Skip to main content
x
[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

[ክቡር ሚኒስትሩ ከቀድሞ ጓደኛቸው ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • አንተ ሰውዬ አለህ እንዴ?
 • አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምንድነው ዓይቼህ አላውቅም?
 • ያው ሥራ ስለሚበዛብኝ ነው፡፡
 • ድሮም የአስተማሪ ነገር ይኼ ነው ትርፉ፡፡
 • የአስተማሪ ነገሩን እንኳን ተውት፡፡
 • ምንድነው እንደዚህ ያጠፋህ?
 • እርስዎም ሚኒስትር ሲሆኑ ተራራቅን፡፡
 • ከእኔ በላይ የጠፋኸው ግን አንተ ነህ፡፡
 • አዲስ ዘርፍ ውስጥ ገብቼ ነዋ፡፡
 • ማስተማሩን ተውኩት እንዳትለኝ?
 • እሱን ካቆምኩ ቆየሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ምን ተገኘ?
 • ነጋዴ ሆኛለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ነጋዴ ሆነህ ሸቀጥ ማስመጣት ጀመርክ?
 • የሸቀጥ ንግድ ሳይሆን በሙያዬ የማማከር ሥራ ጀምሬያለሁ፡፡
 • እሱን ቢዝነስ ነው እስካሁን ያልደፈርኩት፡፡
 • ያው ዝም ብሎ የሚሠራ ቢዝነስ አይደለም፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ዕውቀት ይፈልጋል ሥራው፡፡
 • አንተ ዕውቀቱ የለህም እያልከኝ ነው?
 • እርስዎማ ይመከራሉ እንጂ አያማክሩም፡፡
 • አንተ አሁንም ቀልደኛ ነህ ማለት ነው፡፡
 • ወድጄ አይደለም ቀልደኛ የሆንኩት፡፡
 • እንዴት ነው የማማከር ሥራው ግን?
 • ትንሽ ከባድ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለምን ይከብዳል?
 • የእኛ ሥራ በእናንተ ፖሊሲ ላይ መሠረት ያደረገ ነዋ፡፡
 • ታዲያ የእኛ ፖሊሲ ምን ይወጣለታል?
 • እኔ በዋናነት የምሠራው ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ነው፡፡
 • ታዲያ አገራችን እኮ ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ናት፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ኩባንያዎች የሚቀጥሩዋቸውን ሰዎች ለማግኘት በጣም ይቸገራሉ፡፡
 • ምን እያልክ ነው ሰውዬ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ስንትና ስንት ሥራ አጥ ባለበት አገር የሚቀጠር ሰው ጠፋ ስትል አታፍርም?
 • እንደ እሱ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስማ አገሪቱ እኮ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳላት ረሳኸው?
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • በዚያ ላይ ከሁለት ሦስተኛ በላይ ወጣት የተሰበሰበባት አገር ነች፡፡
 • እነሱ ለመቅጠር የሚፈልጉት መሥፈርት ወጣት መሆን ብቻ አይደለም፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ኩባንያዎቹ የሚፈልጉት የተማረ የሰው ኃይል ነው፡፡
 • ሥራ አጡ ሁላ የተማረ አይደል እንዴ?
 • እ. . .
 • ያውም ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያስተማርነው ሥራ አጥ እኮ ነው ያለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ተማረ የሚባለው ወጣት እኮ በጣም ያሳፍራል፡፡
 • እንዴት?
 • እኔም ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ያቆምኩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡
 • የምትለው አልገባኝም?
 • የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዕውቀታቸው እኮ አሳፋሪ ነው፡፡
 • ስማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የተመሰገንበትን የትምህርት ስኬት ስታጣጥለው አታፍርም?
 • ክቡር ሚኒስትር በየመንደሩ የተቋቋሙት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያወጡት ትውልድ የተማረ የሰው ኃይል ነው ማለት ይከብዳል፡፡
 • ታዲያ ምን ይባል?
 • የተማረረ የሰው ኃይል!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለአንድ ደላላ ወዳጃቸው ይደውላሉ]

