Skip to main content
x

‹‹ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ . . .››

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

2008 ዓ.ም. ሕዝቦች ፖለቲካዊ ሙስናን በመቃወም መብታቸውን ለማረጋገጥ ምን ሊሠሩ እንደሚችሉ የሚያመላክት ነበር፡፡ መንግሥትን ያንቀጠቀጠ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቦች የትግል ተሞክሮዎቻቸውን ቀምረው ለቀጣይ የሚዘጋጁበት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም ነበረው፡፡ ለገዢው ግንባርና ለፖለቲካ ድርጅቶች በአጠቃላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› የሚባለውን ጥልቅ ጉድጓድ ትተው፣ በእውነት ለመታደስ ጥሩ ዕድል ሊሆን ይችል ነበር፡፡ ሕጋዊ ተቃዋሚዎችም በዚህ ማዕበል ውስጥ ለመዋኘት አለመቻላቸው ራሳቸውን ለማስተካከል ዕድል የሚሰጣቸው ካልሆነ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ . . . ›› እንዳይሆን፡፡ ፅንፈኞች የሕዝቡን ምሬትና ቅሬታ ተጠቅመው ምን ያህል ውድመት ሊያደርሱ እንደሚችሉም ያሳየ ነው፡፡

አጠቃላይ የሕዝቦች እንቅስቃሴ ባህሪ ላለፉት 25 ዓመታት በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም፣ ያጣጣሙዋቸው ሕገ መንግሥታዊ መብቶች የበለጠ እንዲጠናከሩና በተለይ በተፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በኅብረተሰቡ አዲስ ማኅበራዊ መዋቅር፣ አዳዲስ ኃይሎችና ፍላጎቶች እያደጉ መሄዳቸው አልቀረም፡፡ ግሎባላይዜሽን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኮሙዩኒኬሽን በኩል የሚተላለፈውን የፖለቲካዊ መብቶች ዕድገት ለበለጠ መብት መጠየቁና መታገልን ይገልጸዋል፡፡ ለተሻለ ዕድገትና መብት መንቀሳቀስ የጤናማ ኅብረተሰብ ምልክቶች ናቸው፡፡

ወደ ተጠናከረ ዴሞክራሲ (Consolidated Democracy) የሚደረገው ረዥም ሽግግር በተለያዩ የአመለካከት፣ የአደረጃጀትና የአመራር ሒደት ማለፉና በየጊዜው የሚያጋጥሙ አጠር ያሉና ብዙውን ጊዜ የሚያናጉ (Shock) ሽግግሮች መታጀቡ አይቀሬ ነው፡፡ ሽግግሩ በተነፃፃሪ የተረጋጋ (Smooth) እና አጠር ያለ እንዲሆን በየጊዜው ለሚመጥነው አመራር ማስረከብ ቁልፍ ሚና አለው፡፡

