Skip to main content
x

ሕዝብ ቆጠራውና ሕገ መንግሥቱ

በገነት ዓለሙ

ከአሥር ቀናት አሰልቺ ንዝንዝና ጭቅጭቅ የበዛበት የአዲስ ዓመት ረዥም ‹‹ሽግግር›› በኋላ እነሆ 2010 ዓ.ም. ውስጥ ገብተናል፡፡ የአዲሱን የ2010 ዓ.ም. መዳረሻ ሁለት ሳምንታት የንዝንዝ ጊዜ ያደገው ባለፈው ሳምንት እንዳመላከትኩት፣ ሕዝባዊ በዓላትን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያ የማድረግ ያልተላቀቀን ክፉ ልምድ ነው፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የመንግሥት ያለስፍራውና ያለቦታው መግባት ነው፡፡

አዲሱ ዓመት በአጀንዳነት ከያዛቸው መደበኛ ግዙፍ ሥራዎች መካከል አንዱ፣ በየአሥር ዓመቱ የሚናወነው፣ መከናወን ያለበት የሕዝብ ቆጠራ ተግባር ነው፡፡ የዘንድሮው አራተኛው የሕዝብ ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ከፈጀው 74 ሚሊዮን ዶላር የበለጠ የሚያስከፍል፣ የኢትዮጵያ የልማት አጋዥ ቡድን (DAG) እንደገለጸው ደግሞ 123 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቅ ግዙፍ ሥራ ነው፡፡

ሥራውን ግዙፍ የሚያደርገው ግን የሚጠይቀው ወጪ፣ የሚከሰከስለት የገንዘብ መጠን አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ወይም ወዲህ (በ1985፣ በ1989፣ በ1991፣ በ1997 በተከታታይ) የወጡት የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ሕጎች፣ የሕዝብ ቆጠራ ውጤት የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ለሚደረገው ሕገ መንግሥታዊ አደረጃጀትና ለፖለቲካዊ ሥርዓቱ ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን፣ ትክክለኛውን የሕዝብ ብዛት ማወቅ በአገር አቀፍ ወይም በተወሰነ የክልል አስተዳደር እርከን ደረጃ ለሚደረጉ ምርጫዎች አፈጻጸም አስተማማኝ መሠረት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ስለተግባሩም አስፈላጊነት ስፋትና ውስብስብነትም ይናገራሉ፡፡ በ2010 ዓ.ም. የሚደረገውን የሕዝብ ቆጠራ ድቅን ተግባር በተለይ ማናቸውንም ይህን መሰል የአሥር ዓመት ሥራ በአጠቃላይ ግዙፍ የሚያደርገው ግን፣ ይህ ሁሉና ከላይ የተጠቀሰው ብቻ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥታዊ ‘ማንዴት’ መሆኑ ግዙፍነቱን ይበልጥ የከበደ ያደርገዋል፡፡ የ2010 ዓ.ም. የሕዝብ ቆጠራ የመንግሥት ተግባር የበለጠ ግዙፍና ልዩ የሚያደርገው ደግሞ የተለየ ጉዳይ አለ፡፡

ይህንን በአጭሩ እናብራራ፡፡ የሕዝብ ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ የሚከናወን ተግባር ያደረገው በተለይም ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 103 የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽንን ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አካል አድርጎ ‹‹ያቋቁማል››፡፡ የሕዝብ ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል፡፡ በውጤቱም መሠረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል ይወስናል ይላል፡፡ አራተኛው የኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ በ2010 ዓ.ም. ይካሄዳል ማለት በዚህ ሥሌት ሦስተኛው የኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ የተካሄደው በ2000 ዓ.ም. ነበር ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ቆጠራ የተካሄደው ግን በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ መጀመርያም በተቋቋመ አሠራርና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሦስተኛው የሕዝብ ቀጠራ መካሄድ የነበረበት በ1997 ዓ.ም. ነበር፡፡

