Skip to main content
x
ያልተጠበቀው የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ የመቀራረብ ጅምር
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ያልተጠበቀው የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ የመቀራረብ ጅምር

ለዓመታት አሜሪካን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚያስችሉ የኑክሌር መሣሪያዎችን ሠርቻለሁ በማለትና የተለያዩ የኑክሌር አረር የተገጠመላቸው ሚሳይሎችን ስትሞክር የቆየችው ሰሜን ኮሪያ፣ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት ማሳየቷ ብዙዎች በግርምትና በአድናቆት የተመለከቱት ሁነት ነበር፡፡

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከቤተሰቦቻቸው የወረሱትን ሥልጣን ከተረከቡ ጀምሮ ሰሜን ኮሪያ ከቻይናና ተመሳሳይ ስም ከምትጋራት ደቡባዊ ጎረቤቷ ጋር  ከንግድና ከአየር በረራ ግንኙነቶች የዘለለ፣ ከሌላ የዓለም አገሮች ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ያደረገችው ጥረት እምብዛም አይታይም፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ያሏት ኤምባሲዎቿም የአቋም መግለጫ ከማውጣትና በስንት ጊዜ አንዴ የሚጠየቁ የቪዛ ጥያቄዎችን ከማስተናገድ ያለፈ ሚና ሲኖራቸው አይታይም፡፡ መሪዋም በሌላ አገሮች ጉብኝቶችን ሲያደርጉ አይታዩም፡፡

የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡንግ
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡንግ

 

በዚህ የተገለለ ኑሮዋ ሰሜን ኮሪያ እንደ በጥባጭ ትታይለች፡፡ በአሜሪካና በሩቅ ምሥራቅ የአሜሪካ ግዛት (የጦር ቀጣና) በሆነችው ጉዋም፣ እንዲሁም የአሜሪካ አጋር በሆኑት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ላይ ከዛሬ ነገ ኑክሌር ትጥላለች የሚል ሥጋት እንጂ፣ ላትጥል ትችላለች የሚል ግምት እንኳን አልነበረም፡፡

የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ፍጥጫ ከዚህ አልፎ የሁለቱ አገሮች መሪዎች ‹‹በጠረጴዛዬ ላይ የኑክሌር መተኮሻ ቁልፍ አለ›› እስከመባባል የደረሱ ማስፈራራቶች ተሰምተውም ነበር፡፡

ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የሚሳይል ሙከራ ማድረጓ ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከቷታል
ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የሚሳይል ሙከራ ማድረጓ ከአሜሪካ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ከቷታል

 

‹‹ሰሜን ኮሪያ በእሳትና በፍም እንገናኛለንና አርፈሽ ተቀመጪ›› ሲሉም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማስፈራሪያ መልዕክት እስከ ማስተላለፍ ያደረሷቸው፣ የሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የኑክሌር ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ አልፈውም የጦር መርከቦችን ወደ ጉዋምና አካባቢው በመላካቸው፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ የኑክሌር ጦርነት ከዛሬ ነገ ተጀመረ የሚል ሥጋት አጭረው እንደነበርም ይታወሳል፡፡

ይሁንና እ.ኤ.አ. ከፌብሩዋሪ 9 እስከ 25 ቀን 2018  በፒዮንግቻንግ የተካሄደው የበጋ የኦሎምፒክ ጨዋታን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃዬ ኢን እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙበት ክስተት መሆኑን፣ በሁለቱ ተቀናቃኝ አገሮች መካከልም ውይይት ማስጀመር የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደተጠቀሙበት ታዛቢዎች ያወሳሉ፡፡

የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ትብብር ሰሜን ኮሪያን ለህልውናዋ ያሠጋታል
የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ትብብር ሰሜን ኮሪያን ለህልውናዋ ያሠጋታል

 

በበጋው ኦሎምፒክ ላይ የሁለቱ ኮሪያዎች ቡድኖች በአንድነት ተመሳሳይ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የተገኙ ሲሆን፣ ተመሳሳይ የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር በጋራ ዘምረዋል፡፡ ይህ እንዲሆንም የመጀመርያውን ጥያቄ ያቀረበችው ሰሜን ኮሪያ ስትሆን፣ ደቡብ ኮሪያ ደግሞ ሁለቱን አገሮች አንድ ላይ ለማምጣት እንደ ተጠቀመችበት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

ሆኖም አሜሪካና ሌሎች የምዕራብ አገሮች ለሰሜን ኮሪያ ይህን ዓይነት ዕድል መስጠት ለአምባገነናዊው መንግሥት ዕውቅና መስጠት ነው ብለው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ነበር፡፡

አሁን ግን ይህ ሁኔታ እየተቀየረ ያለ ይመስላል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር የጦር መሣሪያዎቿን ለማስወገድና ከአሜሪካ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛነቷን ገልጻለች፡፡

