Skip to main content
x
ለክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

ለክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]

 • ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደምታውቀው በርካታ ሥራዎችን እንደምንሠራ ይታወቃል፡፡
 • ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስም ደፋ ቀና እያልን ነው፡፡
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • አየህ ሕዝቡ ጥያቄ የሚያነሳው ሥራ እየሠራን ባለመሆናችን አይደለም፡፡
 • ታዲያ ለምንድነው?
 • የምንሠራውን ሥራ ሕዝቡ ስለማያውቀው ነዋ፡፡
 • ምን ይሻላል ታዲያ?
 • አንተ አማካሪዬ አይደለህ እንዴ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • በዚህ ጉዳይ ላይ እንድታማክረኝ መስሎኝ የጠራሁህ?
 • ለምን ብሮሸር አናሳትምም ታዲያ?
 • አቤት እሱማ ቢሆን እኔም እጠቀም ነበር፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሰሞኑን ማተሚያ ቤቴ አፉን ከፍቶ ነው የሚውለው፡፡
 • ስለዚህ እዛ እናሳትመዋ?
 • ለእንደዚህ ዓይነቱ ወጪ በጀት እንደሌለን አታውቅም?
 • እንደዛ ከሆነ ሌላ ሐሳብ አለኝ፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ለምን ዶክመንተሪ ፊልም አንሠራም?
 • ሰውዬ ጤነኛ አይደለህም እንዴ?
 • ምነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ለእንደዚህ ዓይነት ነገር በጀት የለንም፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
 • አንተን ብሎ አማካሪ?
 • ግራ ገብቶኝ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ እንዲያውም ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • የምን ሐሳብ?
 • ጋዜጣዊ መግለጫ እሰጣለሁ፡፡
 • ጥሩ ሐሳብ ነው፣ አሁኑኑ እጠራቸዋለሁ፡፡
 • ቆይ ቆይ ቆይ፣ የትኞቹን ሚዲያዎች ልትጠራ ነው?
 • ሁሉንም ሚዲያ ነዋ፡፡
 • የምትጠራቸው ሚዲያዎች የሕዝብ የሆኑትንና የእኛ የልማት አጋሮችን ብቻ ነው፡፡
 • የግሎቹስ?
 • እንዳይጠሩ፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ቦታ ስለሌለን ነዋ፡፡
 • ለማን?
 • ለኪራይ ሰብሳቢዎች!

[ክቡር ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡ ሲሉ ከግል ሚዲያ የመጣ ጋዜጠኛ ያያሉ]

 • አንተ ምን ልታደርግ መጣህ?
 • ልዘግብ ነዋ ክቡር ሚኒስትር?
 • አልተጠራህም እኮ?
 • ከልጅ ልጅ ቢለዩ ሲባል አልሰሙም እንዴ?
 • ስማ የአንተን ተረት ለመስማት ጊዜ የለኝም፡፡
 • ስለዚህ በቀጥታ ወደ መግለጫው ይግቡዋ?
 • አሁን የምሰጠው መግለጫ እኮ ስለወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ነው፡፡
 • እኔም መግለጫውን ለሕዝብ ለማስተላለፍ ነው እዚህ የተገኘሁት፡፡
 • እንዲያውም አዳራሹን ለቀህ ውጣ፡፡
 • ለምን ሲባል?
 • አንተ ካልወጣህ መግለጫውን አልሰጥም፡፡
 • እንግዲያውስ እኔም አልወጣም፡፡
 • ካልወጣህማ እኔማ ሰርዤዋለሁ፡፡
 • ምኑን?
 • ጋዜጣዊ መግለጫውን!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ደላላ ወዳጃቸው ደወለላቸው]