የአመፀኛው ትውልድ አመራር (በአመፅ ተወልዶ፣ አድጎ፣ በአመፅ ሥልጣን ወይም የፖለቲካ አመራር የተቆጣጠረ)፣ የዴሞክራሲያዊ ትውልድ (በሰላም ጊዜ የተወለደ/ያደገ፣ የተማረ፣ የተመራመረ፣ ዴሞክራሲን በተግባር መለማመድ የጀመረ) አመራር እንዲረከበው ማድረጉ ለታሪክና ለራሱ ሲል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ካልሆነ ደግሞ የኃይለ ሥላሴና የደርግ ዕጣ ፈንታ እንዳያጋጥመው ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም የሕዝቦችን ጥያቄዎች በእኛ እናውቅሃለን ለመመለስ ሲሞክሩ በኃይል ተጠቅመው ትግሉን እንገታዋለን እያሉ ነው፣ ሱሪያቸውን ሳይታጠቁ የተደረሰባቸው፡፡ ለጊዜው ካልሆነ በአመፀኛው ለሞግዚትነት የሚመራ የዴሞክራሲ ሒደት የለም፡፡ የተወሰነ ጊዜ መደናቀፍ አይቀሬ ነው፡፡ የዴሞክራሲው ትውልድ ሥልጣኑን ለመረክብ ካልተዘጋጀ፣ መደነቀቃፉ ከበዛና ቀጣይነት ካለው ጠቅላላ ሽግግሩን አደጋ ውስጥ ሊከተው ይችላል ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቷ ህልውና አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አመራር ከውስጥም ከውጭም ሲሆን ጎልተው የሚታዩት የዳያስፖራ ፅንፈኞች፣ የውስጥ ሕጋዊ ተቃዋሚዎችና ገዢው ግንባር ኢሕአዴግና የእሱ አጋር ድርጅቶች የሚላቸው ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ተቃዋሚዎችና በአጋር ድርጅቶች ላይ ያለኝ ትዝብት (Observation) አናሳ በመሆኑ በሌሎቹ ላይ ያተኮረ ሐሳብ ነው የምሰነዝረው፡፡ አጠቃላይ አስተያየቴ በሰፊ ጥናት ሳይሆን በግላዊ ትዝብት የተመሠረተ በመሆኑ፣ አንኳር የሚባሉ ጉዳዮችን ለውይይትና ለቀጣይ ጥናት በመጋበዝ የተሳሳተና ወደ ፅንፍ የሚሄድ አስተያየት ካለ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡

እሳት መማገድ የዳያስፖራው ፅንፈኛ ሁነኛ ሴራ

የፅንፈኛ አፈ ቀላጤዎች በአብዛኛው ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) ናቸው፡፡ ወላፈኑ በማያገኛቸው አገር ተቀምጠው እሳት እየማገዱ ሥልጣን ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያን እኛ ነን የምናውቅላችሁ ይሉናል፡፡ ‹‹ቆሞ ቀር›› ኢትዮጵያዊነትን እንጂ እያደገና እየተመነደገ፣ እያበበና እያሸበረቀ፣ ሥር እየሰደደ እየሄደ ያለ እውነትንና የታደሰውን ኢትዮጵያዊነት አይቀበሉም፡፡ ኢትዮጵያ የተወሰኑ ልዩ ብሔሮች፣ የአንድ ሃይማኖት፣ እምነ ይሁዳ ነገደ አንበሳ አገር እንደሆነች ይስሏታል፡፡ እኩልነት የሚባለው ወደ አዕምሯቸው አይንሸራሸርም፡፡ አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው አግላይ ነው፡፡ ሌላው አግላይ ዳያስፖራ ፅንፈኛ በብሔር ስም የተደራጀ፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክ (በበጎም በመጥፎም) እና እሴቶች የሉንም ብሎ የሚክድ ነው፡፡ ገዢዎችና ሕዝቦችን ለያይቶ ማየት ኃጥያት የሚሆንበት ነው፡፡ እንወክለዋለን የሚለውን ሕዝብ ጥቅምና እሴቶች ሳይሆን፣ የራሱን የስግብግብነት የፖለቲካ ዝሙት ያካሂዳል፡፡

እነዚህ ጠቅላይና አግላይ ፅንፈኛ ኃይሎች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ በር ከፋች የሆነውን የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት፣ ሰንደቅ ዓላማውን፣ የሕዝብ መዝሙሩን ጭምር ክፉኛ ይጠላሉ፡፡ እነሱ የማይቆጣጠሩት አስተሳሰብ እንደሌለ ይቆጥሩታል፡፡ በ‹ርዕሰ ዴሞክራሲ ሊቀ ጳጳስ ኢሳይያስ አፈወርቂቅ ተባርከው ለዴሞክራሲ ቆመናል ይላሉ፡፡ ሥራቸው ግን ኢትዮጵያን ለማተራመስ መሞከር ነው፡፡ ጉራ ብቻ ሆነ እንጂ፡፡ በዴሞክራሲ አገር እየኖሩ አማራጭ አስተሳሰቦችን ማስተናገድ ነውራቸው ነው፡፡ ተከታዮቻቸው ትክክለኛ መረጃ እንዳያገኙ ይከላከላሉ፡፡ ከኢትዮጵያ የሚተላለፍ የቴሌቪዥን ሥርጭት የሚያስተናግዳቸው ሬስቶራንቶች/ንግድ ቤቶችን በማግለል ገበያቸው እንዲቀዘቅዝ የተቻላቸውን ያደርጋሉ፡፡

