Skip to main content
x
ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤት ሲገቡ ልጃቸውን ያስጠሩታል

ክቡር ሚኒስትሩ ማታ ቤት ሲገቡ ልጃቸውን ያስጠሩታል

 • አቤት ዳዲ?
 • የፈተና ወረቀትህን አምጣ እስቲ?
 • የትኛውን የፈተና ወረቀት?
 • የሒሳብ የፈተና ወረቀትህን፡፡
 • ባለፈው የተፈተንኩትን ነው?
 • አዎን አምጣና አሳየኝ፡፡
 • ይኼው ዳዲ፡፡
 • ይኼ እኮ የእንግሊዝኛ ነው፡፡ እኔ ያልኩህ የሒሳብ ፈተናህን ነው?
 • ለምን ፈለግከው ዳዲ?
 • ከትምህርት ቤት ተደውሎልኝ ነበር፣ በአስቸኳይ አምጣው?
 • እሱንማ ትምህርት ቤት ረስቸዋለሁ፡፡
 • ከእኔ ጋር እንዳትጣላ በአስቸኳይ አምጣው፡፡
 • እሺ ይኼው ዳዲ፡፡
 • እንዴ? እንዴ? እንዴ?
 • ምነው ዳዲ?
 • እንዲህ ታዋርደኛለህ?
 • ምን ላድርግ ዳዲ?
 • ያገኘኸውን ውጤት አይተኸዋል?
 • ፈተናው ከባድ ነበር፡፡
 • ለመሆኑ ክፍል ውስጥ ገብተህ ተምረህ ታውቃለህ?
 • ምን እያልክ ነው ዳዲ?
 • ክፍል ውስጥ ገብተህ ተምረህ ቢሆንማ፣ እንደዚህ ዓይነት ውጤት ልታመጣ አትችልም?
 • በጣም ከብዶኝ ነው ዳዲ፡፡
 • ሁለት ከመቶ ታመጣለህ?
 • ፈተናው ለየት ባለ መልኩ ነበር የወጣው፡፡
 • ለየት ባለ መልኩ ማለት ምንድነው?
 • በፊት ምርጫ ነበር የሚወጣው፡፡
 • ምርጫ ቢሆንስ?
 • እሱማ ለማጭበርበር ይቀላል፡፡
 • የአሁኑስ ምንድነው?
 • የአሁኑማ ካልኩሌሽን ነው፡፡
 • ካልኩሌሽን ቢሆንስ?
 • ትምህርቱ ካልገባህ እንደዚህ ትዋረዳለሃ?
 • አሁን አንተ የእኔ ልጅ ስትባል አታፍርም?
 • ምነው ዳዲ?
 • እኔ ለአንተ ምንድነው ያስተማርኩህ?
 • ምን አስተማርከኝ ዳዲ?
 • መድፈንና መድፈን ብቻ አይደል እንዴ ያስተማርኩህ?
 • እ. . .
 • ይኸው ባለፈው ምርጫ ፓርላማውን መቶ በመቶ አይደለም እንዴ የተቆጣጠርነው?
 • የእሱንማ ውጤት አየነው እኮ?
 • ምን?
 • አይ ሁሌ መቶ በመቶ መድፈን ጥሩ አይደለም ሲሉ ሰምቼ ነው፡፡
 • ለመሆኑ አንተ ብቻ ነህ የወደቅከው?
 • አብዛኛው ሰው ተረፍርፏል፡፡
 • እና ሁሉም ወድቀዋል?
 • አንዱማ መቶ ደፍኗል፡፡
 • እሱ ነው ቆራጥ፣ ሌላስ?
 • ሁለት ልጆች ሃምሳ ቤት አምጥተዋል፡፡
 • ሌላስ?
 • ቀጥሎ እኔ ነኝ ሁለት ያመጣሁት፡፡
 • እኔ ፈጽሞ ይኼን ውጤት አልቀበልም፡፡
 • እንዴ ዳዲ ከእኔም የባሰ እኮ አለ?
 • ዜሮ ያመጣ ነው?
 • ኧረ ከነጭራሹ ያልተፈተነ፡፡
 • ለምን?
 • ፈርቶ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የቀድሞ ወዳጃቸው ይደውልላቸዋል]

 • ክቡር ሚኒስትር በጣም ነው የኮራሁባችሁ፡፡
 • እንዴት?
 • ያየሁትን ነገር በሕይወት ዘመኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አየዋለህ ብዬ አላምንም ነበር፡፡
 • በምንድነው እንደዚህ የምትገረመው?
 • አፋችንን እኮ ነው ያስከፈተን፡፡
 • ምኑ?
 • ያን የመሰለ ንግግር ስሰማ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነ አልመሰለኝም፡፡
 • ሰውዬ ምነው አካበድክ?
 • እውነት ክቡር ሚኒስትር፣ የሠለጠኑ የምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የሚነገር ንግግር እኮ ነው የሰማነው፡፡
 • ለመሆኑ የት ነው የሰማኸው?
 • በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ነዋ፡፡
 • ስማ በቃ የአገሪቷ ችግር ተፈታ እያልከኝ ነው?
 • ያው ችግሩን ለመፍታት የለውጥ ጉዞ መጀመሩን የሚያበስር ንግግር ነው ባይ ነኝ፡፡
 • ሰውዬ ለውጥ ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ግን በኢትዮጵያዊነቴ እንድኮራ አድርጎኛል፡፡
 • ለምን ትቸኩላለህ?
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ፓርቲው እኮ በአንድ ግለሰብ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ፓርቲያችን የተመሠረተው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር አሁን ግን የምትከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምናምን እየተሸረሸረ ይመስላል፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • ይኸው በአንድ ንግግር በአገሪቱ ላይ የፍቅር፣ የሰላምና የተስፋ መንፈስ ፈሰሰ እኮ፡፡
 • ሰውዬ ተምታቶብሃል ልበል?
 • ይኸው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተፎካካሪ ወንድሞቻችን ማለት ጀመራችሁ እኮ?
 • ባትሳሳት ጥሩ ነው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ሁሉም ወደነበረበት ይመለሳል፡፡
 • አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
 • ሕዝቡን ትንሽ ማስተንፈስ ፈልገን ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የፈለገ ቢሆንም ግን ከኢሕአዴግ እንደዚህ ዓይነት ቃላት ተሰምተው አይታወቅም፡፡
 • ነገርኩህ እኮ ሁሉም ወደነበረበት ይመለሳል፡፡
 • ይኼ ግን የእርስዎ ብቻ ፍላጎት ይመስለኛል፡፡
 • ቢሆንስ ምን ችግር አለው?
 • አሁንማ ምን እንደሆኑ ገባኝ?
 • ምንድን ነኝ?
 • የድሮ ሥርዓት ናፋቂ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሮ አስጠሩት]

