Skip to main content
x
በፈታኙ የዓለም የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የቭላድሚር ፑቲን ድል
ቭላድሚር ፑቲን ለመጪዎቹ ስድስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ለመቆየት ምርጫውን በከፍተኛ ድምፅ አሸንፈዋል

በፈታኙ የዓለም የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የቭላድሚር ፑቲን ድል

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ቭላድሪሞቪች ፑቲን እ.ኤ.አ. ማርች 18 ቀን 2018 እንዲካሄድ ቀን የተቆረጠለትን ምርጫ እንደሚያሸንፉ ሳይታለም የተፈታ እንደሆነ የተረዱት ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን፣ የምርጫውን ውጤት በቅድመ ትንበያ የድምፅ መለኪያዎች ተንብየው የፑቲንን ማሸነፍ ካወጁ ቆይተዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃኑ ውጤቱን ከተነበዩ በኋላ ከምርጫው ይልቅ ትኩረታቸውን የሳበው፣ ከ300 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ግምት ያላቸውን 200 የሚሆኑ የወርቅ ጥፍጥፎች ከሳይቤሪያ አውሮፕላን ማረፊያ ለመብረር ሲነሳ የበተነው አውሮፕላን ነበር፡፡ አውሮፕላኑ 9.3 ቶን የሚመዝኑ የወርቅ ጥፍጥፎችን ይዞ ለበረራ የተነሳ ቢሆንም፣ ከክብደቱ የተነሳ ወርቁን በመንደርደሪያውና በአካባቢው እየበተነ ተነስቶ ከጥቂት ኪሎ ሜትሮች በኋላ በቅርብ ባገኘው የአውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተገዷል፡፡

በግምታቸው መሠረት ፑቲን ያሸንፋሉ ብለው የተቀመጡት መገናኛ ብዙኃን ግን፣ ምርጫው ሲካሄድ ዓይናቸውን ከክሬምሊን ላይ ሊያነሱ አልቻሉም ነበር፡፡

በፈታኙ የዓለም የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የቭላድሚር ፑቲን ድል
ለሩሲያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ክሴኒያ ሶብቻክ ድምፅ ሲሰጡ

 

ከምርጫው አስቀድመው ጠንካራ የሚባሉ ተቃዋሚያቸውን በዘዴ አስወግደው ብቻቸውን የሚጫወቱበትን ሜዳ በማመቻቸት የሚተቹት ፑቲን፣ ከምርጫ በፊት በተደረጉ ትንበያዎች ምርጫውን 69 በመቶና ከዚያ በላይ በሆነ ውጤት ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ግምት ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን፣ ፑቲን 77 በመቶ በሆነ ውጤት ምርጫውን ማሸነፋቸው እምብዛም እንደ አዲስ ዜና አልታየም፡፡ በምርጫው የሚሳተፉ ጠንካራ ተቃዋሚዎች እንዳይኖሩ ለምን ሆነ ተብለው ፑቲን ሲጠየቁም፣ ‹‹የእኔን ተቀናቃኞች ማፍራት የእኔ ሥራ አይደለም፤›› ብለው ነበር የመለሱት፡፡

በምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገቡ መራጮች መካከልም 68 በመቶ ያህሉ ወጥተው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ያኔ ይመሩት በነበረው የሩሲያ ኅብረት ፓርቲ ውክልና ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው መንበረ ሥልጣኑን ቢቆናጠጡም፣ በ2017 ግን ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ በግላቸው እንደሚሆን ሲያስታውቁ የእርሳቸውን የምርጫ ዘመቻና የተለያዩ የምርጫ ዝግጅቶችን ለማድረግ ከ600 በላይ የሆኑ ግለሰቦችን በዙሪያቸው ሰብስበው ነበር፡፡

