Skip to main content
x
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ የሚያደርገው የትራምፕ ረቂቅ ንግግር

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ የሚያደርገው የትራምፕ ረቂቅ ንግግር

አሜሪካ ቀድሞውንም ቢሆን ኢራንንና ሰሜን ኮሪያን የዓለም ሥጋት ብላ ፈርጃቸዋለች፡፡ በመሆኑም በአገሮቹ ላይ ማዕቀብ ከማስጣል አልፋ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ስትዝትና ስታስፈራራ ሁሌም ትሰማለች፡፡ ዓመታዊው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ መስከረም በጠባ ቁጥር ሲደረግም፣ የእነዚህን አገሮች እኩይ የምትለውን ተግባር ሳታነሳ አታልፍም፡፡ መንግሥታትም በአገሮቹ ላይ ዕርምጃ እንዲወስዱ መወትወቷ የተለመደ ነው፡፡

የአሜሪካን የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ከተቆናጠጡ ዓመት ያልሞላቸውና ማክሰኞ ምሽት (ለኅትመት ከገባን በኋላ) በተጀመረው 72ኛው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ የመጀመርያ ንግግራቸውን የሚያደርጉት ዶናልድ ትራምፕ፣ እንደ ቀድሞዎቹ የአገሪቱ መሪዎች ኢራንንና ሰሜን ኮሪያን ዓለም እንዲያወግዝላቸው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ተጠብቋል፡፡

ሲኤንኤን ዋይት ሃውስ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ትራምፕ በመጀመርያው የድርጅቱ ጉባዔ ንግግራቸው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እሳቸው ‹‹መንትያ የዓለም ሥጋት›› የሚሏቸውን ኢራንንና ሰሜን ኮሪያን እንዲገዳደርላቸው ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ‹‹የዓለም ሥጋት›› የሚሏቸውን ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ከመገዳደር ይልቅ፣ ‹‹የታሪክ ተመልካች›› የመሆን አደጋ ውስጥ እንዳይገባም የሚያስጠነቅቁ መሆኑን የዋይት ሃውስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡

አገሮች የራሳቸውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲሉ የሚወስዱትን ኃላፊነት የሚደግፉ መሆኑና ‹‹የማይታመኑ›› በሚሏቸው ሁለቱ አገሮች ላይ የጋራ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ ያቀርባሉም ተብሏል፡፡ ሆኖም ከዚህ ቀደም በነበሩ ሌሎች ንግግሮቻቸው ቁርጥ ያሉ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ እየሆነ የመጣውን ዓለም እንዳያስቀይሙም ተሠግቷል፡፡

ትራምፕ ትዊት በማድረግም ሆነ ባገኙት መድረክ አንድን አጀንዳ እዚያው ወስነውና ጨርሰው መናገር ልማዳቸው ነው፡፡ ይኼም በአሜሪካ የተወሰኑ ባለሥልጣናትም ሆነ በሌሎች አገሮች፣ እንዲሁም በሚዲያው አስተችቷቸዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ የሚያደርገው የትራምፕ ረቂቅ ንግግር
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን የአሜሪካ ማስፈራሪያ ወደ ኑክሌር ጦርነት ይወስደናል እያሉ ነው

 

ሲኤንኤን እንደሚለው፣ ትራምፕ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የሚያደርጉት ንግግር እንደ ከዚህ ቀደሙ ልጓም የሌለው መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ ቀደም በሳዑዲ ዓረቢያ በነበራቸው ቆይታ ከሙስሊም መሪዎች ጋር መክረዋል፡፡ በፖላንድም ጉብኝት አድርገው ተወያይተዋል፡፡ ሆኖም የድርጅቱ ጉባዔ የተለየና የዓለም መሪዎች የሚገኙበት ነው፡፡

የትራምፕ ንግግር የሚደመጠውም በአንድ ወይም በተወሰኑ አገር መሪዎች ብቻ ሳይሆን በመልክዓ ምድር አቀማመጣቸው፣ በባህላቸው፣ በወጋቸው፣ በፖለቲካቸው፣ በኢኮኖሚያቸውና በአኗኗሯቸው የተለያዩ አገሮችንና ሕዝቦችን ወክለው በሚመጡ መሪዎች ነው፡፡