ኢትዮጵያ ብድርና ዕርዳታ እንድታገኝ አልፎም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ እንዳያገኝ ሰፊ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር በተለይ ልማቷንና ሥርዓቷን ከሚፃረሩ አገሮች ጋር ይሠለፋሉ፡፡ የሚማግዱት እሳት እነሱን እንደማይነካ ስለሚያውቁ፣ አራት ኪሎ ለመግባት ሲሉ እሳት ለማቀጣጠል ይሞክራሉ፡፡ በአመፅ የተወለዱ፣ በአመፅ የሚኖሩ በመሆናቸው የዳያስፖራው ብዙኃን ዝምተኛ (Silent Majority) ወግድ ማለት ይገባዋል፡፡

ሕጋዊ ተቃዋሚ ድርጅቶች

እነዚህ ተቃዋሚ ድርጅቶች ሕዝቦች በፈጠሩላቸው ማዕበል እየዋኙ መሆናቸውን የሚያሳይ ጠንካራ ምልክት እያየን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አፈና ተቋቁመው ሕዝቦች ውስጥ በስፋት በመንቀሳቀስ፣ ዘላቂ ፍላጎታቸውንና እሴቶችን በማጤን ፕሮግራማቸውን፣ ፖሊሲያቸውን፣ ስትራቴጂያቸውንና ታክቲካቸውን ሲያሻሽሉ በግልጽ አይታዩም፡፡ በ2008 ዓ.ም. የተፈጠረውን መንግሥትን ያንቀጠቀጠ የትግል ሁኔታ አለን ለሚሉት ዓላማ በማስፋፋት ሕዝቡ ውስጥ በስፋት ሲንቀሳቀሱ አይታዩም፡፡ መቼ ይሆን ሕዝቡ ውስጥ የሚገቡት?

የተቃዋሚዎች አብዛኛዎቹ አመራሮች የአመፀኛው ትውልድ አባላትና የእነሱ ግርፍ በመሆናቸው፣ ከገዢው ግንባር ጋር እየተደራደሩና በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች በቴሌቪዥን እየተንጎማለሉ ኑሮ ያደረጉት ይመስላል የዴሞክራሲው ትውልድ ውስጣቸው ገብቶ ከመሠረቱ ካልቀየራቸው ወይም አዳዲስ ጠንካራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ካልተደራጁ ለአገሪቱ አደጋ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር

ሕዝቦች ለመብታቸው ያደረጉት ከፍተኛ ትግል ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› እንዲያውጅ አስገድዶታል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ የሕዝቦች ግፊት ራሱን ለማደስ ያነሳሳው መሆኑን በማመን እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

‹‹የአገራችን ሕዝቦች በየአካባቢው የሚታዩ ስህተቶች ይወገዱ ዘንድ ጠንከር ባለ አኳኋን ያካሄዱት ትግል ሥራ አስፈጻሚው ለወሰዳቸው የለውጥ አቋሞች ጠንካራ መሠረት ሆኖ አገልግለዋል፤›› ቀጥሎም፣ ‹‹የሕዝቦች ትግል እነሆ ዛሬ ድርጅታችንን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጅት የሚታዩ ችግሮች እንደሆኑ ተገንዝቦ . . .  አስፈጻሚው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ . . . ›› ብሎ ነበር፡፡ ብሎ ነበር፣ ሆነ ቀረ እንጂ፡፡ ጉራ ብቻ!!!

