Skip to main content
x

የግል ባንኮች በዘጠኝ ወራት ውስጥ 8.4 ቢሊዮን ብር አተረፉ

  • የትርፉ መጠን በሙሉ ዓመት ከሚያተርፉት የላቀ ሆኗል

በኢትዮጵያ የተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያሳርፍ ቆይቷል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ በመጠን ተተንትኖ ሲቀርብ ባይታይም፣ በችግሩ ሳቢያ ግን በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው  ታይቷል፡፡ አለመረጋጋቱ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎችንም ነካክቷል፡፡

የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ጫና ውስጥ እንደገቡ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች፣ አለመረጋጋቱ ተበዳሪዎች ዕዳቸውን በወቅቱ እንዳይመልሱ ምክንያት ሆኖ እንደቆየ ይጠቅሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲስ የብድር አሰጣጥ መመርያ ሲታከልበትም በተለይ በዚህ ዓመት የባንኮች የብድር አሰጣጥ እንዲቀዛቀዝ ማድረጉ ይነገራል፡፡

ባንኮች ማበደር እየቻሉም ብድር ከመልቀቅ ተቆጥበው እንደቆዩ ባለሙያዎቹ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ያለገደብ ብድር መስጠት የሚቻለው ለወጪ ንግድ ዘርፍና ኢንዱስትሪዎች ብቻ ይሁን በመባላቸው የተነሳ ባንኮቹ ለሌሎች ዘርፎች መዋል የሚችሉትን ያህል ብድር እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ በአብዛኛው በግል ባንኮች ላይ የታየ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በዚህ በጀት ዓመት ባንኮች በቀደሙት ዓመታት ሲያሳዩ የነበረውን ዓይነት ዕድገት በዚህ ዓመት ያሳያሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ይህ ማለት ግን ባንኮቹ አትራፊ አይሆኑም ማለት እንዳልሆነ የሚገልጹት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች፣ አትራፊ ሆነው መዝለቃቸው፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸውና ከሌሎች አገልግሎቶች የሚያገኙት ገቢ እየጨመረ መሄዱ እንዳልተገታ ያብራራሉ፡፡ ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ባንኮች፣ በቀደሙት ዓመታት ከነበራቸው የዕድገት መጠን አኳያ ዘንድሮ እንደ ወትሯቸው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላያሳዩ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡

ፖለቲካዊ ቀውሱና አለመረጋጋቱ ባይኖር ኖሮ የባንኮቹ ውጤት እንደ ወትሮው ከፍተኛ ሆኖ ሊቀጥል ይችል እንደነበርም ባለሙያዎቹ ይጠቅሳሉ፡፡ ፖለቲካዊ ችግሩ እንዳለ ሆኖ፣ ሪፖርተር ካገኘው የዘጠኝ ወራት የባንኮች አፈጻጸም ግርድፍ ሪፖርት ለመገንዘብ እንደተቻለው ከሆነ ሁሉም ባንኮች ትርፋማነታቸው እንደተጠበቀ ነው፡፡

አንዳንዶቹ ባንኮች በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያስመዘገቡት ግርድፍ የትርፍ መጠን ባለፈው ዓመት ካስመዘገቡት ይልቅ በእጥፍ ማደጉን ለማየት ተችሏል፡፡ የባንኮቹ የዘጠኝ ወራት ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ 16ቱ የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት በድምሩ ያተረፉት መጠን 8.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ አኃዝ የግል ባንኮች በሙሉ ዓመት እንኳ አስመዝግበው የማያውቁት መጠን እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡

ይህ የትርፍ መጠን ባለፈው ዓመት ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በሦስት ቢሊዮን ብር ብልጫ የታየበት ነው፡፡ ባንኮቹ የቱንም ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ቢገለጽም፣ ትርፋማነታቸው ግን እያደገና ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ይልቁንም በዘንድሮው የዘጠኝ ወራት አፈጻጸማቸው የታየው የትርፍ ምጣኔ፣ በጀት ዓመቱ ሳይጠናቀቅ እንኳ የሁለት ባንኮች ግርድፍ ትርፍ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ አመላክቷል፡፡ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት የአዋሽና የዳሸን ባንክ በዘጠኝ ወራት ውስጥ እንዳስመዘገቡት  የተጠቀሰው የትርፍ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ነበር፡፡

በጥቅሉ ሲታይ፣ ዘንድሮ ከ16ቱ ባንኮች መካከል በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተመዘገበው ግርድፍ የትርፍ መጠን እንደየባንኮቹ ደረጃና አቅም ከ82 ሚሊዮን ብር እስከ 1.38 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ አዋሽ ባንክ ዘንድሮም ከፍተኛውን ትርፍ በማስመዝገብ የቀዳሚነቱን ደረጃ አስጠብቆ እየተጓዘ ሲገኝ፣ ዳሸን ባንክ በቅርብ ርቀት ይከተለዋል፡፡