በዚህ መሠረት የማይናጋው የአራተኛው የሕዝብ ቆጠራ ሕገ መንግሥታዊ የካሌንደር ዘመንም 2007 ዓ.ም. መሆን ነበረበት፡፡ ይህንን በሕገ መንግሥቱ ላይ የተመሠረተ የሕዝብ ቆጠራ ዘመን ካሌንደር ያናጋው ምርጫ 97 እና ሕዝብ ቆጠራ 97 በመግጠማቸውና በወቅቱ በይፋ እንደተገለጸው ደግሞ፣ መንግሥት ሁለቱን ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንድ ላይ ማከናወን አልችልም በማለቱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ምርጫ 97 በወቅቱና በሕጉ መሠረት ሲካሄድ የሕዝብ ቆጠራው ግን ወደ 1999 ዓ.ም. ተሸጋግሮ በዚያው ዓ.ም. ተካሄደ፡፡ አራተኛውም ቆጠራ የ2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ያዘ፡፡ ሦስተኛው ቆጠራ የተካሄደበትና አራተኛው ቆጠራ የሚካሄድበት ጊዜ ልዩነትና ሥሌት እንደሚያሳየው ሕገ መንግሥታዊው የአሥር ዓመት የጊዜ ወሰንን ያናጋ አሠራር መኖሩን እንረዳለን፡፡ ለዚህ አሠራር መሠረት የሆነ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ የሕግ ማሻሻያ ተደርጓል ወይ? በዚህ ጽሑፍ በዝርዝር የምንመለከተው አንደኛው ጉዳይ ይኸው ነው፡፡

ከዚህ በፊት ግን ከሕዝብ ቁጥር ጋር የተያያዘ አንዳንድ ጉዳዮች አንስተን እንነጋገር፡፡ በዕድገት እንቅፋትነት ተዘውትረው ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል አንደኛው የሕዝብ ቁጥር ብዛት ነው፡፡ ይህ በተለይም በደርግ ዘመን ልማት ለምን አልሳካልን አለ ተብሎ ሲጠየቅ ከሚቀርቡት ምክንያት አንዱ ነበር፡፡ አሁንም በዘወርዋራ እንደ ችግር ይነሳል፡፡ ሥልጣን ስንረከብ የነበረው ሕዝብ ቁጥር ብዛት ስንት ነበር? አሁንስ ያለው ስንት ነው? እያሉ ጥያቄና መልስ ውስጥ የሚገቡ ባለሥልጣናት ግብ ይህንኑ ለማስረገጥ ነው፡፡ በልማት ፕሮግራም ውስጥ የሕዝብ ቁጥርን ጉዳይ ማካተትና የዕድገት መጠኑንም እንዳስፈላጊነቱ መቆጣጠር አስፈላጊ ቢሆንም፣ 1.5 ቢሊዮን ያህል ሕዝብ ይዛ ቻይና ስትመዘዝ እየታየ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት አደናቀፈን ማለት አይቻልም፡፡

የሕዝብ ቁጥርን ብዛት የዕድገት ፀር ወይም እንቅፋት አድርጎ ማየት ከገዢዎች ማሳበቢያነት በላይ ሕዝብን (ሰውን) በበላተኛነት ወይም በተገልጋይነቱ ብቻ ከማሰብ ጋር የተዛመደም ነው፡፡ ሕዝብ ከአፍና ከሆድ በላይ የማወቅ፣ የመፍጠርና የመሥራት ችሎታን ልምድና ስሜትን የተሸከመ ሀብት ነው፡፡ ችግሩ ያለው ይህ ሀብት የጦርነት፣ የግጭት፣ የድንቁርናና የችጋር፣ የቡዘናና የእንብላው ፍልስፍና መጫወቻ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ለምንድነው ሕዝብ ከዚህ ተላቆ በልማት ላይ የማይሰማራው? ዋናውን ችግር መረዳት የምንችለው በዚህ አቅጣጫ ስንጠይቅ ነው፡፡ ከኢኮኖሚው ዕድገት ፍጥነት በላይ የሕዝብ ቁጥር ፍጥነት እየቀደመ አስቸገረን ብሎ መከራከሪያና መከላከያ ማቅረብም ዞሮ ዞሮ ለኢኮኖሚው ዕድገት ችግር ወይም ቀርፋፋነትና ዘገምተኝነት የሕዝብ ቁጥር ፍጥነትን ማመካኛ ማድረግ ነው፡፡ ለዚያውም ቁጥሩ በዛ ከሚባለው አብዛኛው በረሃብና በከፊል ረሃብ ውስጥ እየኖረ የኅብረተሰቡ ትርፍ ሀብት ግን የጥቂቶች መጫወቻ ሆኖ ሳለ፣ የሕዝብ ቁጥር ፍጥነት አስቸገረ ማለት ዳርዳሩን መዞር ነው፡፡

