Skip to main content
x
ኢትዮጵያና ግብፅ በዳግም ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት

ኢትዮጵያና ግብፅ በዳግም ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ግንኙነት በማንኛውም መሥፈርት እጅግ የተወሳሰበ ነው፡፡ ለዘመናት በእርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭትና ፖለቲካ ፍትጊያ ውስጥ አልፈዋል፡፡ አልፎ አልፎም ሁለት ሆነው በማበር አንዱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ያሴሩበት አጋጣሚም ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥምረቶች በተለያዩ ዓውዶች ውስጥ ሲለዋወጡም ተስተውሏል፡፡ ይሁንና የግብፅና የሱዳን ጥምረት ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ላይ በርካታ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡ ከዚህ እውነት በተቃራኒ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሱዳን ቀስ በቀስ ከግብፅ እየራቀችና ወደ ኢትዮጵያ እየቀረበች በመምጣቷ፣ አንዳንዶች አዲስ ጥምረት በቅርቡ ሊታይ እንደሚችል መገመት ጀምረዋል፡፡

በናይል ጉዳይ ላይ የሚሠሩ የፖለቲካ ተንታኞች ይህ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያለባትን ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት በድል ለመወጣት የተለየ ታክቲክ እንድትጠቀም እንዳስገደዳት ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ከተፋሰሱ አገሮች መካከል አዲስ አጋር ለማግኘት በመኳተን ላይ ትገኛለች፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንትም ወደ እነዚህ አገሮች ሲመላለሱ ማየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡  

ይኼው አዝማሚያ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በቅርቡ ወደ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ባደረጉት ጉብኝት ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ጉብኝቱ ከተደረገበት ጊዜና ቦታ አንፃር ይህን ጉብኝት የተለመደ ነው ብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን የናይል ቤዚን ሁሉን አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ (ሲኤፍኤ) ያፀደቁ ብቸኛ አገሮች ናቸው፡፡ ጉብኝቱ የተደረገበት ጊዜም ቢሆን የግብፅን ሥሌት ያሳያል፡፡ ከሁለት ወራት በፊት በካምፓላ ኡጋንዳ በዩዌሪ ሙሴቬኒ ግብዣ የተፋሰሱ አገሮች መሪዎች በተገናኙበት ወቅት፣ ግብፅ በቅድመ ሁኔታ ታጅባ ወደ ናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ (ኤንቢአይ) ለመመለስ ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡ ቅድመ ሁኔታዋ በሲኤፍኤው አንቀጽ 14 (ቢ) ላይ እንዲካተት ከምትፈልገው የውኃ ደኅንነት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ አዲስ ሲኤፍኤ እንዲረቀቅ ሐሳብ ያቀረበችው ግብፅ በናይል ውኃ ላይ የአንበሳውን ድርሻ የሚሰጣት በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረመው ስምምነት የዚሁ አካል እንዲሆን ጠይቃለች፡፡ አብዛኞቹ አገሮች ግብፅ ኤንቢአይን በድጋሚ ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየቷን ያበረታቱ ቢሆንም ቅድመ ሁኔታዋን አልተቀበሉትም፡፡

