Skip to main content
x

ነገን ማሰብ ማንን ገደለ?

ሰላም! ሰላም! መኖር መቼም ደግ ነው። በመቆየት ብዙ ዓየን። ያደላቸው ደግሞ ላላዩት ጭምር ያያሉ። እሱን ‘ፀጋ’ ብሎ ማለፍ ሳይሻል አይቀርም። የምር ግን እያዩ የማያዩ፣ እየሰሙ የማይሰሙ ሰዎች ቁጥር አልበዛባችሁም? እኩል ኖረን ታሪክ ስንተርክ የምንደባደብ ሰዎች መንገዱን ሞላነው ምነው? በቀደም አንድ ወዳጄን እንዲህ ብለው ቁምነገሩን ስቶ፣ “ተው እንጂ አንበርብር ታክሲ የሚሞላው አንሶ መንገዱን አትሙላው። የት ልንሠለፍ ነው?” ብሎ አፌዘ። ዘመን መቼም ብዙ ብዙ ምዕራፍ እንዳለው አውቃለሁ። ግን እንዲህ ያለ የምናነሳና የምንጥለው ነገር ሁሉ በፌዝ የታጀበ የሚያደርግበት ምዕራፍ እንዳለው አልጠረጥርም ነበር። ብዙ ጊዜ እኮ ቁምነገሩን የምንስተው ፌዝ እየደባለቅን ሆኗል። የባሻዬ ልጅ ይኼን ትችት ሰምቶ፣ “አሁንስ አበዛኸው!” አለኝ። “ምን ብዬ አበዛሁት? ስንት ያበዙት እያሉ አንተስ እኔን መገሰፅ ለምን አበዛኸው?” ስለው፣ “ቆይ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ? የትውልዱ እጥር ምንጥን ያለች የኑሮ ዘይቤ መፈክር ምንድናት?” ብሎ ጠየቀኝ።

“ፈካሪዎቹ እንጂ እኔ ምን አውቄ?” ስለው፣ “ቃና ውስጤ ነው በሚለው ከመተካቱ በፊት አታካብድ ትባል ነበር፤” ብሎ ወደ ትንታኔው ገባ። “እንደግዲህ ይኼ ትውልድ የከበደ ነገር ላይወድ፣ ላይቀበልና ላይደራደር ወደዚህ የዓለም ታሪክ ምዕራፍ የመጣ እስኪመስል ማካበድ አይወድም። ሌላው ቀርቶ የተቆለለ ተራራ፣ እግዚኦ የሚያስብል ደመና ሲያይ አይወድም። ዘመኑም ይኼን አውቆ ከመቼምው ጊዜ በላይ ሲበሉት ቀላል፣ ሲለብሱት ቀላል፣ ሲነካኩት በቀላሉ፣ ሲያላመጡት በቀላሉ፣ ሲውጡት በቀላሉ፣ በአጠቃላይ ቀለል ቀለል ያሉ ነገሮችን የሚያመርት አዕምሮ አስነስቷል፤” አለኝ። ሳስበው ተዋጠልኝም አልተዋጠልኝ ያለው እውነት አለው። እያዩ ያለማየት እየሰሙ ያለመስማት ጉዳይም ከዚህ ጋር እንደሚያያዝ ታየኝ። አቃለን አቃለን ይኼው ቀለን የምኖረውን ቤት ይቁጠረን። እውነቴን እኮ ነው። ብቻ የዚህ ዓለም የቅሌት መዝገብ የተከፈተ ቀን፣ እንደለመደብን ‹ከዓለም አንደኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ› ሆነን እንዳንገኝ ፀልዩ አደራ!

