Skip to main content
x
በጨለማው ጊዜ ደምቃ በብርሃኑ የደበዘዘችው የዊኒ ማንዴላ  ፀሐይ
የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት እስራት እንደተለቀቁ ከቀድሞ ባለቤታቸው ከዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ ጋር

በጨለማው ጊዜ ደምቃ በብርሃኑ የደበዘዘችው የዊኒ ማንዴላ ፀሐይ

‹‹ጊዜ የጣለው ዛፍ ምሳር ይበዛበታል፤›› እንዲሉ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ የቀድሞ የትዳር አጋር ኖምዛሞ ዊኒፍሬድ ዛንዩዌ ማዲኪዜላ ወይም በአጭሩ እንደሚጠሩት ዊኒ ማንዴላ፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የነጮች የግፍ አገዛዝ አፓርታይድን ለማጥፋት ካደረጉት ትግልና የቀድሞ ባለቤታቸው ኔልሰን ማንዴላ በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ ባለቤታቸውን ከማበረታታት አንስቶ የአፓርታይድ ትግሉን በማቀጣጠል ከነበራቸው ሚና ይልቅ፣ ነፃ የተባሉባቸውም ሆነ የተፈረዱባቸው የሙስና፣ የማጭበርበርና የግፍ ግድያዎች ክሶች በታሪካቸው ጎልተው ተጽፈዋል፡፡

ዊኒ ማንዴላ ከባለቤታቸው ኔልሰን ማንዴላ በወረሱት ስማቸው በይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ ሰዎችም ረዥሙን የደቡብ አፍሪካ የጎሳ ስማቸውን ከመጥራት ይኼኛው ይቀናቸዋል፡፡

‹‹የአገራችን እናት›› በማለት በደጋፊዎቻቸው በፍቅር የሚጠሩት ዊኒ ማንዴላ፣ ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ አገዛዝ ማብቂያ ጀምሮ እየመራ በሚገኘው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) አባልነት የፓርላማ አባል ሆነው የቆዩ ሲሆን፣ አገራቸውን በምክትል ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡

በፓርላማ ቆይታቸው የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሴቶች ሊግ ሰብሳቢ በመሆን አገልግለዋል፡፡

በጨለማው ጊዜ ደምቃ በብርሃኑ የደበዘዘችው የዊኒ ማንዴላ  ፀሐይ
በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዊኒ ማንዴላ በኔልሰን ማንዴላ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወቅት

 

ከኔልሰን ማንዴላ ጋር እ.ኤ.አ. በ1958 በጋብቻ የተሳሰሩት ዊኒ ማንዴላ ይበልጥ በሕዝብ ዕይታ ውስጥ ይበልጥ የገቡት፣ ማንዴላ በእስር በነበሩበት ወቅት ነበር፡፡ ለ27 ዓመታት በእስር ለቆዩት ማንዴላ ዊኒ ልክ እንደ ቃል አቀባይ በመሆን ለሕዝቡ መልዕክታቸውን ያስተላልፉላቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በአገር ውስጥ ለነበረው የፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴ ትልቅ ቦታ የነበራቸው ለመሆን በቁ፡፡ በዚህም ምክንያት ዊኒ ማንዴላ ለተደጋጋሚ እስሮችና ስደቶች ተዳርገዋል፡፡ በርካታ ጊዜያቸውንም በገጠር ለመኖር ተገድደው ነበር፡፡

ምንም እንኳን ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ1990 ከእስር ከተፈቱ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለቱ ጋብቻ ቢቋጭም፣ ዊኒ ግን ከኔልሰን ማንዴላ ጋር አልተራራቁም፡፡ ሁለት ልጆቻቸውንም ይጎበኛሉ፡፡ በተለይ ኔልሰን ማንዴላ ታመው በነበረነት ጊዜ ዊኒ ማንዴላ በተደጋጋሚ ሲጎበኟቸው ነበር፡፡ ለአሠርት ዓመታት እስርን ተቋቁሞ ማለፍ የቻለው ትዳር ነፃነትን ግን ሊቋቋም ሳይችል ቀረ ተባለለት፡፡

ሆኖም ደቡብ አፍሪካውያን ለዊኒ ማንዴላ ያላቸው አመለካከት በበጎ ብቻ የሚያስቡት እንዳይሆን የሚያደርጉ ክስተቶች፣ በተለይ ከኔልሰን ማንዴላ ጋር ፍቺ ከፈጸሙ በኋላ በተደረጉባቸው የሕግ አስከባሪዎች ምርመራዎች የተጋለጡባቸው በርካታ ጥፋቶች የወይዘሮዋን ታሪክ ያጠለሹ ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን በርከት ያሉት ክሶቻቸው በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ውድቅ ቢደረጉላቸውም፡፡

‹‹በእስር የቆየሁባቸው ጊዜያት አጠንክረውኛል፡፡ አሁን ፍርኃት የሚባል ስሜት በጭራሽ የለብኝም፡፡ አሁን ምንም የምፈራው ነገር የለም፡፡ መንግሥት ያላደረገኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ያልቀመስኩት ሕመምም የለም፤›› ይላሉ ዊኒ ማንዴላ በተለያዩ ጊዜያት እ.ኤ.አ. ከ1969 ጀምሮ የተፈጸሙባቸውን ድርጊቶች ሲያስታውሱ፡፡

