Skip to main content
x
በዓድዋ ጦርነት የተሰው ጀግኖችን አፅም በክብር ለማሳረፍ ታሰበ
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫው ሲሰጥ

በዓድዋ ጦርነት የተሰው ጀግኖችን አፅም በክብር ለማሳረፍ ታሰበ

በዓድዋ ጦርነት የተሰው ጀግኖችን አፅም በጅምላ ከተቀበሩበት ሥፍራ አንስቶ በክብር ማኖር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው ሚያዝያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ መነሻም በአካባቢው በተደረገ ጥናት ምንድብድብ በሚባል ሥፍራ፣ በጅምላ ተቀብረው የተገኙ የዓድዋ ጀግኖች አፅሞች በቁፋሮ ወቅት እንደ ነገሩ ሆነው በመገኘታቸው ነው ተብሏል፡፡

በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የተወሰኑት በአቅራቢያው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት፣ አብዛኞቹ ደግሞ ከባድ ፍልሚያ በተደረገበት ምንድብድብ በሚባለው ሥፍራ ተቀብረው መገኘታቸውን የተናገሩት የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢተው በላይ ናቸው፡፡ ‹‹በሥፍራው በጅምላ የተቀበሩ፣ እንዲሁም በአንድ ጉድጓድ ሁለትና ሦስት እየሆኑ የተቀበሩ አፅሞች ተገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ የተገኙት አፅሞች በጣም ብዙ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አፅሞቹ የተገኙት የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዲገነባ ከታሰበበት ቦታ ትይዩ በሚገኝ ሥፍራ ላይ ነው፡፡ ሚያዝያ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ የተጣለለትን የዓድዋ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ለማስጀመር የቅድመ ጥናት ሥራዎች፣ በተለይም የአፈር ጥናት በሚካሄድበት ወቅት አፅሞቹ መገኘታቸው ተገልጿል፡፡ የአፈር ጥናቱን ለማካሄድ መሬቱ ሲቆፈር የተኙት አፅሞች በቦታቸው ቢመለሱም፣ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ የአስተባባሪው ኮሚቴ አባላት መስማማታቸው ተነግሯል፡፡ ለዚህም አፅሞቹ በተገኙበት ቦታ ላይ ሙዚየም ለመገንባትና የተሰውት ጀግኖችም ማንነታቸውን የሚናገሩ መረጃዎችን አሰባስቦ በየመቃብራቸው ላይ ለማስፈር መታቀዱን አቶ ቢተው አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ የሚውል 200 ሚሊዮን ብር የመደበ ቢሆንም፣ ከጊዜ በኋላ እንዲገነባ ለታቀደው ሙዚየም በጀቱ በቂ ስላልሆነ ማኅበረሰቡ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ ባለው አቅም እንዲረዳ፣ የባንክ የሒሳብ ቁጥር የማሰናዳት ዓላማ እንዳለ ታውቋል፡፡

ለዓለም የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል ለሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንዲሆን የታሰበው የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ሁለት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ግንባታው እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል የሚል ግምት እንደነበር፣ ነገር ግን በአገሪቱ አጋጥሞ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሌሎችም ምክንያት መጓተቱ ታውቋል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ የተገባውም በቅርቡ እንደሆነና ለቅድመ ግንባታው ወሳኝ የሆኑ የአካባቢ ጥናቶች መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሚያርፈው በ150 ሔክታር መሬት ላይ እንደሆነ፣ በዙሪያው የሚኖሩ 150 የሚሆኑ አባወራዎች እንደሚነሱና ለእነሱም አስፈላጊውን ካሳ ለመስጠት ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ቢተው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሚያዝያ 15 እና 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በዓድዋ ከተማ ‹‹የፓን አፍሪካኒዝም ተቋም መፍጠር፣ የመጀመሪያው የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጉባዔ›› በሚል መሪ ቃል በሚዘጋጀው ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ፣ የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የታወቁ የፓን አፍሪካኒዝም ምሁራንና ተመራማሪዎችን ጨምሮ እስከ 700 የሚሆኑ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ንድፈ ሐሳብ፣ ዓላማዎቹ፣ የሚሰጣቸው የትምህርት ዓይነቶችና የሕንፃዎቹ ዲዛይን መረጣ ለውይይት ከሚቀርቡ ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲውን የሚመራ የዳይሬክተሮች ቦርድም ይመረጣል፡፡ ግንባታው በመጪው ዓመት ወይም በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይጀመራል ያሉት ሰብሳቢው፣ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