ከተፋሰሱ አገሮች በተለይ ኢትዮጵያ የግብፅን ቅድመ ሁኔታ አምርራ ተቃውማለች፡፡ ኢትዮጵያ ሲኤፍኤው ላይ ክርክርና ድርድር ተደርጎ ካበቃ በኋላ ስምምነቱ ለማፅደቅ ክፍት ተደርጎ ሦስት አገሮች በፓርላማቸው አፅድቀውት እያለ፣ በድጋሚ ለድርድር ክፍት የሚሆንበት ምክንያት እንደሌለ አስረድታለች፡፡ ግብፅ በድጋሚ የኤንቢአይ አባል ለመሆን የምታቀርበው ሐሳብ ላይ በቅርቡ የሚካሄደው የናይል ቤዚን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በዝርዝር ለመነጋገር  ቀጠሮ መያዙን ከኤንቢአይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የአልሲሲ ጉብኝትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ለተሳታፊዎቹ ቅድመ ገለጻ በማድረግ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የአልሲሲ ጉብኝት ቻድና ጋቦንን ጨምሮ አራት የአፍሪካ አገሮችን ያካለለ ሲሆን፣ በሩዋንዳና በታንዛኒያ በነበራቸው ቆይታ ወቅት አዲሱን የግብፅ ሐሳብ በማብራራት ለማሳመን መጣራቸው ሚስጥር አልነበረም፡፡ እንደተለመደው እ.ኤ.አ. በ1959 ከሱዳን ጋር የፈረሙትን ስምምነት በመጥቀስ ከናይል ውኃ ዓመታዊ ድርሻቸው 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ላይ መቀነስ የሚታሰብ እንዳልሆነ አሳስበዋል፡፡ አልሲሲ የግብፅን ሥጋት “የሕይወትና የሞት ጉዳይ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የግብፅን ሥጋትና ፍላጎት እንደሚገነዘቡ ቢናገሩም፣ ከሲኤፍኤው ወደ ኋላ የማለት አዝማሚያ አላሳዩም፡፡ ሁለቱም መሪዎች ለናይል ውኃ ችግሮች ሁሉም አባል አገሮችን ያቀፈ መፍትሔ መስጠት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሱዳን በማቅናት ለሦስት ቀናት ይፋዊ  ጉብኝት ያደረጉት፣ በተመሳሳይ ሳምንት መሆኑ የአጋጣሚ ጉዳይ አይመስልም፡፡ እርግጥ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅ በተቃራኒ ይህ ጉብኝት የፖለቲካ ግብ እንደሌለው ገልጿል፡፡ በተለይ ከናይል ውኃ ጋር የተያያዘ ልዩ የውይይት አጀንዳ እንዳልነበረ አስታውቋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረጋቸውም ተመልክቷል፡፡ ይሁንና በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ጉብኝት ከናይል ውኃ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ሁለቱ አገሮች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዳደረጉ የተገለጸ ቢሆንም፣ ኤንቢአይና ዋነኛ ዓላማው የሆነውን ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍልን ዕውን ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆኑ መናገራቸው የመገናኛ ብዙኃኑን ትኩረት ስቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በሰላምና ደኅንነት፣ በኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ በድንበር ጉዳዮችና በመሳሰሉት ላይ መነጋገራቸውም ተገልጿል::

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉብኝት ዓላማ እንደ ፕሬዚዳንት አልሲሲ በግልጽ ከናይል ውኃ ዲፕሎማሲ ጋር የተገናኘ ነው ለማለት አዳጋች ቢሆንም፣ ኢትዮጵያና ግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ ዳግም ስለመግባታቸው ግን ከበቂ በላይ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ውጥረት አንፃር የሲኤፍኤው ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ብሎ መጠየቅም ምክንያታዊ ነው፡፡

ሲኤፍኤው አደጋ ውስጥ ነውን?

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሲኤፍኤውን የአገሪቱና የመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ማሳያ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ የስምምነቱ ዋነኛ ዓላማም በተፋሰሱ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍልና ተጠቃሚነትን ማስፈን ነው፡፡ ስምምነቱን እስካሁን ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያና ቡሩንዲ የፈረሙ ቢሆንም ያፀደቁት ግን ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ብቻ ናቸው፡፡ ስምምነቱ አስገዳጅ ለመሆንና ወደ ሥራ ለመግባት በስድስት አገሮች መፅደቅ አለበት፡፡

ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ. የ1959 ስምምነታቸውን የሚንድ በመሆኑ ሲኤፍኤውን ይቃወማሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን በተለይም ስምምነቱን ፈርመው እስካሁን ያላፀደቁትን ኡጋንዳን፣ ኬንያንና ቡሩንዲን በማሳመን እንዲያፀድቁት በማድረግ ሲኤፍኤውን ወደ ሥራ ለማስገባት እየጣረች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በሲኤፍኤው ያላቸው ልዩነት እንዳለ ሆኖ በ2003 ዓ.ም. የታላቁ ህዳሴ ግድብ ይፋ ከሆነ በኋላ በግንኙነታቸው ላይ ውጥረት ነግሶ ነበር፡፡ ግድቡ በሁለቱ አገሮች ላይ መሠረታዊ ጉዳት ያስከትላል? አያስከትልም? የሚለው ጉዳይ አዲስ የውዝግብ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ በተለይ ግብፅ የግድቡ ግንባታ በፍጥነት ካልተገታ የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ ሁሉ አስጠንቅቃ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ መሠረታዊ ጉዳት እንደማያስከትል እየተገነባ መሆኑን በመግለጽ የተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለማካሄድ ፈቃደኝነቷን አሳየች፡፡ ይህን ለማከናወን የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል በ2004 ዓ.ም. መቋቋሙም ይታወሳል፡፡ በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ጥናቱ ይፋ ሲሆን ተጨማሪ ጥናቶች እንዲደረጉ ነው ምክረ ሐሳብ የቀረበው፡፡ እነዚህን ተጨማሪ ጥናቶች ለማድረግ ሦስቱ አገሮች እስካሁን በርካታ ውጣ ውረዶችን ቢያዩም አልተጠናቀቀም፡፡ ሒደቱ ከግድቡ ግንባታ ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም በሌሎቹ አገሮች ዘንድ መተማመን እንዲፈጠር ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ኢትዮጵያ ትገልጻለች፡፡ ግብፅ አሁንም ግድቡ መሠረታዊ ጉዳት ያስከትልብኛል የሚል አቋም ያላት ሲሆን፣ ሱዳን ግን ግድቡ ከጉዳት ይልቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጣት በሒደት ተቀብላለች፡፡

