Skip to main content
x
የአምስት ዜና መዋዕሎች ትሩፋት

የአምስት ዜና መዋዕሎች ትሩፋት

በግእዝ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ሥፍራ ያለው የነገሥታት ውሎና ጉዞ የሚያትተው ዜና መዋዕል በተለይ ከ14ኛው ምዕት ጀምሮ ከሙያ መዋሉ ይገለጻል፡፡ ይሁን እንጂ ቀደም ባሉት ዘመናት በአክሱም ከመጀመርያ መቶ ዘመን ወዲህም ታሪክ ጠቀስ ጽሑፎች በድንጋይ ላይም ሆነ በብራና ላይ ለመጻፋቸው ማስረጃዎች አሉ፡፡ የንጉሥ ኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፎች በዘመኑ የተደረጉ ጦርነቶች፣ ገድሉን በንጉሡ ሥር የሚተዳደሩ አካባቢዎችና ኅብረተሰቡ ግዳይና፣ ምርኮው ሁሉ ተጽፈው ይታያሉ፡፡ እነዚህም የድንጋይ ላይ ጽሑፎች እንደ መጀመርያዎቹ ዜና መዋዕሎች የሚጠቅሷቸው ምሁራን አሉ፡፡ በሌላ በኩልም በቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች በተለይም በድጓ ውስጥ ከዘመኑ የአገሪቱና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጋር የተያያዙ ነጥቦች አሉበት፡፡ በአክሱምና በዛጉዌ ዘመነ መንግሥት ስለነበሩ ነገሥታት የተጻፉት እንደ ገድለ አብርሃ ወአጽብሐ፣ ገድለ ላሊበላና ገድለ ነአኹቶ ለአብ እንዲሁ ከታሪክ ጋር ተዘምዶ አላቸው፡፡ የታሪክ ጽሑፍ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ታሪክን የሚጽፍ ሰውን በመመደብና ‹‹ጸሐፌ ትእዛዝ›› በማለት ከሌሎች የጽሕፈት ሥራዎች ጋር ደርቦ የነገሥታቱን ታሪክ የሚጽፍ ክፍል የተቋቋመው በ14ኛው ምዕት ዓመት በነበሩት አፄ ዐምደ ጽዮን አማካይነት መሆኑም ይወሳል፡፡ ለኢትዮጵያ ታሪክ በምንጭነት የሚጠቀሱት ዜና መዋዕሎች እስከ 20ኛው ምዕት ድረስ በግእዝ ተጽፈዋል፡፡ በ19ኛው ምዕት በአፄ ቴዎድሮስ፣ በአፄ ዮሐንስና በአፄ ምኒልክ ዘመን በአማርኛም ተጽፏል፡፡ በግእዝ የተጻፉት ዜና መዋዕሎች በዋና ዋና የአውሮፓ ቋንቋዎች (ፖርቱጋልኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሣይኛ. . .) ከተተረጐሙ ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአማርኛ ባለመተርጎማቸው ግእዙንም ሆነ የባሕር ማዶ ልሳናቱን ባለማወቅ ታሪኩን ለማግኘት የተቸገሩ ቁጥር ስፍር የለውም፡፡ ከአፄ ዐምደ ጽዮን አንስቶ በርካታ ነገሥታት ዜና መዋዕላቸው በግእዝ ቋንቋ ተጽፎላቸዋል፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥንት ጽሑፎች ከፍተኛ ባለሙያ በነበሩት አቶ ዓለሙ ኃይሌ ትጋት ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ወደ አማርኛ አምስት ዜና መዋዕሎችን ተተርጉመዋል፡፡ እነርሱም የአፄ ገላውዴዎስ፣ የአፄ ሠርፀ ድንግል፣ የአፄ ሱስንዮስ፣ የአፄ ዘርዐ ያዕቆብና የአፄ በእደማርያም ናቸው፡፡ አቶ ዓለሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመጀመርያዎቹ ሁለቱን ዜና መዋዕሎች ከተጨማሪ ማብራሪያና የግርጌ ማስታወሻዎች ጋር በማዘጋጀት ለሁለተኛ እትም አቅርበዋል፡፡ በቅርቡም የኅትመት ብርሃን እንደሚያይ ይጠበቃል፡፡ ስለዜና መዋዕል ምንነት፣ ይዘትና ተያያዥ ጉዳዮች ከአቶ ዓለሙ ጋር የተደረገውን ምጥን ቆይታ ከነመጻሕፍቱ በማዛመድ ሔኖክ ያሬድ አጠናቅሮታል፡፡

ዜና መዋዕል እንዴት ይጻፋል?