ሕዝቦች የታገሉት የግለሰብና የቡድን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ ነው፡፡ ‹‹ተሃድሶ›› የሚለካው እነዚህን መብቶች ለማስከበር ምን ያህል ዕርምጃ ተወስዷል በሚለው ነው፡፡ ይህ ማለት ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ አመለካከቶች፣ ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና አሠራሮች እስከምን ድረስ መሻሻል ተደርጎባቸዋል ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ድባብ ለማስፋት ተጨባጭ ዕርምጃዎች ተወስደዋል ወይ? ወዘተ ነው፡፡ የሕዝቦች መብቶች በቀጣይነት ሊረጋገጡ የሚችሉት ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት በነፃነት ሲሠሩ በመሆኑ፣ በዚያ በኩል ምን መሻሻል አለ? ከዚህ መሥፈርት አኳያ ሲታይ የ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ሰፋፊ ግምገማዎች፣ የመንግሥትና ሕዝብ ገንዘብ፣ ጊዜና ሌሎች ሀብቶች ከማጥፋት ውጪ የፈየዱት ነገር የለም፡፡ በአጠቃላይ አንድ ዕርምጃ ወደፊት በሁሉም መስክ አልተሄደም፡፡ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ጉራ ብቻ ነው የሆነው፡፡

አይዲዮሎጂካልና ፖለቲካዊ ክስረቱ የበለጠ የተጋለጠበት፣ ፖለቲካዊ ሙስና የገነገነበት እንደ አንድ ፖለቲካዊ ድርጅት መሥራት ያቃተበት (በብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ ያለው ሽኩቻና በእያንዳንዱ ድርጅት አመራር ውስጥ የሚታዩት መጠላለፍ ሲታይ) የነበረውን አቅምና ወኔ አሟጦ ጊዜው የሚጠይቀው ጥንካሬ (Dynamism) የሌለው አመራር ሆኗል፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ግጭት ከተከሰተ በኋላ አፋጣኝ ዕርምጃ አለመውሰዱ፣ ቀደም ብሎ በቅማንት ሕዝብ የተፈጸመው ግፍ፣ በጎንደር አካባቢ የትግራይ ተወላጆችን ለይቶ የተፈጸመው ጥቃት፣ በኦሮሚያ በነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የደረሰው ጥፋት ‹‹ተመጣጣኝ›› ነው ማለቱ፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉራ ፈርዳና በኦሮሚያ ገሶ ሊበን በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው ግፍ ተጣርቶ ዕርምጃ ይወሰዳል ሲባል በዝምታ ማለፍ፡፡ ሕዝቦች/ሃይማኖት ተሰባጥረው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ቅድመ ግጭት ጥናት በማከናወን መከላከል፣ የኃይል ግጭት ከተፈጸመ በኋላ አፋጣኝ ዕርምጃ አለመውሰድ በሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ግድ የለሽነት ያሳያል፡፡ ሕዝባዊነት በፊት ከነበረው ምን ድረስ እንደተሟጠጠ ያሳያል፡፡

በተለይ አንደ ማዕከል (Core) ሲታዩ የነበሩት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከዴሞክራሲ ጋር ጭራሽ መሄድ የተሳናቸው፣ ሕዝባዊነታቸው እያበቃለትና በአጠቃላይ የብቃት መንሸራተት የሚታይባቸው ሆነዋል፡፡ በትጥቅ ትግሉና ባለፉት 26 ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች ሰክረው በዚያ ብቻ የሚንጠራሩ ሆነዋል፡፡ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ዕይታና እንቅስቃሴ አይታይባቸውም፡፡ የሕግ የበላይነት ለስሙም ቢሆን የማይቀርባቸው ሆነዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የአማራው ሕዝብ ተቃውሞ ምን ያህል ስፋት እንደነበረው የሚታወቅ ነው፡፡ ብአዴን ‹‹በጥልቅ ተሃድሶው›› ምንም ዓይነት መሠረታዊ የአስተሳሰብ፣ የአደረጃጀትና አመራር ለውጥ ሳያደርግ እንደነበረው እየቀጠለ ነው፡፡ ለሕዝቡ መብቶች፣ ፍላጎቶችና እሴቶች ምንም ደንታ የሌላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ አንዳንድ ተንታኞች አስተሳሰብ ብአዴን በዋሽንግተን ፅንፈኞች የተጠለፈ፣ ምናልባትም በእነሱ የሚመራ እንዳይሆን ያሠጋቸዋል፡፡

