Skip to main content
x
‹‹ከመጣንበት ይልቅ የምንሄድበት መንገድ በጣም ረዥም እንደሚሆን ይሰማኛል››

‹‹ከመጣንበት ይልቅ የምንሄድበት መንገድ በጣም ረዥም እንደሚሆን ይሰማኛል››

አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ የወወክማ ዋና ዳሬክተር

አቶ ዳግማዊ ሰላምሳ የወወክማ (ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማበር) ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በወጣቶች ልማት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ወወክማ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አማካይነት በኢትዮጵያ የተመሠረተ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያና እንደ ቀይ መስቀል ሁሉ በአዋጅ የተቋቋመ ማበር ነው፡፡ ስያሜው ይማኖታዊ ድርጅት ቢያስመስለውም ከሃይማት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ በሁሉም ለም ላይ የሚገኝ ለም አቀፍ ማኅበር ነው፡፡ 1940 .የተቋቋመው የኢትዮጵያ ወወክማ በትምህርት፣ በስፖርት፣ በኪነ ጥበብ፣ በጤና፣ በሕይወት ክህሎትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከወጣቶች ጋር ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም የተመረተበትን 70ኛ መት አክብሯል፡፡ ማኅበሩ ከተመረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ምን መራት እንደቻለና አጠቃላይ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን አቶ ዳግማዊ ሰላምሳን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማበሩ ምን ያህል ቅርንጫፎች አሉት? አገልግሎቱስ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ ነው ወይ?

አቶ ዳግማዊ፡- እስከ ኃይለሥላሴ ዘመን መጨረሻ ድረስ አስመራ ውስጥ የሚገኘውን ጨምሮ 25 ቅርንጫፎች ነበሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ አሥር ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በአማራ ክልል ባህር ዳርና ደብረማርቆስ ከተማ ላይ፣ በደቡብ ክልል ሐዋሳና ወላይታ ከተሞች ላይ፣ በትግራይ ክልል መቀሌና አደዋ ላይ፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ፣ በአዲስ አበባ 4 ኪሎ ወወክማን ጨምሮ አሥር ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በትምህርት፣ በግብርና፣ የወጣቶች የስፖርት ማዕከላትን በማስፋፋት ዙሪያ ይሠራል፡፡ ለዚህም 4 ኪሎ ወወክማን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ የጎልማሶችን ትምህርት በኢትዮጵያ ያስፋፋውም ወወክማ ነው፡፡ የባድሜንተን፣ የቦክስና የቅርጫት ኳስ ውድድር በአገሪቱ በስፋት ያስተዋወቀው ወወክማ ነው፡፡ አዲስ ከተማ የሚገኘው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤትን ያቋቋመውም ማኅበሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወወክማ ትልቅ ስም ያለው ድርጅት እንደነበር ይነገርለታል፡፡ ይሁንና በነበረበት ሁኔታ መቀጠል አልቻለም፡፡ ችግሩ ምንድነው?

