Skip to main content
x

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው

ይኸው እሳት ላይ አስቀምጣችሁን ሄዳችሁ፡፡ እኛም እኮ ነግረናችሁ ነበር፡፡ ምኑን? አገር መምራት እንዲህ ቀላል እንዳልሆነ፡፡ እናንተ ያጠፋችሁትን እያረምን እኮ ነው የተቸገርነው፡፡ እንዴት ነው ማረም ታዲያ? የጊዜ ጉዳይ እንጂ መጠየቃችሁ አይቀርም፡፡ አለቃችሁን ግን ይኼ ሁሉ የቤት ሥራ ትተው ውጭ መሽከርከራቸው ምንድነው? የእናንተን ስህተት ለማረም ነዋ፡፡ ቢሆንም ሁሉ ነገር ከውስጥ መጀመር ይሻላል፡፡ እንዴት? ተለውጠናል እያላችሁ አይደል እንዴ? ግጥም አድርገን ነዋ የተለወጥነው፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ ከማየት ወደ ውስጥ መመልከቱ ይበጃል፡፡ አሁን እናንተም ለምክር በቃችሁ? ለማንኛውም ሰሞኑን አለቃችሁ የውጭ ጉዞ ስላበዙ ሥልጠናቸው ተቀየረ ወይ ለማለት ነው? ወደ ምንድነው የሚቀየረው? ሳናውቅ ሾማችኋቸው እንዴ? ምን አድርገን? በጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ . . . እ. . . የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር!

ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ደወሉ

ሰው ሁሉ ችግር ነው የሚያወራው፡፡ ለነገሩ እንቅስቃሴ ሁሉ ተዳክሟል፡፡ ኧረ አንተ እንኳን አበረታታኝ፡፡ ምን ተሻለ ታዲያ? እንድታግዘኝ ነው የደወልኩት፡፡ ምን ላግዝዎት? ትኬቱን ሽጥልኝ፡፡ እርስዎን ያልገዙዎት እኔን ማን ይገዛኛል ብለው ነው? አንተ እንደምትሸጠውማ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንዴት ክቡር ሚኒስትር? ይታሰብልሃል፡፡ ምን ክቡር ሚኒስትር? ኮሚሽን፡፡ ስንት ፐርሰንት 10 ፐርሰንት!

ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሥልጣን ስልክ ይደውሉላቸዋል

ክቡር ሚኒስትር የእኛ አገር ዘረኝነት እኮ ከሕዝቡም በላይ ሄዶ መሬቱም ዘረኛ ሆኗል፡፡ አልገባኝም? ማለቴ የአማራ መሬት፣ የኦሮሞ መሬት፣ የትግሬ መሬት ምናምን እያልን ከፋፍለነዋል፡፡ ምን እያልከኝ ነው? መሬቱ ራሱ የሚናገረው ቋንቋ አለው፡፡ ሰው እንዴት ነገረኛ ሆኗል ልበል? ፌዴራሊዝሙ በቋንቋ ስለሆነ መሬቱም ቋንቋውን ለምዶታል፡፡ በፌዴራሊዝሙ ቀልድ የለም፡፡ ኧረ እኔ አልቀለድኩም ክቡር ሚኒስትር፡፡ ፌዴራሊዝሙ ለድርድር የሚቀርብ ነገር አይደለም፡፡ ለማንኛውም ሕዝቡ በመንግሥት ሹመት ትችት እያቀረበ ነው፡፡ የምን ትችት? ሹመት በብሔር ተዋጽኦ መሆን የለበትም እያለ ነው፡፡ ታዲያ በምን ተዋጽኦ ይሁን፡፡ በብቃት ተዋጽኦ!

