Skip to main content
x

የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች እባካችሁ የልዩነት አጥሩን አፍርሱ

በ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ ላይ ዓለም በሥልጣኔ እየገሰገሰ፣ የሳይንስ ሥነ ምርምር የዕደ ጥበብ ግኝቶችን በብዛት እያዥጎደጎደና ተዓምር የሚባሉ እምርታዎችን እያስከተለ ባለበት ወቅት፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት መካከል ግን ከ18 ዓመታት በላይ የዘለቀ ግጭትና አለመግባባት ውስጥ እየዳከሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁለት አገሮች በታሪክ አጋጣሚ ለበርካታ ዘመናት አብረው የኖሩና በደም፣ በሥጋ፣ በባህል፣ በቋንቋና በአስተሳሰብ ተመሳሳይና አንድ ዓይነት የሆኑ ሕዝቦች ናቸው፡፡ አገሩን እየመሩ ያሉት መንግሥታትም ከዚህ ሕዝብ የወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ያላቸውን የሶሻል ካፒታልና የኅብረተሰብ ግንኙነት መጠበቁና ማዳበሩ

 ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። ተመሳሳይ ሃይማኖቶችና ብሔር ብሔረሰቦች/ጎሳዎች በሁለቱም አገሮች ይገኛሉ። እነዚህ ደግሞ በተለያዩ ወቅቶች በአንድ መንግሥት ጥላ ሥር የነበሩ ሕዝቦች ናቸው። ይኼ ለወደፊቱ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ጤናማ ለማድረግ መሠረት መሆኑን በቅጡ መገንዘብና መንከባከብ ያስፈልጋል።

የሁለቱን አገሮች የቅርብ ጊዜውን ቅራኔ ስንመለከት፣ እ.ኤ.አ. 1961 እስከ 1991 የኤርትራ የተለያዩ ኃይሎች የነፃነት/የመገንጠል ጦርነት ማካሄድና ይህም ጦርነት በኤርትራ አሸናፊነት መጠናቀቁ፣ እ.ኤ.አ. 1991 እስከ 1997 በሁለቱገሮች መሀል የኢኮኖሚ ውድድር መፈጠሩና ውጥረት ማምጣቱ፣ እ.ኤ.አ. 1998 እስከ 2000 በሁለቱም ወገን በርካታ የአገሪቱን ወጣቶች ያሳተፈ አላስፈላጊ የድንበር ጦርነት መደረጉ፣ እ.ኤ.አ. 2000 እስካሁን ማለትም እስከ 2017 ቀጥተኛ ጦርነት ባይኖርም በመቶ ሺሕ የሚገመት ሠራዊት ያንዳንዱ በኩል ጎራ ለይቶ አንዱ አንዱን እንዳይወረው እየተጠባባቀ ይገኛል። የዲፕሎማሲውና የፕሮፓጋዳው ጦርነትም ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። በዚህም መካከል የአንዱ አገር መንግሥት የሌላውን ባላንጣ ሲደግፍ ወይም ከለላ ሲሰጥ ይታያል። የሁለቱ አገሮች ተቃዋሚዎችም ሁኔታው እንዳመቻቸው አንዱን ተመርኩዘው ባላንጣቸውን ለመግጠም ሲሞክሩ በተደጋጋሚ እናያለን።

..አ. 2000 በአልጀርስ የተደረሰውም የሰላም ስምምነት እንደተጠበቀው ለሁለቱ ሕዝቦች የሰላም መሠረት ሆኖ ሊያገለግል አልቻለም። ሁለቱገሮች ያቋቋሙት ኮሚሲዮን ውሳኔ በሥራ ላይ አልዋለም። የስምምነቱም ዋስ የነበሩት መንግሥታት ውሳኔውን ማስፈጸም አልፈለጉም።