አቶ ዳግማዊ፡- የወወክማ ማዕከላት በአጠቃላይ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ይደረግባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ጨቋኝ ሥርዓትን በመቃወም ረገድ የወወክማ ማዕከላት ሚና አላቸው ተብሎ ይታሰብ ስለነበር የደርግ መንግሥት ማዕከላቱ እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ በደርግ ዘመነ መንግሥት ወወክማ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ንብረቶቹንም መንግሥት ወርሶት ነበር፡፡ የወወክማ ዋና መሥሪያ ቤት የነበረውንና ትልቁን አገልግሎት ይሰጥበት የነበረውን 4 ኪሎ የሚገኘውን ወወክማ ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙት ሌሎች ቅርንጫፎች ሁሉ ተወረሱብን፡፡ በ1984 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ታምራት ላይኔ በሰጡት ፈቃድ መሠረት ወወክማ እንደ አዲስ እንዲመሠረት ተደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የቅርንጫፎቹ ብዛት 25 ነበር፡፡ መሀል ላይ ተከስቶ በነበረው ክፍተትና ማዕከላቱ ተወርሰው ስለነበር፡፡ ወወክማ ተዳክሞ ነበር፡፡ በአዲሱ ሥርዓት ደግሞ እንደገና መቋቋም ችላችኋል፡፡ ይሁንና የቀድሞ ገናናነቱን አልያዘም ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ዳግማዊ፡- ልክ ነው ይኼ በጣም ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ወወክማ በዚያ ዘመን የነበረው እንቅስቃሴ አመርቂ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ማኅበሩ በአዋጅ የተቋቋመ ስለሆነ መንግሥትም ድጋፍ ያደርግለት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ልክ እንደ አንድ የመንግሥት ፕሮግራም ነበር ይሄድ የነበረው፡፡ 90 በመቶ የሚሆነውን በጀቱን ከመንግሥት ድጎማ ያገኝ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ወወክማ የተቋቋመው በበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ማኅበር በጎ አድራጎት ሆኖ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ነዋሪዎች ማኅበር 90 በመቶ ገቢው ከውጭ፣ አሥር በመቶውን ደግሞ ከአገር ውስጥ ያገኛል፡፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የፋይናንስ አቅም ይኼን ያህል ነው፡፡ ብዙ ሥራ ለመሥራት የሚፈቀድለት አይደለም፡፡ ወወክማ ሙቭመንት ነው፡፡ በየቦታው መስፋፋት መቻል አለበት፡፡ አምቦ፣ ወለጋ፣ ድሬዳዋ ቅርንጫፎች ነበሩት፣ እነሱን እናስከፍታለን፡፡ የነበሩን ብቻ ሳይሆን በፊት ወወክማ ያልደረሰባቸው እንደነ ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ባሉ ክልሎች ወወክማ ሊኖር ይገባል የሚል አቋም አለን፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ የፕሮግራም መዋቅር አዘጋጅቷል፡፡ አንደኛው መዋቅር የባህርይ ግንባታ ላይ መሥራት ነው፡፡ ድርጅቱ በአካል የዳበረ፣ በመንፈስ የጠነከረ በሥነ ልቦናና በአዕምሮ የጎለበተ ወጣትን የማፍራት ተልዕኮ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ከስያሜው መረዳት እንደሚቻለው ፕሮግራማችሁ ተደራሽ የሚያደርገው ወጣት ወንዶችን ብቻ ነው፡፡ የሴቶች ጉዳይ ወደ ጎን ተብሎ ነው ወይስ ሌላ ማብራሪያ አለ?

አቶ ዳግማዊ፡- ስሙ ብራንድ ስለሆነ ለማቆየት ተብሎ እንጂ ተደራሽነቱ ለወንዶች ብቻ አይደለም፡፡ ሁለቱንም ፆታዎች ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ዓለም ላይ ያለው ገጽታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የማዳጋስካርን ወወክማ የምትመራው ሴት ነች፡፡ በዚምባብዌም እንደዚሁ፡፡ እኛም ቢሆን በተለይ በብሔራዊ ጽሕፈት ቤት የሚሠሩ አባላት በአብዛኛው ሴቶቸ ናቸው፡፡ ፕሮግራሞቹም ከ60 በመቶ በላይ ተጠቃሚ የሚያደርጉትው ሴቶችን ነው፡፡ የስሙ ጉዳይ የነበረውን ነገር ይዘን ከማስቀጠል ባለፈ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ ክርስቲያን የሚለውም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የማኅበሩ ዓላማ ከእምነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ የአዲስ ከተማ የአማካሪ ቦርድ ፕሬዚዳንት የነበሩት የፊታውራሪ አመዴ ለማ ልጅ ነበሩ፡፡ አሁንም ከቦርድ አባላት መካከል ቁልፍ ሰው ዶክተር ሰለሞን ዓሊ የሚባሉ ሙስሊም ናቸው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ የለበትም፡፡ ነገር ግን ስሙ አወዛጋቢ ነው፡፡ ለምን አትቀይሩትም የሚል ነገርም ይነሳል፡፡

ሪፖርተር፡- ኃይለ ሥላሴ ወወክማ  እንዲቋቋም ሲያደርጉ ማኅበሩ በሌሎች አገሮች የሚሰጣቸውን የሆስቴል አገልግሎቶች በመመልከት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ የሆስቴል አገልግሎት የሚሰጥ ቅርንጫፍ አላችሁ?

አቶ ዳግማዊ፡- የ4 ኪሎ ወወክማ 60 መኝታ ቤቶች አሉት፡፡ የተሟላ ሬስቶራንት አለው፡፡ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ሲኖሩ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ተሳታፊዎች እንዲያርፉበት ይደረጋል፡፡ እሱ ግን በአሁኑ ወቅት የእኛ የወወክማ ሀብት አይደለም፡፡ ለማስመለስ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አሁን ያለው ወወክማ ግን ሆስቴል የለውም፡፡ ፕሮግራሞች ብቻ አሉት፡፡

ሪፖርተር፡የ4 ኪሎ ወወክማን ጨምሮ ሌሎች የወወክማ ንብረት የነበሩትን ለማስመለስ ጥረት ታደርጋላችሁ?