የ2010 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከባንኮች ትርፍ ባሻገር፣ ዓምና በዘጠኝ ወሩ መጨረሻ ላይ 180.2 ቢሊዮን ብር የነበረው የ16ቱ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ፣ በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት መጨረሻ ላይ 249.5 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም የባንኮቹን የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ዕድገት እያሻቀበ ለመምጣቱ አንደኛው ማመላከቻ ነው፡፡

ባንኮቹ ያላቸው የሀብት መጠንም ቢሆን ዕድገት የታየበት መሆኑን የሚጠቁመው ይህ ሪፖርት፣ በአሁኑ ወቅት የባንኮቹ የሀብት መጠን 314.5 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ያሳያል፡፡ ይህ የሀብት መጠን በቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 237 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ፣ ከ97 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ የተመዘገበበት ነው፡፡

ከብድር አቅርቦት አንፃርም 16ቱ ባንኮች በዚህ ዓመት ዘጠኝ ወራት መጨረሻ ድረስ የሰጡት የብድር መጠን 172.5 ቢሊዮን ብር እንደነበር ታውቋል፡፡ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ሲታይ በወቅቱ የቀረበው የብድር መጠን 127.7 ቢሊዮን ብር በመሆኑ የዘንድሮው ጉልህ ብልጫ የታየበት ሆኖ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የብሔራዊ ባንክ መመርያና የአገሪቱ አለመረጋጋት ባይገድባቸው ኖሮ ባንኮቹ ሊያቀርቡ የሚችሉት የብድር መጠን ከዚህም በላይ ይሆን ነበር፡፡ የብድሩ የዕድገት መጠንም ቢሆን ከዚህ የበለጠ ይሆን እንደነበር ያመለክታሉ፡፡

በተለይ ባንኮች ላይ የተቀመጠው የብድር ገደብ፣ ለተለያዩ የኢኮኖሚና የንግድ ዘርፎች ሊሰጡ ይችሉ የነበረውን ብድር መመርያው ባስቀመጠባቸው ገደብ ምክንያት ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶቹም የሚሰጡት ብድር እንደየዘርፉ ዓይነት የብድር ጣሪያ የተቀመጠበት በመሆኑ፣ ብድር መስጠት እንዳይችሉ የሚያሳስብ ደብዳቤ ከብሔራዊ ባንክ ተጽፎላቸዋል፡፡ ይህንን በማስታወስ ባንኮች መስጠት የሚገባቸውን ያህል ብድር እንዳልሰጡ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡

ዓምና በዘጠኝ ወራት ውስጥ ባንኮች ከ237.3 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ሲያካብቱ ከዚህ ውስጥ የሁለት ባንኮች የሀብት መጠን ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሶ ነበር፡፡ ሦስት ባንኮች ደግሞ የአሴት መጠናቸው ከ20 እስከ 23 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ሁለት ባንኮች ከ14 እስከ 17 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ አሴት የነበራቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ባንኮች ደግሞ ከ1.5 እስከ 9.4 ቢሊዮን ብር የሚደርስ እንደነበር ያመለክታል፡፡

ይህ መረጃ በዘንድሮው የዘጠኝ ወራት ከደረሱበት አንፃር ሲታይ ከፍ ያለ ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ የዓመት መጠኑን ከፍ በማድረግ በዘጠኝ ወሩ መጨረሻ ላይ ዓመቱን 50 ቢሊዮን ብር በማድረስ ቀዳሚው የግል ባንክ ሆኗል፡፡ ከእርሱ በመቀጠል ከፍተኛ አሴት ያለው መሆኑ የተመለከተው ዳሸን ባንክ ነው፡፡ ዳሸን ባንክ በዘንድሮው የዘጠኝ ወራት መጨረሻ ላይ የደረሰበት አሴቱ 40.4 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡

በ2010 በጀት ዓመት የአሴት መጠናቸውን 20 ቢሊዮን ብር በላይ ያደረሱ ባንኮች ስምንት ደርሰዋል፡፡ በቀደመ ዓመት ግን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ዓመት እንደነበራቸው የተገለጹት የግል ባንኮች አምስት ብቻ ነበሩ፡፡

በዘንድሮው በጀት ዓመት አጠቃላይ ዓመታቸው ከአምስት ቢሊዮን ብር በታች የሆኑት ሁለት ባንኮች ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 14 ባንኮች የአሴት መጠናቸው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ይኸው የዘጠኝ ወሮች ግርድደፍ የሒሳብ ሪፖርት ያመለክታል፡፡