Skip to main content
x

የሳምንቱ ገጠመኝ

እንደ መስከረም የታደለ ወር ያለ አይመስለኝም፡፡ የዓመት መነሻ፣ ቁንጮ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ ሕዝባዊ በዓላት የሚገኙበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ክረምቱ እየተገባደደ መሰስ ብሎ የሚወጣበት በመሆኑ ርጥበትና ነፋስ፣ ሙቀትም ድርሻው ነው፡፡ በወሩ ውስጥ ከሚከበሩት በዓላት ሁሉ በተለየ በኢትዮጵያ ሁሉም አቅጣጫ የሚገኙ ክርስቲያኖች የሚያከብሩት የመስቀል በዓል ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ መስቀል ከሃይማኖትም ከባህልም ከወቅት መለወጥ ጋር የተያያዘ በመሆኑ መሥሪያ ቤቶች ዝግ የሚሆኑበት በበዓሉ ቀን መስከረም 17 ብቻ አይደለም ተከባሪው፡፡ እንደየብሔረሰቡ ትውፊት ከመስከረም 13 ቀን ጀምሮ የሚከበር በመሆኑ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ያሉ ቤተሰቦች፣ ቤተዘመዶች ይሰበሰቡበታል፡፡ ከባሕር ማዶ ጭምር ይመጡለታል፡፡ የተነፋፈቁ ይጠያየቁበታል፡፡ በዓሉ የፍቅር፣ የአንድነት፣ ተጣልተው የነበሩ የሚታረቁበት፣ ዕርቀ ሰላም አውርደው አዲሱን ዘመን በስኬት እንዲያስዘልቃቸው የሚመኙበት ነው፡፡ እንዲያውም የበዓሉ ሌላኛው ፋይዳ ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁበት፣ ጎልማሶች ዕውቀትን ከአባቶች የሚቀስሙበት፣ ኃላፊነት የሚረከቡበት፣ ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግናን በመመኘት ጸሎት የሚደረግበት፣ ሕዝቡ የሚዘፍንበት፣ የሚጨፍርበት፣ የሚደሰትበት፣ ግጥም የሚገጥምበት ድምፁን የሚያሟሽበት፣ ወጣቱ የሚኮራበት፣ ባህሉን የሚያጠናበት ነው፡፡

ይኼና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው ዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ የዓለም ወካይ ሆኖ የመስቀል በዓል ለመመዝገብ የቻለው፡፡

የዘንድሮውን በዓል ለማክበር እግር ጥሎኝ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ዓዲግራት ከተማ ጎራ ብዬ ነበር፡፡ የኣጋመና የኢሮብ ባህላዊ አከባበር ከመስከረም 14 ቀን ጀምሮ ያለው ድባብ ልዩነት አለው፡፡ በዓዲግራት ከተማ በሚገኝ ከፍ ያለ ኮረብታ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተተከለው ከ20 ሜትር በላይ የሆነው መስቀል አንዱ መስህብ ሆኗል፡፡ ትግራይ በክልል ደረጃ የመስተዳድሩ ሹማምንት በሚገኙበት በዓሉ የሚከበርበትም ነው፡፡ ከተማው ዘንድሮ እንደቀደምቱ ሁሉ የበዓሉ ማጀቢያዎች በሆኑ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ብስክሌት፣ እግር ኳስ፣ የተራራ ሩጫ፣ ወዘተ እንዲሁም የሙዚቃ ድግስ፣ የቁንጅና ውድድር ሁሉ ነበረበት፡፡

የመስቀል በዓል ዕለት ፍጻሜው በሆነው የእግር ኳስ ውድድር፣ ለዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ የበቁት የዓዲግራትና የመቐለ ከተማ ቡድኖች በሚያደርጉት ግጥሚያ ነበር፡፡ ሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድኖች በጥሎ ማለፍ አሸንፈው ካለፉ በኋላ ረፋድ ላይ ደመራው በተለኮሰበት፣ ሰላም በተሰበከበት ወልዋሎ ስታዲየም፣ ከሰዓት በኋላ ዋንጫውን ለማንሳት የሚያደርጉት ፍልሚያ ለመመልከት ተመልካቹ ከሆታ ጋር ተገኝቷል፡፡ እኔም የሁለቱን አዳዲስ ክለቦች አቅምና ብቃት ለማየት ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ተስፋ ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ፡፡ ስታዲየሙ ወልዋሎዎች ተገኝተው ግጥሚያውን ቢጠብቁም መቐለዎች ግን ድምፃቸው አልተሰማም፡፡ ‹‹ደጋፊዎቼ በስታዲየሙ ውስጥ ተገቢ ቦታ አልተሰጣቸውም፤›› በሚል ቡድኑ መቅረቱን ማስታወቁን አብረውኝ የነበሩ ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ የበዓሉን መንፈስ ያልጠበቀ ድርጊት መፈጸሙንም አክለው ሲናገሩም አዳመጥሁ፡፡ ጨዋታው ፍፃሜውን ማግኘት ነበረበትና ወልዋሎዎች በፎርፌ ዋንጫውን አገኙ፡፡

ከጎልማሳነት አለፍ ያሉ አንድ አባት ‹‹ የፍቅርና የአንድነት የዕርቅም መገለጫ በሆነው፣ በማኅበረሰቡ አባላት መካከል ያለውን ግንኙነት በሚያጠናክረው በዓል ላይ እንዴት የስፖርት ውዝግብ ይፈጠራል፤›› ሲሉ ሰማኋቸው፡፡ ‹‹ነገር የተበላሸው እኮ ገና ከረፋዱ መስቀል ደመራው ከመለኮሱ በፊት በነበረው ሥነ ሥርዓት ላይ ነው፤›› ሲሉ ጆሮዬ ቆመ፡፡

እንዴት አልኳቸው? እሳቸውም ምላሻቸውን አልነፈጉኝም፡፡ እንዲህ አሉ፡፡ ‹‹በዓሉ የቤተ ክርስቲያን ሆኖ ሳለ የመንግሥት በዓል ይመስል መሰናዶው በአብዛኛው ስታጋፍር የነበረችው ጋዜጠኛ መሆኗ ብቻ ሳይሆን የመርሐ ግብሩ ቅደም ተከተል መዛባት የበዓሉ ማሰሪያ ንግግር (ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ) በብፁዕ ጳጳሱ አለመፈጸሙ ቅር አሰኝቶኛል፡፡›› የሳቸውን አስተያየት ሌሎቹም እኔም ተጋርተናል፡፡

በየትም ሥፍራ በዓሉን የሚከፍትና የሚዘጋ ፓትርያርኩ ካሉ ርሳቸው፣ ጳጳሳት ካሉም እነርሱ፣ በተዋረድም እስከ ሊቀ ካህናት ድረስ ይዘልቃል እንጂ የመንግሥት ሹመኛ መንፈሳዊ በዓሉን በዲስኩር አይዘጋውም፡፡ በዓዲግራት የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ በአዲስ አበባው አከባበር ፕሬዚዳንቱ በተገኙበት ከንቲባው ብቻ ሲናገሩ፣ በዓዲግራት ግን የዞኑ አስተዳዳሪና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተከታታይ ከጳጳሱ በኋላ የማጠቃለያ ንግግር ማሰማታቸው ሳያሳዝን አልቀረም፡፡ ገጠመኜ ‹‹በገዛ ዳቦዬ . . . ›› የሚለውን ብሒል ነው ያስታወሰኝ፡፡

(ገብረመስቀል ወልዱ ዘማርያም)