ክቡር ሚኒስትሩ ልጆቻቸው በመኝታ ቤት ሲጨቃጨቁ ከእንቅልፋቸው ነቁ

ሳሎን ቤቱ ላይ እሷ የይገባኛል ጥያቄ አንስታ ነው፡፡ የምን የይገባኛል ጥያቄ ነው? በፊት በፊት የማድርበት እኔ ስለነበርኩ ሳሎኑ የእኔ ነው አለችኝ፡፡ እ . . . ምን እሱ ብቻ የሳሎን ቤቶቹን አትክልቶቹ የምንከባከባቸውና የተከልኳቸው እኔ ስለሆንኩ ሳሎኑ የእኔ ነው አለችኝ፡፡ አንተስ ምን አልካት? እኔማ እንዲያውም ካልሽ ሳሎን ውስጥ ያሉ አብዛኛዎቹ መጻሕፍት የእኔ ስለሆኑ ሳሎኑ የእኔ ነው አልኳት፡፡ እ . . ዳዲ ፕሌይ ስቴሽን እየተጫወትኩ አብዛኛውን ጊዜ የማጠፋው እኮ ሳሎን ቤት ነው፡፡ እኔ የምለው ሁለታችሁም የራሳችሁ መኝታ ቤት አላችሁ አይደል እንዴ? አዎን ዳዲ፡፡ ታዲያ በሳሎን ቤት ምን አጣላችሁ? እሷ ሳሎኑ የእኔ ነው ውጣልኝ ስትለኝ ነዋ፡፡ ለማንኛውም ሳሎኑ የሁለታችሁም አይደለም፡፡ ታዲያ የማን ነው? የሁላችንም!

የቀድሞው ሚኒስትር ወደ ማረሚያ ቤት ይደውላሉ

ሆቴሉ የሚሰጠን አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰብን ነው፡፡ ምን ሆነ? ይኸው እንደበፊቱ የፈለግነውን ምግብ አዘን መብላት አልቻልንም፡፡ እንዴ ለምን? የእስካሁኑን ሒሳብ አልከፈልንማ፡፡ ያሳዝናል፡፡ አንሶላችን እንኳን ከታጠበ ቆይቷል፡፡ ለምን ለሆቴሉ አይናገሩም ታዲያ? ሒሳብ ክፈሉ እያለን ነዋ፡፡ ምን ተሻለ ታዲያ? እኔማ እናንተ እንድትረዱን አስቤ ነበር፡፡ በምን እንርዳዎት? ስማችንን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ጥያቄያችንንም መልሱ፡፡ የትኛውን ጥያቄ? የሆቴል ወጪያችንን ክፈሉልን፡፡ ከየት አምጥተን? ለምን ከበጀቱ ተቀናሽ አድርጋችሁ አትከፍሉልንም? ከየትኛው በጀት? ከታራሚዎች!

የክቡር ሚኒስትሩ ልጆች ግቢው ውስጥ ሲጨቃጨቁ ክብር ሚኒስትሩ ወጡ

- የአያታችን ሐውልት ሊቆም አይገባም ባይ ነኝ፡፡ - ለምን? - በእርግጥ እኔ አያቴን እወደዋለሁ፣ ግን እሱ ከወንድሙ ጋር በመጣላቱ ምክንያት ነው እስካሁን ቤተሰቡ የተከፋፈለው፡፡ - እ. . . - እንዲያውም አንተ ነህ እኮ አስታርቀሃቸው ሰላም መውረድ የቻለው፡፡ - እሱስ ልክ ነሽ፡፡ - ስለዚህ የእሱ ሐውልት እዚህ ሊቆም አይገባም፡፡ - የማን ሐውልት ይቁም እያልሽ ነው ታዲያ? - የቅድመ አያታችን ነዋ ዳዲ፡፡ - አንቺ የት ታውቂዋለሽ እሱን? - እንዴ ዳዲ ይኼ ቤተሰብ እንዲሰባሰብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ የነበረው እሱ አይደል? - በምን አወቅሽ? - ዳዲ ትልቁን የቤተሰባችንን ማኅበር የመሠረተው እሱ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ - ይኼን ማን ነገረሽ? - ሁሌ ማኅበራችን ላይ ሲወራ እሰማለሁ፡፡ - እሱስ ልክ ነሽ፡፡ - እንዲያውም አያታችን በቅድመ አያታችን ይቀና እንደነበር አውቃለሁ፡፡ - ወይ የዛሬ ልጆች? - እውነቴን አይደል ዳዲ? - አሁን ምን እያላችሁ ነው? - እኔ የአያታችን ሐውልት ይቁም እያልኩ ነው፡፡ - አንቺስ? - እኔማ የቅድመ አያታችን ሐውልት ነው መቆም ያለበት የምለው፡፡ - ለማንኛውም እዚህ መቆም ያለበት ሐውልት የማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? - የማን ነው? - የእኔ!