 ይኼን ይዤ ባሻዬ ዘንድ ሄድኩኝ። እሳቸው ደግሞ ለአላቂው ዓመት የይቅርታ መስዋዕት እያቀረቡ ሰሞኑን ከባድ ፀሎት ላይ ናቸው።  በደህናው ጊዜ ልባቸው መንግሥተ ሰማይን ናፋቂ ስለሆነ የዚህ ዓለም ነገር በፊታቸው ከተናቀ ቆይቷል። ለእኛ ደግሞ ሌላ ነው። ‹‹እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም. . .›› የተዘፈነው ለምሳሌ ለእኛ ለእኛ ዓይነቱ በሁለት ልብ ለሚያነክስ ለፍቶ አዳሪ ነው። ማስጠንቀቂያውን ብሰማና የለኝም ብል ደግሞ ንፉግ፣ ቆጥቋጣ፣ ገብጋባ፣ ቋጣሪ፣ ራስ ወዳድና ብዙ ብዙ መሰል ስሞች ጀርባዬ ላይ ሲለጠፉ ይታዩኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት የመለጣጠፍ ችግር የለብንም። አንስቼ ብሰጥ የማንጠግቦሽ ጉምጉምታና የእኔ ላብ መና መቅረት ስቀመጥ ስነሳ ሰላሜን ሊነሱት ነው። ይኼን እያሰብኩ አንድ ሥራ መጣ። ያበደ ዘመናዊ ባለፎቅ ቪላ ይሸጣል ተባልኩ። ወዲያው ቤቱንና አካባቢውን አጣርቼ ሳበቃ ለአራት ቤት ፈላጊ ደንበኞቼ ደወልኩ። ሁለቱ አላነሱም፣ አንዱ ስልኩ አይሠራም። አንደኛው ‹ሃሎ!› አለ። የነገርኩትን ሰማ። ጊዜ ሳያጠፋ አገኘኝና ቤቱን ሄዶ አየ።

ብታምኑም ባታምኑም የዕለቱ ዕለት ሰባት ሚሊዮን ብር በባንክ ወደ ባለቤቱ ከአካውንቱ እንዲዛወር አድርገ። ያንተስ ሲለኝ 7,000 ብር በእጄ ስጥቶኝ ሌላውን ወደ አካውንቴ እንዲያስገባው ነገርኩት። ወዲያው ያቺን ብር ወስጄ ካላበደርከኝ እያለ አማላጅ እየላከ ላስቸገረኝ ሰው ሰጠሁ። አልሰጥም ብል ምን እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ጥሩ ነዋ። ማግኘትና ማጣት እንዲህ ከፍና ዝቅ እያሰኘ የሚያስተያየን ሳያንስ፣ አንተሳሰብም ብንል ማን ሰላም አጥቶ ማን ሰላም ያድራል አይመጣም እንዴ? እሱን እኮ ነው የምላችሁ። ነገን ማሰብ ማንን ገደለ? የምን አለኝ የለኝም ማለት?’ የባሻዬን ልጅ ይኼን ጥያቄ ብጠይቀው፣ “ይኼ ሁሉ ሰው እንዲህ ማሰብ ቢችል እንኳን በግለሰብ ደረጃ እንደ አገር የብድር ድር ላያችን ላይ ያደራብን ነበር?” ብሎ ልክ አስገባኝ። ለካ  እንደ ግለሰብ በአበዳሪነቴ ስታበይ እንደ ማኅበረሰብ ተረጂነቴን ስቼው ነበር። አይገርምም!

እናላችሁ ሰሞኑን የማስበው በገንዘብ አቅም ራስን ከመቻል በፊት በአስተሳሰብ ራስን ስለመቻል ሆኗል። የእናንተን ባላውቅም የብዙ ሰዎች ውድቀትና ስኬት ስታዘብ ሚስጥሩ በአስተሳሰብ ራሳቸውን የቻሉና ያልቻሉ መሆናቸው ይከሰትልኛል። እኛ ደግሞ እንደምታውቁት በአለባበስ፣ በሜክአፕ፣ በምንነዳው መኪና፣ በውፍረትና በክሳታችን ነው ስንመዛዘን የምንውለው። ይኼን ትታችሁት በቀደም አንድ ቅጥቅጥ  ላሻሽጥ ደንበኛዬን እየጠበቅኩ ካፌ ተቀምጬ ሁለት ወንድማማቾች ሲነጋገሩ የሰማሁትን ላጫውታችሁ። አንደኛው አክራሪ ሃይማኖተኛ ነው። አንደኛው ልዝብ መሆኑ ነው። በማን ዓይን? በአክራሪው ዓይን፡፡ እናም ይመክረዋል። ‹‹አንተ እስከ መቼ ነው ዕድሜህን፣ ገንዘብህንና ዕውቀትህን አልባሌ ቦታ የምትጨርሰው? መቼ ነው ሰው የምትሆነው? መቼ ነው ወደ ፈጣሪ ፀጋ የምትመጣው? እስካሁን እኮ የኖርከው ሁሉ ከንቱ ነው፤›› ይለዋል።

