Skip to main content
x

ለፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣንን ለዜጎች ፍትሕን የነፈጉት የሰበር ውሳኔዎች

በውብሸት ሞላ

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13(1) መሠረት ሁሉም የፌዴራልና የክልል ሕግ አስፈጻሚ፣ ሕግ አውጪና የዳኝነት አካላት ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በተጠቀሰው ድንጋጌ የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የዜጎችን ሰብዓዊና መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡

ሆኖም የተጠቀሰው ድንጋጌ በሕገ መንግሥት በመካተቱ ብቻ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች ዋስትና አግኝተዋል ለማለት አይቻልም፡፡ የዜጎች መብቶች ተጥሰው ሲገኙ በገለልተኝነትና በነፃነት በማየት ለመብቶቹ ጥበቃ ለማድረግ ከሚያስፈልጉ ተቋማት መካከል አንዱና ዋነኛው ነፃ የዳኝነት አካል ነው፡፡

ነፃ የዳኝነት አካል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78 (1) ተቋቁሟል፡፡ ዳኞች፣ የዳኝነት ተግባራቸውን ከማንኛውም ባለሥልጣንም ሆነ ሌላ ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በሕግ ብቻ በመመራት መሥራት እንዳለባቸው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 79(3) ተመልክቷል፡፡ ይህ የዳኝነት ነፃነት በሕገ መንግሥቱ የተካተተው በራሱ ግብ ሆኖ ሳይሆን ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ ገለልተኛና ነፃ የዳኝነት አካል ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት ባለበት አገር የመንግሥት ሥልጣን በሕግ የተገደበ ይሆናል፡፡ ዜጎችም ሰብዓዊ መብቶቻቸው በዋነኛነት የሌሎችን መብት ለማክበርና በኅብረተሰቡ ውስጥ ሕግና ሥርዓትን ከማስፈን አንፃር ሊገደብ ይችላል፡፡ ነፃ የዳኝነት አካላት በመንግሥት ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥልጣንና በዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ መካከል ያለውን ሚዛን ነፃና ገለልተኛ ሆነው ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማለት ፍርድ ቤቶች በመንግሥት ባለሥልጣንና በተራው ዜጋ፣ እንዲሁም በዜጎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርጉ ሚዛናዊ ዳኝነት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡

ከሰብዓዊ መብት በተጨማሪም ከሌሎች ሕጎችና ሕጋዊ ውጤት ካላቸው ሁኔታዎች የሚመነጩ መብቶችንና ግዴታዎችን መነሻ በማድረግ ዳኝነት ሲጠየቅ አንድ ጤናማ የዳኝነት ሥርዓት የሚያከናውናቸውን የሚተገብር ፍርድ ቤት ሊኖር ይገባል፡፡ ነፃና ገለልተኛ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የመጨረሻ ግቡ ፍትሕን ማስፈን ነው፡፡ ፍትሕን ለማስፈን ደግሞ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የግድ ተፈላጊ ነው፡፡ እነዚህን ለማከናወን ደግሞ የዳኝነት ሥርዓቱ እንደ አንድ የመንግሥት አካል በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ግዴታ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

ሕገ መንግሥቱ 79(1) ላይ የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ከማንኛውም የመንግሥትም  ይሁን ከሌላ አካል ነፃ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ ስለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በሚናገረው አንቀጽም ላይ በፌዴራልም ይሁን በክልል ፍርድ ቤቶች ከሚሰጧቸው የመጨረሻ ውሳኔዎች  በተጨማሪ ማናቸውም የመጨረሻ ውሳኔዎች መሠረታዊ የሕግ ስህተት ከተፈጸመባቸው  የማስተካከል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ በአንቀጽ 37(1) ላይ ደግሞ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡

በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ስለ ፍርድ ቤቶች ሁኔታና አቋም በሚናገርባቸው አንቀጾች ላይ በግልጽ እንደተገለጸው የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤት ብቻ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቹ የክልልም የፌዴራልም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱ የተፈጠሩት ወይም የተዋቀሩት የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ተልእኮ የላቸውም፡፡ የተፈጠሩት ወይም የተቋቋሙት ለዳኝነት ከሆነ ሌሎች የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች በልዩ ሁኔታ ሊቋቋሙ ከመቻላቸው በስተቀር ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን አላቸው አያሰኝም፡፡ እነዚህ የአስተዳዳር ፍርድ ቤቶች በአዋጅ ወይንም በሌላ ሕግ ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ግን በሕገ መንግሥቱ ተፈጥረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው በሌላ ሕግ የተቋቋመ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው ተቋም እስከሌለ ድረስ ማንኛውም በፍርድ ሊያልቅ የሚችልን ጉዳይ ዳኝነት የሚጠይቁት ከፍርድ ቤት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ፍርድ ቤቶች በጉዳዮች ላይ ዳኝነት እንዳይሰጥ እስካልተከለከለ ድረስ የተፈጠረው ለዳኝነት ነውና የዳኝነት ሥልጣን አለው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከላይ ከተገለጸው በተቃራኒ ፍርድ ቤቶችን ከዳኝነት ተግባር እንዲቆጠቡ የወሰነባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የተወሰኑ የሰበር ውሳኔዎችን በአስረጅነት እንመልከት፡፡

የመጀመርያው ማሳያ ደግሞ በሰበር መዝገብ ቁጥር 23608 በኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪና የአቶ ኑርበዛ ተረጋ ወራሾች መካከል የተደረገው ክርክር ላይ የተሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የሆነ የዳኝነት ሥልጣን እንደሌላቸው ወስኗል፡፡ የተከራካሪዎቹን ጉዳይ የፌዴራል የመጀመርያ ፍርድ ቤት ፍርድ ሲሰጥ የሚከተለውን ምክንያት በማቅረብ ነው፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 79(1) ላይ የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ በአንቀጽ 37(1) ላይ ደግሞ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት የማቅረብና ውሳኔ የማግኘት መብት እንዳለው የተደነገገ ከመሆኑም በላይ በአስተዳደር አካላት የተሰጡ ውሳኔዎችን ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማየት ተፈጥሯዊ የሆነ ሥልጣን ያላቸው ስለሆነ በተከሳሽ በኩል የቀረበው መቃወሚያ በአግባቡ የቀረበ አይደለም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡

ጉዳዩ መጨረሻ ላይ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲደርስ ውሳኔውን ሲሽር ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የሆነ ሥልጣን እንደሌለው ገልጿል፡፡ ለውሳኔው የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርቧል፡፡ በቅድሚያ ያስቀመጠው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37(1) ላይ ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይንም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት እንዳለው መገለጹ ፍርድ ቤቶች አንድን አቤቱታ ተቀብሎ ውሳኔ መስጠት የሚችሉት ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ለሌላ አካል ያልተሰጠ ከሆነ ብቻ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን ይኖራቸዋል የሚል ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሌላ የዳኝነት ሥልጣን የተሰጠው የአስተዳዳር መሥሪያ ቤት በሚኖርበት ጊዜ ይኼው ተቋም የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻና አሳሪ ከሆነ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ሥልጣን አይኖራቸውም የሚል ይዘት አለው፡፡

በእነዚህ ብቻ ሳይገደብም የመጨረሻና አሳሪ ውሳኔን በፍርድ ቤት በድጋሜ ለማየት የሚስችል የሕግ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ ሳይኖር ፍርድ ቤቶች በአስተዳደር አካላት የተሰጡ ውሳኔዎችን መከለስ እንደማይችሉ ውሳኔው ያመለክታል፡፡ በመደምደሚያነትም፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ የዳኝነት ሥልጣን ከሕግ የመነጨ እንጂ ተፈጥሯዊ  ባለመሆኑ መጀመርያ ላይ በሕግ ሥልጣን መሰጠቱ መረጋገጥ እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በመጀመርያ በምሳሌነት የቀረበው የሰበር ውሳኔ ቅጽ ሦስት በእነ ወ/ሮ ጽጌ አጥናፌና ባላምባራስ ውቤ ሺበሺ በመዝገብ ቁጥር 14554 ላይ የሰጠውን ውሳኔ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ፣ ሥልጣን ባለው አካል የተሰጠን የባለቤትነት ማስረጃ ደብተርን ሐሰተኛ በሆነ መንገድ ነው የተገኘው በሚል የመሰረዝ ሥልጣን አለው? ወይስ የለውም? የሚል ጭብጥ በመያዝ የሰጠውን ውሳኔና ምክንያቱን እንመልከት፡፡