የሚያደርጉት ንግግር በመላው ዓለም የሚስተጋባ ከመሆኑ አንፃርም፣ አገሮች ካላቸው የውጭ ፖሊሲ ጋር የሚመቻች የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከአዲሱ የአሜሪካ መሪ ይጠበቃል፡፡ ይኼንንም ተንተርሶ ትራምፕ ጥልቅ ፍልስፍና የተሞላበት ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡

ትራምፕ የሚያደርጉት ንግግር ረቂቅም፣ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አገሮች የራሳቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ እንዲሠሩ የሚያበረታታ መሆኑን ማስፈሩን ዘገባው ያሳያል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ የሚያደርገው የትራምፕ ረቂቅ ንግግር
የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሐኒ አገራቸው በሰዓት ውስጥ የኑክሌር ፕሮግራሟን እንደምታስጀምር አሜሪካን አስጠነቅቀዋል

 

ለሲኤንኤን ስማቸውን ያልገለጹ ባለሥልጣን፣ ‹‹ይኼ የማይታመን አጋጣሚና የአሜሪካን አመራርና እሴት ለማሳየት ትልቅ አጋጣሚ፤›› ብለውታል፡፡ አገሮች የጋራ ፍላጎትን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚያስችላቸውን ዘዴ የሚተገብሩበት ይሆናል፡፡ ሆኖም የሌሎችም አገሮች ፍላጎት በሆኑና ሊያጋሯቸው በሚችሉት ላይ አብረው ከሠሩ የተሻለ ውጤት እንደሚያገኙም የንግግራቸው ረቂቅ ያሳያል፣ እንደ ዘገባው፡፡

ትራምፕ ከዚህ ቀደም ሲናገሩት እንደነበረው፣ አገሮች እንዴት መኖር እንዳለባቸው ሌሎች አገሮች ሊነግሯቸው አይገባም፡፡ በድርጅቱ ጉባዔ የሚያደርጉት ንግግርም ይኼንኑ የሚያመላክት ይሆናል፡፡ አገሮች ለአንድ ዓላማ አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ ቢኖርም፣ አንድ መንግሥት የሚከተለውን አሠራር ይከተሉ ማለት እንደማያስፈልግም አጽንኦት ይሰጡበታል ተብሏል፡፡

ትራምፕ አገሮች የራሳቸውን ፍላጎት ለማስጠበቅ ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት አለባቸው ያሉት እንዲሁ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ማንም ጠልቆ መግባት የለበትም ሊሉ ፈልገው ብቻ አይደለም፡፡ ሕዝባቸው ላይ ጫናና አፈና ይፈጥራሉ ተብለው በምዕራባውያኑ የዜና አውታሮች የሚወነጀሉትን ሰሜን ኮሪያና ኢራን ለመምታት ነው፡፡

የትራምፕ ንግግር ማጠንጠኛው የኢራንና የሰሜን ኮሪያ መንግሥታት የሕዝባቸውን ፍላጎት እያስጠበቁ አይደለም የሚል ነው፡፡ አገሮች የውስጥ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት አለባቸው ሲሉ፣ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ፍላጎት ቅድሚያ እየሰጡ አይደለም የሚለውን መከራከሪያ ይዘው ብቅ ይላሉ ተብሏል፡፡ የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ደግሞ ትራምፕ በንግግራቸው ያካትቱታል እንደተባለው፣ አገሮች በይበልጥ የግል ፍላጎታቸውን መሠረት አድርገው፣ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚኖራቸው የጋራ ዓላማ ላይ እንዲሠሩ የሚያበረታታ ነው የሚል ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ የሚያደርገው የትራምፕ ረቂቅ ንግግር
የሰሜን ኮሪያ ኃይድሮጂን ቦምብ በአኅጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳይሎች ላይ ለመጫን ዝግጁ መሆኑ የዓለም ሥጋት ሆኗል

 

አሜሪካ በሁለቱ አገሮች ላይ ያላት አቋም በማዕቀብ የታጠረ ቢሆንም፣ አገሮቹ ለአሜሪካ ምላሽ ከመስጠት አልተቆጠቡም፡፡ የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ማዕቀብ ከኑክሌር ማበልፀግ ፕሮግራማቸው ከማደናቀፍ ይልቅ ይበልጥ ጥንካሬ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ ዛቻና ማስፈራራት ግን ወደ ኑክሌር ጦርነት ያመራል በማለትም አስጠንቅቀዋል፡፡