‹‹ለደኅንነቴ የሚያሰጋኝ ነገር እስከሌለና በኮሪያ ላይ የተጋረጠው የወታደራዊ ሥጋት መፍትሔ እስከተበጀለት ድረስ የኑክሌር መሣሪያ መታጠቅ ፍላጎቴ አይደለም፤›› ስትል ሰሜን ኮሪያ ለውይይት ክፍት መሆኗን፣ ከሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡንግ ጋር የተወያዩት የደቡብ ኮሪያ የደኅንነት ኃላፊ ቹንግ ኢ-ዮንግ ገልጸዋል፡፡

ኪም ጆንግ ኡን ከቹንግ ኢ-ዮንግ ጋር ፊት ለፊት ያደረጉት ውይይት፣ ፕሬዚዳንቲ ሥልጣን ከጨበጡበት እ.ኤ.አ. 2011 አንስቶ ከደቡባ ኮሪያ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው የተነጋገሩበት የመጀመሪያው ስብሰባ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡

የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንቶች ተገናኝተው ሊነጋገሩ መሆናቸውን በማስመልከት የወጡ ዘገባዎች የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል
የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንቶች ተገናኝተው ሊነጋገሩ መሆናቸውን በማስመልከት የወጡ ዘገባዎች የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል

 

ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ ሊያደርጉት ያቀዱት ወታደራዊ ልምምድ ለደኅንነቴ ሥጋት ነው በማለት ተደጋጋሚ የኑክሌር ሙከራዎችን ስታደርግ የነበረው ሰሜን ኮሪያ፣ አሁን በምን ምክንያት የኑክሌር ትጥቅ እስከ መፍታት ድረስ ሊያደርሳት የሚችል ስምምነት ለማድረግ እንደተዘጋጀች በግልጽ የተነገረ ነገር የለም፡፡

ሆኖም በተደጋጋሚ የተጣሉትና ከተለያዩ የዓለም አገሮች ተለይታ እንድትኖር ያደረጓት ማዕቀቦች፣ ሰሜን ኮሪያ ሳትወድ በግድ ወደ ጠረጴዛው እንድትመጣ አድርገዋታል የሚሉ አሉ፡፡ ሰሜን ኮሪያ ለኑክሌር መሣሪያ ምርቶቿን ገቢ ከምታገኝባቸው ምንጮችና ከንግድ አጋሮቿ ጋር የነበራት ግንኙነት እንዲቋረጥ መደረጉና፣ ማንኛውም አገር ከሰሜን ኮሪያ ጋር የንግድ ግንኙነት ካደረገ የማዕቀቡ ፍላፃ እንደሚያገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአሜሪካ የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች አገሪቱን አዳክመዋታል፡፡

ምንም ሆነ ምን የሰሜን ኮሪያ ወደ ድርድር የመምጣት ፍላጎትን በበጎ ጎኑ የተመለከቱት ብዙ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2020 ምርጫ ካሁኑ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ሰላም ትፈልጋለች፤›› ሲሉ ለተሰበሰቡት ደጋፊዎቻቸው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ተመልከቱ ምን ሊከሰት እንደሚችል ማን ያውቃል? ስብሰባውን በደቂቃዎች ረግጬ ልወጣ አልያም ዓለም ዓይቶት የማያውቀውን ዓይነት ስምምነት ልፈጽም እችላለሁ፤›› ሲሉ ደጋፊዎቻቸውን አስፈንድቀዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያ የውይይት ጥያቄና የኑክሌር ትጥቅ የመፍታት ሐሳብ በአሜሪካ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ ቀጥተኛ የሆነ ንግግር ከመጀመሩ በፊት ግን ‹‹ተጨባጭ የሆነ›› ኑክሌር የማስወገድ እንቅስቃሴን እስካላየ ድረስ ንግግሩ ሊጀመር አይችልም ሲል ኋይት ሀውስ፤›› አሳስቧል፡፡

ባለፈው ወር ደቡብ ኮሪያን ከጎበኙ በኋላ መግለጫ የሰጡት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ፣ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ሙሉ በሙሉ የኑክሌርና የባለስቲክ ሚሳይል ፕሮግራሟን ለማቆም ግልጽ ዕርምጃዎችን እስካልወሰደች ድረስ፣ የኢኮኖሚና የተለያዩ ተዕዕኖዎችን ለማሳደር ያሉንን አማራጮች በሙሉ እንጠቀማለን፤›› ሲሉ የአገራቸውን አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

ይህ የውይይት ዕርምጃ እጅግ እየተደነቀ ያለ የሰሜን ኮሪያ ጅምር ሲሆን፣ ውይይቱ ከተሳካም የደቡብ ኮሪያ መሪ ሙን ስኬት እንደሆነ በርካታ ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡ (ጥንቅር በብሩክ አብዱ)