ጉዳዩ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ስለሻረውና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ስላፀደቀው ከላይ የተገለጸውና ሌላም ጭብጥ በማውጣት ለሰበር ያስቀርባል ተብሏል፡፡ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላይ የሥር ፍርድ ቤቱን በመሻር ውሳኔ ሲሰጥ በሥር ፍርድ ቤት አመልካች ከነበሩት ሰዎች አንደኛ የቤት ባለሀብትነት ማረጋገጫ ደብተር ያገኘው ሐሰተኛ በሆነ መንገድ ስለሆነ በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 1195 ላይ የተቀመጠው የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር የያዘ ሰው ባለቤት እንደሆነ ይቆጠራል የሚለው የህሊና ግምት ተስተባብሏል፡፡ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 1196 (ለ) መሠረትም እንደፈረሰ ወሰነ፡፡ በዚህ መሠረትም በአስተዳደር አካል የተሰጠ ደብተር ተሰረዘ፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት ግን አንቀጽ 1196 አንድ አስተዳደደር መሥሪያ ቤት የሰጠውን ደብተር የሚሰርዝበት ድንጋጌ እንጂ ፍርድ ቤቶች እንዲሰርዙ ሥልጣን የሰጠ ባለመሆኑ የሥር ፍርድ ቤት በሐሰተኛ መንገድ የተገኘ ነው በማለት የመሰረዝ ሥልጣን አልተሰጠውም በማለት ወሰኗል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለውሳኔው በማጠናከሪያነትም አንቀጽ 1198(2)ን ጠቅሷል፡፡

በዚህ መንገድ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የባለቤትነት ማረጋገጫ እስካልሰረዘ ድረስ በአንቀጽ 1195 (1) መሠረት በስሙ ተመዝግቦ የሚገኘው ሰው ባለቤት ሆኖ ከመቀጠል ውጭ ፍርድ ቤት በሐሰተኛ መንገድ ያገኘው ነው በማለት መወሰን አይችልም በማለት አስገዳጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ከመሆኑም በላይ በአስተዳደር አካላት የተሰጡ ውሳኔዎችን ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማየት ተፈጥሯዊ የሆነ ሥልጣን ያላቸው ስለሆነ በተከሳሽ በኩል የቀረበው መቃወሚያ በአግባቡ የቀረበ አይደለም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ የሰበር ችሎቱ ውድቅ በማድረግ ሳይወሰን አንድ የአስተዳዳር መሥሪያ ቤት የሰጠውን የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር በሐሰተኝነትም መንገድ ቢገኝ እንኳን መሰረዝ የሚችለው ራሱ ሰጪው እንጂ ፍርድ ቤት ምንም ሥልጣን እንደሌለው ያሳያል፡፡

ከላይ ከቀረበው ውሳኔ ላይ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ለያዝነው ጭብጥ እንዲያመች ፍርድ ቤቱ ሥልጣኑን በራሱ ጊዜ በመቀነስ የዜጎችን መብት እንዴት እንደሚያጣብብ ብቻ እንመልከት፡፡ አንድ የአስተዳደር መሥሪያ ቤት ኃላፊነትና ተግባሩን የሚወጣበት ሕግ ወይም አሠራር ይኖራል፡፡ በእነሱም መሠረት ለዜጎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ ሕጉና አሠራሩን ተከትሎም ይሁን ሳይከተል በመሥራቱ ምክንያት የሌላ ሰው መብት ሊያጣብብ ወይም ሊጎዳ ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ጉዳት የደረሰበት ሰው በአስተዳደራዊ መልኩ ውሳኔ ማግኘት ከቻለ ጉዳዩ በዚያው ያልቃል፡፡ ካልሆነ ግን የተበደለው ሰው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንዳያመጣ ሕገ መንግሥቱ አልከለከለም፡፡ ሌላ ሕግ እንዲሁ፡፡

