Skip to main content
x
የቀድሞ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር በስኳር ኮርፖሬሽን ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክር ሆነው ቀረቡ
የቀድሞ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው

የቀድሞ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር በስኳር ኮርፖሬሽን ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክር ሆነው ቀረቡ

በሚኒስትር ማዕረግ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አማካሪና የቀድሞ የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር፣ ዓቃቤ ሕግ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ በመሠረተባቸው በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሸን የኦሞ ኩራዝ 5 ስኳር ፕሮጀክት ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

የዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው በተከሳሾቹ ላይ የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት አቶ ተፈራ ደርበው ናቸው፡፡ አቶ ተፈራ ምስክር ሆነው የቀረቡት፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ስለነበሩ፣ ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋል ስለተባለው የሙስና ተግባር ተያያዥነት ያላቸውን የሥራ አፈጻጸሞች እንዲያስረዱ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ አቶ ተፈራ የሚያስረዱለት ወይም የሚሰጡት ምስክርነት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ለሚያካሂዷቸው የስኳር ፕሮጀክቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ ሲፈጽም፣ በሦስት ወራት ውስጥ ለቦርዱ ማሳወቅ እንዳለበት የኮርፖሬሽኑ የግዥ መመርያ የሚያስገድድ ቢሆንም፣ ለኦሞ ኩራዝ 5 ፕሮጀክት ከ10.3 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ወይም ውል ፈጽሞ እያለ በመመርያው መሠረት ሪፖርት አለማቅረቡን እንደሚያስረዱለት ጭብጥ አስይዞ ምስክርነታቸውን ቀጥሏል፡፡

አቶ ተፈራ ስለተጠቀሰው ጭብጥ ተጠይቀው እንደተናገሩት፣ ከመጋቢት 15 ቀን 2003 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ ወር 2007 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡ ለስኳር ፕሮጀክቶች ግዥ ሲፈጸም ግዥው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ግዥው በተፈጸመ ሦስት ወራት ውስጥ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያቀርብ የግዥ መመርያ ያስገድደዋል፡፡ በመሆኑም የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ጃርሶ በነበሩበት ወቅት የቻይና ዜጎች ወደሳቸው ቢሮ መጥተው ለኦሞ ኩራዝ 5 ፕሮጀክት የግዥ ወይም ውል ካደረጉ ሦስት ዓመታት ቢሆናቸውም፣ ወደ ሥራ አለመግባታቸውን አቤቱታ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ አቤቱታ ላቀረቡት ቻይናውያን የኮርፖሬሽኑን ማኔጅመንት አነጋግረው ምላሽ እንደሚሰጧቸው የነገሯቸው ቢሆንም ባለባቸው የሥራ ብዛት ምክንያት ማኔጅመንቱንም አለመጠየቃቸውንና ምላሽ አለመስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ግዥው ወይም ውሉ ከተፈጸመ ሦስት ዓመታት እንደሞላው እንዴት እንዳወቁ ተጠይቀው፣ በ2008 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርት መቅረቡንና ከዚያ በኋላ እየታየ የፕሮጀክት ሥራ መቀጠሉን እንደሚያውቁ አስረድተዋል፡፡ ውሉ የተፈጸመው በ2005 ዓ.ም. ቢሆንም ፕሮጀክቱን ወደ መተግበር የተገባው ግን በ2008 ዓ.ም. መሆኑንና ሪፖርትም የደረሳቸው ሥራ ሲጀመር መሆኑን አክለዋል፡፡

ግዥውን በሚመለከት ግን በኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችም ሆነ በሌላ አካል ለቦርዱ የቀረበ ሪፖርት እንዳልነበረም አቶ ተፈራ አረጋግጠዋል፡፡ ወደ ቦርዱ ቢሮ ቀርበው አቤቱታ ያቀረቡትን ቻይናውያን በመልክ መለየት ይችሉ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ተፈራ፣ ‹‹እነሱን በመልክና በቁመት መለየት ቢያስቸግርም ልሞክር፤›› ብለው ወደ እስረኞቹ በመዞር ተከሳሽ ሆነው በእስር ላይ የሚገኙትን ቻይናዊ ለፍርድ ቤቱ አሳይተዋል፡፡

ፕሮጀክቱንም ሆነ ግዥውን በሚመለከት ኃላፊነቱ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ስለመሆኑ በተከሳሾች (ስምንት ናቸው) ጠበቆች መስቀልኛ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተፈራ፣ የዋና ዳይሬክተሩ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ለቦርዱ በሦስት ወራት ውስጥ ስለግዥው የማቅረብ ግዴታ መኖር አለመኖሩን ተጠይቀው፣ ግዥው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ከሆነ በሦስት ወራት ውስጥ ለቦርዱ የማቅረብ ግዴታ የዋና ዳይሬክተሩ መሆኑን በመመርያው መቀመጡን ተናግረዋል፡፡ ቦርዱ ግዥ የማፅደቅ ወይም ያለማፅደቅ ሥልጣን እንዳለው ሲጠየቁ፣ ‹‹ሥልጣን የለውም፣ ሪፖርት የማየት ሥልጣን ብቻ አለው፤›› ካሉ በኋላ፣ ይኼም ያስፈለገው ፕሮጀክቱ በተያዘለት የአፈጻጸም ጊዜና በተያዘለት በጀት በአግባቡ እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አፈጻጸሙ ጥሩ ካልሆነ በተጠቀመው ፖሊሲ መሠረት አቅጣጫ ለመስጠት መሆኑን አክለዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑን አቋምም ለማየትና ፋይናንስ ለማድረግም ጥንቃቄ ለማድረግ መሆኑንም ጠቁመው ምስክርነታቸውን አጠናቀዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ስኳር ፕሮጀክት ግንባታን ለማካሄድ ጃንዚ ጃንግሊያን ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ያለ ጨረታ በደላሎች አገናኝነት የ550 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ10.3 ቢሊዮን ብር በላይ ውል ተፈራርሟል መባሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ውል ከተገባበት ገንዝብ ላይ በድለላ ለተሳተፉና በክሱ ላይ ለተጠቀሱ ግለሰቦች ተገቢ ያልሆነ ክፍያ መፈጸሙንም ዓቃቤ ሕግ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በመሠረተው ክስ መጥቀሱን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

ተከሳሾቹም በኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱ የተለያየ ክፍል ኃላፊዎች አበበ ተስፋዬ (ኢንጂነር)፣ አቶ ሽመልስ ከበደ፣ አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁና ወ/ሮ ሳሌም ከበደ (ነጋዴ)፣ አቶ ፀጋዬ ገብረ እግዚአብሔር (ነጋዴ)፣ አቶ ፍሬው ብርሃነ (ነጋዴ)፣ ዩአን ጃሊን (ስቲቨን) የጃንዚ ጃንግሊያን ኢንተርናሸናል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ተወካይና አቶ ሳድሳዊ ገብረ እግዚአብሔር መሆናቸው ይታወቃል፡፡