ዜና መዋዕሎች እንዲጻፉ ሐሳቡ የሚመነጨው ከንጉሡ ነበር፡፡ ከዚያም ራሱ ጸሐፌ ትዕዛዙ ታሪኩን መጻፍ ይጀምራል፡፡ የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች የሚጽፉት ራሳቸው ያዩትን ወይም ከሌላ ሰው የሰሙትን መረጃዎች መሠረት በማድረግና የተለያዩ ጥቅሶችን ለማጠናከሪያ ወይም ለማስረጃ በማስገባት ነበር፡፡ የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች በአብዛኛው የሚጽፉት ታሪክ፣ የዓይን ምስክሮች ወይም የድርጊቱ ተሳታፊዎች ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ የአፄ ሱስንዮንስ ታሪክ ሁለተኛ ከፍልን የጻፈው አዛዥ ተክለ ሥላሴ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ ‹‹ይህን ነገር ራሴ በዓይኔ ዓይቼ የጻፍኩት ከሦስት ወር በኋላ ነው፤ የምዋሽ ከሆነም መሳፍንቱና መኳንንቱ፤ አገረ ገዥዎችና ሹሞች ይፍረዱብኝ?›› ይላል፡፡ ከአፄ አድያም ሰገድ ኢያሱ ታሪክ ውስጥም የጊቤን ዘመቻ ታሪክ የሚመለከተው ክፍል የጻፈው አዛዥ ሲኖዳም ከንጉሡ ጋር አብሮ ወደ ጊቤ የዘመተ መሆኑ በጽሑፉ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም ሌላ የዜና መዋዕል ጸሐፊዎች ከሌሎች ሰዎች ያገኙዋቸውንም መረጃዎች ይጠቀሙባቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ የሚጻፈውን ዜና መዋዕል ንጉሡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጸሐፊ እንዲያነብለት በማዘዝ ክትትል ያደርግ ነበር፡፡

ይዘታቸው

በእርግጥ በዘመኑ እሳቤ መሠረት የታሪክ ሒደት የሚወሰነው በነገሥታቱ እንቅስቃሴ ቢሆንም ይህን እንቅስቃሴ በጽሑፍ ለማንፀባረቅ ግን የጸሐፊዎችን ችሎታ ይጠይቃል፡፡ በዚህ አንፃርም ጸሐፊዎቹ የታሪኩን አቀራረብ በሚመለከት የአንዱን አቀራረብ ወይም አካሄድ ዘዴ ዝም ብሎ በደፈናው ከመከተል ይልቅ የየራሳቸውን አዲስ መንገድ ለመተለም ጥረት አድርገዋል፡፡ ስለዚህም ታሪክ ነገሥታቱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ የአፄ ዐምደ ጽዮን ዜና መዋዕል በንጉሡ ዘመን ስለተፈጸሙ ድርጊቶች በአጠቃላይ የተጻፈ ሳይሆን፣ ንጉሡ ከጠላቶቹ ጋር ያደረገውን የጦርነት ታሪክ እየዘረዘረ ጀግንነቱን የሚያነግሥ አንድ ወጥ የጀብድ ታሪክ ነው፡፡  የአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል በይዘቱም፣ በአቀራረቡም የተለየ ነው፡፡ እንደ አፄ ዐምደ ጽዮን ዜና መዋዕል አንድ ወጥ ሳይሆን ርዕስ ባላቸው ምዕራፎች የተከፋፈለና ትኩረቱንም ያደረገው በመንግሥት ግንባታና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ የአፄ ገላውዴዎስን ዜና መዋዕል ስንመለከት ደግሞ የንጉሡን አሟሟት አጉልቶ በማውጣት ሰማዕት መሆኑን ለማሳየት የሚጥር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህም ይህ መጽሐፍ የዜና መዋዕልንና የገድል አጻጻፍ ስልት አጣምሮ የያዘ ነው፡፡