ነገር ግን፣ የሰበር ችሎቱ ራሱ በደል አድራሹ ተቋም፣ ማለትም ሌላን ሰው ሐሰተኛ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር የሰጠው፣ ዳኝነት በመስጠት ደብተሩን ካልሰረዘ ፍርድ ቤት የባለቤትነትን መብት የሚያስከብርበትን ሥልጣኑን ብሎም ዜጎች ለመብታቸው ዋስትና እንዲያጡ የሚያደርግ ውሳኔ ነው፡፡

ሌላ ሦስት ምሳሌ እንጨምር፡፡ በሰበር መ/ቁ.26480፣ የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅና አቶ ቢንያም ዓለማየሁ ተከራካሪ በሆኑበት መዝገብ የሥር ፍርድ ቤት አስተዳደራዊ አካሄዳቸውን ተከትለው የተሰጡት የመጨረሻ የዲሲፕሊን ውሳኔዎችን እንደገና መርምሮ ለመወሰን የሚያስችለው የሕግ ሥልጣን ስለመኖሩ በውሳኔው ሳያመለክት ኮሌጁ አቶ ቢንያምን ከሥራ ያገደውና ያሰናበተው በአግባቡ መሆን አለመሆኑን? እንዲሁም ማግኘት የሚገባውን ደመወዝና የደረጃ ዕድገት የተነፈገው በተገቢው መንገድ ነው? ወይስ አይደለም? የሚልና ሌሎች ጭብጦችን በመያዝ ሕግ አውጪው ለትምህርት ተቋማት የሰጠውን ተቋማዊ ነፃነት በፅኑ እንደሚፃረር በመግለጽ የዳኝነት አካላቱ በሕግ ተለይቶ ባልተሰጣቸው ተግባር ያከናወኑት ተግባር እንደሆነ ወስኗል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነና የግለሰቦችን መብት በእጅጉ የሚያጣብብ አተረጓጎም ተስተውሏል፡፡ ይኼው ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ተቋማት ያወጧቸውን መመርያዎችና ደንቦች ማክበራቸውን ወይም አለማክበራቸውን ማረጋገጥ እንደማይችሉ ገደብ የሚጥል በመሆኑ ነው፡፡ ኮሌጁ፣ የተለያዩ መመርያዎችን የማውጣት ሥልጣን ቢኖረው እንኳን ከሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣረስ መሆኑ፣ ባይጣረስ እንኳን በትክክል በመመርያው መሠረት ዜጎች መብታቸው ካልተከበረ ዳኝነት ሲጠይቁ ኮሌጁና ሌሎች መሰል ተቋማት የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች እንዳይከልሱ፣ እንዳይተረጉሙ የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ ካልተከለከሉ ደግሞ ለዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ፣ ራሳቸውም ላይ ተገቢ ያልሆነ ገደብ ማድረግ የለባቸውም፡፡

አራተኛው ውሳኔው ደግሞ ይህን ይመስላል፡፡ የሰ/መ/ቁ. 63417 በአቶ ትዕዛዙ አርጋውና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ ምክር ቤት መካከል በነበረው ክርክር ላይ ደግሞ የሚከተለውን ወስኗል፡፡ አቶ ትዕዛዙ አርጋው የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እየሠሩ በነበረበት ወቅት ቀደም ሲል ሲሠሩበት ከነበረው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለቀው በተሰጣቸው ሹመት ላይ እያለ በተወሰደባቸው የፖለቲካ ዕርምጃና የአስተዳደር ውሳኔ ከሥራቸው በመነሳታቸው ጉዳዩ በክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ መሠረት ሊታይ የሚገባ መሆን አለመሆኑን መመርመር ተገቢ መሆን ወይም አለመሆኑን አስምሮበታል፡፡

 

በሌላ በኩል ተጠያቂነት አንደ የመልካም አስተዳደር ማዕቀፍ ሲሆን፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 12(2) ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በግልጽ የተደነገገ ሲሆን፣ ተጠያቂነቱ የሕግና በመረጠው ሕዝብ ጭምር ስለሆነ ጉዳዩ በፍርድ ማለቅ የሌለበት መሆኑን ሰበር አመልክቷል፡፡

