት መብቱ ታልፎ መዝገቡ ላይ በተሰሙት ምስክሮችና ሌሎች ማስረጃዎች ብይን እንዲሰጥላቸው መጠየቃቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙ በቀሪ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች አቀራረብ ላይ ያነሷቸውን ክርክሮች ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች፣ ከወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች አንፃር መመርመሩን ተናግሯል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(1) የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ የመሰማት መብት ያላቸው መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ይኸው መብት ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ውስጥ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀጽ 14(3) (ሐ) እንደሚያብራራው፣ የቀረበበት የወንጀል ክስ በሚታይበት ጊዜ፣ ማንኛውም ተከሳሽ አግባብ ባልሆነ ሁኔታ ሳይዘገይ የመዳኘት መብት እንዳለው ተመልክቷል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንዱ በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) ደግሞ ይህ ስምምነት የአሪቱ ሕግ አካል እንደሆነ በመደንገጉ፣ ከዚህም አንፃር ሲታይ ተከሳሾች ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው ሊጠበቅላቸው እንደሚገባ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾች ክሱን ክደው በመከራከራቸው ለሦስት ቀጠሮዎች ረዥምና በቂ የሚባሉ ጊዜዎች ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ተፈቅዶለት በርካታ ምስክሮችን አቅርቦ ማሰማቱን ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከክስ ማመልከቻው ጋር ያቀረበው የማስረጃ ዝርዝር ከተጠቀሱት 85 ምስክሮች ውስጥ ቀሪ 28 ምስክሮች ያልቀረቡለት መሆኑን ገልጾ፣ ተለዋጭ ቀጠሮ የጠየቀውና በቂ ምክንያት አለኝ በማለት ያቀረበው ቀሪ ምስክሮቹ ከነበሩበት ማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ አድራሻቸው ሊታወቅ ባለመቻሉ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ፖሊስ በመላው አገሪቱ ፈልጎ እንዲያቀርብለት ሲሆን፣ የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 94(2)(ለ) የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ሳይቀርቡ የቀሩ እንደሆነ የቀጠሮ ቀን የሚሰጥበት አንድ ምክንያት ቢሆንም፣ ከላይ ከተጠቀሱት ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንፃር ሲታይ፣ ገደብ የሌለውና ያለበቂ ምክንያት ቀጠሮ የሚሰጥበት እንደማይሆን ይደነግጋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በቂ ምክንያት ያቀረበባቸውና ቀጠሮ ሊሰጥባቸው የሚገቡት ለየትኞቹ ምስክሮች ነው የሚለውን ፍርድ ቤቱ ሲመለከት፣ ዓቃቤ ሕግ በምስክርነት ከቆጠራቸው ምስክሮች ውስጥ በተራ ቁጥር ሦስት እና 28 የተጠቀሱት ፖሊስ የፍርድ ቤት መጥሪያ ሰጥቷቸው፣ መጥሪያው የደረሳቸውና ፍርድ ቤት ለመቅረብ መተማመኛ ፊርማቸውን በማስቀመጥ አረጋግጠው ያልቀረቡት፣ በፖሊስ ወይም በዓቃቤ ሕግ ችግር ምክንያት አለመሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ደርሷቸው ላልቀረቡ ምስክሮች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ማስከበር ያለበት ራሱ በመሆኑ፣ ለሁለት ምስክሮች ተለዋጭ ቀጠሮ ለመስጠት በቂ ምክንያት መሆኑን እንደተገነዘበ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ለቀጣይ ቀጠሮ ፖሊስ 3ኛ እና 28ኛ ምስክሮችን በአድራሻቸው አፈላልጎ ለ24 ሰዓት አስሮ እንዲያቀርባቸውም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተራ ቁጥር 30 የተጠቀሱ ምስክር ስለመታመማቸው የሚያስረዳ ማስረጃ በዓቃቤ ሕግ በኩል ያልቀረበ በመሆኑ፣ ሌሎቹን ቀሪ ምስክሮች በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ካለፈው ቀጠሮ በኋላ የሰጠው የአምስት ወር ጊዜ፣ ቀሪዎቹን ለማቅረብ በጣም ሰፊና አፈላልጎ መጥሪያ ለማድረስ በቂ ጊዜ በመሆኑ፣ ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ ምስክሮችን ማፈላለግ ያልቻለ ከመሆኑም በላይ ወደፊትም ምስክሮች ትክክለኛ አድራሻቸው ስለማይታወቅ፣ በመላ አገሪቱ ተፈልገው እንዲቀርቡ የቀረበው የዓቃቤ ሕግ ጥያቄን አለመቀበሉን አስታውቋል፡፡ የተከሳሾችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላገናዘበ፣ ምስክሮችም የመገኘታቸው ዕድል ጠባብ በሆነበትና ተለዋጭ ቀጠሮ የሚሰጥበት በቂ ምክንያት ያለው ሆኖ ስላላገኘነው ቀሪ ምስክሮችን ዓቃቤ ሕግ የማሰማት መብቱ እንዲታለፍ ውሳኔ መስጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በዓቃቤ ሕግ የማስረጃ ዝርዝር ተራ ቁጥር 3 እና 28 የተጠቀሱት ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