ፑቲን ለቀጣይ ስድስት ዓመታት የዓለም ትልቋን አገር ለመምራት የሚያስችላቸውን ምርጫ ያሸነፉበት ወቅት ሩሲያ ከምዕራባውያን አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በሻከረበት ጊዜ መሆኑ፣ ለፕሬዚዳንቱ ፈተና ሊደቅንባቸው ይችላል የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ ወጣም ወረደ ግን ቭላድሚር ፑቲን ከጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል በሩሲያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳደሩ መሪ እንደሆኑና በዚህም ከሩብ ምዕተ ዓመት የዘለለ ተሰሚነት ማግኘት የቻሉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡

በፈታኙ የዓለም የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የቭላድሚር ፑቲን ድል
ከ73 ሚሊዮን በላይ ሩሲያዊያን ድምፅ በሰጡበት ምርጫ ቭላድሚር ፑቲን ከ76 በመቶ በላይ ድምፅ ማግኘታቸው ተገልጿል

 

ቭላድሚር ፑቲን እ.ኤ.አ. በ2024 ሁለተኛውን የምርጫ ዘመናቸውን ሲያጠናቅቁ 71 ዓመት የሚሆናቸው ሲሆን፣ በእነዚህ ስድስት ዓመታት ሩሲያ ከምዕራባውያን የተሻለ ወታደራዊ ቁመና እንዲኖራት ለማድረግና የሕዝቦችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጡ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በቀዩ አደባባይ በፕሬዚዳንታቸው ድጋሚ መመረጥ ጮቤ የረገጡ ደጋፊዎቻቸው በተሰበሰቡበት ሥፍራ፣ ባለ ዘርፍ ካቦርታቸውን ደርበው የተገኙት ፑቲን፣ የሕዝቡ ምርጫ ፕሬዚዳንቱ እስከ ዛሬ ለሠሯቸው ሥራዎች ዕውቅና መስጠት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

‹‹ይኼንን አንድነት መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለእናት አገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እናስባለን፤›› ሲሉ ደጋፊዎቻቸው በደስታ በማስጨፈርና ከእርሳቸው እየተቀበሉ ‹ራሺያ› እያሉ እንዲዘምሩ አድርገዋቸዋል፡፡

ፑቲን ከአሜሪካ ጋር በምርጫ ጣልቃ ገብነት፣ ከእንግሊዝ ጋር ደግሞ በቀድሞ የሩሲያ ሰላይና በልጁ ላይ በተደረገ የነርቭ መርዝ ጥቃት ጫፍ የደረሰ የዲፕሎማሲ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከአሜሪካ 45፣ ከእንግሊዝ ደግሞ 23 የሩሲያ ዲፕሎማቶች ተባረው ሩሲያም ተመሳሳይ ዕርምጃ ወስዳ ነበር፡፡ ይሁንና ይኼ የዲፕሎማሲ ጦርነት ፑቲን በዱማ (ፓርላማ) ፊት ቀርበው፣ በምርጫ ዘመናቸው ማጠናቀቂያ ዓመት ብሔራዊ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ይፋ ያደረጓቸው የትኛውንም የዓለም ክፍል ሊመቱ የሚችሉና የአየር መከላከያ ሊለያቸው በማይችሉ ሚሳይሎች ምክንያት፣ ከምዕራባውያን አገሮች ጋር ያለውን ውጥረት በእጅጉ እንዲካረር አድርጎታል፡፡

በፈታኙ የዓለም የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የቭላድሚር ፑቲን ድል
ፕሬዚዳንት ፑቲን ድምፅ ሲሰጡ

 

ይሁንና ፑቲን አንድም የተመረጡት በምዕራባውያን አገሮች ላይ ያላቸው ጠንካራ አቋምና የሩሲያን የበላይነት ለማስጠበቅ የሚያደርጉት ጥረት ተወዳጅ ስላደረጋቸው እንደሆነም ይነገራል፡፡ ፑቲን የአሜሪካ የዓለም አመራር እንዳበቃለትና ቀጣዩን የዓለም የአመራር ሥፍራ መረከቢያ ጊዜ እንደሆነም ተረድተዋል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ብዙ ናቸው፡፡ ለዚህም እንደማመላከቻ የሚነሳው ሩሲያና ቻይና በተለይ ከዩክሬን ውዝግብ በኋላ በእጅጉ መቀራረባቸውን ነው፡፡