አቶ ዳግማዊ፡- ለማስመለስ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ የተዘጋጀ የወጣቶች ኮንፈረንስ ነበር፡፡ በዚያ ኮንፈረንስ ላይ የነበሩ የወወክማ አባሎች ይህንን ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ እሳቸውም አለ የምትሉት ማስረጃ ካላችሁ ሰብስባችሁ ወደቢሮ መምጣት ትችላላችሁ አሉን፡፡ በዚያ ጊዜ ብቻችንን ከመሄድ እንደኛ ንብረት ከተወረሰበት ወሴክማ ጋር በጋራ በመሆን ጥያቄያችንን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረብን፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ እሳቸው በማለፋቸው ጉዳዩ ተድበስብሶ ቀረ፡፡ አሁን የተቋቋመው ቦርድ ጉዳዩን ለማስቀጠል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በወቅቱ የነበረው የንብረት ይመለስንን ጥያቄ እንጂ እኔ እንዳየሁት ጠለቅ ያለ ነገር አልነበረውም፡፡ ገቢውንም በተመለከተ በግልጽ የተቀመጠና ንብረትነቱ ቢመለስ ይህንን ዓይነት የተሻለ ነገር እናደርግበታለን የሚል የተጠናከረ ነገር አልተያዘም፡፡ አሁን ግን በአዲሱ የድርድር ሥራችን ውስጥ ይህ ተካቶበታል፡፡ በከፊል ተረክበነው የነበረው መቀሌ ያለው ወወክማም ሙሉ ለሙሉ እንዲመለስልን የሚል ጥያቄም ያካተተ ነው፡፡ ንብረቱን ከማስመለስ ባሻገር እንዴት አድርጌ ላስተዳድረው እችላለሁ የሚል ጥርት ያለ ሥልት ይዘን አይደለም ብዙ ጊዜ የምንጠይቀው፡፡ አዲስ የተመረጠው ቦርድ ግን የተሻለ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ቦርዱ ሁሉንም ነገሮች በአዲስ የመተካት ሐሳብ የለውም፡፡ ነገር ግን ትንሽ ሻል ያለ መንገድ ይከተላል፡፡ መንግሥት ጋር ሄዶ ዕቃ መልሱ ማለት ሳይሆን የጠራ ዕቅድና የጠራ አካሄድ ሊኖረን ይገባል፡፡ ሆስቴሉ ምን ያህል ገቢ ያስገኛል? አጠቃላይ ንብረቱስ ምን ያህል ገንዘብ ይተመናል? ስለሚለው ጉዳይ በባለሙያ አስጠንተን መሄድ ይገባናል፡፡ ከመጣንበት ይልቅ የምንሄድበት መንገድ በጣም ረዥም እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ አንዳንዶቹን ወደኋላ ተመልሰን የባለቤትነት ጥያቄ ልናነሳባቸው አንችልም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ መተኪያ ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ ባህር ዳር ላይ ጅምናዚየም ያለው ወወክማ አለ፡፡ ወላይታ ላይም እንደዚሁ ጅምናዚየም እየተነባ ሲሆን፣ በመጪው ዓመት ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ አዳማ እና ደብረ ማርቆስ ላይም ምትክ ቦታ ተሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ውጪ የሆኑትን ለምሳሌ የ4 ኪሎ ወወክማ እስከ አጠቃላይ ንብረቱ፣ የተጠቀሙበትን ዓመታት ግምት አስልተው እንዲሰጡን የሚል በቁጥር (በገንዘብ) ያልተቀመጠ ነገር ግን በሐሳብ ደረጃ የተቀመጠ ድርድር ነበር፡፡ ይህ እንዲህ ነው ብዬ የገንዘብ ተመን ለማውጣት አልችልም፡፡ ነገር ግን የወቅቱ ወጣቶችን ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚችል ሀብት አለው ማለት እችላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ 4 ኪሎ ወወክማ ያሉ አቅም ያላቸው የማኅበሩ ቅርንጫፎች ሕጋዊ ባለቤትንነታችሁ ተረጋግጦ ቢመለስላችሁ እስካሁን ያጣችሁትን ጥቅም የመጠየቅ ሐሳብ አላችሁ?