ክቡር አቶ ዓባዬ ፀሐይ ‹‹ውራይና›› ለሚባለው የትግርኛ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የትግራይ ሕዝብ ተመችቶት ሳይሆን ትዕግሥት ማድረጉንና አመራሩ በሕጋዊ መንገድ ራሱን ማስተካከል ካልቻለ፣ ሕዝቡ የግርግር መንገድ ሊከተል እንደሚችል ነበር የገለጹት፡፡ 

ብዙ የማይታወቀው የ2007 እና የ2008 ዓ.ም. የትግራይ ሕዝብ ትግል እንደተፈለገው ባይሳካም፣ ለዘርፉ ተመራማሪዎች ጥልቅ ጥናት የሚጋብዝ ነው፡፡ የእምባሰነይቲ ዓይነት እንቅስቃሴዎች በደረጃቸው ቢለያዩም በመላ ትግራይ የነበሩ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ መታየት ያለበት ግን በ2007 ዓ.ም. የሕወሓት ጉባዔ ሕዝቡ ያደረገው ከፍተኛ ተፅዕኖ ነው፡፡ የሕዝቡ ምሬት በቀጥታ በጉባዔው የሚንፀባረቅበት መንገድ እንዴት እንደተፈጠረና ድርጅቱ እንዲታደስ ከታች ወደ ላይ የነበረው ተፅዕኖ ሲታይ፣ ሕዝብ ድንጋይ ሳይወረውርና ደም ሳይፈስ ምን ሊሠራ እንደሚችል ያሳየና የአመራር ጉዳይ እንዴት ቁልፍ እንደሆነ ያመላከተ ነበር፡፡

 

ይህ ጉባዔ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅና ዋናውን አመራር ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር በፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ በመጠላለፍ (Networking)፣ የውሸት ሪፖርትና በብቃት ማነስ ክፉኛ ሒስ ቀርበውታል፡፡ መሠረታዊ የአመራር ለውጥ ይመጣል ሲባል ግን ከሸፈ፡፡ የለውጥ አመራር ታጣ፡፡ በተወሰነ ደረጃ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትም ወላወሉ፡፡ እነሱንም ጠራርጎ እንዳይጥላቸው ፈሩ መሰለኝ ተሞዳሞዱ፡፡ የሕዝቡና የጉባዔተኛው መንፈስ የማይገልጸው አመራር መሆኑን ለመግለጽ የትግራይ ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ‹‹ከክፍል 21ኛ ከዩኒት አንደኛ›› በማለት የሕወሓት የፖለቲካ ውጥንቅጥን ይገልጹታል፡፡

ሕወሓትም ልክ እንደ ብአዴን አዲስ ራዕይ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አደረጃጀትና አመራር ሳያስተካክል አመራሩ ተሸማግሎ ቀጠለበት፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የወልቃይት ጉዳይን አስመልክተው የሁለቱም ክልሎች አመራሮች ጥፋት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ግን ሥር የሰደደ ነበር፡፡ በትምክህትና በበላይነት ሲወናጀሉ የነበሩት ሁለቱ ድርጅቶች በጎንደር የተፈጸመው ጥቃት የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ቅራኔ እንደሆነ በማስመሰል የእርቅ ጉባዔ አካሄዱ፡፡ ሕዝቡ ቀድሞውንም አልተጣላም፡፡ በቡዙ ቦታዎች አማራው የትግራይ ወንድሞቹን ከወንጀለኞች ተከላከለ እንጂ!! የላይኛው አመራር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ እያለ ነው ግፍ የተፈጸመው፡፡