በዚህ መሀል በ2007 ዓ.ም. ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ላይ የመርህ መግለጫ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ ከዓለም አቀፍ የውኃ ሕግና ከሲኤፍኤው የተወሰኑ ድንጋጌዎችንና መርሆዎችን ይዟል፡፡

የመርህ መግለጫ ስምምነቱ ይፋ ከሆነ በኋላ በሁሉም አገሮች ማለት ይቻላል ውዝግብ አስነስቷል፡፡ አንዳንዶች እንደ ትልቅ ስኬት ሲቆጥሩት፣ ሌሎች ግን በናይል ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ መሰናክል እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

ሱዳናዊው የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርት ዶ/ር ሳልማን መሐመድ በዚህ ስምምነት ግብፅና ሱዳን ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች በናይል ውኃ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላቸው በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ዕውቅና ከመስጠታቸው አንፃር፣ እንደ ትልቅ ዕርምጃ እንደሚወስዱት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ “በእኔ እምነት የ1902፣ 1929 እና 1959 ስምምነቶችን የሻረ ነው፤” ብለዋል፡፡ ሌሎች ኤክስፐርቶች ግን ሰነዱን እንደ ሕግ ሰነድነት እንኳን ለመውሰድ ይቸገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት የዓለም አቀፍ ሕግ ኤክስፐርቱ ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ ከዚህ በተቃራኒ የመርህ መግለጫ ስምምነቱ ለዘመናት ከቆየው የኢትዮጵያ የውኃ ፖሊሲ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ይከራከራሉ፡፡ “ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ የሚያመጣ ነው፡፡ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች እንዲጠራጠሯት ያደርጋል፡፡ ዋነኛዋ የአጀንዳው ባለቤት ሲኤፍኤውን ከሚቃወሙ አካላት ጋር በአንድ ፕሮጀክት ላይ የጎንዮሽ ስምምነት የምታደርግ ከሆነ፣ ሌሎች አገሮች ስለቀጣይ ዕርምጃቸው እንዲጠነቀቁ ያደርጋቸዋል፡፡ በሲኤፍኤው ኢትዮጵያ ሌሎች አገሮችን ስታግባባ የነበረው የውኃ ጉዳይን ሁሉ ተቋማዊ አሠራር በመዘርጋት ሕግና መርህ ላይ ተመርኩዞ እንዲፈታ የማድረግን አስፈላጊነት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ይህን ስምምነት መፈረሟ ኃላፊነት የጎደለው ዕርምጃ ነው፡፡ ሎሎቹ አገሮች ከግብፅ ጥቅም ለማግኘት ብለው ሲኤፍኤውን ቢተውት አይገርመኝም፤” ብለዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ የመርህ መግለጫ ስምምነቱን መሰል ስምምነት በተናጠል ከሌሎች አገሮች ጋር የመፈጸም ዕድል ካገኘች ግብፅ ሲኤፍኤው ተረስቶ እንዲቀር ልታደርግ እንደምትችል ይጠራጠራሉ፡፡ ‹‹በናይል ውኃ ጉዳይ ላይ ያላትን ፍፁም የበላይነት ለመጠበቅ እንድትችል ተቋማዊና ሕጋዊ አሠራር እንዳይኖር ትሠራለች፡፡ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ አገር የሚፈልገውን አንገብጋቢ ጉዳይ መስጠት አንዱ ታክቲክ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣናቸው አስተማማኝ መሠረት የሌላቸው መንግሥታት በገንዘብ ሊገዙም ይችላሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ያላቸው የበላይነት መሠረታዊ ለውጥ እንዳያሳይ ጠንክረው ይሠራሉ፡፡ በዚህም እየተሳካላቸው ነው ብየ አምናለሁ፤” ብለዋል፡፡

የሱዳን ቁልፍ አጋርነት

የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት ካላቸው የኋላ ታሪክ አኳያ በከፍተኛ ውጥረት የተሞላ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት አሁን የያዘውን የወደጅነትና የትብብር ቅርፅ ከመያዙ በፊት ያሉት ጊዜያት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በጥርጣሬ፣ ይበልጡን ደግሞ በጠላትነት እየተፈራረጁ ነው ያሳለፉት፡፡

የኋላውን አንድ ክፍለ ዘመን ትተን አሁን ሥልጣን ከያዘው ኢሕአዴግ ወይም ከመሥራቹ ሕወሓት ጋር ያለው ግንኙነት ቢታይ፣ የወዳጅነትና የጠላትነት ጊዜያት መፈራረቃቸውን እናስተውላለን::