ዜና መዋዕሎች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያንፀባርቁ ብቻ ሳይሆኑ ከዘመን ወደ ዘመን ለውጥ እያሳዩ መጥተዋል፡፡ በመጀመርያ ወቅት ላይ የተጻፉት ዜና መዋዕሎች ከአፈ ታሪክ ብዙም ያልተላቀቁ ስለነበር የተጋነነ አገላለጽ የሚበዛባቸውና የዘመን ቅደም ተከትልን እምብዛም የጠበቁ አልነበሩም፡፡ ከ16ኛው ምዕት ጀምሮ ግን ዜና መዋዕሎች በይበልጥ ተጨባጭና የዘመናትንና የቀናትን ቅደም ተከተል የጠበቁ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡ በሌላ በኩልም የነገሥታት ታሪኮች ለየብቻቸው የቆሙ ሳይሆኑ ተያያዥነትና ተወራራሽነት ያላቸው መሆኑን ጸሐፊዎች ቀስ በቀስ እየተገነዘቡ መሄድ ስለጀመሩ የነገሥታቱን ታሪክ በማዋሃድ አንድ ወጥ የሆነ የታሪክ መጽሐፍ ለመጻፍ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ምስክር የሚሆነው ‹‹አጭር ታሪከ ነገሥት›› የሚባለው የታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ በመጨረሻም በ18ኛው ምዕት መጨረሻ ላይ የማዕከላዊ መንግሥት እየተዳከመና የነገሥታቱም ኃይልና ዝና እየቀነሰ ሲሄድ የታሪክ አጻጻፉም እየወደቀ ሄደ፡፡

የአፄ ሱስንዮስ ታሪክ ጸሐፊ ‹‹የጊዜው ንጉሥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስፈጽማል፣ ትዕዛዙን ያስከብራል እንጂ በራሱ የሚሠራው የለውም›› እንዳለው፣ ታሪክን የሚሠራው እግዚአብሔር እንጂ ንጉሥ ወይም ሕዝብ አይደለም የሚል እምነት ጸሐፊዎቹ ነበራቸው፡፡ ይህም ጸሐፊው ታሪኩን የሚጽፈው የክርስትና ሃይማኖት መሠረተ ሐሳብ ተከትሎ መሆኑን ያሳያል፡፡  

በዜና መዋዕል ውስጥ ዋና ተዋናይ ሆኖ የሚቀርበው ንጉሡ ነው፡፡ የዘመኑ ታሪክ ጸሐፊ የንጉሡን እንቅስቃሴ መሠረት አድርጎ ስለነበር የሚጽፈው ከንጉሡ እንቅስቃሴ ውጭ የሆኑ ነገሮች ብዘም ትኩረት አያገኙም ነበር፡፡ ስለአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ስለተራው ሕዝብ አኗኗርና ባህል የሚገልጹ መረጃዎችን በዜና መዋዕሎች ብዙም አናገኝም፡፡ ዜና መዋዕሉ እንደ ሁኔታው ከንጉሡ ልደት፣ ዘውድ ከደፋበት ቀን፣ ወይም ከእሱ በፊት ከነበረው ንጉሥ የመጨረሻ ዓመታት ሊጀምር ይችላል፡፡

የዜና መዋዕል አጀማመር

ዜና መዋሎች መነሻቸውን የእግዚአብሔርን፣ የእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስን ስም በመጥራት የክርስትናን መሠረተ እምነትን በመግለጽ ያደርጋሉ፡፡ በቀጣይ ምዕራፍም ዜና መዋዕሉ ስለሚጻፍለት አፄ መግለጫቸውን እንደየግንዛቤያቸው መጠን ይጽፋሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የአፄ ገላውዴዎስን ዜና መዋዕል የጻፈው ጸሐፊ በምዕራፍ 2 ዘይቤ በደመቀ አጻጻፍ እንዲህ ጀምሮ ፈጽሞታል፡፡

