Skip to main content
x
ጉሬዛ

ጉሬዛ

ጉሬዛ ዛፍ ላይ የሚኖር እንስሳ ነው፡፡ በግንባሩ፣ በጉንጮቹና በአገጩ ላይ ነጭ ፀጉር አለው፡፡ በጅራቱ ጫፍና በጎንና በጎኑ ነጭ አለው፡፡ በተረፈ ፀጉሩ ጥቁር ነው፡፡ አዲስ የተወለዱት፣ እንደ ትልልቆቹ ፊታቸው ጥቁር ሳይሆን ቀይ ነው፡፡ ፀጉራቸውም በመላ ነጭ ነው፡፡

ዶ/ር ሰሎሞን ይርጋ በአጥቢዎች መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ሴቷ በአማካይ 9.2 ኪ.ግ ስትመዝን፣ ወንዱ ደግሞ 13.5 ኪ.ግ ይመዝናል፡፡ ዋነኛ ምግባቸው ቅጠላ ቅጠሎችና ፍራፍሬዎች ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚበሉት ግን ቅጠል ነው፡፡ አንዳንዴ ያልበሰሉ ፍሬዎችና እንቡጦች ሲያገኙም አይተዉም፡፡ 

በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙና በአብዛኛው ቦታዎች እንደጻድቃን ይቆጠራሉ፡፡ ምክንያቱም ዛፍ ላይ ቅጠላቸውን እየበሉ ነው የሚኖሩት፡፡ እናም፣ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ የተከዙ መስለው ብዙ ሳይንቀሳቀሱ ስለሚታዩና፣ የባሕታዊን የመሰለ እይታ ስላላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ኢሉባቡር ውስጥ ሰብል ከሚያጠፉ የጦጣ ዘሮች ውስጥ ጉሬዛዎችም የሚጠቃለሉ ሆነዋልና እዚያ ጻድቃን የሚላቸው የለም፡፡

ጉሬዛዎች ብዙም ሳይንቀሳቀሱ የሚበቃቸውን ያህል ቅጠላቸውን ስለሚበሉ፣ የቡድናቸው አባላት ተሰባስበው ይኖራሉ፡፡ በመኻከላቸው እጅግም ፀብ የለም፡፡ በተቃራኒው፣ ብዙ ጊዜ እርስ በርስ ስለሚቀማመሉ፣ ያለው ወዳጅነት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ጉሬዛዎች ካላቸው የርስ በርስ መግባቢያ መንገድ አንዱ ድምፅ ነው፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚውሉ 5 ዓይነት ድምጾች አላቸው፡፡ በብዛት በሚገኙባቸው ሥፍራዎች እንደሚታወቀው በጠዋት የሚያሰሙት ከፍተኛ ድምፅ በማኅበር ከመሆኑ ጋር ተደምሮ እንግዳ ሰሜት ይፈጥራል፡፡ አልፎ ፈልፎ ዋነኞቹ ወንዶች ከጎረቤት ወንዶች ጋር ግጭቶች ያደርጋሉ፡፡

የተለየ የመውለጃ ወቅት የላቸውም፡፡ ሆኖም ግን ብዙዎቹ በክረምት ወራት ይወልዳሉ፡፡ የእርግዝናቸው ርዝመት 6 ወር ሲሆን፣ አንዲት ሴት በየ20 ወራት (በአማካይ) ትወልዳለች፡፡ ለአካለ መጠን ለመድረስ ከ4 እስከ 6 ዓመቶች ይፈጅባቸዋል፡፡