በሌላ ጎን፣ የጊዜያችን የኢትዮጵያ ሕዝብ የዕድሜ ጥንቅር በአዲስ ትውልድ የተሞላ የልማት በረከት እየተባለ በሚካሄደው ሙገሳ ውስጥ የተጋረደ አሳሳቢ ጥያቄ አለ፡፡ በሥልጣኔ በበለፀጉ አገሮች ያለው ሥር የሰደደ የቤተሰብ ምጣኔና በጣም የተሻሻለ የአማካይ ዕድሜ ርዝማኔ፣ የማታ ዕድሜን ለመንከባከብ ከሚያስችል ማኅበራዊ ዋስትናና ግላዊ ጥሪት ጋር ተገናዝቦ የኅብረተሰቡን ጥንቅር ወደ አሮጌ ትውልድ የማጋደል ዝንባሌ ውስጥ እየወሰደ መሆኑ እንደ ችግር ይወሳል፡፡ በእኛ አገር ውስጥ ልጆችና ወጣቶችን ያበረከታቸው ምንድነው? በድህነት የሚዳፋ ኑሮ ያራባው ወሊድ? አንጋፋዎችን የመንከባከብ ማኅበራዊ ማህፀናችን ተናግቶ? ከቅርብ ዓመታት በፊት ሰባ ምናምን ሚሊዮን ተቆጠረ የተባለ የሕዝብ ብዛት መቶ ሚሊዮን ደረሰ እየተባለ ዛሬ መነገሩ እውነትን የሚያንፀባርቅ ከሆነ፣ ‹‹በሰፊ ገበያነት ኢትዮጵያ ብዙ ፈላጊ አላት›› ከማለት በበለጠ የዚህ ዓይነቱ የሕዝብ ቁጥር አስተዳደግ ሊያስደነግጠን ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ትክክለኛ ምላሽ እስካላገኙና ልጅ መውለድ በአግባቡ አንፆ ከማሳደግ አቅም ጋር ካልተገናኘ፣ የሕዝብ ቁጥር የጋሸበ አስተዳደግ የብዙ ችግሮች መፍሊያ ሆኖ የእነ ሜክሲኮ/ ብራዚል ዓይነት ወጥመድ ውስጥ መክተቱ የማይቀር ነው፡፡