በዚህም ከስኳርና ከማር ጣዕም ይልቅ፣ ለአፍና ለጉሮሮ የሚጥም መልካም ዜናን መጻፍ እንጀምራለን፡፡ በአንድነት እንደሚመሰገን ማህሌትና ወይን፣ ልብ ብለው ለሚያዳምጡ ተድላ ደስታን የሚያጎናጽፍ፣ ለሚሰሙት ጆሮዎችም የሚያስደንቅ ነው፤ ከስመ ገናናው፣ ከፍ ከፍ ካለው፣ ከተከበረው ንጉሥ ታሪክ የተነሣ፡፡ መታሰቢያው የተትረፈረፈ፣ ከአባቶቹ ሥራ ይልቅ ሥራው የተመሰገነ፣ ሥርዓተ መንግሥቱ ያማረ፣ ሕገ መንግሥቱ ንፁህ የሆነ፣ ምስክርነቱ የታመነ፣ አገዛዙ የቀና፣ ፍርዱ እውነተኛ፣ ትዕዛዙ ብሩህ የሆነ ነው፡፡ የሚቃወመው ሳይኖር ከበር አጀም እስከ በር ሰዓደዲን ድረስ፣ ጠላቶችን በማባረርና በማሸነፍ፣ በታላቋ በኢትዮጵያ፣ በደጋዋና በቆላዋ በተራራዎቿም ሁሉ፣ በገዥዎቿና በሠራዊቷ፣ በአዋቂዎቿና በሰነፎቿ፣ በደሴቶቿና በባሕሮቿ፣ በአውራጃዎቿና በቤተክርስቲያኖቿ ሁሉ፣ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የነገሠ፣ የማር  ገላውዴዎስን፣ የማሸነፍ ዜናውንና በጎ ሥራውን በሚገባ ቦታ እናስቀምጣለን፡፡ ይህ ቦታ የአባቶቹ ታሪክ ቦታ ነው፤ ዜና ልደቱንም እንደምን እንደሆነ እንናገራለን፡፡

ሥርዓተ ንግሡ ምን ይመስል ነበር?

በጥናቱና በመካከለኛው ዘመን ታሪክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ የሚቀመጠው ሥርዓተ ንግሡ የሚፈጸመው በአክሱም ነበር፡፡ የአፄ ሱስንዮስ ዜና መዋዕልም ስለዚህ ገጽታ ሳይዘግብ አያልፍም፡፡ እንዲህ ከትቧል፡፡

አፄ ሱስንዮስ በግራም በቀኝም ያለው አገር ለጊዜው ረግቶ ከተገዛላቸው በኋላ፣ በ1600 ዓ.ም. የዘውድ በዓላቸውን ለማክበር ወደ አክሱም ሄዱ፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ ታላቅነትና ጥንታዊነት ማስረጃ የሆነ›› ሲሉ የውጭ ምሁራን ሳይቀሩ የጻፉለትና የተደነቁለት የደመቀ ሥርዓተ መንግሥት ተደረገ፡፡ ዘውዱ፣ በትረ መንግሥቱ፣ ሰይፉ፣ ብርቅና ድንቅ በሆኑ በውድ ጌጣ ጌጥ የተሸለሙት ፈረሶች፣ በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት ያሸበረቁት ሹማምንት፣ በልዩ ልዩ አልባሳት የተንቆጠቆጡ የቤተ ክህነት ሊቃውንትና የጽዮን ቆነጃጅት፣ አጀቡ፣ ሠልፉ ልዩ ሆኖ በደስታ፣ በእልልታ፣ በሆታ፣ በእንቢልታ፣ በመለከት፣ በከበሮ፣ በጽናጽል በዝማሬ፣ በሽብሸባ፣ በውዳሴ፣ በቅዳሴ ሥርዓተ መንግሥቱ ተጠናቆ በእግዚአብሔር ስም ኢትዮጵያን እንዲመሩ ቃለ መሐላ ገቡ፡፡

የተጻፈበትን ዘመን የሚገልጹት እንዴት ነበር?