የሱዳን መንግሥት ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ለሱዳን ተቃዋሚዎች ድጋፍ በመስጠት አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጉዳት ለማድረስ ሥራ የጀመሩት ከሱዳን ነፃ መውጣት ጀምሮ ነው፡፡ በተጨማሪም በ1980ዎቹ በእስልምና ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተው የሱዳን መንግሥት የሃይማኖት ጽንፈኝነትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት እንደሚሠራ ኢትዮጵያ ትተች ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ራሷን ከሽብር ጥቃት ለመታደግ፣ በዓባይ ወዝን አጠቃቀም ዙርያ ሱዳን ያላት አቋም፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ሱዳን ያላት ግንኙነት፣ ሱዳን በምሥራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ ያለው የልማትና የደኅንነት እንቅስቃሴ ላይ ያላት ተፅዕኖ፣ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል እንደገፋፏት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይተነትናል፡፡

በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካ ሳይንስ የፒኤችዲ ዕጩ ተማሪው አቶ ጎይቶም ገብረልዑል “Revamping Ethiopia’s Foreign Policy Strategy” በሚል ርዕስ በቅርቡ ዲስኮርስ መጽሔት ላይ ባወጡት ጽሑፍ፣ ስተራቴጂው ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገሮች ጋር በተለይ ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታሻሽል ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ገልጸዋል፡፡ የሱዳንን ስኬት ልዩ የሚያደርገው የሁለቱ አገሮች የኋላ ታሪክ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ከዚህ የታሪክ ሸክም ወጥተው ንግድ፣ ትምህርትና ዲፕሎማሲን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መልካም ግንኙነት ማድረግ መቻላቸው የሚደነቅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከሁሉም በላይ የዚህ መልካም ግንኙነት መገለጫ እ.ኤ.አ. በ2013 ሱዳን ለህዳሴ ግድቡ ዕውቅና መስጠቷ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ይሁንና ሱዳን ሲኤፍኤው ላይ ያላት አቋም አሁንም አልተቀየረም፡፡ የፖሊሲ ስትራቴጂው ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ሁለቱ አገሮች በፍትሐዊ የውኃ አመቃቀም ላይ መስማማታቸው ቅድመ ሁኔታ እንደማይሆን ይገልጻል፡፡ ለግንኙነቱ ዘላቂነት በዚህ ጉዳይ መስማማታቸው ስለሚጠቅም ይህ እንዲቀየር ኢትዮጵያ እንደምትጥርም ተመልክቷል፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት ሁለቱ አገሮች ጥሩ ግንኙነት ቢፈጥሩም የሱዳን አቋም ባለመለወጡ፣ በርካቶች መቼ እንደሚለወጥ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

ይህ መሠረታዊ ልዩነት ይኑር እንጂ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በበርካታ ዘርፎች ላይ እመርታ እያሳየ ነው፡፡ በዚህም ሁለቱ አገሮች እርስ በርስ እየተሰጣጡ ካለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ዕርዳታና ድጋፍ አንፃር ሱዳን በቅርቡ ሲኤፍኤውን ፈርማ ከኢትዮጵያ ጎን ልትሠለፍ ትችላለች በሚል ተስፋ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ሆኖም ሱዳን ይህን መሠረታዊ የአቋም ለውጥ ብታደርግ የሚመጣባትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መቋቋም ስለመቻሏ የሚጠራጠሩ አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጥያቄዎች ለኢትዮጵያም ይሠራሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት እንደ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ያሉ አገሮችን ቅር ሊያሰኝ ይችላል፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ አደጋ ለሱዳን ስትል በመጋፈጥ የምታገኘው ትርፍ ምን እንደሆነ በድጋሚ እንድታጤን የሚጠይቁት በርካቶች ናቸው፡፡ ለግብፅ የልብ ልብ የሰጠውን ሲኤፍኤው ላይ በድጋሚ እንደራደር አጀንዳ ያመጡት የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ናቸው፡፡ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት የደቡብ ሱዳን ደጋፊ የነበሩት ሙሴቬኒ ከሱዳን ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት የላቸውም፡፡

ዶ/ር ደረጀ ሲኤፍኤው ላይ ከግብፅ ጋር አንድ አቋም ያላት ሱዳን የአቋም ለውጥ ማምጣቷ የዲፕሎማሲ ስኬት ሆኖ መቅረቡ እንደማይዋጥላቸው ገልጸዋል፡፡ “ከግብፅ እየሸሸች ወደ ኢትዮጵያ እየቀረበች ነው ከተባለ ሲኤፍኤውን ከመፈረም ምን ያዛት?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