 • ክቡር ሚኒስትር ከትናንት ወዲያ እኮ የሚገርም ነገር ነው ያየነው፡፡
 • ምኑ ነው የሚገርመው?
 • አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደረጉት ንግግር በጣም ልቤን ነካው፡፡
 • እንዴት?
 • ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • የሚገርምዎት ከታላቁ መሪ ሞት በኋላ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር ነው ለመጀመርያ ጊዜ ያለቀስኩት፡፡
 • ሁለቱን ለንፅፅር እያቀረብክ ባልሆነ?
 • ክቡር ሚኒስትር ፓርላማ አልነበሩም እንዴ?
 • ነበርኩ እንጂ?
 • ታዲያ ስንት የፓርላማው አባላት በእንባ ሲራጩ አልነበረ እንዴ?
 • እኔ ማንም ሲያለቅስ አላየሁም፡፡
 • ለማንኛውም ትልቅ ተስፋ በልቤ ተጭሯል፡፡
 • የአንተ መነፋረቅና አለመነፋረቅ ዋናው ጉዳይ አይደለም፡፡
 • ዋናው ጉዳይማ እንደ ኢትዮጵያ አንድ ሆነን መቀጠላችን ነው፡፡
 • አንቀጠልም ብለህ ታስብ ነበር?
 • እንደ አያያዛችንማ የምንበታተን ነበር የሚመስለው፡፡
 • ስማ እኔን የሚያስጨንቀኝ አንድነት ምናምን የምትለው ዝባዝንኬ አይደለም፡፡
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ከዚያ በላይ የሚያስጨንቁኝ ጉዳዮች አሉ፡፡
 • እኮ ምን?
 • አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙን ረሳኸው እንዴ?
 • እሱማ አውቃለሁ፡፡
 • አየህ ሁሌም አዲስ ነገር ሲመጣ መፍራትና መበርገግ አለብህ፡፡
 • ምን ያለበት ምን አይችልም አሉ?
 • ምን አልክ አንተ?
 • ምኑን ነው የፈሩት ክቡር ሚኒስትር?
 • አዲስ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡
 • እሱማ ብዙ አዳዲስ ለውጦች መኖራቸው አይቀርም፡፡
 • እሱ ነው አሳሳቢው ጉዳይ፡፡
 • ምኑ ነው ያሳሰበዎት?
 • ቢዝነሶቼ፡፡
 • እ. . .
 • ከዚያም አልፎ ተርፎ ሌላ የሚያሳስበኝ ጉዳይ አለ፡፡
 • ምን?
 • መቀጠሌ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • ስማ ወዳጄ?
 • አቤት ክቡር ሚኒስትር?
 • እኔ አንድ ሐሳብ መጥቶልኛል፡፡
 • ምን ዓይነት ሐሳብ?
 • ትናንት ቴሌቪዥን ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሸኙ ዓይተሃል?
 • እኔማ በቦታው ነበርኩ፡፡
 • እንደዚህ ዓይነት ክብር ያየ መሪ በአገራችን አለ?
 • እሱማ ትልቅ ታሪክ ነው የሠራነው፡፡
 • ታዲያ ምን ተሰማህ?
 • ትልቅ ደስታ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንደ እሳቸው መሆን አልተመኘህም?
 • ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን?
 • ኧረ እንደዚህ በክብር መሸኘት?
 • እሱማ ሁላችንም የምንፈልገው ነው፡፡
 • አሁን እኮ እሳቸው ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸው ነው የተሸኙት፡፡
 • ማለት?
 • ቤት፣ መኪና፣ ጥበቃ በቃ ሁሉ ነገር፡፡
 • የአገር መሪ ነበሩ እኮ?
 • በዚያ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መባላቸው ያስደስታል፡፡
 • እኛም አንድ ቀን የቀድሞ ሚኒስትር መባላችን አይቀርም፡፡
 • የቀድሞ ብቻ መባል ምን ያደርጋል?
 • ምን እያሉ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • ቤቱ፣ መኪናው፣ ጥበቃው የት አለ?
 • እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር?
 • የምን ቀልድ ነው?
 • አሁን እርስዎ በየክፍለ ከተማው አይደል እንዴ ቤት ያለዎት?
 • የማከራያቸው ናቸዋ፡፡
 • ታዲያ ምን ፈልጉ?
 • የምኖርበት ነዋ፡፡
 • መኖሪያዎትማ ተሠርቶ አልቋል፡፡
 • የት?
 • እስር ቤት!