ዜና መዋዕል የተጻፈበት ዘመን የሚገለጸው በተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮችና በሥነ ፈለክ ጭምር ነው፡፡ እንደ አሁን ዘመን በአንድ የዘመን አቆጣጠር (ካሌንደር) በዓመተ ምሕረት ብቻ አይደለም፡፡ ለማሳያ የአፄ ገላውዴዎስ ዜና መዋዕልን ብንመለከት ይህን እናገኛለን፡፡

ይህ መጽሐፍ ሁለት ሥልጣን ባለው ከእስክንድር ዓመት ሰባት ሺሕ ሃምሳ ሁለት ዓመት (7052 ዓመተ እስክንድር)፣ ክብር ይግባውና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በአንድ ሺሕ አምስት መቶ ዓመት (1500 ዓ.ም.)፣ ከዓመት ሰማዕታት በአንድ ሺሕ ሁለት መቶ አርባ ዓመት (1240 ዓመተ ሰማዕታት)፣ በእስላሞች በዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሰባት ዓመት (957 ዓመተ ተንባላት)፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ገላውዴዎስ ተብሎ በተሰየመው በንጉሥ አጽናፍ ሰገድ መንግሥት ጊዜ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ሚናስ ተብሎ በተሰየመው በወንድሙ በአድማስ ሰገድ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ተፈጸመ፡፡ መጀመርያውም መጨረሻውም ለሮማውያን ሦስተኛ በሆነው በወርኃ ኅዳር ነው፤ ይኸውም በተንባላት በስድስተኛው ወር በጅማድ አልአኸር ነው፡፡ በአምስተኛው ዕለት ተፈጸመ፡፡ ያም በመጋቢት 23 በረቡዕ ዕለት፣ በማኅፈደ ሐሙስ ፀሐይ በትልልቅ መዓርጋት በ23 መዓርግ ሳለ፡፡ ሁሉን በየወገኑ ላኖረ ክቡርና ልዑል ለሚሆን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡

ሙሾ በዜና መዋዕል

ነገሥታት ዜና ዕረፍታቸው ሲሰማ ሐዘን ይሰፍናል፡፡ ከዚህ አንፃር ዜና መዋዕል ጸሐፊም ሐዘኑን በድርሰቱ ይገልጻል፡፡ ሰቆቃውን (ለቅሶውን) በጽሑፉ ያንፀባርቃል፡፡ በመዝሙረ ዳዊት አምሳልም በዕብራውያን የፊደል ገበታ ልክ በአበገደ ቅደም ተከተል አ አሌፍ፣ በ ቤት፣ ገ ጋሚል፣ ዳ ዳሌጥ እያለ እስከ 22ኛው ፊደል ይዘልቃል፡፡ ለማሳያ የአሌፍ እነሆ፡፡

ስለጌታዬ ክቡር ገላውዴዎስ ፍቅር፣ በዕብራውያን ሃያ ሁለቱ ፊደላት ርእስ ላይ፣ የሰቆቃው (ለቅሶ) መጽሐፍ ጻፍኩ፡፡ አሌፍ፡፡ የጌታዬን የገላውዴዎስን የነብሱን  ሞት፣ ማን በነፍሴ ላይ ባመጣ? ማንስ ወደ ውጭ የወደቅሁ እንድሆን ባደረገኝ፣ ወዮልን፣ ወዮታ አለብን፣ የንጋት ኮከብ መግቢያውን ዐወቀ፡፡ የምሽት ኮከብ ጠፋ፡፡ ቀን የማናውቀው ሌሊት ሆነ፣ ጨለማም ያልተለመደ ሆኖ መጣ፡፡ ሰውንና እንስሳን ጋረደ፡፡ ከእንግዲህ ጦርነትን ድል የሚያደርግልን የለም፡፡ የኃይላችን መልአክ አሁን ወደ ምድር ንቃቃት ገባ፡፡ የአርበኞቻችን አዝማችም ከከተማችን መካከል ጠፋ፡፡