የድሮ መሳፍንቶች ከጦርነት በኋላ ወይም ግፍ ከተፈጸመ በኋላ በጋብቻ ትስስር ሁኔታውን ሊያቀዘቅዙት ይሞክሩ ነበር፡፡ የሕግ አገዛዝ (Rule By Law) እንጂ የሕግ የበላይነት (Rule Of Law) ባልነበረበት በመሆኑ ምን ይደረግ ማለት ነው የሚቻለው፡፡ የአሁኖቹ መሪዎች ሥልጣናቸው ከዚህም ከዚም ተግዳሮት ሲበዛበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ግን የሕግ የበላይነት ሳይረጋገጥ በሽልማት ታርቀናል አሉን፡፡

በአመፀኛው ትውልድና እነሱ በጠመቋቸው የሚመሩት ሕወሓትና ብአዴን የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን እየመሩ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ማጥ ለማውጣት አይችሉም፡፡ ዴሞክራሲ ለእነሱ ባዕድ ነው፡፡ አሁንም ለሚቀጥለው ጉባዔ የሕዝቦች ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የሚለያዩበት የፖለቲካ አጀንዳ ሳይኖር አንዱ አንጃ በሌላኛው ላይ የበላይነት ለማረጋገጥ የመጠላለፍ (Networking) እንቅስቃሴ በሰፊው ይታያል፡፡ የሕዝቡን ንብረትና ጊዜ በሚያባክን መልኩ እየሄዱበት ነው፡፡

ታገልንለት ለሚሉት ሕዝብና ለራሳቸው ሲሉ የአመራር ለውጥ ካልተደረገ ሁኔታው አደገኛ ነው፡፡ ወጣቱ በተለይ ምሁሩ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ መሪነቱን እንዲረከብ ሁኔታው የሚጣራ ይመስላል፡፡ የችግሮቹ ዋነኛ ተዋንያን የሆኑትን ድርጅቶች ከውስጥ ታግሎ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት፣ ያሉትን ድርጅቶች ቀላቅሎ እነሱንም በመቀየር ወይም አዳዲስ ድርጅቶች ፈጥሮ መታገል፣ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኗል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ስላለበት ሁኔታ ያለኝ ትዝብት በጣም ውስን በመሆኑ፣ ከዴሞክራሲ ጋር ያለው አሠላለፍ ይኼ ነው ለማለት ያስቸግረኛል፡፡ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተደረገው ጥናት ከአራቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ለሕዝብ የቀረበ፣ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት የተሻለ መሆኑንም የሚያሳይ ነበር፡፡ አመራሩ ከአመፀኛው ትውልድ የራቀ በመሆኑ እስኪ በተስፋ እንየው፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ፍሬ እያሳየ ነው እንዴ?

የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በኦሕዴድና በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኩል ለውጥ እንዲታይ ያደረገ ይመስላል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መስተዳድር መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን ከወዲሁ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በስሜት ኮርኳሪ (Populist) አስተሳሰብ እየተነዳ እንዳይሆን ማስተዋል ተገቢ ሆኖ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም ለመመለስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ መነሳሳት የአንድ ድርጅት የመጀመርያ ጤናማ ጉዞ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ መነቃቃት የት ያደርሳል? የሚለው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድጋፍ ሊቸረው ይገባዋል፡፡

ሀ. ኦሕዴድ ከሌሎች የኢሕአዴግ ድርጅቶች በተለየ አዲስ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ የዚህ ለውጥ ውጤትም የተማሩን ማዕከል ያደረገ ካቢኔ በማቋቋም ፈር ቀዳጅ ሆኗል፡፡ ቀጥሎ በፌዴራል ደረጃ የተደረገው ለውጥም በዋናነት በኦሮሞ ሚኒስትሮች በተደረገው ነው የሚገለጸው፡፡ ይህ አመራር የሕዝብን ፍላጎት በተለይ የወጣቶችን ችግሮች ለመመለስ ያልተለመዱ ዕርምጃዎች መውሰድ ጀምናል፡፡

ለ. ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያደረገው ምክክር ከክልሎች አንፃር ሲታይ ፈር ቀዳጅ ነው፡፡