 • አንተ ሰውዬ ትንሽ አልጠገብክም?
 • ምን አደረኩ ክቡር ሚኒስትር?
 • ብደውል ብደውል አታነሳም፡፡
 • ስብሰባ ውስጥ ሆኜ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የትኛው ስብሰባ?
 • መቼም የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ወይም ምክር ቤት ስብሰባ አልልዎትም፡፡
 • እሱን ስብሰባም ለመካፈል አስበሃል?
 • ኧረ ከውጭ ከመጡ ኢንቨስተሮች ጋር ስብሰባ ይዤ ነው፡፡
 • እኔም የደወልኩልህ ስለኢንቨስትመንት ላወራህ ፈልጌ ነው፡፡
 • ምን ዓይነት ኢንቨስትመንት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰሞኑን ከተዋማ እንዴት በዋጋ ንረት እየታመሰች መሆኑን መቼም ሰምተሃል?
 • የምን የዋጋ ንረት?
 • ይኸው የብረት ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል፡፡
 • እሱን እንኳን ሰምቻለሁ፡፡
 • የሲሚንቶንም ነገር እየተከታተልከው ነው፡፡
 • የኮንስትራክሽን ዘርፉ ሊቃወስ ይችላል፡፡
 • ስማ ቢዝነሱ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ቀውስ ሲመጣ ለእኛ ይመቻል አላልኩህም?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለሕዝቡ አማራጭ ሐሳቦችን ይዘን መቅረብ እንችላለን፡፡
 • ምን ዓይነት አማራጭ?
 • ለምሳሌ የብረት ዋጋ አይነኬ እየሆነ ነው፡፡
 • ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?
 • አየህ አሁን በአንድ ለአምስት ማደራጀት እንችላለን፡፡
 • ማንን?
 • ቆራሌዎችን፡፡
 • ምን?
 • ቆራሌዎችን አደራጅተን ውድቅዳቂ ብረቶችን ማሰባሰብ እንችላለን፡፡
 • ከዚያስ ክቡር ሚኒስትር?
 • ከዚያማ ይኼንን ውድቅዳቂ ብረት አቅልጠን ለብረት እጥረቱ ጥሩ መፍትሔ ማምጣት እንችላለን፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ሁሌም አደንቅዎታለሁ፡፡
 • ሁሌም በችግር ውስጥ የሚፈጠረውን አጋጣሚ ነው ማየት ያለብህ፡፡
 • እኔ ግን የሚገርመኝ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡
 • ምንድነው የሚገርምህ?
 • እንደ እርስዎ ዓይነት አባ መላ ኢሕአዴግ ውስጥ እያለ እንዲህ መተራመሱ ይገርመኛል፡፡
 • አይሰሙማ፡፡
 • እ. . .
 • ሁሌም የምነግራቸውን ነገር አይሰሙም፡፡
 • ለዚህች አገር ችግር እኮ እንደ እርስዎ ዓይነት አባ መላ ነው የሚያስፈልገው፡፡
 • ብዬ ነበር ሰሚ አጥቼ ነው፡፡
 • እርስዎን ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያደርጉዎት እኮ ሁሉም ጥያቄ መፍትሔ ያገኝ ነበር፡፡
 • እኔም አድርጉኝ ብዬ ነበር፡፡
 • እርስዎማ ቢሆኑ እኛም እንከብር ነበር፡፡
 • ምን ታደርገዋለህ?
 • ለእኛ ግን ሁሌም ጠቅላይ ሚኒስትራችን እርስዎ ነዎት፡፡
 • እናንተ እነማን ናችሁ?
 • ልማታዊ ደላሎች!

[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ አንድ ብሎገር ይመጣል]