በኢራን የኑክሌር ፕሮግራም ላይ እ.ኤ.አ. በ2015 የተደረገውን ስምምነት ‹‹የባሰበት መጥፎ›› ሲሉ የሚገልጹት ትራምፕ፣ በጉባዔው የጎንዮሽ ውይይት ላይ ስምምነቱ መልሶ እንዲከለስ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ማመላከታቸውን ተከትሎም፣ የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሐኒ ‹‹አሜሪካ ታላቅ ዋጋ ትከፍላለች፤›› ብለዋል፡፡ ትራምፕ የኢራን የኑክሌር ስምምነትን እንደ ሥጋት ዓይተው ለመቀልበስ የሚያደርጉትን ጥረት እንደማይደግፉም ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም ኢራን በሰዓታት ውስጥ የኑክሌር ፕሮግራሟን ማስጀመር እንደምትችልም አስታውቀዋል፡፡

በጉባዔው ለመሳተፍ አሜሪካ የገቡትን ሮሐኒ ሲኤንኤን ቃለ መጠይቅ አድርጎ እንዳሰፈረው፣ ‹‹አሜሪካ የኢራኑን የኑክሌር ስምምነት ካፈረሰች ዋጋ ትከፍላለች፡፡ በግሌ አሜሪካውያን ለማይጠቅማቸው ነገር ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ ይሆናሉ ብዬ አላምንም፤›› ብለዋል፡፡

ሮሐኒ እንደሚሉት፣ ትራምፕ አሜሪካ ከኢራን ጋር ያደረገችውን የኑክሌር ስምምነት ካፈረሱ፣ አሜሪካ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰጣትን አመኔታ ታጣለች፡፡

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት በኢራን ላይ ተጥሎ በነበረው ማዕቀብ ላይ የተሰጠውን የዕፎይታ ጊዜ በስምምነቱ መሠረት ያራዘመች ሲሆን፣ ትራምፕ ይኼንን አይደግፉትም፡፡

ኢራን ያላትን የኑክሌር ፕሮግራም አስመልክቶ የተደረገው ስምምነት፣ ኢራን የበለፀገ የዩራኒየም ክምችቷን 97 በመቶ፣ እንዲሁም የኑክሌር ማብላያዎቿን በሁለት ሦስተኛ እንድትቀንስ፣ የኑራኒየም ማበልፀግ ፕሮግራሟ በአገሪቱ ለሚሠራጨው የኃይል አቅርቦት እንጂ ለኑክሌር ቦምብ እንዳይሆን፣ የኑክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታዛቢ እንዲፈተሽ መፍቀድ፣ ስምምነቷን ስለማክበሯ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በየ90 ቀኑ ለኮንግረሱ ማረጋገጫ መስጠት እንዳለበትና ኢራን ለስምምነቱ ካልተገዛች በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኑክሌር ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶች ላይ የተጣሉና የማዕቀብ ዕፎይታ ጊዜ የተሰጣቸው ማዕቀቦች ዳግም ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገኝበታል፡፡

ኢራን ስምምነቱን አክብራ ስለመገኘቷ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኑክሌር ዘብ፣ ኢራን ፍተሻ መፍቀድን ጨምሮ ለሁሉም ስምምነቶች ተገዥ መሆኗን መስክረዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ የሚያደርገው የትራምፕ ረቂቅ ንግግር
አሜሪካ ሰሞኑን በኮሪያ ልሳነ ምድር በተዋጊና በቦምብ ጣይ ጄቶች በረራ ማካሄዷ ሌላ ሥጋት ፈጥሯል

 

የፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂን ቪዝ ድሪያን በበኩላቸው ስምምነቱ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፣ አሜሪካ ከስምምነቱ ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡ ከስምምነቱ መውጣቷ የኑክሌር ፕሮግራሙ እንዲቀጥል ብሎም መካከለኛው ምሥራቅ እንዲበጣበጥ ምክንያት ይሆናልም ብለዋል፡፡

ለስምምነት ሆነ ለዛቻ ቦታ የማትሰጠው ሰሜን ኮሪያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ የተጣለ ቢሆንም፣ ይኼ ከኑክሌር ፕሮግራሟ ሊያግዳት አልቻለም፡፡ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ‹‹ጦርነት ትሻለች›› በማለትም በተደጋጋሚ ትናገራለች፡፡ በተመድ ጉባዔ ላይም ትራምፕ ኢራንና ሰሜን ኮሪያን ዒላማ አድርገው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