ሐ. በአገራችን ቁልፍ ችግር የሆነውን ጠቅላይነት (Centralism) የፌዴራል ሥርዓቱን እስከ ማፍረስ የሚሄደውን መንገድ በመቃወም፣ ሕገ መንግሥቱን በማክበር፣ የፌዴራሊዝምን መርህ የሚጥሱ መመርያዎች በመቃወም፣ ጤናማ ሥርዓት እንዲኖረን የሚያደርገው እንቅስቃሴ መበርታት አለበት፡፡ በኢሕአዴግ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከልነት›› በተግባር ግን ‹‹አውቶክራቲክ ማዕከልነት›› ሁሉም ነገር ከአንድ ማዕከል እንዲፈስ ማድረግ አገራችንን የሚያጠፋ በመሆኑ መገዳደር መጀመራቸው መበረታታት የሚገባው ነው፡፡

ይህ እንቅስቃሴ ለወደፊቱም ቢሆን አስተማሪ ነው፡፡ በቀጣይ ምርጫዎች በአንዱ ወይ በሌሎች ክልሎች ከኢሕአዴግ ውጪ ሌሎች ፓርቲዎች ቢያሸንፉ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ በከፍተኛ ደረጃ ሳይናጋ (Shock) ለመቀጠል ጥሩ ተሞክሮ ይሆናል፡፡ ፌዴራልና የክልል መንግሥታት በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ መሠረት ሥራቸውን አከናወኑ ማለት የሕግ የበላይነት ተረጋገጠ ማለት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የጠቅላይነት አዝማሚያ ፀረ ሕገ መንግሥት ነው፡፡  

መ. የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ መስተዳድር ከ21 ዓመታት በላይ ሲንከባለል የነበረ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ይህ መብት እንዲረጋገጥ መንገድ አስይዞታል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ድምፅ መሰማት የጀመረው ኦሕዴድ ጠንከር ብሎ በመያዙ ነው፡፡ በካቢኔ ደረጃ በቀረበው ረቂቅ ሕግ ላይ ያለውን በተአቅቦ ገልጿል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ድርድር መኖሩ የጤናማ ሥርዓት ምልክት ነው፡፡ በእኔ አመለካከት በአዲስ አበባ  የኦሮሚያ ፍትሐዊ ልዩ ጥቅም የሁላችን ኢትዮጵያውያን ጥቅም ነው፡፡ የፌዴራል ዋና ከተማ ሐዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ወይም መቐለ ቢሆን ኖሮ በተመሳሳይ የሚታይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መንፈስ መሠረት ልዩ ጥቅም እንዲረጋገጥ ኢትዮጵያውያን ሁላችን መታገል ይገባናል፡፡ ፍትሐዊ እስከሆነ ድረስ የአንድ ክልል ጥቅም የሁላችን በመሆኑና ኢትዮጵያዊነት በሰማይ ላይ የተንጠለጠለ መንፈስ ባለመሆኑ፡፡

ሠ. ኦሮሚፋ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ለማድረግ የሚደረገው ትግል መበረታታት ያለበት ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 5/1፣ ‹‹ማናቸውም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በእኩልነት በመንግሥት ዕውቅና ይኖራቸዋል›› ይላል፡፡ የዚህ መንፈስ (Spirit) ማንኛውም ቋንቋ የሥራ ቋንቋ ሊሆን ይችላል ነው፡፡ በጂኦግራፊ ማዕከልነትና ከፍተኛ ብዛት ባለው ሕዝብ ቢጀምር ተገቢ ነው፡፡ ለሌላው በር ከፋች ነው፡፡ ኦሮሚፋ እንኳን የሥራ ቋንቋ መሆን ሁላችንም ብናውቀው አገራችን ትደምቃለች፡፡ እኛም የኦሮሞ ፍልስፍናና ባህል ለማወቅ እንታደላለን ማለት ነው፡፡