 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎን ለማግኘት እኮ በጣም ተቸገርኩ፡፡
 • ለመሆኑ ለምን ፈልገኸኝ ነው?
 • ያው በወቅታዊ የአገሪቷ ሁኔታ ላይ ለማውራት ነዋ፡፡
 • ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ስትል አልገባኝም?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ እኮ ቀንደኛ ደጋፊ ነኝ፡፡
 • የማን?
 • የሥርዓቱ ነዋ፡፡
 • ታዲያ ምን ይጠበስ?
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር አገሪቷ በቀጣይ ስለምትጓዝበት መንገድ እንድናወራ ብዬ ነው?
 • አገሪቷ የምትጓዝበትን መንገድ ቀያሽ ማን አደረገህ?
 • እኔን አያውቁኝም እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • በሚገባ ነው ጠንቅቄ የማውቅህ፡፡
 • ይኸው ክቡር ብሎገር ለመባል ትንሽ የቀረኝ ሰው ነኝ፡፡
 • በነገራችን ላይ ሁላችሁም ያው ናችሁ፡፡
 • እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር?
 • ጭፍኖችና ጽንፈኞች፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ደጋፊዎቹም ሆናችሁ ተቃዋሚዎቹ ሁላችሁም ጭፍኖችና ጽንፈኞች ናችሁ፡፡
 • እሱማ እኔም በጭፍን ነው የምደግፋችሁ፡፡
 • አየህ ችግሩ እሱ ነው፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በሬ ወለደ የሆነ ወሬ እያወራችሁ መንግሥት እንዲጠላ የምታደርጉት እናንተ ናችሁ፡፡
 • እ. . .
 • ደግሞ ሁላችሁም ተንታኝ ነን ባዮች፣ አዋቂ ነን ባዮች፣ ኤክስፐርት ነን ባዮች ናችሁ፡፡
 • ምን ነካዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ይኸው እንደ አንተ ዓይነቱ ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ ሕዝቡን በመከፋፈል ጥላቻ እየዘራችሁበት ነው፡፡
 • አላበዙትም ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁላችሁም የምትጽፉት ውሸትና በሬ ወለደ መሆኑ ደግሞ ያሳዝናል፡፡
 • ኧረ እኔ ውሸት ጽፌ አላውቅም፡፡
 • ስማ እኔ ራሱ ስለነበርኩባቸው በርካታ ስብሰባዎች የጻፍካቸው ምንም እውነት የላቸውም፡፡
 • እ. . .
 • የሚገርመው ግን ተቃዋሚዎቹም ልክ እንደ እናንተ ከአንድ ወንዝ ነው የተቀዱት፡፡
 • አልገባኝም?
 • ሁላችሁም ቀዳዳዎች ናችሁ፡፡
 • እንግዲህ እንከባበር ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተ ክብር አይገባህም፡፡
 • እንግዲያው ከሰሞኑ ይጠብቁኝ፡፡
 • ምን ልታደርግ?
 • አብዮት ነው የማስነሳብዎት፡፡
 • የምን አብዮት?
 • የፌስቡክ አብዮት፡፡
 • እኔን ደግሞ ተረቱን አስታወስከኝ፡፡
 • የትኛውን?
 • ብሎገር ቢንጫጫ. . .
 • እ. . .
 • በአንድ ሙቀጫ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከታጩ ባለሥልጣን ጋር እያወሩ ነው]

 • ክቡር ሚኒስትር እንዴት ነዎት?
 • በእርግጠኝነት አንተን ማስመረጥ እችላለሁ፡፡
 • እንዴት አድርገው?
 • የአራቱም ፓርቲዎች ቁልፍ ሰዎች በእጄ ናቸው፡፡
 • ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ አይደለም በአገር አቀፍ ደረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖርህ ማስደረግ እችላለሁ፡፡
 • ሁሌም እኮ ያስገርሙኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ በሁሉም ነገር ስኬታማ መሆኔን ታውቃለህ አይደል?
 • በሁሉም ነገር ሲሉ?
 • ይኸው በቢዝነሱም ከዜሮ ተነስቼ አንቱ የተባልኩ ሀብታም ሆኛለሁ፡፡
 • እሱን እንኳን አውቃለሁ፡፡
 • ስለዚህ በእርግጠኛነት አስመርጥሃለሁ፣ እኔም ከአንተ የምፈልገው ነገር አለኝ፡፡
 • ከእኔ ምንድነው የሚፈልጉት?
 • ወሳኝ የሆነ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ትሰጠኛለህ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔን እኮ የሚያስመርጠኝ ብቃቴ ነው፡፡
 • ከብቃትህ በላይ እኔ አስፈልግሃለሁ፡፡
 • እንደተረዳሁት በሚቀጥለው ካቢኔ በጣም መግባት የፈለጉ ይመስለኛል፡፡
 • መግባቴማ የማይቀርና ግዴታ ነው፡፡
 • ስለዚህ አንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያስተዳድራሉ፡፡
 • የምን ሚኒስትር ነው የምሆነው?
 • የሽንኩርትና የድንች ሚኒስትር!