ተተቺው በትህትናና በየዋህነት፣ “ለእኔ ስለምታስብ እንዲህ እንደምትለኝ አውቃለሁ። ግን እኔ የራሴ የሆነ ከፈጣሪ ጋር የምገናኝበት መንገድ አለኝ። የግድ የአንተን መምሰል የለበትም። እኔንም አንተንም ፈጣሪ እኩል ነው የሚያየን። ምናልባት አንተ ጠንካራ እምነት ሊኖርህ ይችላል። እኔ ደግሞ ደካማ ልመስል እችላለሁ። ነገር ግን ሁሉንም የሚያውቀው ፈጣሪ ነው። የአንተን ምክርና ሐሳብ እረዳለሁ፣ እቀበለዋለሁ። ግን በሕይወቴ ዘመን የማደርገውን ሁሉ ማድረግ የምፈልገው በራሴ ጊዜና ውሳኔ እንዲሆን ስለምፈልግ ታገሰኝ፤” ይለዋል። ያኛው አይሰማውም። “አልገባህም። ዛሬ ወደ ትክክለኛው መንገድ ካልተመለስክ ከዚህ ካፌ ተነስተህ ስትሄድ ሰይጣን ሲኖትራክ ሊወስድህ ይችላል፤” ሲለው ተተቺው በዝምታ ተነስቶ መኪናውን አስነስቶ ተፈተለከ። እኔ አልኩኝ፣ ‘እስከ መቼ ይሆን በቡድን ፍረጃ፣ በቡድን አስተሳሰብ፣ በቡድን ብያኔ ሕይወታችን እየተቃኘ ስንራብ አንድ ላይ፣ ስንጠግብ አንድ ላይ፣ ስንፀድቅ አንድ ላይ፣ ስንኮነን አንድ ላይ መሆኑ የሚያከትመው?’ ደግሞ ደግሞ አሁን በቡድን ተደራጅተንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹የዳቦ ስም› ማውጣት ጀምረናል አሉ። የዴሞክራሲያችንም ማነቆ ዋነኛ እንከኑ የሚጀምረው መደራጀት መሀል ይሆን እንዴ? ጥያቄ የመጠየቅ መብት ያለው ሕፃን ብቻ ነው ያለው ማን ነው?!

ደግሞ በቀደም ይኼንም ያንንም እያሰብኩ ግራ ግብት ብሎኝ የሆድ የሆዴን የማጫውተው ሰው ብፈልግ አጣሁ። የባሻዬ ልጅ ሥራ፣ ሥራ እያለ ቀልቡ ከእሱ የለም። ባሻዬ የተጣላ ሲያስታርቁ፣ ቀብር ሲደርሱ ዕድሩን ሲመሩ ጊዜ አጡ። ነገሩ ዙሪያውን ባስስ ሆነብኝ። እናንተ ሆናችሁብኝ እንጂ  ሰው በሞላበት አገር ሰው አጣሁ ብሎ ማውራትም እኮ ያሳፍራል። ኋላ ዘወር ስል አንድ መጽሐፍ አዟሪ ‹መጽሐፍ› ብሎ ‹ወዳጄ ልቤ› የሚል አስነበበኝ። ባሻዬ፣ ‹‹እግዜር የሚናገርለት ሰው ቢያጣ ድንጋይ ያናግራል፤›› የሚሉት ነገር ትዝ ብሎኝ መዥረጥ አድርጌ ከኪሴ ብር አወጣሁና መጽሐፉን ገዛሁት። ግን አታስዋሹኝ እስካሁን አላነበብኩትም። በቆምኩበት ለአንድ ዘመናዊ ስካኒያ ገልባጭ ግብይት የቀጠርኳቸውን ሰዎች እየጠበውኩ በቆምኩበት ከልቤ ጋር ጨዋታ ያዝኩ።

