Skip to main content
x
ውኃ የማታውቀው ሉቄ ቀዱሳ ያገኘችው ዕፎይታ
አዲስ የተተከለውን የውኃ ማጣሪያ በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩት ነዋሪዎች እንግልታቸውን እንደሚቀንስላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል

ውኃ የማታውቀው ሉቄ ቀዱሳ ያገኘችው ዕፎይታ

ውኃ በየመንደሩና በየቤቱ በገባበት የከተሜ ኑሮ የአንድ ጀሪካን ውኃ ዋጋ ከአንድ ብር አይበልጥም፡፡ ለገጠር ነዋሪዎች በተለይም የቤት ውስጥ የሥራ ጫና ለሚሸከሙ እናቶችና ልጃገረዶች ግን አንድ ጀሪካን ውኃ ግምት በአንድ ብር የማይገደብ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፡፡ ጢሻ በጥሰው ወጣ ገባውን የገጠር መንደር አቋርጠው ከጎርፍ የማይሻል ድፍርስ ውኃ ለመቅዳት የሚያደርጉት የእግር ጉዞ በትንሹ ግማሽ ቀን ሊሆን ይችላል፡፡ አቅሙ ያላቸው የቀዱትን ውኃ በአህያ አስጭነው ይህም ቅንጦት የሆነባቸው ደግሞ ጀሪካኑን እንደ ልጅ በጀርባቸው አዝለው ወደ የቤታቸው ያዘግማሉ፡፡ ታዲያ ለእነኚህ የገጠር ሴቶች እያንዳንዱ ጀሪካን የዕድሜያቸው የተወሰነ ክፍል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ኪውቢክ ኪሎ ሜትር ውኃ አለ፡፡ 97 በመቶ የሚሆነው ጨዋማ፣ 2.1 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በምድር ዋልታ አካባቢዎች የበረዶ ግግር ሆኖ ይገኛል፡፡ ካለው ጠቅላላ የውኃ ክምችት አገልግሎት ላይ የሚውለው አንድ በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ለኃይል ማመንጫነትና ለተለያዩ የግብርና ተግባራት ይውላል፡፡ የተቀረው ለመጠጥና ለቤት ውስጥ መገልገያነት ይውላል፡፡ ይህ በቂ ባለመሆኑ በዓለም ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁህ ውኃ ለማግኘት እንዳይታደሉ ሆኗል፡፡

‹‹ዘስቴት ኦፍ ዘወርልድስ ወተር 2017›› በሚል ወተር ኤድ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ 51 በመቶ የሚሆኑ በገጠር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ንፁህ ውኃ አያገኙም፡፡ ኢትዮጵያ በንፁህ ውኃ ተደራሽነት ረገድ ከመጨረሻዎቹ አሥር አገሮች ተርታም ትሠለፋለች፡፡

በገጠር አካባቢ ያለው መሠረታዊ የውኃ ተደራሽነት ችግርም በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ላንፎሮ ወረዳ ሉቄ ቀዱሳ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ በዚህች ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የውኃ መሠረተ ልማት የራቃቸው ናቸው፡፡ ውኃ ለማግኘት ከቤታቸው እስከ ስምንት ኪሎ ሜትሮች በእግራቸው ለመጓዝ የሚገደዱ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ብዙ የሚቸገሩ ናቸው፡፡ የሚጠቀሙት የኩሬ ውኃ ለጊዜው ጥማቸውን ያስታግስ እንጂ ብዙ የጤና ችግሮች እንደሚያስከትልባቸው ያውቃሉ፡፡ ውኃው በፍሎራይድ የተጠቃ ሲሆን፣ ሕፃን፣ አዋቂ ሳይል ጥርሳቸው እንዲበለዝ አድርጓል፡፡ ከዚህም ሲያልፍ የተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ዳርጓቸዋል፡፡  

ወ/ሮ ባድገሌ ሁሴን በአካባቢው መኖር ከጀመሩ ከ15 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ባድገቤ የኩሬ ውኃ ለመቅዳት በአቅራቢያቸው ወደ ሚገኘው የሻንቃጦ ቀበሌ በእግራቸው ለስድስት ሰዓታት ይጓዛሉ፡፡ በሌሊት አህዮቿን እየነዳች ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ኩሬው ደርሳ የምትቀዳው የኩሬ ውኃ በሰዎችና በከብቶች ሽንት የተበከለ፣ የደፈረሰና አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚከብድ ነው፡፡