እነዚህ ሁለት መንግሥታት እርስ በርሳቸው በድንበር ምክንያት ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ ገብተው በርካታ ዜጎቻቸውን አጥተዋል፡፡ በርካታ የሕዝብ ሀብትና ንብረት ለጦርነት አውለዋል፡፡ በዚህም ሁለቱ አገሮች ለጦርነቱ ያወጡት ወጪ በቀላሉ ሊመልሱት የማይችሉት ኪሳራ ውስጥ እንዲዘፈቁ አድርጓቸው አልፏል፡፡ የሁለቱ አገሮች ውጥረት በባድመ ዙሪያ ቢያተኩርም ጉዳዩ ከዚያ በጣም የሰፋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል በድንበር አካባቢ ያሉ ሕዝቦች  አሁን ያለውን የልዩነት አጥር እንዲፈርስ የሚፈልጉ ናቸው። ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ አገር ተለያይተው ሲመሠረቱ በሁለትና ከዚያ በላይ ተመሳሳይ ጎሳዎች ተከፍለው ለመኖር መገደዳቸው ሀቅ ቢሆንም፣ ይኼው መከፈላቸው ደግሞ የድንበሩን የማካለልና የማስመር ጉዳይ ተመልሶ የግጭት መንስዔ ሆኖ መገኘቱ መዘንጋት የለበትም። 

ዛሬ ከዚህም በላይ የሁለቱ አገር ዜጎች ወላጅ ከልጁ፣ ሚስት ከባልዋ፣ ወንድም ከእህቱ ተለያይተው እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ እነዚህ ሁለት ሕዝቦች በነበራቸው የረዥም ዘመናት ማኅበራዊ መስተጋብር በርካታ ኤርትራውያን ከበርካታ ኢትዮጵያውን ጋር ተጋብተዋል፡፡ ተዋልደዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከበርካታ የኤርትራ ዜጎች ጋር የጋብቻ ውህደት በማድረግ ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ይህን ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ እንዲሁም እንደ ጎረቤት አገር አብሮ የማደግ መርህ መሠረት እናንተ ሁለት የአገሪቱ መሪዎች፣ የእነዚህን ሁለት አገሮች ዕጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ አቅምና ብቃቱ ስላላችሁ የልዩነት አጥሩን አፍርሳችሁ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት የወንድማማችነት መንፈስ እንዲመጣ እንድታደርጉ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

የልዩነት አጥሩን ማፍረስ የሚጠቅመው ለሁላችንም በመሆኑ፣ የሁለቱ አገሮች መሪዎችና ፖለቲከኞች በጎ ፈቃድና ቀና ትብብር ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን በማድረጋችሁ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ከሚደረገው መቀራረብ በላይ፣ በሁለቱ አገሮች የሚገኙ ሕዝቦች በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ግንኙነት በቀናነት መጣመር የሚያስከትለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነቶችና የግጭት አፈታት ዘዴ ሒደት ከሌሎች አዲስ አገሮች አፈጣጠርና ግጭቶች እንደሚለይ ግንዛቤ ማድረግ ያስፈልጋል። ስለዚህም በዓለም ደረጃ የተያዙ መድኃኒቶች ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ቅራኔዎች ቀጥተኛ ፈውስ ሊያመጡ እንደማይችሉ በገሀድ ለ18 ዓመታት ዓይተነዋል። ዛሬም በተግባር እያየነው ነው።

ስለዚህ ኢትዮጵያን እየመራ ያለው ኢሕአዴግ፣ እንዲሁም አገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ኤርትራን እየመሩ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ይህንን በሕዝቦች መካከል የተጋረጠ የልዩነት አጥር በሠለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙርያና በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት፣ እንዲሁም ለረዥም ዘመናት አብረን የኖርን ሕዝቦች በመሆናችን ሌላ አስታራቂ ወይም ሦስተኛ ወገን ሳያስፈልግ እርስ በርሳችሁ በቀናነትና በትብብር መንፈስ ተወያይታችሁ፣ በችግር ውስጥ ላለው ሕዝባችሁ መፍትሔ እንድታመጡ ተስፋ በማድረግ፣ ይህን የእርቀ ሰላም ውይይት መነሻ ሐሳብ እንዲሆን እያቀረብኩ በቅርቡ በሙሉ ተስፋ ወደ ተግባር በመግባት ለሕዝባችሁና ለአገራችሁ የሚጠቅመውን የሰላም መንገድ እንደምትከተሉ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

በተስፉ (ኢትዮጵያ) አልታሰብ

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