አቶ ዳግማዊ፡- ያጣነውን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ እንጠይቃለን የሚል ነገር የለም፡፡ ይኼ በአንድ ወቅት ላይ የነበረ ፍላጎት ነው፡፡ አሁን እንደዚህ ነገር የለም፡፡ መንግሥት የሚያስተዳድርበት ሁኔታ መጥፎ ነው ማለት አይደለም፡፡ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ምናልባት ከዚያ በተሻለ ሁኔታ ልንይዘው አንችልም ይሆናል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ 4 ኪሎ ወወክማን በጥሩ ሁኔታ ነው የያዘው፡፡ ሌላ ትልቅ ጅምናዚየምም ከጎኑ ሠርቶለታል፡፡ ንብረቶቹ ኃይለ ሥላሴ በገነቡበት ደረጃ ነው ያሉት ማለት አይቻልም፡፡ መንግሥት ብዙ ኢንቨስት አድርጎባቸዋል፡፡ ነገር ግን ንብረቶቹን ባሉበት ሁኔታ ብናገኛቸው እኛ ለወጣቶች ምቹና በተሻለ መንገድ መጠቀም የሚችሉበትን አቅም እንፈጥራለን የሚል አቋም አለን፡፡ መቀሌ የሚገኘውን ወወክማ ንብረት መልሱልን ብለን ስንጠይቅ ሌላ ተለዋጭ ቦታ ነው የምንሰጣችሁ የሚል ምላሽ ሰጡን፡፡ ተለዋጭ ቦታ የምትሰጡን ከሆነ የማሠሪያ ወጪውን አንድትሰጡን እንጠይቃለን አልን፡፡ አራት ኪሎ ወወክማን በተመለከተ ለምናነሳው የይገባኛል ጥያቄም እንዲህ ዓይነት ጉዳይ የሚነሳ ከሆነ በሚሰጠን የምትክ ቦታ ላይ የማሠሪያ ወጪውን እንጠይቃለን ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ባሉን ንብረቶች ለወጣቶቹ ተገቢውን አገልግሎት ማድረስ ተቀዳሚ ዓላማችን ነው፡፡ አንድ ተቋም ንብረት በማስመለስ ተጠምዶ ይኖራል ማለት አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ለወጣቶች ምን ምን ዓይነት ፕሮግራሞችን ቀርፃችሁ ተደራሽ ታደርጋላችሁ?

አቶ ዳግማዊ፡- በእያንዳንዱ ወቅት ወጣቶች የሚፈልጓቸው አገልግሎቶች አሉ፡፡ የሕይወት ክህሎትን ከመገንባትና ማንነትን ከመቅረፅ አኳያ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉን፡፡ የወጣቶችን የአመራር አቅም ከመገንባት አንፃር የሚሠሩ ሥራዎችም እንዲሁ፡፡ ዘርፈ ብዙ የጤና ፕሮግራሞች ማለትም የሥነ ተዋልዶ ጤና፣ ኤችአይቪ፣ በሥርዓተ ምግብና በንፅህና ላይ ምንሠራቸው ፕሮግራሞችም አሉ፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጎልቶ የሚታየው የሥነ ተዋልዶ ጤና ፕሮግራሙ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 እና ከ20 እስከ 24 የሆኑ ወጣቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ወወክማ ባለባቸው በሁሉም ቦታዎች የምንሠራው ነው፡፡ 6,000 የሚጠጉ ወጣቶችን ዒላማ አድርገናል፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ ፕሮግራም በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ለመጀመር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ከአንድ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅት ጋር በመሆን በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ላይ የፓይለት ፕሮግራም ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምን ያህል መሥራት ችላችኋል?

አቶ ዳግማዊ፡- የሥነ ተዋልዶ ጤና ሆኖ በውስጡ የተለያዩ ነገሮችን ይይዛል፡፡ ወንዶችን አሳታፊ ያደረገ የፆታ ጥቃት መከላከል ሥራ 12 የሕይወት ክህሎት ዓይነቶችን ያካተተና ያልተፈለገ እርግዝናን ከመከላከል አኳያ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉን፡፡ ደብረ ማርቆስ፣ ወልቂጤ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ አክሱምን ጨምሮ ከአሥር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ አዲግራትን የመረጥነው ግን አዲግራት ላይ የሚሠራ አጋር በማግኘታችን ነው፡፡ ፕሮግራሙ በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ለአራት ዓመታት የሚቆይም ነው፡፡