ወደ ዋናው የሕዝብ ቆጠራ ጉዳይ እንመለስ፡፡ የሕዝብ ቆጠራ ‘የጥበብ ሁሉ መጀመርያ’ ነው፡፡ ለ‹‹ሕገ መንግሥታዊ አደረጃጀትና ለፖለቲካዊ ሥርዓቱ ዝግጅት አስፈላጊ›› ነው (አዋጅ ቁጥር 449/97 መግቢያ)፡፡ በሕገ መንግሥቱም እንደተደነገገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር የተመሠረተውም በሕዝብ ቁጥር ላይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በዜጎች በኩል መቆጠርና የሕዝብ ቆጠራ መረጃ መስጠት ግዴታ ነው፡፡ ከመንግሥት አንፃር ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ግዳጅ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በተመዘገበው ታሪክ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ከናዝሬት ውጪ ቤተልሔም የተወለደው ዮሴፍና ማርያም ከመደበኛ መኖርያቸው (ናዝሬት) የሮማ መንግሥትን የሕዝብ ቆጠራ ሕግ ግዴታ ለመፈጸም (ሊቆጠሩ) ወደ ቤተልሔም መሄድ ስላለባቸውና ስለሄዱ ነው፡፡ ይህን ያህል የከበደ ግዴታ ነው፡፡ የሕዝብ ቆጠራ የመንግሥት ግዴታ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የገባው፣ ግዴታውንም ያቋቋመው ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት በላይ ከፍ ያለ የሥልጣን አካል እንዲሆን የተደረገው ጉዳዩ የምርና ብርቱ ሥራ በመሆኑ ነው፡፡

ምርጫና ቆጠራ 1997 ላይ የገጠሙት ሳይታወቅና ድንገት አይደለም፡፡ ወይም የምድር ሠራዊት የሰማይ መላዕክት ሊያስቡትና ሊገምቱት በማይችሉበት ሁኔታ አይደለም፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ መደበኛነቱ በሕግ የተቋቋመው የየአሥር ዓመት የሕዝብ ቆጠራ ‹‹በአጋጣሚ›› ሥርዓት ተሻጋሪ ለመሆን ታድሎ፣ በ1985 ዓ.ም. በወጣው የሕዝብና የቤት ቆጠራ ኮሚሽን ሕግ ተፈጻሚነት መሠረት ቀጠለ፡፡ በደርግ አንድ ብሎ የተጀመረው የሕዝብ ቆጠራ ሁለት ብሎ በኢሕአዴግ ቀጠለ፡፡ የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት የወጣው የ1991 ዓ.ም. የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን (እንደገና) ማቋቋሚያ ሕግ ‹‹በየአሥር ዓመቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ›› ማከናወንን ዘላቂ የመንግሥት ሥራ አድርገው አቋቋሙ፡፡

የሕዝብ ቆጠራውና አጠቃላይ ምርጫው በየአሥር ዓመቱ መገጣጠማቸው እውነት ቢሆንም፣ የማይታወቅና አስቸጋሪ እንዲሁም ሁልጊዜም እውነት አይደለም፡፡ ባይሆን የቆጠራው ውጤት ከምርጫ በፊት ዝግጁና ስንዱ፣ የታወቀም ሆኖ መገኘት አለበት ከተባለ ይህን አስቀድሞ ‹‹መደቆስ›› (መዘጋጀት) እንጂ ‹‹ድስት ጥዶ ማልቀስ›› አይደለም መፍትሔው፡፡ ምርጫው ከሕዝብ ቆጠራው ጋር መገጣጠሙ ሁልጊዜም እውነት አይደለም ያልኩበት ምክያት ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት መሆኑ፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቅ እንዳለበት መደንገጉ እውነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የስም ጌጥ ከመሆን ያለፈ ሥርዓት በተዘረጋበት አገር ውስጥ ለአምስት ዓመት የተመረጠው ምክር ቤት የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት ሊበተንና አዲስ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 60 በሚደነግጋቸው ሁለት ሁኔታዎች መሠረት ምክር ቤቱ ተበትኖ አዲስ ምርጫ እንደሚደረግ በተገለጹት ሁኔታዎች ምክንያት ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ፣ አዲስ ምርጫ ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መደረግ እንዳለበት አዲሱ ምርጫ በተጠናቀቀ በሠላሳ ቀናት ውስጥ የተመረጠው አዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን እንደሚጀምር ይወስናል፡፡