‹እሳትስ ይነዳል እንጨት ካልገደዱ፣ ሰው ከርሞ ይርቃል ልብ ነው ዘመዱ› ተብሏል አይደል? ታዲያ ከብቸኝነቴ ብሶ ከልቤ ጋር ጨዋታ መያዜ ይባስ ብቸኛ አደረገኝ። ወጪ ወራጁን ስታዩት ልቡን ልብ የሚልም ጠፍቷላ። እንዲያውም ካነሳነው አይቀር ሰው ልቡ የሚመክረውን ከመስማት የሰው ምክር እየሰማ መስሎኝ መከራ እየመከረ ያስቸገረው። እውነቴን እኮ ነው። ልብ ይስጠን ነው መቼም። ታዲያ አጫውተኝ ያልኩት ልቤ ከጥያቄ ጥያቄ እያስከተለ ሕመሜን አባሰው። ‘ምነው ሰው ነፍሱ እርቃኑዋን ቀረች?’ ይለኛል። ‘ኧረ ተወኝ’ ስለው ‘ምነው ፍቅር ቀዘቀዘች?’ ይለኛል። ‘እኔ ምን አውቄ’ ስለው ‘ምነው እንዲህ እነ አባ ውሸት፣ እነ እሜት ምቀኝነትና እነ ፍቅረ ንዋይ ናኙ?’ ይለኛል። ‘ጉድ ነው’ እላለሁ አፍ አውጥቼ። ታዲያ ከልቤ አስጥሉኝ ብዬ አልጮህ። ለነገሩ ብንጮህም የሚጥለን እንጂ የሚያስጥለን ጠፍቷል። ወይ ልቤና እኔ!

በሉ እንሰነባበት። ግሮሰሪያችን ጢም ብላለች። አዳሜ በአዲስ ዓመት ሽልማት በተንቆጠቆጥኩ እያለ ይኼን ቆርኪ ይፍቀዋል። ይኼ ቢራ ይጠጣል። ቆርኪ ይፋቃል ይጣላል። ይፋቃል ይጣላል። አንዱ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ፣ ‘’እኔ ድሮም ዕድል የለሽ ነኝ፤” ብሎ በራሱ ይማረራል። “ማን ዕድል ያለው ዓይተሃል?” ይለዋል ከወዲያ። “ዕድሌ ዋዛ ነው እንዴ? ዕድለኛ ለመሆን መጀመርያ ፀንቶ በጨዋታው ሕግ መሠረት ጨዋታውን መጫወት ያስፈልጋል፤” ይላሉ ከባሻዬ አንድ አሥር ዓመት አነስ የሚሉ አዛውንት። “አንቺ አገር?” የሚለው ደግሞ መጣ። ጥንብዝ ብሎ ሰክሯል።

‹‹ዜጋሽ ቤት የለው። ትዳር የለው። እንባውን የሚጠርግለት መንግሥት የለው። የታመነው ዘራፊ፣ የተሾመው አውዳሚ። ዜጋሽ አይሟገት። የደከመው ብቻ ወኔ የከዳው። እህሳ? ቁጭ ብሎ ከቆርኪ ጋር ይላፋል። እናንተ? . . . ›› አለን አንድ በአንድ እየገላመጠን፡፡ “ትንሽ ህሊናችሁን አይፍቃችሁም? በገዛ አገራችሁ ቤትና መኪና ሠርታችሁ ከማግኘት ይልቅ፣ በሽልማት ማግኘት ቀላል መንገድ ሆኖ ስታዩ? ኡኡኡ ማለት አልነበረባችሁም?” ሲል ሁሉም ሊበሉት ተነሱ። ግሮሰሪያችን በጩኸት ደመቀች። ዲዮጋንም መራመድ እስኪያቅተው ተቀጥቅጦ መሬቱ ላይ ተኛ። እኔም ትንሽ ቆያይቼ ቤቴ ገብቼ ተኛሁ። ‹‹ከትጋት ይልቅ ዕጣ ኑሮ በሚያደላድልባት አገር በጊዜ ተኝቶ አርፍዶ ከመነሳት የተሻለ ምን አማራጭ አለ?›› የሚል ሐሳብ በሰመመን ብልጭ ቢልልኝም፣ እኔ ግን እውነት እላችኋለሁ ነገን ማሰብ ማንን ገደለ እያልኩ ነበር፡፡ አይደለም እንዴ?  መልካም ሰንበት!