ረ. ችግሮችን ውስጣዊ የማድረግ አዝማሚያ የጤናማ ድርጅት ሌላ ምልክት ነው!! ኦሕዴድ የኦሮሚያ መንግሥትን እስከ መራ ድረስና በፌዴራል ደረጃም የገዥው ግንባር አባል እስከሆነ ድረስ የኦሮሞን ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማረጋገጥ በተሟላ መንገድ ራስን ማስተዳደርና በፌዴራል ደረጃ  የኦሮሞ ሕዝብ ተገቢውን ቦታ ማስያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠለት መብት ሲጎድል በሌላ ሊያመኻኝ አይችልም፡፡ ችግር አለ ከተባለ በውስጡ ኢዴሞክራሲያዊ በመሆኑና በውጭ ደግሞ አጎብዳጅ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ሁለቱም ችግሮች ካሉበት አልቻልኩም ብሎ ሥልጣኑን ማስረከብ ነው፡፡ ስለዚህ የውስጣችን ችግሮች ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሊከለክለን አይችልም፣ አይገባም ማለት ለሌሎች አርዓያ መሆን ነው፡፡

ቀ. ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ ለወጣቶች በኦሮሚፋና በአማርኛ መረጃ ማስተላለፍና ፅንፈኞችን መታገል ለሁሉም ክልሎች ቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምንም መረጃ የማይሰጡ ክልሎች ደግሞ አሉ፡፡ የተወሰኑትማ ሐሰተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ (Fake Account) ነው ያላቸው፡፡ ከዘመናችን ጋር በመራመድ በኩል የኦሮሚያ መንግሥት አሁንም አርዓያ ነው፡፡

በ. የኦሮሞን ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞችና እሴቶች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በማስተሳሰር ለሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ያለው የጠራ አመለካከት (በተለይ የክልሉ ፕሬዚዳንት) ለአገራችን ትልቅ ተስፋ ነው፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ታግሎ መንግሥትን አነቃንቆ የተወሰነ የለውጥ እንቅስቃሴ በመጀመሩ እንኳን ደስ አለህ እያልን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ይህን አርዓያ እንዲከተሉ መገፋፋት፣ የጠቅላይና የአግላይ ኢትዮጵያዊነት አራማጆች እንቅስቃሴውን እንዳያደናቅፉትና እየተጠናከረ እንዲቀጥል የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ትግል ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን የታየው ፍንጭ እንደ አብነት መደገፍ ቢገባውም ወደሚፈለገው ለመድረስ ገና ‹‹ሀ . . . ›› እየተባለ ነው፡፡ የኦሮሚያን ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ግዳጃቸውን የሚወጡበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ ተቃዋሚዎችን እንደ ፀጋ ተቀብሎ ያለማወላወል ሕጋዊ መብቶቻቸውን ማክበርና በአገር ግንባታ የአቅማቸውን ያህል እንዲሳተፍ ማድረግ፣ የሲቪልና የሙያ ማኅበራትን ነፃነት መጠበቅና ሙሰኞችን መታገል ይጠይቃል፡፡

አሁን እየታየ ያለው መነቃቃት ቀጣይና ጠንካራ እንዲሆን የማይንቀሳቀሰውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመቀየር የተሟላ ራዕይ፣ ስትራቴጂና ሥልት መቀየስ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል ምሁራንን በአጠቃላይ ወጣት ምሁራንን በተለይ የኦሕዴድ ደጋፊ ነው አይደለም ሳይባል፣ ኦሮሞ ነው አይደለም ሳይባል ሰፊ ተሳትፎ ያስፈልገዋል፡፡ በሒደትም ሥልጣኑን እንዲረከብ ማመቻቸት ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚህ በፊት በአንድ መጣጥፌ የፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጋቢሳን የኦሮሞን እንቅስቃሴ በሚመለከት የጠቀስኩትን እያስታወስኩ፣ ምን ዓይነት ትንቢት (Prophecy) እንደሆነ እስኪ እዩልኝ፡፡

“At no other time in Ethiopia’s political history has a non-violent transition to democracy more desirable and achievable. Pololitionary at no other time in the past have Ethiopians viewed the Oromo as a force for democratization, the Ethiopians Empire State.”

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆኑ፣ በሰላምና ደኅንነት (Peace and Security) የዶክትሬት ዕጩ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