ከአጀማመራችን የተነሳ የሕዝብ ቆጠራና ምርጫ በየአሥር ዓመቱ መገጣጠማቸው እውነት ቢሆንም፣ ሁሌም በአዲስ ዘመን መባቻ ላይ እንደሚባለው እንደ መስቀል ወፍና እንደ አደይ አበባ የሞት ቀጠሮ ግን የላቸውም፡፡ ሁለቱም ግዙፍ ሥራዎች ናቸው፡፡ ሁለቱንም አንድ ላይ ማስተናገድ አይቻልም ተብሎም ጭራሽ እንዳይደራረሱ እናድርግ አይባልም፡፡ ሁለቱም የየራሳቸውን ዝግጁነትና ድንገተኛ ስንዱነት የሚጠይቁ ሥራዎች ናቸው፡፡ ይልቁንም የሕዝብ ቆጠራ ዋና ፋይዳ ምርጫ ብቻ ባይሆንም፣ የሕዝብ ቆጠራ ለምርጫ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ እሱን ያገለግል ዘንድ ሆኖ መታቀድ አለበት፡፡

ሦስተኛው የሕዝብ ቆጠራ የተካሄደው ሁለተኛው ምርጫ በተካሄደ በአሥር ዓመቱ ላይ አይደለም፡፡ አራተኛውም ምርጫ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) ‹‹በየአሥር ዓመቱ ያካሄዳል›› የሚለውን ድንጋጌ ከማክበር ነፃ የወጣ ይመስላል፡፡ ለምን? የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ባለፉት 26 ዓመታት ተሻሽሏል ወይ? ይህ ጥያቄና አቤቱታ (አቤቱታው የጋዜጣ ጩኸትና ጫጫታ ሆኖ ቀረ እንጂ) የ1995 ዓ.ም. መጨረሻና የተከታይ የሪፖርተር ጋዜጣ ልዩና የብቻ ዜናና አስተያየት/ሙግት ሆኖ ሲቀርብ አስታውሳለሁ፡፡

አሁንም መጠየቅ ያለበት መልስ ሊገኝበትም የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም. የታወጀው ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ውሏል›› የተባለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ ማሻሻያ ተደርጎበታል ወይ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ መንገድ የሚያሳየን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 6/2008 ነው፡፡ የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. የወጣ ቢሆንም ስለሕገ መንግሥት ማሻሻያ መታተም የሚገልጸው የመጀመርያው የአገር ሕግ ይህ ደንብ ነው፡፡ የዚህ ደንብ የአንቀጽ 59 ድንጋጌ፣

  1. የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚኖርበት ጊዜ እያንዳንዱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ቁጥር ተሰጥቶት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ መታተም ይኖርበታል፡፡
  2. እያንዳንዱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚታተመው ሕገ መንግሥት መጨረሻ ላይ ‹‹ማሻሻያ›› የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ይካተታል፡፡
  3. የተሻሻሉት የሕገ መንግሥት አንቀጾች እንደነበሩ ይቀመጣሉ፣ ማሻሻያ የተደረገባቸው መሆኑን የሚገልጽ ምልክት ሊደረግባቸው ይችላል ይላል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ሕገ መንግሥቱ የተሻሻለ መሆኑን የሚነግረን ምንም የለም፡፡

ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ጉዳይ የተነሳባቸው ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ከአንድ በላይ ብዙ ስለመሆናቸው መገመት የሚቻልና የሚታወቅ ቢሆንም፣ ሕዝብ የሚያውቀውና ይፋ የወጣው አንደኛው ጉዳይ ግን በ1995 ዓ.ም. ተጀምሮ በ1996 ዓ.ም. የተጠናቀቀው የማሻሻያ ተግባር ነው፡፡ ከ1995 ተጀምሮ በ1996 ዓ.ም. ተጠናቀቀ ስንል ሕገ መንግሥቱን የማሻሻሉ ተግባር ረዥም ጊዜና ‹‹እልህ አስጨራሽ›› ሥራና ጥረት ወስዷል ያልን እንዳይመስልብን፡፡ መጀመሪያ ይህን አፍታትተን እንግለጽ፡፡