በቀበሌው ስድስት ኩሬዎች ቢኖሩም ሁሉም በፍሎራይድ ኬሚካል የተጠቁና ለበሽታ ሲያጋልጣቸው መቆየታቸውን ለኩላሊት፣ ለጨጓራ፣ ለተቅማጥ፣ ለጥርስ መበለዝና ለሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች መጋለጣቸውን ይናገራሉ፡፡ በበጋ መጠኑ የሚቀንሰውን የኩሬ ውኃ ለማግኘት ልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታ አስቀርተው ውኃ እንደሚያስቀዷቸው፣ በአግባቡ ምግብ አብስለው ለመመገብ የሚቸገሩባቸው ጊዜያት ቀላል አለመሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ይህንኑ የኩሬ ውኃ ለማግኘት ለሦስትና አራት ቀናት ወረፋ ለመጠበቅ እንገደዳለን፡፡ ልጆቻችንን በዚህ ምክንያት ለረሃብና ለበሽታ ተጋልጠው የሚሞቱበት አጋጣሚ ነበር፤›› በማለት አንድ ጀሪካን ውኃ ለማግኘት የሚደርስባቸውን እንግልት ለሪፖርተር ያብራራሉ፡፡

ሌላዋ የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ ዙልፋ ሐሰን፣ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘው የሚቀዱት ውኃ በከብት ለማጓጓዝ ያልታደሉ አንዳንድ እናቶች፣ የቀዱትን የኩሬ ውኃ በወገባቸው ተሸክመው በሚጓዙበት ጊዜ እየተንበጫበጨ በላያቸው ላይ የሚፈሰው በሰውነታቸው ላይ ሲያርፍ የማቃጠል፣ የማሳከክና ወዝ የማሳጣት ባህሪ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ በጉዞ ላይ ከሚያጋጥሙ የውርጭ፣ የፀሐይ፣ በድካም ምክንያት መንገድ ላይ የማደር አጋጣሚዎች በተጨማሪ የመደፈርና ሌሎችም አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት የደረሰባቸው እናቶች እንዳሉ ወ/ሮ ዙልፋ  ያስታውሳሉ፡፡

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጥናት መሠረት ከሆነ 1.5 ሚሊ ግራም ሊትር በላይ የኬሚካል ይዘት ያለው ውኃ በፍሎራይድ የተጠቃ ነው፡፡ ፍሎራይድ ጤናን ከሚጎዱ ኬሚካሎች አንዱ ሲሆን፣ ከባድና ቀላል የጤና ችግር ያስከትላል፡፡

አቶ በላይ ሥዩም የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርና ፍሎሪንሲሲ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪ እንደሚሉት፣ ፍሎራይድ ጥርስ የማበለዝ፣ አጥንት የመብላት ባህሪ አለው፡፡ የኬሚካሉ አስከፊነት በይበልጥ የሚስተዋለውም በሕፃናት ላይ ነው፡፡

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ከሆነ በተለይ ሕፃናት ጥርሳቸውን ከመንቀላቸው እስከ ስምንት ዓመታቸው ድረስ በፍሎራይድ የተበከለ ውኃ ከጠጡ ከጥርስ አልፎ ለአጥንት በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን አቶ በላይ ያስረዳሉ፡፡

በፍሎራይድ የተጠቃ ውኃ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ላይ በስፋት የሚስተዋል ሲሆን፣ በሦስት ክልሎች በኦሮሚያ፣ በደቡብና አፋር የሚገኙ 31 ወረዳዎች ከመጠን ያለፈ ፍሎራይድ ተጠቂ መሆናቸውን አቶ በላይ ይናገራሉ፡፡

በሉቄ ቀዱሳ ያለውን ሥር የሰደደ የውኃ ችግር ለመፍታት  የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተለያዩ የውኃ ማጣሪያዎችን በሥፍራው ላይ ቢተክሉም በውኃ ውስጥ ያለውን ፍሎራይድ ሙሉ በሙሉ ማጥራት ባለመቻሉ ችግሩን መቅረፍ ሳይቻል መቆየቱ ተገልጿል፡፡

አሁን ግን ዕፎይታ የሚያገኙበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኮሪያ የንግድና ኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ኤጀንሲ ከኮትረ አሲ ትሬዲንግና ቲኤንድሲ ጋር በጋራ በመሆን በሶላር ኃይል የሚሠራና በፍሎራይድ የተበከለን ውኃን አምስት እጥፍ የሚያጠራ ቴክኖሎጂን ለቀበሌው ነዋሪዎች አበርክተዋል፡፡

ስምንት ወራት የፈጀው ይኼ የውኃ ማጣሪያ ቴክኖሎጂ በስምንት ሰዓት ውስጥ ስድስት ሺሕ ሊትር ውኃ የማጣራት አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡

ከ200 ሺሕ ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት የተገነባው ይህ የውኃ ማጣሪያው ቴክኖሎጂ 5,000 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎለታል፡፡

አዲስ የተተከለው የውኃ ማጣሪያ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለፍጆታ ክፍት የሚሆንበትን የምረቃውን ቀን በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች በጥቂቱም ቢሆን የነበረባቸውን እንግልት እንደሚቀንስላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በከፍተኛ ፍሎራይድ የሚጠቃ ውኃ ይጠቀማሉ ተብለው የሚገመቱት ከስምንት እስከ 12 ሚሊዮን ሰዎች በስምጥ ሸለቆ አካባቢ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ናቸው ተብሏል፡፡