ክቡር ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

- አገሪቱ ውስጥ ያለውን ሪፎርም መቼም እየተከታተልሽው ነው? - ምነው? - ይኼን ሪፎርም እኛም ቤት ውስጥ አስገብተነው ሪኖቬሽን ማከናወን አለብን፡፡ - ምንድነው የምታወራው? - ቤታችንን ማደስ አለብን፡፡ - በጣም ቅርብ ጊዜ ነው እኮ ያስመረቅነው? - አዎን ግን እድሳት ማድረግ እንዳለብን ተሰምቶኛል፡፡ - ምን ዓይነት እድሳት? - ቤዝመንቱ መጋዘን መሆን የለበትም፡፡ - የተሠራው ለዚያ ነበር እኮ? - አዎ ቢሆንም ቤዝመንቱ ውስጥ መዋኛ ማሠራት አለብን፡፡ - እ… - ከዚያም ውጪ አሪፍ አሪፍ ክፍሎችን መገንባት አለብን፡፡ - ኧረ ሰውዬ ተው? - ከመንግሥት የተሰጠውን አቅጣጫ ተከትዬ እኮ ነው እድሳት ለማድረግ የፈለግኩት፡፡ - ምንድነው የምታወራው? - የእኔ ስም ከብዙ ወንጀል ጋር እንደሚነሳ ታውቂያለሽ አይደል? - ታዲያ ለምን አርፈህ አትቀመጥም? - አየሽ መጨረሻዬ እስር ቤት ሊሆን ይችላል፡፡ - እና ምን ይጠበስ? - ስለዚህ እኔ መንግሥት እየቀለበ እንዲያስረኝ አልፈልግም፡፡ - ምን እያልክ ነው? - ወደፊት መታሰሬ የማይቀር ከሆነ ከአሁኑ ነው መገንባት ያለብኝ፡፡ - ምንድነው የምትገነባው? - የግል እስር ቤት!

ክቡር ሚኒስትሩ ለደላላ ወዳጃቸው ስልክ ይደውላሉ

- ለመሆኑ ሰሞኑን ሚዲያ እየተከታተልክ ነው? - ምን አዲስ ነገር አለ ክቡር ሚኒስትር? - በየቦታው እኮ ባንኮች እየተዘረፉ ነው፡፡ - እሱን ሰምቻለሁ፡፡ - ታዲያ ቶሎ ብለህ ሥራውን አትጀምርም እንዴ? - የቱን? - የእጥበቱን ነዋ፡፡ - እ. . . - በአዲስ መልክ ጀምረናል ብለህ ማስታወቂያ ማስነገር እኮ ነው፡፡ - በሚዲያ? - ኧረ በኔትወርክህ፡፡ - የምን እጥበት ነው ግን? - የገንዘብ!

የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች

የጥምቀት በዓል ሁሉን አቀፍ ነው፡፡ እንዴት? በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀውም፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተጠመቀውም፣ በሙስና የተጠመቀውም ሊያከብረው ይችላል፡፡ እየቀለዱ ነው ክቡር ሚኒስትር? የእውነቴን ነው የምልሽ፡፡ ለማንኛውም ላስፈቅድዎት ነበር፡፡ ምንድነው የምታስፈቅጂኝ? ታቦት ለመሸኘት ልሄድ ነበር? ችግር የለውም አብረን እንወጣለን፡፡ እርስዎም ይሸኛሉ እንዴ? አዎን፡፡ እኔ አላምንም ታቦት ሊሸኙ? ታቦት አይደለም የምሸኘው? ታዲያ ማንን ነው? ጓደኛዬን፡፡ ወዴት? ወደ ቂሊንጦ!