የማንኛውም ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥራ መደበኛ ሕግ ከማውጣት የከበደ ተግባር ነው፡፡ በእኛም አገር ሁሉም ሕገ መንግሥቶቻችን ይህን ባህል ከመከተል የአንደበትና የጽሑፍም ወግ ሰንፈውና ከዚሁ ወጥተው አያውቁም፡፡ ከተጻፈ ሕግ አኳያ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ድንጋጌዎችም ፅኑና ብርቱ የሚባሉ ናቸው፡፡ ዝርዝሩ ውስጥ አንገባም፡፡ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 104 እና 105 ይመለከቷል፡፡

በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ወደ 1999 ዓ.ም. የተላለፈውና የሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ቆጠራ ድንጋጌ የተሻሻለው ወይም ተሻሻለ የተባለው ግን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ነው፡፡ ጉዳዩና ዝርዝሩ በአጭሩ እንደሚከተለው ነው፡፡ ምርጫ በሚካሄድበት በ1997 ዓ.ም. በየአሥር ዓመቱ መካሄድ ያለበት የሕዝብ ቆጠራም አብሮ ይገጥማል፡፡ ይህም በመሆኑ ምርጫውንና ቆጠራውን አንድ ላይ ማካሄድ አይቻልም ይባላል፡፡ ምርጫውን ማራዘም አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቆጠራው እስከ 1999 ዓ.ም. እንዲዘገይ ይፈለጋል፡፡ ይህ ፍላጎት የመንግሥት አቋምና ከዚያም በላይ የሕግ ረቂቅ ሐሳብ ሆኖ ለምክር ቤት ይቀርባል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ፓርላማ በ1992 ዓ.ም. የተመረጠው ሁለተኛው ፓርላማ ሲሆን፣ ይህም ፓርላማ ጉዳዩ ሲቀርብለት (በ1995) ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ላይ ነበር፡፡ ከሰኔ 30 ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ ዋዜማ ድረስ እረፍት ላይ መሆን የነበረበት ይህ ፓርላማ፣ በ1995 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜን 6 ቀን ድረስ ዕረፍት አልወጣም፡፡ ዕረፍት የወጣው የጳጉሜን 6ቱን ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ነው፡፡

የዕለቱ የፓርላማ ውሎ ካስተናገዳቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ ስለዚህ ጉዳይ ነበር፡፡ ‹‹በ1997 ዓ.ም. የሚካሄደው የቤትና ሕዝብ ቆጠራ ወደ 1999 ዓ.ም. የሚተላለፍበትንና ቤትና ሕዝብ ቆጠራን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) የተቀመጠው ድንጋጌ የሚሻሻልበትን አስመልክቶ [የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ] ያቀረባቸውን ሪፖርቶችና የውሳኔ ሐሳቦች መርምሮ ማፅደቅ›› የሚል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርላማው ተወያየ፡፡ የኮሚቴውንም ውሳኔ ሐሳብ ሰማ፡፡ የኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቦች ሁለት ናቸው፡፡ በአንደኛው የውሳኔ ሐሳብ የሕዝብ ቆጠራውንና አገር አቀፍ ምርጫውን አንድ ላይ ማካሄድ ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ፣ ምርጫውን ማራዘም ስለማይቻል ቆጠራው እስከ 1999 ዓ.ም. እንዲዘገይ ጠየቀ፡፡

በሁለተኛው የውሳኔ ሐሳብ ሕገ መንግሥቱ ‹‹የሕዝብ ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል›› በማለት ያስቀመጠው ድንጋጌ ወደፊት ለሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል በሚቻልበት መንገድ መቅረፅ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጽና ከ1999 ዓ.ም. በኋላ የሚካሄደው የሕዝብ ቆጠራ ወደፊት በሚደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲወሰን፣ ፓርላማው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ አቋም እንዲይዝ የውሳኔ ሐሳብ አቀረበ፡፡