 • ኧረ በጣም ጠፉብኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሰሞኑን ያለሁበትን ስብሰባ ታውቀው የለ እንዴ?
 • እኔስ ያስጨነቀኝ የስብሰባው ውጤት አይደል እንዴ?
 • ምኑ ነው የሚያስጨንቅህ?
 • የእኛ ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚሆነው?
 • የእኛ ስትል?
 • የእኔና የእርስዎ ነዋ፡፡
 • እኔ ምን እንዳልሆን?
 • ስንትና ስንት ወንጀል አይደል እንዴ የሠራነው?
 • ስማ አንተ ወንጀለኛ ልትሆን ትችላለህ፡፡
 • እርስዎስ?
 • እኔማ አገሬን ለማልማት ደፋ ቀና የምል ታታሪ ዜጋ ነኝ፡፡
 • ምን?
 • ያን ሁሉ መሬት የቸረቸሩት ለአገር ልማት ነው?
 • ሰውዬ አሁን ራስህን ችለህ ቁም፡፡
 • ያኔ መሬት ስንቸበችብ ምነው እንዲህ አላሉ?
 • አሁን ለምንድነው እንደዚህ የፈራኸው?
 • አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመጣ ማኖ እንዳያስነካን ነዋ፡፡
 • እንግዲህ ለራስህ አስብ፡፡
 • እርስዎንም እኮ ይመለከታል፡፡
 • ሰውዬ እኔ ላይ ምንም አይመጣም፡፡
 • ለምን አይመጣም?
 • ግፋ ቢል ሒስና ግለሒስ ባደርግ ነው፡፡
 • እኔን አሳልፈው ሊሰጡኝ?
 • እሱን ሲደርስ እናየዋለን፡፡
 • እየቀለዱ መሆን አለበት፡፡
 • እኔ ቀልድ እንደማልወድ ታውቃለህ?
 • ስለዚህ ምን እናድርግ ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔማ ነገርኩህ የራሴን ስትራቴጂ ተግባራዊ አደርጋለሁ፡፡
 • የምን ስትራቴጂ?
 • ቆዳዬን መቀያየር ነዋ፡፡
 • እኔንስ ለማን ሊተውኝ ነው?
 • አንተንማ ሥራህ ነው የሚያወጣህ?
 • ለነገሩ እርስዎ ለዚህ የበቁት ቆዳዎትን እየቀያየሩ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
 • የቅፅል ስሜን ረሳኸው እንዴ?
 • ማን ነበር?
 • እስስቱ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ ዳያስፖራ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]

 • ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነህ ወዳጄ?
 • ኧረ ክቡር ሚኒስትር ምንድነው?
 • ምን ሆንክ ደግሞ?
 • ይኸው እዚህ በጥፍራችን ቆመን እኮ ነው የምንጠብቀው?
 • ምኑን ነው የምትጠብቁት?
 • የስብሰባውን ውጤት ነዋ፡፡
 • ምነው ቸኮልክ?
 • ሁላችንንም ቁርጠት ይዞናል፡፡
 • የምን ቁርጠት ነው?
 • እንዲያውም አገር ቤት የቁርጠት መድኃኒት ጠፍቷል እየተባለ ነው፡፡
 • ቀልደኛ ነህ በእናትህ፡፡
 • ሆዳችንን አጮሃችሁት እኮ?
 • ለምን ይጮሃል?
 • እኛም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያቸውን ካስገቡ እኮ አርባ ቀን ሞላቸው፡፡
 • ይኸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልቀቂያ በአርባኛው ቀን ተቀበልናቸው፡፡
 • መቼም በባህላችን አርባኛ ቀን በጣም እንደሚከበር ያውቃሉ?
 • አልገባኝም?
 • ያው በሐዘንም ሆነ በደስታ አርባኛው ቀን ይከበራል፡፡
 • እንዴት እንዴት ማለት?
 • ለሐዘን የአርባ ቀን መታሰቢያ ሲኖር፣ ለደስታ ደግሞ ክርስትና በአርባ ቀን ነው የሚነሳው፡፡
 • ታዲያ ለእኛ የሐዘን ነው የደስታ?
 • ፍቺውን እንግዲህ ለእርስዎ ትቸዋለሁ፡፡
 • ለማንኛውም ነገረኛ ሆነሃል፡፡
 • ሰሞኑን በጣም ያዝናናኝን ነገር ግን ላጫውትዎት፡፡
 • ምንድነው እሱ?
 • ሰሞኑን በፌስቡካችሁ የለቀቃችሁት ፎቶ ነዋ፡፡
 • የምን ፎቶ?
 • አንቨርሰሪ ስታከብሩ የለቀቃችሁት ፎቶ ነዋ፡፡
 • ምን ሆነ ደግሞ?
 • አለቆቻችሁ ኬክ እየቆረሱ የተነሱትን ነዋ፡፡
 • ለምን ዳቦ አልሆነም ነው ጥያቄህ?
 • እናንተም ውስጥ ኒዮ ሊብራሎች ገብተዋል ማለት ነው?
 • መቼ ይጠፋሉ ብለህ ነው?
 • ለማንኛውም ቤቢ ሻወራችሁን እያከበራችሁ ነው የሚመስለው፡፡
 • ምንድነው እሱ ደግሞ?
 • ያው ሴቶች ከመውለዳቸው በፊት ስጦታ የሚሰጥበት ባህል ነው፡፡
 • ልጁ ሳይወለድ እንዴት ስጦታ ይሰጣል?
 • ያው የፈረንጆች ባህል ነው፡፡
 • በእኛ ባህል ግን ከተወለደ በኋላ ነው ስጦታ የሚሰጠው፡፡
 • እሱንማ አውቃለሁ፡፡
 • እኛም ኬክ የቆረስነው ለቤቢ ሻወር አይደለም፡፡
 • ታዲያ ለምንድነው?
 • ለአራስ ጥሪ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሌላ ሚኒስትር ይደውላሉ]

 • ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • አገር እየመራን ነው ወይስ ቀልድ ነው የተያዘው?
 • ምን ሆኑ ክቡር ሚኒስትር?
 • ምንድነው እየተሠራ ያለው?
 • ሥራ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔ ግን አልመሰለኝም፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • እንዴት ነው ወሳኝ መረጃን እየተደባበቅን ሥራ እየሠራን ነው የምንለው?
 • የምን መረጃ ነው?
 • አገሪቱ ላይ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ክስተት እያለ እንዴት ልሰማ አልችልም?
 • የምን ክስተት ነው?
 • ነዳጅ መገኘቱን ነዋ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ሁሉን ነገር ማወቅ አለብዎት ብዬ አላስብም፡፡
 • ችግሩ እኮ ይኼ ነው፡፡
 • የምን ችግር ነው?
 • እንዲህ ዓይነት አለመተማመን በመካከላችን እያለ እንዴት አገር ልንመራ እንችላለን?
 • ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እኮ ማወቅ ያለብዎትን ብቻ ነው የሚያውቁት፡፡
 • ስለነዳጅ መገኘት ማወቅ የለብኝም?
 • ጊዜው ሲደርስ ያውቁታል፡፡
 • አሁንማ አወቅኩት፡፡
 • ማን ነገረዎት?
 • ሚዲያ ላይ ወጥቷል እኮ?
 • ኧረ ወሬው ለሚዲያም አልተነገረም፡፡
 • ከሚዲያ ነው የሰማሁት ስልህ?
 • እነሱ ከየት እንደሰሙት አላውቅም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለማንኛውም እኔ በዜናው በጣም ተደስቻለሁ፡፡
 • እሱማ በጣም አስደሳች ዜና ነው፡፡
 • እኔ እኮ መዘጋጀት ፈልጌ ነው ወሬውን ለምን ደበቅከኝ ያልኩህ?
 • ምንድነው ነው የሚዘጋጁት?
 • ይኼ ዜና እኮ የእኔን ሕይወት በጣም ይቀይረዋል፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ፕሮጀክት አልተጀመረም አይደል?
 • እሱማ ገና ነው፡፡
 • ስለዚህ እኔም ምን እንደማደርግ አውቃለሁ፡፡
 • ምን ሊያደርጉ ነው?
 • ወሳኝ የኢንቨስትመንት ዕድል ታይቶኛል፡፡
 • የምን ዕድል ነው?
 • በአፋጣኝ ነው የማስመጣው፡፡
 • ምንድነው የሚያስመጡት?
 • ነዳጁን ማመላለሻ ነዋ፡፡
 • እኮ ምን?
 • ቦቴ!