በዚህ  ጉዳይ ላይ ለሰበር አቤቱታ አቅራቢው፣ የቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ፈጽመዋል በተባለት ድርጊቶች የሕዝብ ውክልና ያለው የክልሉ ምክር ቤት ከሥልጣናቸው ወይም ከሹመታቸው አንስቷል፡፡ ይህን የፖለቲካ ውሳኔ አመልካች በፍርድ ቤት ለማስለወጥ ማቅረባቸው ያላአግባብ ሲሆን፣ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ፍርድ ቤቶች ተቀብለው አከራክረው ተገቢውን ፍርድ ለመስጠት የዳኝነት ሥልጣንም አይኖራቸውም በማለት ወስኗል፡፡

ይህ ፍርድ ደግሞ ሌሎች እንከኖች አሉበት፡፡ የመጀመርያው ነገር፣ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ሲሰጥ መሠረት ማድረግ ያለበት የክልሉን ሕገ መንግሥት ሆኖ ሳለ በፌዴራሉ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥትም ይሁን የክልሉ አንድ የሕዝብ ወኪል የሆነ ተመራጭ ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ እንደሚወርድ የሚገልጽውን አንቀጽ ብቻ መሠረት በማድረግ ውሳኔ  ማሳለፉ ነው፡፡

ሕዝብ አመኔታ ያጣባቸውን ወኪሎች የሚነሱበት ሕጎች አሉ፡፡ ያም ባይሆን እንኳን አንድ ሹመኛ በምን መንገድ እንደሚሾምና ከሹመት እንደሚነሳ፣ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ የሚያገኛቸው ጥቅማ ጥቅሞች (ካሉ) ውሳኔ ማሳለፍ እንጂ በደፈናው የፖለቲካ ውሳኔ ከሆነ ምንም ዓይነት ዳኝነት ማግኘት እንደማይችሉ መተርጎም የዜጎችን መብት በእጅጉ የሚያጣብብ ነው፡፡ ወደ ቦታው ይመለስ ማለት በዳኝነት የማይወሰን ቢሆንም ሌሎች ጥቅማ ጥቅም መኖር ወይም አለመኖራቸው የሚረጋገጠው በሕግ ስለሆነ ሕጉን መሠረት ተደርጎ ላልተፈጸሙ ድርጊቶች ፍርድ ቤት ዳኝነት አይሰጥም የሚል ሕግ የለም፡፡

አምስተኛ ማሳያ እንጨምር፡፡ ጉዳዩ የገቢዎችና ጉምሩክ የነበሩ ሠራተኞችን የሚመለከት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 578/2000  አንቀጽ 19/1/ለ/ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/1999 ቢኖርም የባለሥልጣኑ ሠራተኞች አስተዳደር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት እንደሚመራ ተደንግጓል፡፡

በዚሁ መሠረትም የሚኒስሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 155/2000 ያወጣ ሲሆን፣ በዚህ ደንብ አንቀጽ 37/1/ ሥር በደንቡ በሌላ ሁኔታ የተደነገገ ቢሆንም ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና የተጠረጠረውንና እምነት ያጣበትን ማንኛውንም ሠራተኛ መደበኛውን የዲስፕሊን ዕርምጃ አፈጻጸም ሥርዓት ሳይከተል ከሥራ ማሰናበት እንደሚችል የተደነገገ ሲሆን፣ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ድንጋጌ ደግሞ ከላይ በተመለከተው ሥርዓት መሠረት ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ በየትኛውም የፍርድ አካል ውሳኔ ወደ ሥራ የመመለስ መብት እንደማይኖረው አስገዳጅነት ባለው መልኩ አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሠረት ዳይሬክተሩ በርካታ ሠራተኞችን አባረሩ፡፡ ሠራተኞቹም በአስተዳደር ፍርድ ቤት ቢያቀርቡም መፍትሔ አላገኙም፡፡

የተለያዩ ሒደቶችን በማለፍ ሰበር ላይ ደረሱ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሠራተኞቹም ወደ ሥራ የመመለስ ወይም የመደመጥ መብት በፍርድ የሚያልቅ ጉዳይ አለመሆኑን አይደለም በማለት ወሰነ፡፡ አንድ ጉዳይ በፍርድ ሊያልቅ የሚችለው ዳኝነት የተጠየቀበት ጉዳይ በሕግ ከሌላ አካል ያልተሰጠ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ መሆኑንም በሐተታው ላይ አስቀምጧል፡፡ ሠራተኞቹ የተባረሩት በሕግ መሠረት ነው፡፡ በመሆኑም የአስተዳደር ፍርድ ቤት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሊታይ የሚችል ሳይሆን ይልቁንም የአስተዳደር አካል በሕጉ አግባብ የተሰጠውን ሥልጣን ያከበረ ነው እንደሆነ ወሰነ፡፡