በውይይት ወቅት የሕዝብ ቆጠራውን ወደ 1999 ዓ.ም. ለማራዘምም ቢሆን ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ያስፈልጋል የሚል ሐሳብና ተቃውሞ ቢቀርብም፣ በውሳኔ ሐሳቦች ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት ተደርጎ ምርጫው በ1997 ዓ.ም.፣ ቆጠራው ደግሞ በ1999 ዓ.ም. እንዲካሄድ በአምስት ተቃውሞና በሦስት ድምፀ ተአቅቦ ተወሰነ፡፡

በ1996 ዓ.ም. ክልሎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተለያዩ ጊዜያት በጻፉት ደብዳቤ መሠረት፣

  1. የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለየክልሎች በጻፈው የጥቅምት 1996 ዓ.ም. ደብዳቤ የሕዝብ ቆጠራው ወደ 1999 ዓ.ም. እንዲሸጋገር፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) እንዲሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ገልጾ፣ በሁለቱ የፌዴራል ምክር ቤቶች የተወሰደውን ዕርምጃ አስታውቆ፣ ክልሎች በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ድምፅ እንዲሰጡበት ይጠይቃቸዋል፡፡
  2. ክልሎችም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከየካቲት እስከ ሐምሌ ድረስ ባሉት የተለያዩ ጊዜያት ውስጥ በጻፉት ደብዳቤ የሕገ መንግሥቱን መሻሻል መደገፋቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሕዝብ ቆጠራው ወደ 1999 ዓ.ም. የተራዘመው ሕገ መንግሥቱም የተሻሻለው ወይም ተሻሻለ የተባለው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ ለሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት እንክብካቤ፣ ጥበቃና መታዘዝ ሲባል መጀመሪያ ነገር ሊተላለፍ የማይችል አገር አቀፍ ምርጫ ስላለ፣ እሱን በየአሥር ዓመቱ መካሄድ ካለበት የሕዝብ ቆጠራ ጋር በአንድ የበጀት ዓመት ማካሄድ አልቻልኩም፣ የበጀት ችግር አለብኝ ብሎ ይህን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ምክንያት አድርጎ ማቅረብ በገዛ ራሱ ምክንያት ኃላፊነትን መዘንጋት አይደለም ወይ?

ሕገ መንግሥቱ የተሠራው ለክፉም ለበጎም ጊዜ ነው፡፡ በምርጫ ወቅት ለሕዝብ ቆጠራ ጊዜ ብሎ የለየው ጊዜ የለም፡፡ ምርጫና ቆጠራ አንድ የበጀት ዓመት ውስጥ ዋሉብኝ ብሎ ሕገ መንግሥት ይሻሻል ማለት ሳያንስ፣ ሕገ መንግሥቱ ሳይሻሻል የሕዝብ ቆጠራው ለ1999 ዓ.ም. ዞሯል ማለትን ተወካዮች ምክር ቤት ማነኝ ብሎ መወሰን ቻለ?

ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ ወደፊት ለሚደረግ የሕዝብ ቆጠራ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም፣ ቆጠራው በመንግሥት ውሳኔ ይቅር ወይም ይራዘም የሚባልበትን ሥልጣን ከሕገ መንግሥት አውጥቶ ለአስፈጻሚው አካል ውሳኔ መስጠት እስኪያስፈልግና እስኪቻል ድረስ፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ከሕግ በላይ መሆን አልመጣም?

ያም ሁሉ ሆኖ ዛሬም በሕገ መንግሥቱ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ ማየት አልቻልንም፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? ሕገ መንግሥቱን ያሻሻለ ዕርምጃ አልወሰድንም? ወይስ ሕገ መንግሥቱን ያሻሻልንበት አካሄድ ራሱ ለወሬ የማይመች አስፈሪ ሆኖብን ነው?

 ሊመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው ዋናው ባለጉዳይና መልስ ሰጪ ሌላ ቢሆንም፣ በተለይ ማዕከላዊ ጠቅላይ ስታትስቲክስና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን በምን ሕግ መሠረት እየተረማመዱ እንደሆነ ሊነግሩን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