በአፓርታይድ ሥርዓት ዊኒ ማንዴላ ለብቻቸው በጠባብ ክፍሎች ከመታሰር ወደ ገጠር እስከ መሰደድና ቤታቸው እስኪቃጠል ድረስ መከራ ዓይተው ነበር፡፡

ዊኒ ማንዴላ የአፓርታይድ አገዛዝ ሲያበቃ ኔልሰን ማንዴላ ያደረጉትን ስምምነት ያጣጥሉም ነበር፡፡ ‹‹ጥቁሮችን አሳልፎ የመሸጥ›› ድርጊት ነው ሲሉም ይተቹ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ ልዩነት በሁለቱ መካከል ቢኖርም ኔልሰን ማንዴላ መንግሥት ሲመሠርቱ ዊሊን ምክትል ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸው ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን አባረሯቸው፡፡ በፍርድ ቤት በተደረገ ክርክር ኔልሰን ማንዴላ ዊኒን በድጋሚ ወደ ሥልጣናቸው መልሰዋቸው የነበረ ቢሆንም፣ በድጋሚ አባረዋቸዋል፡፡

በጨለማው ጊዜ ደምቃ በብርሃኑ የደበዘዘችው የዊኒ ማንዴላ  ፀሐይ
ኔልሰን ማንዴላና ዊኒ ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ1957 ዓ.ም. ጋብቻቸውን ሲፈጽሙ

 

ዊኒ ማንዴላ ቆራጥነታቸውንና ለነፃነት የሚያደርጉት ትግል እስከ መጨረሻው ጥግ እንደሚደርሱት ሲናገሩ፣ ‹‹በክብሪት ፓኮና በአንገታችን ታግለን ይህን አገር ነፃ እናወጣታለን፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ይኼ ንግግር ግን በደቡብ አፍሪካ በወቅቱ ሰዎችን ጎማ ላይ በማሰር  በእሳት በቁማቸው እያቃጠሉ የመግደልን ድርጊት ዕውቅና መስጠት ነው በማለት ብዙ መዘዝ አምጥቶባቸዋል፡፡ በጠባቂያቸው የተጋለጡባቸው ሰዎችን የማፈንና የማስገደል ድርጊቶች  መልካም ስማቸውን ጥላሸት የቀቡ ነበሩ፡፡ በርካታ የሙስና ክሶችም ነበሩባቸው፡፡

ከመንግሥት ሥልጣን ከተሰናበቱ በኋላ ዊኒ ማንዴላ በርካታ ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡ ሆኖም ከጠለፋ ወንጀል በስተቀር ዊኒ ማንዴላ ጥፋተኛ የተባሉበት ክስ አልነበረም፡፡ በተለያዩ ጥፋቶች ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው የነበረ ቢሆንም፣ በይግባኝ ወደ ገንዘብ ቅጣት ተቀይሮላቸዋል፡፡

በጨለማው ጊዜ ደምቃ በብርሃኑ የደበዘዘችው የዊኒ ማንዴላ  ፀሐይ
ዊኒ ማንዴላ በፀረ አፓርታይድ ትግሉ ጊዜ

 

ወደ ፖለቲካ ሕይወታቸው እንዲመለሱም ያደረጋቸው የፓርቲያቸው ኤኤንሲ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ሲያደርግ፣ እ.ኤ.አ. በ2007 በአንደኝነት ከፍተኛውን ድምፅ ማግኘታቸው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ በተደረጉ የፓርቲያቸው ምርጫዎች ለፕሬዚዳንትነት በተራ ከታሰቡ በፓርቲው ተስፋ የተጣለባቸው ግለሰቦች አምስተኛ ደረጃ ላይ ነበሩ፡፡

ምድራዊው ሕይወታቸው ሲያበቃ እ.ኤ.አ. በኤፕሪል 2 ቀን 2018 ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዊኒ ማንዴላ ታሪክ ሁለት መልክ አለው፣ ጥቁርና ነጭ፡፡ ሆኖም በጥንካሬያቸው ይበልጡኑ እየተወደሱ ነው፡፡ ዊኒ ማንዴላ ሰሞኑን ሕይወታቸው ያለፈው በ81 ዓመታቸው ነው፡፡

‹‹ልክ ነው ቀስታችን ወድቋል፣ እዚህ የተገኘነውም ቀስቱን አንስተን ትግሉን ለመቀጠል ነው፣ ይኼንን ማድረግ ደግሞ የእኛ ድርሻ ነው፤›› ሲሉ ለሐዘን ለመጡ ደቡብ አፍሪካውያን ንግግር ያደረጉት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ታጋዩ ጂሊየስ ማሌማ ናቸው፡፡ ‹‹በዚህ ቤት ሳለን እንግዶች አይደለንም፡፡ ልጆች እንጂ፡፡ ከዚህ በልተንና ጠጥተን ነው ያደግነው፤›› ብለዋል፡፡

የኖምዛሞ ዊኒፍሬድ ዛንዩዌ ማዲኪዜላ (ዊኒ ማንዴላ) የቀብር ሥነ ሥርዓት እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 14 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩ መንግሥታዊ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

በጨለማው ጊዜ ደምቃ በብርሃኑ የደበዘዘችው የዊኒ ማንዴላ  ፀሐይ
ደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ታጋያቸውን ዊኒ ማንዴላ የተሰናበቱበት ስሜት በሚዲያዎች ተንፀባርቋል