ይህ ውሳኔ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ላይ ከጣለው ማዕቀብ በተጨማሪ አንድ አዋጅና ደንብ መጣጣማቸውን ለመመርመር እንኳን አልፈለገም፡፡ አንድ አዋጅና ደንብ በሚጋጩበት ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉምም አያስፈልገውም፡፡

ሌላው በሕግ ለአስተዳደር አካል የተሰጠ ሥልጣንን ፍርድ ቤቶች ማየት እንደማይችሉ በማድረግ የቀረበውም እንዲሁ አሳማኝ አይደለም፡፡ ደንቡን ያዋጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሆኖ ሳለና የወጣውን ደንብ ከእናት ሕጉ (ከአዋጁ) ጋር መጣጣሙን ሳያረጋግጡ በደፈናው በሌላ ሕግ ሥልጣን እንደሌለው በማድረግ መተርጎም የለበትም፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም፣ በፍርድ የሚያልቁ ጉዳዮች ትርጓሜ የተሰጠበትም ሁኔታ ካላይ በሰፊው እንደቀረበው ዜጎችን ከፍርድ ቤት የሚያርቅ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውሳኔዎች ተወስነዋል፡፡

ፍርድ ቤት ተፈጥሯዊ የመዳኝነት ሥልጣን የላቸውምን? በእንግሊዝና በሌሎች ተመሳሳይ የሕግ ሥርዓት በሚከተሉ አንዳንድ አገሮች ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የሆነ የመዳኘት ሥልጣን አላቸው፡፡ በፍርድ ማለቅ የሚችልን ማንኛውም ጉዳይ ፍርድ ቤት ከቀረበ ጉዳዩን መርምሮ የመወሰን ሥልጣን አላቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን በሚኖራቸው ጊዜ፣ በግልጽ ተለይቶ ለሌላ የዳኝነት ሥልጣን ላለው እስካልተሰጠ ድረስ በማናቸውም ጉዳዮች አከራክሮ፣ መርምሮ፣ ማስረጃ መዝኖ ውሳኔ መስጠት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

በመሆኑም፣ ለሌላ ለአስተዳዳራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ሥልጣን የሚሰጥ ሕግ ከሌለ በስተቀር ፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ ተግባራቸው መዳኘነት ነው፡፡ ተፈጥሯዊ የዳኝነት ሥልጣን ሲባል በዋናነት የሚከተሉትን አራት ዋና ዋና ነጥቦች ይይዛል፡፡ ፍትሐዊና ምቹ የዳኝነት ሒደት መኖሩን ማረጋገጥ ተቀዳሚው ነው፡፡ የፍርድ ሒደቶችን የሚያደናቅፉ ዕርምጃዎችን እንዲወገዱ ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው ነው፡፡

የአሠራር ሁኔታዎችና ሒደቶችን አልግባብ ወይም ለግል ጥቅም እንዳይውል ማድረግ ሦስተኛው ነው፡፡ ይህን የሚሆነውና የሚረጋገጠው ደግሞ ዜጎች መብቶቻቸው አላግባብ የተጣበቡባቸው መሆኑን ሲያመለክቱ በሚሰጥ ዳኝነት ነው፡፡ በመጨረሻም፣ የበላይም ይሁን የበታች ፍርድ ቤቶችን እርስ በርሳቸው በመተባበር ፍትሕ እንዲሰፍን ማደረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋትና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችም የበታቾቹን መቆጣጠር መቻላቸው ነው፡፡

እነዚህን ለመተግበር ደግሞ ሕገ መንግሥቱን በቅጡ በመተርጎም ዜጎች መብታቸው እንዳይጣበብ ማድረግ ሲገባ በተቃራኒው እየሆነ መሄዱ ደንብ ሆኗል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