ምርጫው እንደተጭበረበረና የተለያዩ ግለሰቦች በምርጫ ኮረጆዎች ውስጥ የመምረጫ ወረቀቶችን ሲያጭቁ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በብዛት መሠራጨታቸውን በማንሳት፣ ምርጫው ተዓማኒ አይደለም የሚሉ ዘገባዎች በስፋት እየወጡ ሲሆን፣ ያም ሆነ ይህ ማዕከላዊው የምርጫ ኮሚሽን አብዛኛዎቹን ቅሬታዎች እርባና ቢስ ብሎ የምርጫውን ሒደት ፍትሐዊ ነው እንደሚለው ይጠበቃል፡፡

የምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኃን ፑቲን እንደሚያሸንፉ ሳይታለም የተፈታ እንደሆነ ካረጋገጡ በኋላ ትኩረታቸው የነበረው፣ ፑቲን ይኼኛው የምርጫ ዘመናቸው ሲያልቅ በድጋሚ ይወዳደሩ ይሆን የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡

ከምርጫው ውጤት በኋላ ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቁት ፑቲን፣ ‹‹መቶ ዓመት እስከሚሆነኝ በሥልጣን መቆየት የምፈልግ ይመስላችኋል? በፍጹም፤›› ሲሉ ነበር የመለሱት፡፡

ፑቲን የሩሲያ ወጣቶች ‹ጀግና› ናቸው፡፡ ብዙዎችም አርዓያ አድርገው የሚያዩዋቸው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በወጣቶች ዘንድ ያላቸው የተቀባይነት ደረጃ 86 በመቶ ነው፡፡

የቀድሞው የኬጂቢ ኮሎኔል የነበሩት ፑቲን አገራቸውን ይወዳሉ ብለው የሚያምኑ ወጣቶች የእርሳቸውን አቅጣጫ ያደንቃሉ፡፡ ከአውሮፕላን እስከ ባህር ሰርጓጅ መርከብ ማንቀሳቀስ የሚችሉት፣ ከበረዶ ላይ መንሸራተት እስከ ካራቴ ስፖርቶችን አሳምረው የሚጫወቱት ፑቲን የወጣቶች ምሳሌ ተደርገው ቢወሰዱ እምብዛም አይደንቅም፡፡

እሳቸው ሥልጣን ከያዙ በኋላ የሩሲያውያን የኑሮ ደረጃ በእጅጉ ተሻሽሏል፡፡ ወጣቶች የዛሬ አሥር ዓመት ከነበረው የተሻለ ዕድል አላቸው፡፡

ፑቲን ሕዝባዊ በዓላትን ከሕዝቡ ጋር ያሳልፋሉ፡፡ በጥምቀትና በፋሲካ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ከምዕመናን እኩል የሥነ ሥርዓት ተካፋይ ሆነው ይውላሉ፡፡ ለሕዝቡም ቅርብ ስለሆኑ ‹‹የእኛ ነው›› የሚል ስሜት በብዙኃኑ ዘንድ ፈጥረዋል፡፡

የዓለም አመራር እየተቀያየረና ኃይልነትም ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እየዞረ ባለበት ወቅት በድጋሚ የተመረጡት ፑቲን፣ በስድስት ዓመታት ውስጥ ለሩሲያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን አኑረው ሊያልፉ ይችላሉ የሚለው የብዙዎች ትኩረት ሆኗል፡፡ 

በፈታኙ የዓለም የፖለቲካ ውጥንቅጥ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የቭላድሚር ፑቲን ድል
ሩሲያውያን ድምፃቸውን እየሰጡ